ኪነጥበብ ለሀገር ያለው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ነው። ዘርፈ ብዙ ነው ሲባል በሀገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እና ዕድገት ላይ መልከ ብዙ ሚና እንደሚኖረው እና የገዘፈ ጥቅም እንደሚያስገኝ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው። ለአብነት እንደህዳሴ ግድብ ያሉ ታላላቅ ሀገራዊ ልማቶች በኪነጥበብ ተደግፈው ዛሬ ላይ እንደደረሱ የሚታወቅ ሐቅ ነው።ከተዝናኖት ባለፈ በጎ ማንነቶችን ከማስተዋወቅ እና ትውልድ በመቅረጽ አኳያም ኪነጥበብ ሊጠቀስ የሚችል ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሃሳብ ሊያጋሩን የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የኪነጥበብ ሀብቶች ልማት መድረኮች እና ኹነት ዝግጅት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ደኑ ከአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ አድርገዋል። የሚመሩት የኪነጥበብ ቢሮ የሥራ ኃላፊነት ምን እንደሆነ በመግለጽ ወጋችንን ጀምረናል።
ባህል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ዘርፍ፣ የኪነ ጥበብ እና የቱሪዝም ዘርፍ በሚል በሦስት የተከፈለ ነው። እያንዳንዱ ዘርፍ የራሱ ዓላማ አለው። በተለይ ከኪነ ጥበብ ዘርፉ ጋር በተያያዘ ሲታይ በዋናነት የሚሠራው በከተማው ውስጥ የሚገኙ የጥበብ ዘርፎች እውቅና እንዲያገኙ፣ ድጋፍ እና መድረክ እንዲመቻችላቸው፣ ከታች ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ኪነጥበቡን ማስተሳሰር እንደሆነ ይገልጻሉ።
የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ በየዓመቱ በርካታ ፌስቲቫሎችን እንደሚያካሄድ ገልጸው፤ ለአብነት የቱሪዝም ሳምንት፣ የባህል ፌስቲቫሎች እንዲሁም በዓመቱ መጨረሻ ላይ የሚካሄደውን የኪነጥበብ ሳምንት ጠቅሰዋል። የኪነጥበብ ፌስቲቫሉ በባህል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ስር ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት ሲከወን መቆየቱን አንስተው፤ ከአምስት ዓመታት ወዲህ ግን የኪነጥበብ ዘርፉ ከባህል ውጪ ራሱን ችሎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።በእነዚህ አምስት ዓመታት ውስጥ የኪነጥበብ ዘርፉ የራሱን መሪ ቃሎች በመቅረጽ ዝግጅቶችን ሲያካሄድ ቆይቷል።
እነዚህ መሪ ቃሎች የሚቀረጹት ደግሞ በየዓመቱ ያሉትን ልዩ ሁኔታዎች እና አጋጣሚዎች ታሳቢ በማድረግ በተለይም ኪነጥበቡን ሊያጎሉ እና ሊጠቅሙ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ ገልጸው፤ በዚህም መሠረት ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት የኪነጥበብ ቬስቲቫል ሳምንት ሲካሄድ መቆየቱን ጠቁመዋል።
የኪነጥበብ ሳምንት ፌስቲቫል በዋናነት ከወረዳ እስከ ማዕከል ድረስ የሚገኙ አማተር የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ተማሪዎች፣ እንዲሁም ፕሮፌሽናል የሚባሉ አንጋፋ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት፣ የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት የኪነጥበብ ቬስቲቫል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህ የኪነጥበብ መድረክ ላይ በርካቶች ከመሳተፋቸው አንጻር ውድድሮችን በማዘጋጀት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እንደሰሩ ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ከግንቦት 15 እስከ ግንቦት 17 ድረስ በሃገር ፍቅር ቲያትር ቤት እንደዚሁ በመስቀል አደባባይ እና በኤግዚቢሽን ማዕከል ከሰኔ 7 እስከ ሰኔ 9 ድረስ ተከታታይ ፌስቲቫሎችን ማካሄዳቸውን ጠቁመዋል።
ባሳለፍነው የኹነት መድረክ ላይ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫሉ መሪ ቃል ‹‹ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት›› የሚል ሲሆን፤ ይሄን መሪ ቃል መሠረት በማድረግ ባለፉት አምስት ወራት ከወረዳ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን አንስተዋል። ከዚህ ሁሉ ጋር ተያይዞ የኪነጥበብ ፌስቲቫል ዋና ዓላማ በሚል የተያዙ ነጥቦች መኖራቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህ ዓላማዎች መካከል በኪነ ጥበብ ዘርፍ ላይ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ባለሙያዎች መድረክ የሚያገኙበትን ዕድል ማመቻቸት፣ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ማዕከል ድረስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ለኪነጥበብ ባለሙያዎች ተሰጥዖዋቸውን የሚያዳብሩበት መድረክ ይሠጣል። እንደዚሁም አንጋፋ ባለሙያዎች ልምዳቸውን ለተተኪዎች የሚያካፍሉበት ዕድል እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
አማተር እና ነባር የኪነጥበብ ከያኒያንን በየደረጃቸው በማወዳደር እውቅና እንደሚሰጡ በእውቅናው መሠረት ደግሞ እየተበረታቱ የሚሄዱበትን መድረክ የማመቻቸት ሥራ ከዓላማቸው አንዱ እንደሆነም አንስተዋል። ሌላው በብዙዎች እንደሚታወቀው ከተማው ውስጥ በተለይ በኪነ ጥበብ ዘርፉ ላይ የሚካሄዱ ሥራዎች ከማዝናናት ባለፈ በጣም በርካታ አስተዋፅዖ እንዳላቸው ገልጸው፤ የኪነ ጥበብ ሳምንት ቬስቲቫሉ ደግሞ በተለየ ሁኔታ ብዙዎች የሚገኙበት ከወረዳ እስከ ማዕከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ወደ አምስት መቶ ሺህ የሚጠጋ ማኅበረሰብ ይሳተፍበታል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም በከተማዋ በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ እነዚህ ግለሰቦች ባለድርሻ አካላት ናቸው። እነሱም በዚህ የኪነጥበብ ፌስቲቫል ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ሥራዎችን ለሕዝብ እንዲያቀርቡ ይደረጋል ብለዋል። በአጠቃላይ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫሉ ዋነኛ ጠቀሜታ፤ ቀደም ሲል በዓላማው ላይ እንደጠቀሰው ተተኪ የኪነጥበብ ትውልድን መፍጠር መሆኑን አስታውሰው፤ በከተማዋም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች በተለያየ ዘርፍ ላይ የሚሠሩ በርካታ አማተር ክበባት መኖራቸውንም ተናግረዋል። ለእነዚህ ክበባት ከኪነጥበብ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በጋራ በመሥራት የተሻለ ዕድል እንደሚፈጠርላቸው ገልጸዋል።
እንደዚሁም በሚቀረጹት መሪ ቃሎች አማካኝነት የሚኖሩ ውድድሮች፣ ዓውደ ርዕዮች በሀገሪቱ እና በከተማዋ ውስጥ ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን እንዲያሳዩ መነሻ መንገድ በመሆን፤ በማኅበረሰቡ ላይ ንቃትን በመፍጠር አይነተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ ብለዋል። ከተማዋ አሁን ባላት ሁኔታ በጣም በርካታ የገጽታ ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ ያሉት አቶ ሰለሞን፤ እነዚህ የገጽታ ግንባታ ሥራዎች በኪነጥበብ ዘርፉ በኩል እየታዩ የሚሄዱበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።
በሚኖሩ አጠቃላይ ዝግጅቶች ማኅበረሰቡን በማሳተፍ፣ የወንድማማችነት መንፈስን በመፍጠር ኪነጥበብን ለአንድነት እና ለአብሮነት ዓላማ ከማዋል አኳያ ለበጎ ነገር እየሠሩ እንደሚገኙ አመላክተዋል። ከዚህ ባሻገር ሃያ አንድ የሚደርሱ የተለያዩ የውድድር ዘርፎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ እንደአጠቃላይ ትስስርን እና ኅብረትን በመፍጠር አንዱን ከአንዱ በማስተዋወቅ በጎ ነገር ያበረክታሉ ብለው እንደሚያስቡ ነግረውናል።
‹‹ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት›› የሚለው መሪ ቃል፤ የኪነጥበብ ባለሙያውን ከሌላው ጋር የሚያስተሳስር መሪ ቃል ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በፌስቲቫሉ ላይ ወደአምስት የሚጠጉ ተግባራት ተፈጽመዋል። የመጀመሪያው የአዲስ አበባ የሥነጥበብ ውድድር ነው። ቀደም ሲል እንደተገለፀው፤ በሀገር ፍቅርም ሆነ በመስቀል አደባባይ እና ኤግዚቢሽን ማዕከል በተካሄዱ ፌስቲቫሎች በዕይታዊ ኪነጥበባት፣ በክውን እና መልቲሚዲያ ጥበባት፤፣ በሥነ ጽሑፍ ዘርፎች በርካታ ውድድሮች እንዳካሄዱ አመላክተዋል።
ከስብጥር አንጻር ሲታይ ትምህርት ቤቶች አሉ። አማተር ክበባት፣ የባህል ቡድኖች፣ በግል የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት የሚሳተፉበት እንደሆነ ጠቁመው፤ ፊላ ከሙዚቃ በላይ የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ የሚቀርብበት ‹‹ኅብራዊነት በኢትዮጵያ ሥነጥበብ ውስጥ›› የሚል የሲምፖዚየም መድረክ እንደነበርም አንስተዋል። የፌስቲቫሉ አንድ አካል የሆነው ጥናታዊ ጽሑፉ በጊዮን ሆቴል ከማለዳው ጀምሮ መቅረቡን ገልጸዋል።
ጥናቱ ደራሼ ድረስ በመሄድ ፊላ የሙዚቃ መሣሪያ ላይ የተጠና ጥናት መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ባህላዊ እና ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ከማስተዋወቅ፣ ከመጠበቅ፣ እውቅና ከመስጠት አኳያ ፌስቲቫሉ አስተዋፅዖ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የፊልም ፌስቲቫል መካሄዱንም አንስተውልናል። ይሄ የፊልም ፌስቲቫል የአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ከፊልም ፕሮዲውሰር ማኅበር ጋር በመተባበር የተሠራ ሲሆን፤ በሦስቱ የመንግሥት ሲኒማ ቤቶች (በሲኒማ ኢትዮጵያ፣ በሲኒማ አምፒር እና በአምባሳደር ሲኒማ) የተመረጡ ፊልሞችን ማኅበረሰቡ በነፃ እንዲያይ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።
ከፊልሞቹ መካከል በ1957 ዓ.ም የተሠራው የመጀመሪያው ፊልም ‹‹ሂሩት አባቷ ማነው?›› የሚለው በዚህ ፌስቲቫል ላይ ለተመልካች ቀርቧል። እንደዚሁም በ1984 ዓ.ም ተሠርቶ በአሁኑ ሰዓት በቢሯቸው ዲጂታላይዝ የተደረገው፤ ‹አስቴር› ፊልም እንደዚሁ በመድረኩ ላይ ለዕይታ መቅረቡን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
እነዚህ ፊልሞች ከቆይታ ዘመናቸው እና ከሌሎች ተያያዥ ሁኔታዎች ጋር ለማኅበረሰቡ ቅርብ ያልነበሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከቀደምትነታቸው አኳያ በጀት በመመደብ፣ ዲጂታላይዝ በማድረግ ማኅበረሰቡ እነዚህን ፈልሞች የሚመለከትበትን ዕድል ተፈጥሮለታል ብለዋል።
የድሮ ፊልሞች ተደራሽነታቸው አናሳ በመሆኑ ብዙዎች ጋር የመድረስ ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው። ከይዘትም ሆነ ከጥራት አኳያ ተጠብቀው ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ፣ የቀድሞውን ጊዜ ፈጠራም ሆነ የኪነጥበብ ማንነት የአሁኑ ትውልድ እንዲገነዘበው ለማድረግ እየተሠራ ነው። ከሚሠሩት ሥራዎች መካከል በጀት በመመደብ ግሪክ ሀገር ድረስ ተልከው ዲጂታላይዝ እንዲደረጉ በማድረግ ረገድ ቢሯቸው በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ጠቁመዋል። ከነዚህ ከሁለቱ ፊልሞች ሌላ ሌሎች ተጨማሪ ፊልሞችም በመድረኩ ላይ ለዕይታ እንደቀረቡ ጠቁመዋል።
እንደዚሁም ‹‹ትላንት ዛሬና ነገ›› የሚል መነሻ ሀሳብ በመስቀል አደባባይ ምሽት ፕሮግራም ላይ የሚዘጋጁ የሙዚቃ ኮንሰርቶች የዲስኩር እና የሥነጽሑፍ ምሽቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት፣ የሥነ ጥበብ ማኅበራት፣ የግል ዘርፍ እና የተለያዩ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት፣ የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ማኅበር፣ ሴት ሰዓሊያን ማኅበር፣ ማሠልጠኛ ተቋማት የተጋበዙበት እንዲሁም የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይን ጨምሮ ትልቅ የስዕል ኤግዚቢሽን በምሽቱ የመስቀል አደባባይ ዝግጅት ላይ እንደተከናወነ ነግረውናል።
ሌላው የፌስቲቫሉ አንድ አካል የሆነው በሳምንቱ የተካሄደው ‹‹ዛሬን ለነገ›› በሚል መነሻ ሃሳብ የተዘጋጀው ፌስቲቫል የሚጠቀስ ሲሆን፤ አንጋፋ የኪነጥበብ እንግዶችን ያሳተፈ እና እውቅና ያሰጠ መድረክ እንደነበር ገልጸዋል። በፌስቲቫሉ ላይ ከአንድ እስከ ሦስት የወጡ ተወዳዳሪዎች የተለየ እውቅና ያገኙበት እንዲሁም ሽልማት የተሰጠበት ልዩ የማጠቃለያ መርሐ ግብር መሆኑን ጠቁመዋል።ከአካታችነት አኳያ የኪነጥበብ ፌስቲቫሉ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ያሳተፈ እንደሆነ ጠቁመው፤ በተለይ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል። ሳምንታዊ ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ የሚካሄዱ ዝግጅቶች ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል የነኩ፣ ያቀፉ፣ ያሳተፉ እንደሆኑ አንስተዋል። በሀገር ፍቅር ሲኒማ ቤት በተደረገው ዝግጅት ላይ መስማት የተሳናቸው ባለተሰጥዖዎች በድራማ የተሳተፉበትን አጋጣሚ አስታውሰው፤ እንደመስቀል አደባባይ ባሉ ሌሎች ዝግጅቶች ላይ በዘመናዊ ዳንስ፣ በባህል ውዝዋዜ እንዲሁም በስዕል የተሳተፉ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ከዚህ በፊት ከነበረው በቁጥርም፣ በልምድም ከፍ ያሉ አካል ጉዳተኛ ተሳታፊዎች መኖራቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በአስራ አምስተኛው የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ላይ በተለየ ሁኔታ መስማት የተሳናቸው ግለሰቦች ከትምህርት ቤት እንዲሳተፉ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩን አንስተው፤ኪነጥበብ ከሁሉ ለሁሉ በመሆኗ አቃፊነቷም የዛኑ ያህል ሰፊ ነው ሲሉ ነግረውናል።
አካል ጉዳተኞች የማኅበረሰቡ አንድ አካል ስለሆኑ እነሱን ያገለለ የትኛውም ነገር መኖር የለበትም። ብዙዎቹ በእምቅ ችሎታቸው በጎ ተፅዕኖ በማድረስ ዕድሉን ቢያገኙ ምን ያክል መሥራት እንደሚችሉ አሳይተዋል። መቼም የትም የሚዘጋጁ የኪነጥበብ ፌስቲቫሎች ሁሉንም ያቀፉ፣ ለሁሉም እኩል ዕድልን የፈጠሩ እና የሚፈጥሩ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ጥበብ መልከ ብዙ ናት። አንዱን ከአንዱ በማነካካት እና በማስተያየት ጉድለትን በመሙላትም ሆነ እንከንን በማሳየት መዳፈ ሰፊ ናት። ሕዝብን በማንቃትም ሆነ በማሳተፍ ለሀገር ግንባታ ሰፊ ድርሻዋን ትወጣለች፤ በመወጣትም ላይ ትገኛለች። ካሉን ድንቅ እና እልፍ ፀጋዎች አኳያ ጥበብ ቤተኛ መሆኗ ባያጠያይቅም የበለጠ ለመጠቀም መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ አንስተውልናል።
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም