ለሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች ከምንጊዜውም በላይ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል

አዲስ አበባ:- በአሁኑ ጊዜ ለሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች ከምን ጊዜው በላይ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስቴር ውል የተገባለት የመድኃኒት ፍላጎት እና አቅርቦት ሥርዓት አተገባበር” ማስጀመሪያ ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ ትናንት ሲካሄድ እንደገለፁት፤ መንግሥት የፈውስ ሕክምናንና መከላከልን ማዕከል ያደረገ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በትኩረት እየሠራ ነው።

በእናቶችና ሕፃናት፤ በዜጎች ጤና ላይ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታ መከላከል መስክ ተጨባጭ ለውጥ የተመዘገበ ቢሆንም በፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ መስክ ግን ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠይቅ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በሕክምና ግብዓት ራሷን ለመቻል የትኩረት አቅጣጫ ተነድፎ እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ በአሁኑ ጊዜም ለሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች ከምን ጊዜው በላይ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

አምራቾችን በማበረታታት፣ ተኪ ምርትን በማሳደግና የሀገርን ኢኮኖሚ በዘላቂነት በመገንባት ሂደት ለመድኃኒት የሚወጣ ወጪን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የሚቻልበት ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች በዘላቂነት መድኃኒት ማቅረብ እንዲችሉ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ የሰባት ዓመት ውል ማሰር የሚችሉበት ሥርዓት ተፈጥሯል። ከዚህ በፊት ውሉ ለሦስት ዓመት ብቻ የሚቆይ እንደነበር ተናግረዋል።

መድኃኒት አምራቾች ጥራት ላይ ትኩረት በማድረግ ወደ ውጭ ሀገራት መድኃኒቶችን በብዛት በመላክ ገቢ ማስገኘት ይኖርባቸዋል። ለዚህም ተባብሮ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የቁጥጥር አሠራሮችን የማጠናከር ሥራ እየተሠራ ነው። በዚህም ተጠያቂነት ማስፈን ይቻላል ያሉት ዶክተር መቅደስ፤ አምራቾች ማምረት ብቻ ሳይሆን ማሰራጨት ላይም ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይ የግል ዘርፉ በዚህ ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ገልገሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ “ውል የተገባለት የመድኃኒት ፍላጎት እና አቅርቦት ሥርዓት አተገባበር” ሆስፒታሎችና የሕክምና ተቋማት የሚፈልጉት መድኃኒት በፍጥነት እንዲረከቡ በማድረግ አክሞ የማዳን አቅም እንዲጠናከር ያደርጋል ብለዋል።

ክልሎች የሚፈልጉትን መድኃኒት ለአገልግሎቱ በወቅቱ ማሳወቅ እንደሚገባቸው ገልፀው፤ ለመድኃኒቶቹ የሚያስፈልገውን በጀት መያዝ ላይም ትኩረት ማድረግ አለባቸው ብለዋል። ይህ በመድኃኒት አቅርቦት ሠንሠለት ላይ የሚስተዋለውን ተግዳሮት መቅረፍ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማመጣጠን የበጀት፣ የቴክኖሎጂ ክፍተት፣ የሕክምና ተቋማት ፍላጎታቸውን በትክክል አለማሳወቅ፣ የፖሊሲ እና ሌሎች ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰዋል። ከ60 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኅብረተሰቦች ጤና መድን ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አንስተው፤ አቅርቦትና ፍላጎትን ማመጣጠን በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

መድኃኒትን ከውጭ አስመጥቶ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ውስብስብ ሂደትን እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ የመድኃኒት አቅርቦትን በሀገር ውስጥ ለመተካት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

አሁን ላይ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ የሚያወጣባቸውን 253 የመድኃኒት ዓይነቶች ለኅብረተሰቡ በነፃ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

 

ሳሙኤል ወንደሰን

 

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You