
ጌታቸው? ‹ጌታቸው ደባልቄ… የጥንት የጠዋቱ? ተንቀሳቃሹ ቤተ-መዘክር ብለው የሚጠሩት? አንጋፋው የቲያትር አዋቂ?…› አዎን እርሱ ግን ከእዚህም ሌላ ነው። አንጋፋዎቹን ሙዚቀኞቻችንን በግጥምና ዜማዎቹ ያንበሸበሸ ትልቅ ሰው ነው። በቀደመው ዘመን የሀገራችን የቲያትር ጀርባን ከተመለከቱ፣ ከፊት ተጠቃሽ ከምናደርጋቸው ጥቂቶች መካከል አብሮ የሚቆጠር አንጋፋ ነው። በዋናነት በብሔራዊ ቲያትር እና ማዘጋጃ ቤት፣ የሁለቱ ቲያትር ቤቶች መድረክ ጌታቸውን የለመዱና የተላመዱ ናቸው። በቲያትርና ተውኔት ዘርፍ ጌታቸው አዘጋጅና ጸሐፊ ተውኔት በመሆን ብዙ አበርክቷል። በማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን በትወናውም ብቅ ሲል ይታይ ነበር። ከ50 በላይ የግጥምና ዜማ ድርሰቶቹን ለድምጻውያኑ በማበርከት ስሙን በሙዚቃው ደሴትም አስፍሮታል። ብዙዎች ባያውቁለትም፣ ጌታቸው መጽሐፍ ጽፎም አሳትሟል። ጌታቸው ብዙ አዋቂ፣ ሁለገብ ከያኒ ነው። ለጥበብ በረካ ሆኖ የተፈጠረ ታላቅ ነው። ገጸ በረከቶቹም ተመዘው የማያልቁ፣ ፈሰው የማይደርቁ ናቸው።
ከአዲስ አበባ 50 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ በምትገኘው አዲስ አለም፣ ከነጋዴ ሠፈር ውስጥ ጌታቸው ደባልቄ ተገኘ። ሚያዚያ 28 ቀን 1928ዓ.ም አዲስ አለም ላይ ተወለደ። ፊደል ቆጥሮ ከትምህርት ሕይወቱ ጋር የተዋወቀው በእዚያው የትውልድ መንደሩ ነበር። አስቀድሞ በቤተክርስቲያን ከድጓ እስከ ጾመ ድጓ ዘልቋል። በትምህርት ቤቱ ውስጥ የተለያዩ መዝሙሮች ይዘጋጁ የነበረ ሲሆን፣ ጌታቸውም በእዚህ የመዝሙር ስብስብ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ነበር። ሰኔ 30 ለሚዘጋጀው የወላጆች ቀን መምህራኖቹ የተለያዩ ተውኔትና ድራማዎችን ጽፈው ያዘጋጁ ነበርና ጌታቸው በትወናውም አይታጣም ነበር። በአንድ ወቅት ንጉሠ ነገሥቱ ጃንሆይ አዲስ አለም ላይ በተገኙበት አጋጣሚ ጌታቸው ግጥም አቅርቦ፣ 3 ሽልንግ(አንድ ብር ከሃምሳ) ተሸለመ። በንጉሥ ፊት ቀርቦ ገና በልጅነት ይህን በረከት ማግኘቱ ለእርሱ ትልቅ ስንቅ ነበር።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመቀጠል ከአዲስ አለም ወደ አዲስ አበባ አቀና። አዲስ አበባ ገብቶ፣ የአዲስ አበባን አየር ተላምዶ፣ ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት መማር ጀመረ። ጌታቸው ትምህርቱን ብሎ የመጣ ቢሆንም፤ ከትምህርቱ ጋር ለመዛለቅ ግን አልሆነለትም። ይህቺ ጥበብ የሚሏት ነገር አንድ ጊዜ የለከፈች እንደሆን፣ እርሷ እንደምትፈልገው እንጂ እንደሚፈልጉት ለመኖር አትፈቅድም። ጌታቸው በኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ውስጥ የቆየው ለአንዲት መንፈቅ፣ ለስድስት ወራት ብቻ ነበር።
1944ዓ.ም፣ የ16 ዓመቱ ጌታቸው ኮከበ ጽባህን ትቶ ወደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አመራ። ያ ጊዜ ማለት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ቤት(የአሁኑ ብሔራዊ ቲያትር) ገና በመደራጀት ላይ ነበር። ጥንስሱ የተጣለውም በአዲስ አበባ ማዘጋጃ የቲያትርና ሙዚቃ ክፍል ውስጥ ነው። ታዳጊው ጌታቸው የተቀላቀለውም ይህንን ክፍል ነው። ለብሔራዊ ቲያትር እርሾ በሆነው የማዘጋጃ ቤቱ የቲያትርና ሙዚቃ ማስፋፊያ ክፍል ውስጥ ከነበሩት መካከል አንደኛው ሆነ። እርሱም ራሱን ለጥበብ አስፋፍቶ አመቻቸላት። ምሷን ያገኘች ጥበብም እፎይ አለች።
ከእዚህ ቀደም ውስጡ ያደረውን የትወናና የሙዚቃ ፍቅሩንና አምሮቱን ለመወጣት በግሉ ቢፍጨረጨርም ይህን ዓይነቱን ዕድል ግን አላገኘም ነበር። አሁን የማዘጋጃ ቤቱ የማስፋፊያ ክፍል ለሁሉም ጥሩ ሆነለት። እየሞካከረ በነበራቸው ነገሮች በአንዴ ተመዞ ለመውጣት ባይችልም፣ ለቀጣይ መንገዱ ዓይኖቹን አብርተውለታል። ተሰጥኦውን ለማውጣት ጊዜ አልፈጀበትም። በተለይ በትወናው ለመታየት ችሏል። “የፍቅር ጮራ”፣ “እድሜ ልክ እስራት”፣ “ድንገተኛ ጥሪ” የተሰኙትን ጨምሮ ሌሎች ቲያትሮች ላይም የትወና ብቃቱን አስመስከሯል። ግን ድንገተኛ የጥበብ ጥሪ ከሌላ አቅጣጫ ደረሰው።
ከሁለት ዓመታት በኋላ፤ በ1947ዓ.ም ጉዞውን ከማዘጋጃ ቤት ወደ ብሔራዊ ቲያትር የሚያደርግበት አጋጣሚ ተፈጠረ። 1948ዓ.ም ብቅ ላለው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ቤት ምልመላው ተጀምሮ ነበር። በወቅቱ ለቲያትር ቤቱ የመጀመሪያው ዳይሬክተር ተደርገው የተሾሙት ኦስትሪያዊው ፍራንስ ዞልቬከር ለቲያትር ቤቱ 20 መሥራች አባላትን አሠልጥነው ነበር፤ ከሃያዎቹ አንደኛው የ20 ዓመቱ ጌታቸው ነው። በቲያትር ቤቱ የምረቃ ዝግጅት ላይ የሚታይ አንድ ቲያትር፣ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ጻፉ። ቲያትሩም “ዳዊትና ኦሪዮን” ይሰኛል። የቲያትሩ አዘጋጅ ደግሞ ዳይሬክተሩ ፍራንስ ዞልቬከር ነበር። ለአዲሱ ቲያትር ቤትና ለመድረኩም የመጀመሪያው በሆነው በእዚህ ቲያትር ላይ ጌታቸው ደባልቄም ተውኖ በኩርነቱን አሳይቷል።
ሁሉም ሰው፣ ሁሉም ጥበብ የራሱ የሆነ ቦታና ጊዜ አለው። ትልቁ ስኬት የሚጀምረውም ይህንን ቦታና ጊዜ ከማወቅና ከማግኘት ነው። ጌታቸውም አወቀበት፤ ቦታውንም አገኘ። ለርሱ የተጻፈችው ትክክለኛዋ ቦታ ብሔራዊ ቲያትር እንደሆነች ልቡስጥላው ነግሮታል። የነገረውም ሆነ ያመነው ስህተት አነበረም፤ የውስጡ እሳት መንደድ፣ ተሰጥኦው መመዘዝ ጀመረ። ልቡ በፍቅር በወደቀባቸው፣ በትወናና በሙዚቃ ዘርፎች ውስጥ ጌታቸው ቁልፍ ሰው እየሆነ መጣ። የሚዝግ፣ የሚሰበር ወይንም ለመክፈት የሚያስቸግር ቁልፍ አነበረም። ውስጡ ያለች ጥበብ ለራሱም ሆነ ለሌሎች ቅን ነበረች።
ጌታቸው ደባልቄ ብሔራዊ ቲያትር ቤት ውስጥ ተዋናይ፣ አዘጋጅ ወይንም ሙዚቀኛ ብቻ አይደለም። ቀናዒ ጥበቡ ሁሉንም ጉዳዮች ‹ይመለከተኛል› በሚል ስሜትና የኃላፊነት መንፈስ ነበርና የሚንቀሳቀሰው፤ በጊዜው እምብዛም ብቅ የማይለውን ተመልካች ለመሳብ ቅስቀሳም ያደርግ ነበር። ዝግጅቶች በሚኖሩ ጊዜ ከብሔራዊ ቲያትር ወደ መንገድ ወጣ ይልና ወጪ ወራጁን በዘፈን እያዝናና ቲያትሩን ያስተዋውቃል። አንዳንዴ የተመልካቹን ልብ ለመርታት እንዲህ በመንገድ ዳር ሲታገል ቲያትሩ የሚጀመርበት ሰዓት ይደርሳል። የገባው ተመልካች ሁሉ ገብቶ፣ በቲያትሩ ውስጥ የሚተውነው ጌታቸው ግን እዚያው በመለፈፍ ላይ ነው። ቲያትሩን የሚያቀርቡ ሁሉ ለባብሰው፣ አስተዋዋቂው ከመድረክ ወጥቶ…ጌታቸው አሁን ገና ሲሮጥ ይመጣና በፍጥነት ልብሱን ቀያይሮ ይዘጋጃል። ለሥራው ያለው ትጋትና ለሙያው ያለው ፍቅር የተለየ ነው። ማንም አስገድዶት ሳይሆን ለጥበብ ከነበረው ቀናተኛነት የተነሳ ወርዶ ተመልካቹን የመቀስቀስ ግብር ይፈጽም ነበር።
የጌታቸው አንዲት የግጥምና ዜማ ሥራው በውድድር መድረክ ላይ ወጥታም ነበር። ጊዜው በ1954ዓ.ም፣ ወሩ ጳጉሜን 5፣ ዕለቱም የአዲስ ዓመት ዋዜማ ነበር። ብሔራዊ ቲያትርን ጨምሮ የተለያዩ ኦርኬስትራዎች፣ በመሣሪያ፣ በግጥምና ዜማ፣ በድምጽ፣ በግልና በቡድን የተደረገ የሙዚቃ ውድድር ነበር። የብሔራዊ ቲያትሩ ጌታቸው ደባልቄም “የእኔ ሃሳብ” የምትለዋን ግጥምና ዜማ ለውድድር አቀረባት። በድምጽ የተጫወታት ሌላ ሰው ቢሆንም ሙዚቃዋ ግን አሸነፈች። ለብሔራዊ ቲያትርና በአጠቃላይ በሙዚቃዋ ለተሳተፉ በድምሩ ከተሰጠው 250 ብር፣ ሃያ አምስት ብሯን ጌታቸው ተሸለማት።
ጌታቸውን ‹ተንቀሳቃሹ ቤተ-መዘክር› ብለው እንዲጠሩት ያደረገው ነገር ምንድነው? ጌታቸው ሲበዛ ታሪክ አዋቂ ነበር፤ በተለይ የኢትዮጵያን የኪነ ጥበብ ታሪክ በተመለከተ ውር! የምትል ዝንብ እንኳን አታመልጠውም። እያንዳንዱን ጉዳይ እግር በእግር እያስከተለ ሲተነትን አፍ የሚያስከፍት ነው። ተንቀሳቃሽ ቤተ መዘክርነቱ በተለይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ነው። የቲያትር ቤቱ ሕንጻ ሲገነባ አንስቶ ዐሻራና ማህደሩ፣ ስምና ዝናው አለበት። በኪነ ጥበብም ሆነ በተቋማዊ አደረጃጀቶች ውስጥ ሲደረጉ የነበሩ እያንዳንዱን ርምጃዎች በአዕምሮው ማህደር ውስጥ ሰንዷቸዋል። እናም ብሔራዊ ቲያትር በተመለከተ መረጃና ማስረጃ የሚሹ ሁሉ በቅድሚያ የሚያመሩት ወደ ጌታቸው ደባልቄ ዘንድ ነው። እርሱ ግን ለየትኛዎቹም ጥያቄዎች ሌላ መዛግብት ማገላበጥ አያስፈልገውም፤ ሁሉንም በብልት ብልቱ ከደረደረበት ከጭንቅላቱ እየመዘዘ ከነትዝታዎቹ ያስቀምጣቸዋል። ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን በጻፋቸው ታሪካዊ ተውኔቶች ውስጥ የጌታቸው ደባልቄ የታሪክ ዕውቀት የታከለባቸው ናቸው።
በ1944ዓ.ም ከኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ወደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፣ ከማዘጋጃ ቤት ወደ ብሔራዊ ቲያትር በመዘዋወር የጥበብን ከራማና ውቃቤ ለማስደሰት ሲምስላት የኖረው ጌታቸው ደባልቄ የዋለላት ብዙ ነው። ሃምሳ ትወደዋለች ወይ ይወዳታልና ከትውልድ ቀዬው 50 ኪሎ ሜትር ርቆ እንደመጣው ሁሉ በጥበብ ቤት የቆየውም ለ50 ዓመታት ነበር። 50 የግጥምና ዜማ ድርሰቶችን አስደምጧል። 52 ቲያትሮች ላይ ተውኗል። በጊዜው በብሔራዊ ቲያትር ከነበሩ የቲያትር አዘጋጆች አንዱም ነበርና 15 ያህሎቹን በአዘጋጅነት ሠርቶባቸዋል። ከአዘጋጅነት፣ ከትወና አልፎም 10 ድርሰቶችን ማበርከት የቻለ ጸሐፊ ተውኔትም ጭምር ነው።
ጌታቸው በድርሰቱ ረገድ “በድሉ ዘለቀ” የተሰኘው ቲያትር ለመጀመሪያ ጊዜ ጸሐፊ ተውኔትነቱን ያሳየባት ሥራው ናት። የቀረበችውም ሆነ የጻፋት በማዘጋጃ ቤት ሳለ ነበር። “የፍቅር ሰንሰለት”፣ “የሮምነሽ”፣ “ያስቀመጡት ወንደ ላጤ” እና “ደህና ሁኚ አራዳ” የተሰኙት ደግሞ ከብሔራዊ ቲያትር አበርክቶዎቹ መካከል ናቸው። በትወናው ደግሞ በብዙ ቲያትሮችና ተውኔቶች ተሳትፏል። ለአብነትም ቢትወደድ እንዳልካቸው መኮንን በደረሰውና ፍራንስ ዘልቬከር ባዘጋጀው “ዳዊትና ኦርዮን” በተሰኘው ቲያትር ላይ ጌታቸው በትወና ተሳትፎበታል። በመንግሥቱ ለማ “ጠልፎ በኪሴ” ላይም ተውኗል። “ዋናው ተቆጣጣሪ” በሚለው የኒኮላይ ጎግል ተውኔት ውስጥ ጌታቸው ድንቅ የትወና ብቃቱን አሳይቶበታል። እኚህ ብቻም ሳይሆኑ የከበደ ሚካኤልን “ሃኒባል” እና የጸጋዬን “ሀሁ በስድስት ወር” የተሰኙት የተወነባቸው ናቸው። የአዛውንቶች ክበብ፣ ተሀድሶ፣ ሻጥር በየፈርጁ፣ በቀይ ካባ ስውር ደባ እርጉም ሐዋሪያ እና ሌሎችም ይገኙበታል። ስሙን ካነሱ የከርሞ ሰው፣ ቴዎድሮስ፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ በልግ፣ ስነ ስቅለት፣ ኦቴሎ…አንድ በአንድ እየተግተለተሉ ከቲያትር ተውኔት ሰማይ ስር ይታያሉ። “በንጉሥ አርማህ” ከጡረታ በኋላ የተወነባት የመጨረሻው ነበረች።
ጌታቸው የቲያትር ብቻ ሳይሆን የሙዚቃም ሰው ነው። ከገጠመ ከልቡ የሚገጥም የግጥምና ዜማ ደራሲ ነው። ስለ ግጥምና ዜማ ደራሲነቱ ጥላሁን ገሠሠ፣ ማህሙድ አህመድ፣ ግርማ ነጋሽ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ጠለላ ከበደ እና ብዙዎች የሚመሰክሩለት ነበሩ። ውብ ሙዚቃዊ ጨዋታዎቻቸው ይመሰክራሉ። ከእነርሱ ድምጽ ውስጥ ሙዚቃዎቹን የሰማን ማናችንም ልንመሰክረለት እንችላለን።
“ምነው ተለየሽኝ መስከረም ሳይጠባ
ዕንቁጣጣሽ እያልን ሳናጌጥ በአበባ…”
የምትለዋን ዜማ ከግርማ ነጋሽ ድምጽ ጋር ተመቻችታ እንድትሄድ አድርጎ የቀመራት ጌታቸው ነው። “እንገናኛለን” እና “አልበቃኝም” የሚሉ ሌላ ሁለት ሥራዎችንም ሰጥቶታል። “አደረች አራዳ” እና “አልማዝዬ አሰብኩሽ” በምኒልክ ወስናቸው ተቀንቅነዋል። “ዓለም እንዴት ሰነበተች” የሚለውን ግጥምና ዜማ ደግሞ ለብዙዎቻችን ድምጻዊም ጭምር የነበሩ ለማይመስሉን ተስፋዬ ሳህሉ(አባባ ተስፋዬ) ሰጥቶ ተጫውተውት ነበር። “ፍቅር እውር ነው አትበሉ” የተሰኘው የመኮንን በቀለ ዜማም አለ። “በል ተነሳ” የሚለውን ሥራ ያገኘችው አስናቀች ወርቁ ግን የጌታቸውን 9 ግጥምና ዜማዎችን በመጫወት ግንባር ቀደሟ ናት። መዘዝ ያስከተለው የጠለላ ከበደ “ሎሚ ተራ ተራ” የሚለው ሙዚቃም አለ። በእዚህ ሥራ የተነሳ ጌታቸው ደባልቄ በዘመነ ደርግ ወህኒ ቤት ወርዷል። ነገርዬው በቀላሉ አልታለፈም ነበርና የ4 ዓመታት እስር ለመከናነብ ተገዶ ነበር።
ግን ‹ሁሉም ለበጎ ነው› ማለትም እንዲህ ነው፤ በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ ሲያወጣና ሲያወርድ አንዲት መጽሐፍ የመጻፍ ሃሳብ ተከሰተችለት። ርዕሱንም “ደንቆሮ በር” አለው። በእስር በከረመባቸው አራት ዓመታት በእስር ቤቱ ውስጥ የተመለከታቸውን፣ የሰማቸውንና ያጋጠሙትን ነገሮች ሁሉ ሰብሰብ አድርጎ ለመጽሐፍነት አበቃው። ምንም እንኳን በአነስተኛ ገጾች የተቀነበበች ብትሆንም እንደ ግለታሪክ ጥሩ ተዋጥቶላታል። ጌታቸው ግን ሌላም መጽሐፍ ጽፏል። መጽሐፉ የተስፋዬ ሳህሉን(አባባ ተስፋዬን) እና የአስናቀች ወርቁን የሕይወት ታሪክ የሚዳስስ ነው። ከልጅነት እስከ እውቀት በሥራዎቻቸው ያበረከቷቸውን ገጸ በረከቶችን ጨምሮ የሕይወት ጉዟቸውን የሚያስቃኝ ድንቅ ሥራ ነው። ደግሞ ሌላም አለው “ያስቀመጡት ወንደላጤ” ‹ህብረ ሰብአዊ ቲያትር ነው› ይላታል። በውስጧ የቲያትር ገጸ በረከቶቹን የተሸከመች መጽሐፍ ናት።
ብሔራዊ ቲያትር ቤት በጌታቸው ልብ ውስጥ የተለየ ስፍራ የነበራት መናገሻው ነበረች። ስለ ቤቱ ከነበረው ቀረቤታና የጠለቀ መረጃ መጽሐፍ ለማውጣትም ብዙ አሰላስሏል። በእዚያ እንደ አንድ የጥበብ ባለሙያ ቲያትርና ሙዚቃ ሲያዘጋጅ፣ ሲተውን ብቻ አልነበረም ያሳለፈው። በአንድ ወቅት የቲያትር ክፍሉ ኃላፊም ነበር። በፕሮዳክሽን ክፍል ውስጥም ቀላል የማይባል ኃላፊነት ነበረው። እንዲሁም እስከ 1966ዓ.ም ድረስ በሕዝብ ግንኙነት ክፍል ውስጥ ኃላፊ ሆኖ ሲሠራ ነበር።
ወደኋላ መለስ ብለን የጌታቸውን እንቅስቃሴዎች ከጊዜው ጋር ስንመለከተው አንድ ነገር እንድንመሰክርለት ያደርገናል። ከጥበብ ጋር የተቆራኘበት 1940ዎቹ አጋማሽ አብዛኛዎቹ ጥበባት ገና አፈር ምሰው በመነሳት ላይ የነበሩበት ነው። በ1950ዎቹ ሕይወት ዘርተው ማቆጥቆጥ የጀመሩበት ነው። የወርቃማው ዘመን ቅርንጫፎች ልምላሜም ከእዚህ የሚጀምር ነው። ጌታቸውን እዚህ ውስጥ ስንፈልገው፣ ከቁር እስከ ወላፈኑ ድረስ አብሮ ነበር። ከወርቃማው ዘመን በፊትም በኋላም ነበር። በእዚያ ወርቃማ ዘመን ከጥበባት መካከል ቲያትር፣ ሙዚቃ እና ሥነ ጽሑፍ ዋነኞቹ ግንባሮች ነበሩ። ጌታቸው ደግሞ በሦስቱም ግንባሮች ውስጥ ነበረበት። ብዙዎች በአንደኛው ወይም በሁለቱ ታላላቅ የጥበብ ጀብዱ አኑረዋል። እንደ ጌታቸው በሦስቱም የድል ተራሮች ቆመው የታዩ ጥቂቶች ብቻ ናቸው። እናም ለእዚህ ከያኒ አንድ የተለየ ቦታ፣ የተለየ ክብር፣ የተለየ ኒሻን የሚገባው አይመስለንም?
የኢትዮጵያ ሥነ ጥበባት እና መገናኛ ብዙኃን ያዘጋጀው በነበረው ዓመታዊ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የ1994ዓ.ም የኢትዮጵያ የተውኔት ዘርፍ የሕይወት ዘመን አሸናፊ፣ ጌታቸው ደባልቄ ነበር። በእዚህ የወርቅ ተሸላሚ ሆኗል። ካጠለቀው የወርቅ ሜዳሊያ በተጨማሪ የሃያ ሺህ ብር የገንዘብ እና የዕውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶለታል። ብቸኛው ሽልማቱ ባይሆንም፤ ለእርሱ ግን የትኛውም የሚያንሰው እንጂ የሚበዛበት አይደለም።
በመጨረሻም ሁሉንም ለእኛ ትቶ፣ እርሱ ከማይቀርበት ሄዷል። የሦስት ልጆች አባት፣ የብዙ ጥበብ ባለቤት ነበር። የካቲት 24 ቀን 2011ዓ.ም ሩጫውን ፈጸመ። በ83 ዓመቱም ሞተ። አሁንም ከጥበብ በረከቶቹ ይድረሰን።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም