የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞንና በሰሜን ሸዋ የተከሰተውን የሠላም መደፍረስ ለማረጋጋት አስፈላጊው ህጋዊና ተመጣጣኝ ርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ አስተላልፏል። የትዕዛዙ ዓይነተኛ ማጠንጠኛ ደግሞ የዜጎችን ሠላም ማረጋገጥና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ነው።
አዎን! ከዜጎች ሠላምና ደህንነት በላይ ምንም ነገር የለም። የመንግሥት ትልቁ ኃላፊነት ይህንን ማረጋገጥ ነው። መንግሥት የዜጎችን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ደግሞ በሥልጣን ገደቡ የተሰጡትን ማናቸውም ህጋዊ ርምጃዎች የመውሰድ ሥልጣን አለው። ይህ ኃላፊነቱም ግዴታውም ነው።
እንደነዚህ ዓይነት በየአካባቢው እየተዘዋወሩና ጊዜ እየጠበቁ የሚከሰቱ ችግሮች በጥቂት አውቆ አጥፊ ወገኖች የሚፈጠሩ ስለመሆናቸው መጠራጠር አይገባም። በመሆኑም፤ ችግሮቹ የህዝብነት ባህሪይ መላበሰ የለባቸውም። በተከሰቱት ችግሮች መንስኤነት የሚበደለውና የሚጠቃው ግን ህዝብ መሆኑ እውነት ነው። ያውም ለፍቶ የሚያድረው ሰፊው ህዝብ።
ከዚህ ቀደም በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ ወሰን አካባቢ፤ ምዕራብ ወለጋና በቤንሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኞች፤ በጌዴኦና በጉጂ አካባቢ፤ እንዲሁም በምዕራብና በመካከለኛው ጎንደር አካባቢ በተነሱ ግጭቶች የሰዎች ህይወት አልፏል፤ በርካታ ንብረትም ወድሟል። ይህ ሁሉ እኩይ መንፈስ በተጠናወታቸው አካላት የተጠነሰሰና የደረሰ ጉዳት ነው።
ታዲያ በነዚህ ሁሉ አካባቢዎች በርካታ ህዝብ ከቤቱና ከቀየው ይፈናቀል፤ ንብረቱና ጥሪቱ ይውደምበት እንጂ የጉዳቱና የእንግልቱ ምክንያትም ሆነ ሰበብ ህዝብ ነው የተባለበት የትኛውም አጋጣሚ አልነበረም። ይልቁንም የተፈናቀሉትንና የተጎዱትን ያቀፋቸውና ያቋቋማቸው ህዝብ ነው እንጂ፤ መንግሥትንም ቢሆን እነዚህን ጥቂት አጉራ ዘለሎች አንድ ይበልልን፤ ያስታገስልን ከማለት በዘለለ ሌላ ጠይቆ አያውቅም።
መንግሥትም በየጊዜው የሚወስዳቸው ርምጃዎች ያስተምራሉ፤ መክረው ይመልሳሉ የሚል ይዘት ያላቸው በመሆናቸው በተለያየ መልክ ተፈርጀዋል። በአንድ በኩል፤ አጥፊዎቹና ጥቂቶቹ ወገኖች መንግሥት አቅም እንደሌለው ወደመቁጠር ያደጉ ይመስላሉ። በሌላ በኩል፤ የመንግሥት ትዕግስት ማብዛትና እናስተምር ባይነት ከልኩ አለፈ የሚሉ ወገኖች እንዲፈጠሩ ሳያደርግ አልቀረም። መንግሥት ፈጠን ብዬ ርምጃ ብወስድ አምባገነን እባላለሁ ብሎ በመሥጋቱ ነው ባዮችም አልጠፉም። የሆነው ሆኖ ግን አጥፊ መቀጣት አለበት የሚለው ድምዳሜ ሁሉንም ያስማማል።
አዎን መንግሥት ሆደ ሰፊ መሆን አለበት። ግን ፈሪና አቅመቢስ እንዳይደለና ለህዝብ ደህንነት አለኝታ መሆኑንም በተግባር ሊያሳይ ይገባል። “መሬትህ የምትዘራውን ዘር አላበቅል ካለ፤ እንዴት እንዳለሰለስከው ራስህን ጠይቅ” እንደሚባለው መንግሥት የትዕግሥቱን መጠንም ይሁን ድግግሞሽ ሊያጤነው ይገባል።
ሁሉም ጥፋቶች የሚታረሙበት ተመሳሳይ ደረጃና ምላሽ የላቸውም። አይኖራቸውምም። በተለይ ደግሞ ሆን ተብለው የሚደገሱ፤ ጊዜ፤ ቦታና ስልት እየቀያየሩ የሚሠሩ ጥፋቶች ዝም በተባሉ ቁጥር የአጥፊውን ወገን ስነ ልቦና የአሸናፊነት መንፈስ ማላበሳቸው አይቀርምና መንግሥትን ስለማይችል ነው ያሰኘዋል። ግን አይደለም። ሕዝቡም ቢሆን ሁሉንም ኃላፊነት ለመንግሥት ብቻ ሊጥለው አይገባም።
መንግሥት ትዕግሥቱን በአቅመ ቢስነት ለሚተረጉሙትና በህዝብ ላይ አደጋ ለሚደቅኑ ኃይሎች አግባብ ያለውን ቅጣት ማሳየቱ ተገቢ ነው። ሕግ ማስከበርና የሕግ የበላይነት በልመና ተግባራዊ አይሆንም። አንዳንዴ ከ“በሕግ አምላክ!” በላይ መሄድን የሚጠይቁ፤ ሕግ የሚፈቅዳቸው ህጋዊ ርምጃዎችም አሉ።
ስለሆነም መንግሥት በብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤቱ በኩል እንደሰጠው ትዕዛዝ ዓይነት ተገቢ ርምጃዎችን መውሰድ ይገባዋል። አሁን ላይ ለዚህ ውሣኔ ያበቁት ጉዳዮች በሙሉ ቀደም ሲል በማስተማር ሰበብ በትዕግሥት ሲታለፉ ከርመው የተከማቹ የማንአለብኝነት ስነልቦና ውጤቶች ናቸው። እናም ሕጉ በሚፈቅደው ልክ ህጋዊና አግባብ ያለው ርምጃ መውሰድ ከፌዴራልም ሆነ ከክልል መንግሥታት የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች ይጠበቃል። እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለወደፈቱም መለመድ አለበት።
ሕግን በማክበር ሕግን ለማስከበርና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ሲባል የሚወሰድ እርምጃ በምንም መንገድ ህገወጥ ወይም የአምባገነን ርምጃ ሊባል አይችልም። የአምባገነንነት መገለጫው ሌላ ነውና! ሕዝቡም ቢሆን ልዩነቱን አያጣውምና! በመሆኑም መንግሥት ይህንን እባላለሁ ብሎ እንደግለሰበ በይሉኝታ መሸበብ የለበትም። ይልቁንም ተጎጂው በመጠንም በአካባቢም በዝቷልና ተገቢውን የርምት ርምጃ በአፋጣኝ መውሰድ አለበት።
ከመንግሥት እርምጃ ባሻገር በየአካባቢው የሚነሱትን ግጭቶች የማስቆምና የመግታት ኃላፊነት የሁሉም ወገን ሊሆን ይገባል። ፖለቲከኞች ተከታዮቻቸው የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት፤ የሕግን የበላይነት ያማከለ ተግባር እንዲፈፅሙ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ህዝቡም በተለይ፤ ወላጆች የአካባቢያቸውን ወጣቶችና ልጆቻቸውን ሊገስፁ በምግባር ሊያንፁ ተገቢ ነው። መገናኛ ብዙኃንም ሕዝቡ በሀሰት ዘገባዎችና አሉባልታዎች እንዳይበረዝና ቸግሩ የህዝብ ሳሆን የጥፋት ኃይሎች መሆኑን የሚያሳዩ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን የማድረስ ድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።
በአጠቃላይ አሁን በመንግሥት የተጀመረው አካሄድ አግባብ ነው። ለወደፊቱም ቢሆን ትዕግሥት ልክና አግባብ ሊኖረው ይገባልና በአጥፊዎቹ ላይ ህጋዊ ርምጃ ወስዶ ለህዝብ በማሳወቅ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል እንላለን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2011