
አዲስ አበባ፡– ከ2014 እስከ 2016 ባለው ጊዜ በፌደራል ፖሊስ የተመዘገበው ባልታወቀ ተሽከርካሪ የደረሰ የትራፊክ አደጋ ብዛት 2 ሺህ 136 መሆኑን ተጠቆመ፡፡ የጉዳት ካሣ የተከፈላቸው ተጎጂዎች ለስድስት በመቶ ብቻ መሆኑን የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ገለጸ፡፡
በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት የሂሳብ የፋይናንስ የሕጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት አቅርቧል፡፡
ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት እና የሦስተኛ ወገን የመድን ፈንድ አገልግሎት አፈፃፀም በተመለከተ ኦዲት ሲደረግ ባልታወቁ ተሽከርካሪዎች 2ሺህ 136 የትራፊክ አደጋ ቢደርስም የጉዳት ካሣ የተከፈለው ለስድስት በመቶ (128) ብቻ ነው፡፡ በአዋጁ መሠረትም አብዛኛው ተጎጂዎች የጉዳት ካሣ ያልተከፈላቸው መሆኑም ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት የተሽከርካሪ ብዛት ለማወቅ የተደራጀ ትክክለኛ መረጃ ባይኖርም፤ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ እና ትራንስፖርት ሚኒስቴር ተጠይቆ በሰጡት ምላሽ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተሽከርካሪ መኖሩንና ከዚህ ውስጥ 962 ሺህ ተሽከርካሪ (69 በመቶ) ብቻ የመድን ሽፋን ያላቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ቀሪዎቹ 438ሺህ ተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን የሌላቸው መሆኑም ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል፡፡
በሲዳማ ክልል ብቻ ካሉት 40 ሺህ ሞተር ሣይክሎች ሁሉም የመድን ሽፋን የሌላቸው እና 12 ሺህ ብቻ ሕጋዊ መንጃ ፈቃድ ባላቸው ሰዎች የሚሽከረከሩ መሆኑ ጠቁመው፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያሉ ሞተር ሣይክሎች በአብዛኛው በሕገወጥ መንገድ የገቡ መሆኑን የክልሉ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮና ትራፊክ ፖሊስ የገለፁ ሲሆን ትክክለኛ ብዛታቸውን ለመግለጽ የሚያስችል መረጃ የሌላቸው መሆኑም አብራርተዋል፡፡
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከጉምሩክ ኮሚሽንና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በመተባበር በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ፣ ያለሕጋዊ መንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩ እና የ3ኛ ወገን መድን ሽፋን የሌላቸው ሞተር ሳይክሎች ላይ መፍትሔ እንዳልወሰደም ተናግረዋል፡፡
እንደ ዋና ኦዲተሯ ማብራሪያ፤ በአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 799/2005 ላይ በተደነገገው መሠረት የሦስተኛ ወገን መድን ባልተገባለት ወይም ባልታወቀ ተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ሰው አስቸኳይ ሕክምና እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል፡፡ የአካል ጉዳት የደረሰበት ሰው ካሣ እንዲከፈለው ማድረግ ወይንም በአደጋው ለሞተ ሰው ቤተሰብ አባላት ካሣ እንዲከፈለው ማድረግ ይገባል፡፡
ነገር ግን የፌዴራል መንገዶች፣ በክልል ደረጃ ወረዳን ከወረዳ ከሚያገናኛቸው መንገዶች ውጪ ያለ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና ግንባታቸው ተጠናቆ ርክክብ ባልተደረጉ መንገዶች ላይ በሚያሽከረክሩ ተሽከሪካሪ ለሚከሰት የትራፊክ አደጋ ፖሊስ የአደጋ ሪፖርት ማረጋገጫ ስለማይሰጥ ተጎጂው የጉዳት ካሣ እና ነፃ የ3ኛ ወገን አስቸኳይ ሕክምና ተጠቃሚ አለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች የሚፈፅምላቸውን የካሣ ክፍያ ኃላፊነት ከተሰጣቸው አካላት አደጋው እንደደረሰ ወዲያውኑ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ተመላሽ ሊያስደርግ የሚገባ ቢሆንም፤ ገጭተው ባመለጡ እና የ3ኛ ወገን በሌላቸው ተሽከርካሪዎች ከ2005 እስከ 2016 በጀት ዓመት በደረሱት የትራፊክ አደጋዎች ለ555 ተጎጂዎች ብር 16 ሚሊዮን 51ሺህ 275 ክፍያ መፈጸሙ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የ44 ተጎጂዎች ብር 1ሚሊዮን 937ሺህ 857 የካሣ ክፍያ ብቻ ተመላሽ የተደረገ መሆኑም ጠቁመዋል፡፡
በየዓመቱ የትራፊክ አደጋ ደርሶባቸዋል ተብሎ በጤና ሚኒስቴር የሚቀርቡ መረጃዎች ከፌዴራል ፖሊስ እና ከመንገድ መድኅን ፈንድ አገልግሎት የተያዙት መረጃዎች የማይጣጣሙ እና የጤና ሚኒስቴር መረጃ ከሁለቱ ተቋማት ብልጫ የሚያሳይ ነውም ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት እየተሠራበት ያለው የደኅንነት ቀበቶ መመሪያ ቁጥር 36/2012 መሠረት ሚኒባሶች፣ የሕዝብ ማመላለሻዎች፣ ከአምስት እስከ ስምንት መቀመጫ ያላቸው ተሽከርካሪዎች እና ረጅም ርቀት የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች የደኅንነት ቀበቶ እንዲኖራቸውና ተሳፋሪዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚወስን ቢሆንም ተግባራዊ ያልተደረገ መሆኑም ዋና ኦዲተሯ አስታውቀዋል፡፡
ዋና ኦዲተሯ በንግግራቸው፤ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የመንገድ ዳር ምልክቶች እና የፍጥነት መቆጣጠሪያ የሚሠራበት ስታንዳርድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ሊያደርግ እና፣ ለኅብረተሰቡ ስለምልክቶቹ ግንዛቤ ሊሰጥ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት እየተሠሩ ያሉ የፍጥነት መቆጣጠሪያ በመስፈርቱ (በስታንዳርድ) መሠረት የተሽከርካሪውን ከፍታ ያልጠበቁ፣ ዜብራ ምልክቶች ያልተቀቡ እና የፍጥነት መቆጣጠሪያ መኖሩን አመልካች ምልክቶች ያልተተከለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም