የሰብዓዊ መብት ተሟጋችዋ ዝምድና

በአሁኑ ወቅት መቀመጫውን ዑጋንዳ ካንፓላ ያደረገው ‹‹SIHA Strategic Initiative for Women in the Horn of Africa›› የተሰኘው ኔትወርክ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ሆና በመሥራት ላይ ትገኛለች። በፈረንጆቹ 2024 ከአፍሪካ ሴቶች አዋርድ ከ100 ምርጥ የአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች በቀዳሚነት ተመርጣም ለሽልማት በቅታለች። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችም ነች።

የዘረኝነትን አፀያፊ ገጽታ በዘጠኝ ዓመቷ ከወላጆቿ ጋር ህንድ ተጉዛ በነበረችበት ወቅት እንዲሁም፤ በ15 ዓመቷ ወደ አውሮፓ ባቀናችበት ጊዜ ተመልክታለች። በመሆኑም ዘረኝነትን፤ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ አድሏዊ አሠራሮችን፣ አመለካከቶችን አጥብቃ የምትቃወም የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝም ነች።

እስከ ዑጋንዳ በመሄድ ተደፍረውና የሰውነት ክፍሎቻቸው ተቆራርጦ የተጣሉትን 40 ሴቶች ግድያ በሰላማዊ ሰልፍ በመቃወም ድምጿን አሰምታለች። ችግሮች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት መድረክ በማመቻቸት እና የሰላም ጉዞ በማድረግም ትታወቃለች። ሴት ተማሪዎች ከጾታዊ ጥቃት ነፃ ናቸው ተብሎ በሚታሰቡት ዓለም አቀፍና የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመመከት የሴቶች ፎረም እስከ መመስረትና ፎረሙን እስከ መምራት የደረሰች ታጋይም ነች።

የ37 ዓመቷ ዝምድና አበበ በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ የሚጣለው ቅጣት ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ሕጉ እንዲሻሻል ካደረጉት ሴቶች መካከልም በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። የከፍተኛ ትምህርቷን ስትከታተል በነበረችበት 2008 ዓ.ም የመጀመረያ ሴት የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጣም አገልግላለች።

የተመቻቸ ኑሮ ቀርቶ የትምህርት ዕድል በሌለበት የገጠሩ የሀገራችን ክፍል ተወልደው ያደጉት ወላጆቿ ትምህርት ለመማር የተወለዱበትን ቀዬ ጥለው አዲስ አበባ በመምጣት የከፈሉት ዋጋ በልጃቸው እንዳይደገም በተሻለ ሁኔታ እንድትማር በማድረጋቸው የዛሬ እንግዳችን በተለይ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ በርካታ አስተዋጽዎች በማበርከቷ የሕይወት ተሞክሮዋን ልናካፍላችሁ ወድደናል።

ውልደትና እድገት

እንግዳችን ዝምድና አበበ የተወለደችው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቅሎ ቤት አካባቢ ነው። እድገቷም እዚሁ ነው።ሆኖም እናትና አባቷ እንደ አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የተደላደለ ኑሮ ቀርቶ የተመቻቸ የትምህርት ዕድል እንኳን ከማይገኝበት ከገጠሩ የሀገራችን ክፍል ነው ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጥተው የወለዷት። እናቷ ሲመጡ ከማንበብና መጻፍ የዘለለ ዕውቀት አልነበራቸውም። አባቷም እንዲሁ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ለመማር ያላለፉበት ውጣ ውረድ አልነበርም። ሁለቱም የተሻለ ኑሮ ለመኖር ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። በተሻለ መመገብ፣በተሻለ ቤትና ሁኔታ መኖር፣ በተሻለ ሁኔታ መማር፣የተሻለ ሥራ መሥራት የጀመሩት እሷ ከተወለደች በኋላ በመሆኑ ‹‹ገዳም ናት›› ይሏታል።

እናቷ ‹‹ወርልድ ቪዥን›› የተሰኘ የውጭ ድርጅት፤ አባቷ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጥረው መሥራት የጀመሩትም እሷ ከተወለደች በኋላ ነው። በእዚህም እነሱ ያለፉበት እሾህና አሜክላ የሞላበት አስከፊ ሕይወት በእሷ እንዳይደገም ሲሉ ከትንሿ ቤታቸው ወጥተው የግሏ መኝታ ክፍል ያለው ቤት እንድትኖር ለማድረግ ሞክረዋል። በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዋ ጥንቃቄ እና እንክብካቤ የተሞላበት ጉዞ እንዲኖራትም ለፍተዋል።

የመጡበትን ሂደትና የሌሎችን ችግር እንድትገነዘብ ነገር ግን የእሷን ምቾት እንዳይጓደልም የቻሉትን ሁሉ ያደርጉላታል። በእዚህም በንግግሯ ሁሉ ይህንን ሃሳብ ታነሳለች። ‹‹ይህንን ማወቄ እንድጠነክርና ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ምቾት እንድኖር አድርጎኛል። ለሌሎች ምቾት እንድታገል ብሎም ራሴን በአግባቡ እንዳውቅ አድርጎኛል” ስትል ያሳደረባትን በጎ ተጽዕኖ ታስታውሳለች።

የምትናገረው የሚደመጠው፤ ማንበብ እና በአዕምሮዋ የሚመጣውን ሃሳብ ሥነ-ጽሑፋዊ ገጽታ ባለው ጽሑፍ የማስፈር ተስጥኦ ያላት ዝምድናን ወላጆች የመብቷን ጉዳይም ቢሆን በዋዛ እንድትመለከተው አልተዋትም። ሥነ -ምግባሯን ከማነጽ ጎን ለጎን ሴትነቷን እና ሀገሯን ብሎም አፍሪካዊነቷን እንድትወድና እንድታከብር፤ ደግሞም ለእዚሁ እና ለጾታ አጋሮቿ በብርቱ እንድትታገል በጎ ተጽዕኖ አሳድረውባታል።

ተፈጥሮም ብትሆን የዛሬ እንግዳችንን ዝምድናን ለእዚህ ዓይነቱ ትግል ምቹ ሆና እንድትወለድ አድርጓታል። በልጅነቷ ለምን እንዲህ ይሆናል ብላ ወላጆቿን ትጠይቅ ፣ ትክክል ያልሆነውንም አልቀበልም ትል ነበርና እናቷ “ኃይለኛ ነሽ” ሲሉም በመግለጽ መታገሏን እያበረታቱ ነው ያደገችው።

የትምህርት ሁኔታ

ዝምድና ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተማረችው የተሻለ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን በሚያስተምሩባቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው። ትምህርት ቤቶቹ በሴት ልጅ ላይ ከሚደርስ ማንኛውም ጥቃት እና ከትምህርት ገበታ ከሚያስተጓጉል ተጽዕኖ ነፃ ናቸው ተብለውም የሚታሰቡ ናቸው።

ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች አንዱ በሆነው አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ ሦስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን ተከታትላበታለች። ከሦስተኛ ክፍል በኋላ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን ደግሞ የተማረችውና ያጠናቀቀችው ”ስኩል ኦፍ ትሞሮ” በተሰኘው የግል ትምህርት ቤት ነው። ከእዚህ በኋላ ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ስለተሰማራች የሁለተኛም ሆነ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርቷን መቀጠል አልቻለችም። ሆኖም የተለያዩ ሥልጠናዎችን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ከመከታተል አልቦዘነችም። ለአብነት ከአፍሪካ ከተመረጡ 50 ሴት አመራሮች ውስጥ አንዷ በመሆኗ ወደ አሜሪካ አቅንታ ‹‹የማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎ ሽፕ›› ሥልጠና የተከታተለችበት ሁኔታ የሚጠቀስ ነው።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ እያለች ምንም እንኳን ወላጆቿ በቤት ውስጥ እየተለማመደች እንድትመጣ መሠረት የጣሉላት ቢሆንም በተፈጥሮም ገና ከታች ክፍል ጀምሮ የፈለገችውን ማድረግ የምትወድ ነች። ራሷን የምትገልጽበት ሁኔታም ነጻነትን የተላበሰ ነው። ይህ ደግሞ በራስ መተማመኗንም የበለጠ እያዳበረች እንድትሄድ አድርጓታል።

የኋላ የኋላም ከፍተኛ ነጥብ የምታመጣ ልጅ እንድትሆን አስችሏታል። ከአማርኛ ትምህርት በስተቀር ሁሉም የትምህርት ዓይነቶች በሙሉ ይሰጥበት በነበረው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ጥሩ ውጤት ታስመዘግብ ነበርም። የእንግሊዝኛ ቋንቋን በሚገባ መጠቀሟ መቻሏ ደግሞ በተለይ በቀድሞ ሥርዓተ ትምህርት ለከፍተኛ ትምህርት ወደ የሚያዘጋጀው የመሰናዶ ትምህርት እንድትገባ አግዟታል። በእንግሊዝኛ ቋንቋዋ አቅሟም በምሳሌነት የምትጠቀስ አድርጓታል።

የትምህርት ቤት ተሳትፎና አበርክቶ

ዝምድና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ወላጆቿ ውጤታማ እንድትሆን ከሚፈልጉት የቀለም ትምህርት ይልቅ ተማሪዎች በማደራጀት፣ በማንቀሳቀስ ፣ መድረኮች በመምራት፣በመድረኮች ንግግር በማድረግ ታተኩር ነበር። በተጨማሪም ከመደበኛው ትምህርቷ ጎን ለጎን በትምህርት ቤቱ እና ሌሎች ትምህርት ቤቶች እየሄደች በኤች አይቪና ሌሎች የጤና ጉዳዮች ዙሪያ ለተማሪዎች በተለያየ መልኩ ግንዛቤ ትፈጥራለች። አንዱ መንገዷ የምትወደው ግጥምና ሥነ-ጽሑፍ ነው።

ሌላው ደግሞ ተማሪዎችን በማደራጀትና በማንቀሳቀስ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ንግግር በማድረግ በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ የምታደርግበት ነው። በእዚህም ብዙ ጊዜ ትምህርት ቤቱን ወክላ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ትሳተፋለች፤ ትወዳደራለችም። በውድድሮቿ ደግሞ ብዙ ጊዜ አሸናፊ ስትሆን የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችንም አግኝታለች።

የምታገኛቸውን የምስክር ወረቀቶች ዝም ብላ የማታያቸው ዝምድና ከዩኒሴፍና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተጨማሪ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር አቅሟን ማጎልበት የሚያስችል መልካም ግንኙነት መመስረት የቻለች ነች። በእዚህ ደግሞ የሀገር መሪዎችን እና ትልልቅ ሰዎችን መተዋወቅ ችላለች። ይህ ነገሮችን ቶሎ ወደ ሥራ የመቀየር ባህሪዋ በርካታ ከእዚህ ቀደም የማታውቃቸው የኢትዮጵያን አካባቢዎችንም እንድታያቸው እድል ሰጥቷታል።

ዝምድና የዓለም ሀገራትን ጭምር የመጎብኘትና ልምዳቸውን የመቅሰም እድል ያገኘችው ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ነው። የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ስብሰባን በስፋት የምትሳተፈው ዝምድና፤ ገና ተማሪ እያለች ዳጎስ ያለ የዶላር ክፍያ ታገኝም ነበር። ይህ ደግሞ ቤተሰቦቿ ከእርሷ ምንም የሚሹ አልነበሩምና ለአንዳንድ እንቅስቃሴዎቿ የምትጠቀምበት ሆኖ አገልግሏታል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት

ዝምድና እንደምትለው ለራሷ መብትና ምቾት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች መብትና ምቾት መታገል እና መኖርን የተማረችው ከቤተሰቦቿ ነው። እነርሱ በመልካም ሥነ-ምግባር ሲቀርጿት ለሌሎች እንድትተርፍ አድርገው ነው። እናም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ይህንን የትግል ሥራ አሀዱ ብለዋለች። ምንም እንኳን ትምህርት ቤቱ የተሻለ እና ዓለም አቀፍ ቢሆንም በሴቶች ላይ ሊደርስ ከሚችል ጥቃት ጋር በተያያዘ ሙሉ በሙሉ ነፃ ነው ማለት የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረውም። አንዳንድ አድሏዊ አሠራሮች ይታዩበት ነበረ። እንዲያውም ከእዚህ ጋር በተገናኘ የገጠማትን እንዲህ ስትል ታስታውሰዋለች።

‹‹አንዴ በጣም የሚያበሳጭ ስድብ ሰድባኝ ከክፍል ጓደኛዬ ጋር ተጣላን። በማግስቱ እጅግ ከፍተኛ ሀብትና ሥልጣን ያላትን እናቷን ይዛ መጥታ በመክሰስ ዳይሬክተሩ ጋር አቀረበችኝ። ዳይሬክተሩ ጥፋተኛ ልጅቱ እንደሆነች ቢያውቅም ሴትዮዋ ፊት ጥፋተኛ አድርጎ የሚያወራው እኔን ነበር›› ስትልም የነበረውን አድሏዊ አሠራር ታብራራለች።

ዝምድና እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች በአሳማኝ ንግግር ታረግባቸዋለች። እንደ ሌላው ተማሪ ዳይሬክተሩን ሳትፈራ ትክክል የሆነውን በድፍረት ታስረዳለች። ይህ ደግሞ በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በሙሉ ተወዳጅ አድርጓታል።

በእነ ዝምድና ትምህርት ቤት ከአንድ መምህር የማይጠበቁ ሴት ተማሪን የሚያሸማቅቁ፣ ለወንድ ተማሪዎች መሳቂያ የሚያደርጉ ንግግሮች፤ በተለይ ስፖርት ማሠራት አስመስለው አግባብ ያልሆነ ንክኪ የሚፈጽሙ አልፎ ተርፎም የሚጎነትሉ፣ የሚማቱም መምህራን ነበሩ። ይሄ ድርጊት ደግሞ እሷን ጨምሮ ሴት ተማሪዎችን ይረብሻቸው ነበር። አብዝተው ያነሱት የነበረውም ጾታዊ ጥቃትም ይሄው ነው። ከትምህርት ቤት ሲወጡና ሲገቡ በአካባቢው ያለ ፍላጎታቸው የሚደርስባቸውም ተመሳሳይ ተግባር ነበር።

በተለይ በትምህርት ክፍለ ጊዜና በግቢው ውስጥ እነዚህ ድርጊቶች ተዘውትረው የሚታዩ ነበሩ። ሆኖም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቢሆኑም አብዛኞቹ ሴቶች መምህራኖቻቸውን ስለሚፈሩ በድርጊቱ ያፍሩ እና ይሸማቀቁ ነበር እንጂ ለምን ብለው አይቃወሙም። እርስ በእርሳቸው ግን ስለሚደረግባቸው ነውረኛ ነገር አግባብ አለመሆን ያወሩ ነበር። እርሷም ብትሆን ‹‹መቼ ነው እንዲህ ያደረገሽ›› የሚል ጥያቄ ይቀርብብኛል በሚል ስጋት እንደ ሌሎች ሴት ተማሪዎች ከማፈርና ከመሸማቀቅ ባሻገር ምንም ለማለት አልደፈረችም።

ዝምድና ‹‹ከድሮም ጀምሮ አንዲት ሴት ልጅ እንደፈለገች ወጥታ መግባት የማትችለው ሁሉም ሰው የሚለክፋት ፣ የሚጎነትላት ፣ጥበቃ የማይደረግላትስ ለምንድነው›› የሚል አስተሳሰብ ነበራት። በእዚህም ዘወትር ቤተሰቦቿን ‹‹አንዲት ሴት ልጅ እንዲህ ታድርግ፣ ይሄ የወንድ ሥራ የሆነው ለምንድነው ፣ እኩልነት

ምን ማለት ነው›› እያለች መልሱን በጊዜው ቶሎ ማየት ባትችልም በጥያቄ ታጨናንቃቸዋለች።

ዝምድና እንደምትለው፤ እያደር የሴቶች ጥያቄዎች ሲበራከቱና ጫናውን የሚቃወሙ እንዲሁም መብታቸውን የሚያስከብሩ ሴቶች መበራከት ሲጀምሩ የሴቶች ፎረም ወደ መመስረቱ ገቡ። ከአምስቱ መስራች ሴት ተማሪዎች አንዷና ሃሳቡን ያፈለቀች የፎረሙም መሪ ሆነች። በወቅቱ እሷ ከትምህርቷ ጎን ለጎን በኤች አይቪ ፣በጤና፣ በግጥምና ሥነ-ጽሑፍ በተለያዩ ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ አብራቸው ትሰራ ከነበሩ መካከል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጨምሮ የተለያዩ የውጭ ድርጅቶች እየሰበሰቡ ያወያይዋቸውም ነበር። በተለይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕድሜያቸው ከ22 ያነሰ ልጃገረዶች በእጅጉ ለኤች አይቪ/ኤድስ እየተጋለጡ መሆናቸውን ሪፖርት የወጣበት ወቅት ስለነበረ ለፎረሙ መመስረት በብዙ መልኩ ተደግፈዋል።

‹‹ሴቶች ላይ በትምህርት ቤት እና በትምህርት ቤት አካባቢ የሚደርስ ጥቃት ይቁም›› የሚል ሰፊ ንቅናቄ ተፈጥሮም ጾታዊ ጥቃትን የመከላከል ትግል ተቀጣጠለ። ይሄም ተሞክሮ እንደ ሀገር ባሉ ትምህርት ቤቶች ሰፍቶ ፀረ-ጾታዊ ጥቃትን በተቻለ መጠን ለመከላከል ተቻለ ስትልም አጫውታናለች።

የፀረ- ዘረኝነት ትግል

እንግዳችን የፀረ- ዘረኝነት ትግልን የጀመረችው ገና የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ ልጅ ሳለች ነው። ምክንያቷ ደግሞ ከ20 በላይ ወደሚሆኑ የዓለም ሀገራት ጉዞ ስታደርግ ያየቻቸው ወጣ ያሉ አመለካከቶች ናቸው። እሷ እንዳጫወተችን በዘጠኝ ዓመቷ ከወላጆቿ ጋር በመሆን ወደ ህንድ ሀገር ተጉዛ ነበር። እናቷ ውብና ቆንጆ ሆና ለመሄድ በማሰብ ጸጉሯን ተተኩሳ አሳምራዋለች። ሆኖም የሕንዱ ብርቱ ሙቀት የእናቷን ጸጉር ቀጥ አድርጎ በማቆምም አበላሽቶታል። በእዚህም ህንዳዊያኑ ልጆች የተለያዩ ነገሮች እያሉ ይጠቋቆሙባት ጀመር። ያኔ ለምን እንደዛ እንዳሉ ባይገባትም እናቷን በእዚያ ልክ ማንቋሸሻቸው በጣሙን አናዷታል። በተለይ ደግሞ ልጆቹን ያነሳሳቸው ጉዳይ ጸጉሯ ሳይሆን ጥቁር መሆኗ እንደሆነ ስትረዳ ይበልጥ ተናደደች። የሰው ሀገር ነችና ምንም ማድረግ ግን አልቻለችም ነበር።

ዝምድና ሁለተኛውን የውጭ ሀገር ጉዞ በ15 ዓመቷ ላይ ስታደርግ ነው ይህ የዘረኝነት ጥላቻ በእጅጉ የገባት። ምክንያቱም ዛሬም እንደ ትናንቱ በሆላንድ ሀገር ላይ ጥላቻውንና ንቀቱን እንዲሁም መጥፎ የዘረኝነት ገጽታውን አይታለች። መንገድ ላይ ስትንቀሳቀስ አንድ ሕጻን ልጅን ሌሎች ሕጻናት ልጆች ሲሸሿት በማስተዋሏም ነው ነገሩን ይበልጥ እንድታውጠነጥነው የሆነችው።

ሕጻኑ ወደ እነሱ በቀረበ ቁጥር እነሱ ይርቁታል። ምክንያታቸው ደግሞ ሕጻኑ አፍሪካዊ በመሆኑ ከእነርሱ የቀለም ሁኔታው ይለያል። በእዚህም በቀረባቸው ቁጥር እየተፀየፉና እየፈሩት ይሸሹታል። የሚሸሹት ሕጻናትም ሆኑ እሱ ሕጻን በመሆናቸው ‹‹ስለቀለም ልዩነት ምን አውቀው ነው›› ስትል ዝምድና ራሷን ጠየቀች። በኋላ እንደተረዳችውም ሕጻናቱ ሕጻኑን ይሸሹት የነበረው ቤተሰቦቻቸው ጥቁር ሲያዩ ስለሚሸሹ ነው። ሕጻናቱ ሲያደርጉ የነበረው ወላጆቻቸው ሲያደርጉ ያዩትን እንደሆነ አወቀች።

ይሄኔ መሰል ያየቻቸው የተዛቡ አመለካከቶች የፓን አፍሪካኒዝምን ዓላማ እንድታራምድ ገፋፋት። ፓን አፍሪካኒስትም አደረጋት። በተለይ ቅኝ ተገዥ በነበሩ ሀገራት ለቀለም የሚሰጠው ትኩረት የተለየ ነው። ቀይ ሲሆን የተለየ ከበሬታ የሚሰጥበት፤ ያለእሱ ንጉስ እንደሌለ የሚታይበት የተዛባ አመለካከት ይስተዋላል። እናም ይሄን ከቀለም ልዩነት ጋር ተያይዞ ያለን የተዛባ አመለካከት ማሊ ውስጥ እ.አ.አ በ2015 ለአንድ ዓመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስትሠራ በቆየችበት ወቅት ቀይ በመሆኗ የተለየ ከበሬታ ይሰጣት እንደነበርም አትረሳውም። ይህ ግን በጣሙን ያበሳጫት ነበር። ምክንያቱም እርሷ ኢትዮጵያዊ ነች። ሀገሯ ደግሞ አፍሪካዊት፣ የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ነች። እናም በጥቁሮች ላይ የሚደርሰው የዘረኝነት አድሎ እርሷን በመሰሉ ሰዎች መገታት እንዳለበት ታምናለች።

ሰዎች ‹‹ኢትዮጵያዊት አይደለሽም ወይስ ክልስ ነሽ›› ሲሏትም የሚሰማት መድሎና መገለሉ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ሆና ሳለች፣ ጥቁር ሆና ሳለች ቀይ ስትሆን ዋው! ጥቁር ሆና የሚሏት ዓይነት መሆንን አትሻም። እርሷ አፍሪካዊ በመሆኗ ብቻ እንድትከበር ትፈልጋለች። ቆንጆነቷም ከአፍሪካዊነቷ እንዲቀዳና በእዚያው እንዲመነዘር ፍላጎቷ ነው። ስለዚህ በእዚያ ቅኝት ውስጥ እንድትሆን በብዙ ታግላለች።

የከፍተኛ ትምህርት ትውስታ

ዝምድና የከፍተኛ ትምህርቷን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው የተማረችው። ቤተሰቦቿ እዚሁ አዲስ አበባ ስላሉ ትምህርቷን ትከታተል የነበረችው ዶርም በማደር ሳይሆን እየተመላለሰች ነበር። ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ ትምህርቷ ጎን ለጎን በፀረ- ጾታዊ ጥቃቱም ሆነ በሰብአዊ መብት ሙግቱ እና በዘረኝነት ትግል ንቅናቄው መደላድል ፈጥሮላታል።

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተሻሉ እድሎችን ማግኘቷ ደግሞ በሥልጠናዎች፣በትምህርት በተለያዩ ልምዶች የበለጠ አቅሟን እንድታጎለብት አግዟታል። በውጭ እና በሀገር ውስጥ ከተዋወቀቻቸው አንቱ የተሰኙ ትልልቅ ሰዎች ጋር እንድትገናኝም አስችሏታል። ያገኘችው እውቀት ደግሞ ግንዛቤዋን በማስፋት የበለጠ እንድትሠራ አደርጓታልም። ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ተጽእኖ ስር ሳትወድቅ ገለልተኛ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ንቁ እንቅስቃሴ ታዋቂ ሆና ቆይተዋን እንድታጠናቅቅም ረድቷታል።

በባህሪዋም ሆነ በሥራዋ ምስጉን የነበረችው እንግዳችን፤ይሄንን አቅሟን ያስተዋሉ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በ2008 ዓ.ም እሷ ትወክለን ሲሉ በሙሉ ድምጽ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት እንድትሆን መርጠዋታል። በእዚህም በዩኒቨርሲቲው በርካታ ለውጦች እንዲመጡ አስችላለች። የወጣቱን አስተሳሰብም በአፍሪካዊ መንፈስ ቀይራለች። በተለይም ኢትዮጵያን እና አፍሪካን የምትወድ እንደመሆኗ መጠን የምታራምደው አስተሳሰብም አፍሪካዊ እሴቶች እና ተጠቃሚነቶች ጎልተው እንዲወጡ ማድረግ ላይ ስለሆነ ወጣቶችም የእዚህ አስተሳሰብ አራማጅ እንዲሆኑ በቻለችው ልክ ሠርታለች። አህጉራዊ የእርስ በእርስ ትስስርና አንድነት እንዲኖርም ታግላለች።

ባለታሪካችን እንደምትለው፤ እሷ የምትከተለው ፓን አፍሪካኒስት ፊሚኒዝም አስተሳሰብ በምዕራባውያንም ሆነ በሌሎቹ ነጮች ጫና የመጣ አይደለም። ይሄ በአፍሪካ ቫሊዮች የተመራ አፍሪካዊነቷ ሴትነቷ እኩል ጠቃሚ ናቸው ብላ የምታስብ የኔ ፌሚኒዝም ወይ ለሴቶች መብት መሟገት ያመጣው ነው። በነጮች ወይም በምዕራባውያኑ ጫና ከሌላ የመጣ ሃሳብ ሳይሆን በጥቁር ሴቶች በተማሩ ተጽእኖ ፈጣሪዎች የተፈጠረ ነው።

አፍሪካን ወዳድ አፍሪካዊ ነኝ ከሚሉ ከራሳቸው ከተማሩ እና ከተመራመሩ አፍሪካዊያን ሴቶች የመነጨ ፍልስፍና ነው። በመሆኑም እርሷም አስተሳሰቡን ተቀብላው ዛሬ ድረስ እየሠራችበት ትገኛለች።

የሥራ አበርክቶ

እ.አ.አ በ2024 ከ100 የአፍሪካ ምርጥ ተጽእኖ ፈጣሪ ሴቶች አንዷ በመሆን ሽልማትን ያገኘችው እንግዳችን፣ ፓን አፍሪካኒስት የሴቶችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እንደመሆኗ መጠን በእዚህ ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን ሠርታለች። በበጎ ተጽእኖ ፈጣሪነቷም በርካታ ሴቶች ለውጥ እንዲያመጡ አስችላለች። ይህ አበርክቶዋ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ የተገደበ ሳይሆን አህጉራዊ ጭምር ነው።

አፍሪካ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ የተሻለች እንደሆነች በገባችባቸው መድረኮች ሁሉ ታስረዳለች። ዓለም ሀገራት ጭምር ይህንን እንዲረዱም ታደርጋለች። አሁንም ይህንኑ ተግባሯን እያከናወነች ትገኛለች።

ዝምድና በአብዛኛው ይህንን ተጽእኖ ፈጣሪነቷን ያጎለበተችባቸው ቦታዎች ትምህርት ቤቶቿ ናቸው። ለአብነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪ በነበረችበት ወቅት በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ የአህጉረ አፍሪካዊቷ ሀገር በሆነችው ማሊ ትሠራ ነበር። እዚህ ትሠራ የነበረው “አፍሪካ ቋንቋ አካዳሚ” ውስጥ ሲሆን፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አድርጓታል። የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ የመሆኗም ምስጢር ከእዚህ የመነጨ ነው።

አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ቅኝ ተገዥ በመሆናቸው ተጽእኖው ቋንቋን ጭምር የቀየረ ነው። በእዚህም የራሳችንን ቋንቋ እንጠቀም ጥያቄ እየተቀነቀነ እንደሆነ አውስታ፣ እርሷም የእዚህ ሃሳብ ደጋፊ እንደሆነች ታስረዳለች። የራሷን ዐሻራ ለማሳረፍም እንደምትጣጣርም አጫውታናለች።

”እኔ አማርኛ እና ኢንግሊዝኛ ቋንቋ ነው የምችለው‘ የምትለው እንግዳችን፣ አብዛኞቹ የማስተላልፋቸው መልዕክቶች ግን ወደተለያዩ ቋንቋዎች ይቀየራሉ። ይህ ግን እኔ ችያቸው ቢሆን ኖሮ የተሸለ አቅም ይኖራቸዋል ባይ ነች።

የእርሷ ንግግሮችና ጽሁፎች በአብዛኛው በተለያየ ቋንቋ በመተርጎሙ የተነሳና እንደ ልብ የሚሰራጨች በመሆኑ እንዲሁም የቋንቋ አካዳሚው ውስጥ መስራቷ ብዙ ሰው ጋዜጠኛ እንደሆነች እንደሚያስብ የምታስረዳው ባለታሪካችን፣ እርሷ ጋዜጠኛ ሳትሆን የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ በስፋት የምትሰራ አክቲቪስት መሆኗን በዚህ አጋጣሚ ታስረዳለች።

ዝምድና ከዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ሕብረት አባላት ጋር በመሆን ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ የሚጣሉ ቅጣቶች አናሳና የሚያስተምሩ ባለመሆናቸውም ቅጣቱ እንዲሻሻል አድርጋለች። የሰብዓዊ መብት ጥምረቶች ፤የሰላም ጉዞዎች ሌሎች የአፍሪካን ወጣቶች መብት የሚያስከብሩ እንቅስቃሴዎች ላይም ትሳተፋለች።

የሰብዓዊ መብት እና የፀረ-ጾታዊ ጥቃት ጥምረቶች እንዲሁም የሴቶች ፎረሞች በየደረጃው እንዲመሰረቱ አድርጋለችም። ለአብነት ባለፈው ዓመት ለአፍሪካዎች ይከፈል በነበረ ካሳ ላይ ለውጥ እንዲመጣ ያደረገችው ትግል በእጅጉ የሚጠቀስ ነው። በተጨማሪም ዴሞክራሲ እንዲሰፋ፤ሴቶች በብሄራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሰርታለችም።

በዋናነት በሱማሌ ላንድ የተመሰረተውና መቀመጫውን ዑጋንዳ ካንፓላ ያደረገው ‹‹SIHA Stra­tegic Initiative for Women in the Horn of Africa›› የተሰኘው ኔትወርክ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ሆና በመሥራት ላይ ብትሆንም ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ እና የተለያዩ ቦታዎች ላይ በመሳተፍ ሀገሯን ከማገልገል ወደኋላ አላለችም።

ኔትወርኩ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የሴቶችን ጥቃት ማስወገድና ማስቀረት ፤ሴቶች የሕግ ማዕቀፎችን መገልገል እንዲችሉ ማድረግ፣ ሴቶች በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚደርስባቸውን በደል፤ እኩልነት ማጣት፤ሰብዓዊ መብት ጥሰት በማትናት የሚያደርግ ሲሆን፣ መወሰድ ስላለባቸው ተግባራትም የመፍትሄ ሀሳብ የሚጠቁም ነው። አምስት የትኩረት አቅጣጫዎችን ለይቶ በመቅረጽም የሚሰራ ድርጅት ነውና እርሷም ከሀገሯ ባሻገር ዓለምን የሚያዳርስ ሥራ በመስራት የራሷን አሻራ እያሳረፈች ትገኛለችም። እንዲህ አይነት ወርቃማ ሴቶች ለሀገርም ሆነ ለዓለም ያስፈልጋሉና ልምዷን ወስዳችሁ ተጠቀሙበት በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን። ሰላም!!

ሠላማዊት ውቤ

 

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You