የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ለኮንክሪት ልዩ ዝንባሌ አላቸው። ብዙዎችን ግራ ሊያጋባ በሚችል መልኩ፤ ‹‹እንጀራዬም ሆነ ዳቦዬ ኮንክሪት ነው›› ይላሉ። የህልውናቸው መሠረት፤ የማደጋቸው ምሥጢር ከኮንክሪት ጋር የተሳሰረ ነው። የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በልጅነታቸው፤ የሲ ኤም ሲ ቤቶች ሲገነቡ ያዩት የኮንክሪት አሠራር ውስጣቸው አድጎ ሕይወታቸው በዚያ ላይ እንዲመሠረት ምክንያት ሆኗል።
አሁን ላይ በከተማዋ ካሉ ትላልቅ የኮንክሪት አምራቾች መካከል አንዱ ለመሆን በቅተዋል። ጥንካሬ እና ሥራ ወዳድነት ከትህትና ጋር ሞገስ የሠጣቸው፤ የጄንቲም ኮንክሪት ኢንዱስትሪ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሀገር ውስጥ አጋር ባለቤት ናቸው። አቶ ዘላለም ሃብተጊዮርጊስ ይባላሉ።
አቶ ዘላለም ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በካቶሊክ ገዳመ ኢየሱስ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል በዚሁ ትምህርት ቤት ተምረዋል። ኮተቤ አካባቢ በሚገኘው ወንድራድ ትምህርት ቤት ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ቦሌ ከፍተኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማራቸውን ይናገራሉ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 5ኪሎ ቴክኖሎጂ ግቢ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
በደርግ ጊዜ ለኤንባሲዎች በሚል ሲ ኤም ሲ አካባቢ ቤቶች ሲገነቡ፤ አቶ ዘላለም በልጅነታቸው ሲ ኤም ሲ የሚባል የጣሊያን ኮንትራክተር ኮንክሪት ሲያመርት አይተዋል። አቶ ዘላለም ጣሊያኖቹ የሚሠሩትን ሲያዩ ይገረሙ ነበር። የልጅነት ዕይታቸው ኮንክሪት ላይ የመስራት ፍላጎት አሳደረባቸው። ይሁንና ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ ሊገቡ ሲዘገጃጁ፤ በኢትዮጵያ የኮንክሪት ኢንዱስትሪ በጣም ገና ነበር። በሀገራቸው የሚወዱትን እና የሚፈልጉትን መሥራት እንደማይችሉ በመረዳታቸው ሀገር ለቀው ለመሰደድ አሰቡ።
አቶ ዘላለም፤ አማራጭ ሲፈልጉ የሚወዱትን ለመሥራት ዩናይትድ አረብ ኢምሬት ምርጥ መሆኑን ተረዱ። ያኔ ከዛሬ 25 ዓመት በፊት ዱባይ እየተገነባች ነበር። ስለዚህ ወደ እዛ መሄድን መረጡ። ለ20 ዓመታት ዱባይ ተቀጥረው ሠሩ። ዱባይ በሠሩበት ጊዜ የሥራ ባልደረባቸው አሁን ደግሞ አጋራቸው የሆነው ሰው፤ ከ37 ዓመት በላይ በዚሁ ሥራ ላይ ቆይቷል። ዱባይ በሠሩባቸው ዓመታት ሙሉ ጊዜያቸውን ለኮንክሪት ሥራ ሠጥተው ቆይተዋል።
‹‹ከኮንክሪት ውጪ ሌላ ሥራ አላውቅም።›› የሚሉት አቶ ዘላለም፤ ኮረና ሊከሰት የተወሰኑ ጊዜያት ሲቀሩት፤ የኢትዮጵያ ሁኔታን መጥተው አዩ። የእርሳቸው ወንድሞችም ከዚሁ ሥራ ጋር የተቀራረበ ትምህርት ተምረው ስለነበር ኢትዮጵያ ላይ ድርጅቱን ለማቋቋም አሰቡ።
ከአሁኑ አጋራቸው ጋር እ.አ.አ በ2020 ኢትዮጵያ ውስጥ መቀመጫቸውን በማድረግ ወደ ሥራ ለመግባት ማጥናት ጀመሩ። ሊያጋጥማቸው የሚችለውን እንቅፋት አስቀድመው በመገመት እና መፍታት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ በመነጋገር ድርጅቱን ለማቋቋም ቅድመ ሁኔታውን አጠናቀቁ። ከአምስት ዓመት በፊት በዩናይትድ አረብ ኢምሬት እና በኢትዮጵያ ውስጥ በጋራ ጄንቲም የኮንክሪት ኢንደስትሪ የተቋቋመ ሲሆን፤ አቶ ዘላለም ኢትዮጵያ ውስጥ በአጋርነት የሚሠራ ካምፓኒ ባለቤት ሆነው ሥራቸውን ቀጠሉ።
አቶ ዘላለም፤ አሁን ላይ ትልልቅ ከሆኑ የከተማዋ የኮንክሪት አምራቾች መሃል አንዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከአዲስ አበባ አልፈው ሞጆ እና ደብረብርሃን ድረስ በሚሠሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ይገልጻሉ። እሳቸው እንዳመላከቱት፤ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ ካምፓኒ በቆይታው፤ አዲስ አበባ ላይ በሚካሄዱት የመሠረተ ልማት እና የቤት ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ኮንክሪቶችን አቅርቧል። የኮሪደር ፕሮጀክቶች ላይ ለእግረኛ መንገድ ከሚያስፈልገውን ኮንክሪት በተጨማሪ ትልልቅ ድልድዮችን እና የመኪና ማቆሚያ ህንፃዎችን ለመገንባት የሚያስችሉ ኮንክሪቶችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። በተለይ ከአዲስ አበባ እስከ ሞጆ እየተከናወኑ ላሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ኮንክሪት እያቀረቡ ይገኛሉ።
ሥራውን ሲጀምሩ አብዛኞቹ የሥራ አስተዳዳሪዎች (ማናጀሮች) የውጪ ዜጎች እንደነበሩ አስታውሰው፤ ለአብነት የካምፓኒው ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምርት ሥራ አስኪያጅ፣ የግብይት ሥራ አስኪያጅ፣ የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ እና ሌሎችም ሥራን የማስተዳደር ሙያዎች ይከወኑ የነበረው በውጪ ሀገር ዜጎች ነበር ይላሉ። አሁን ከአምስት ዓመት በኋላ ሁለት ሥራ አስኪያጆች ሲቀሩ፤ ሶስቱ ሥራ አስኪያጆች በኢትዮጵያውያን ተተክተዋል። እነዚህ የተተኩት ሥራ አስኪያጆች ድርጅቱ ሲቋቋም ጀምረው የነበሩ ሲሆን፤ ተምረው እና ልምድ ቀስመው በውጭዎቹ እግር ለመተካት የበቁ ናቸው ብለዋል።
ተቀጥረው ሲሠሩ እንደገቢ የነበራቸው 10 ሺ ዶላር ነበር። ካምፓኒው ሲቋቋም 200 ሚሊየን ብር ካፒታል ነበራቸው። አሁን ላይ የካፒታል አቅማቸው አንድ ቢሊየን መድረሱን ጠቁመው፤ ካምፓኒው ይሸጥ ቢባል ሃምሳ ሚሊየን ዶላር ሊያወጣ እንደሚችል አመላክተዋል።
ድርጅቱ ለ24 ሰዓታት የሚሠራ መሆኑን እና ከ300 በላይ ሠራተኞችን ቀጥረው በማሠራት ላይ እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ ዘላለም፤ ከቤተሰቦቻቸው አንደኛው ወንድማቸው በሙያው ሲቪል ኢንጂነር ሲሆን፤ ሌላኛውም በተመሳሳይ መልኩ ሞያተኛ መሆኑ አጋጣሚው ለቤተሰባቸውም ሆነ ለካማፓኒው ትልቅ ዕድል መሆኑን አስረድተዋል።
ከ300 ሠራተኞች ሌላ በቀን ከ200 የጭነት መኪናዎች በላይ ጠጠር እና አሸዋ ለማቅረብ እንደሚሠማሩ ጠቁመው፤ ይህ ማለት 200 አሽከርካሪዎችም ከካምፓኒው ጋር በተያያዘ የሚሠሩ በመሆናቸው የሥራ ዕድሉ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን ያስረዳሉ።
‹‹ስንጀምር እዚህ ላይ እንደምንደርስ እናውቃለን። በሌላ በኩል ደግሞ ትልቅ ቦታ ለመድረስ ሲታሰብ እንቅፋት ሊኖር እንደሚችል መገመት አያዳግትም።›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ ዘላለም፤ ኮቪድን አስቀድሞ ለማሰብ አስቸጋሪ ቢሆንም፤ ዋናው ጉዳይ ብዙ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ አስቦ ችግሩ የሚፈታበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆኑን ያብራራሉ።
ለዚህ የበቁት ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ ሌሎች ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን ለማለፍ አስቀድመው በመዘጋጀታቸው መሆኑን አስረድተው፤ ሥራው ላይ ልምድ ስላላቸው ከአቅም በላይ የሚሆኑና የሚያንበረክኩ ችግሮች እንዳያጋጥሙ አስቀድመው ለማሰብ አለመቸገራቸውን ይናገራሉ። ጨምረውም ቀድመው ተንብየው በመሥራታቸው ከፈጣሪ ጋር ድርጅቱን ጥቅምት ላይ አቋቁመው ጥር ላይ ማምረት መጀመራቸውን ያመለክታሉ።
እሳቸው እንደሚገልጹት፤ ያሰቡት እና የገመቱት አልቀረም። ድርጅቱን ከማቋቋም ጀምረው በሥራ ሒደትም ሆነ አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ እስኪደርሱ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል። ድርጅቱን ጥቅምት ላይ አቋቁመው ወደ ዱባይ ከተመለሱ በኋላ የመጀመሪያው ችግር ተከሰተ። የአየር በረራ ተቋረጠ።
አቶ ዘላለም ተግዳሮቱ የጀመረው ገና ድርጅቱን ለማቋቋም ሲነሱ እንደነበር ያስታውሳሉ። በስድስት ወራት ውስጥ የተለያዩ ማሽኖችን ከቻይና ለማስመጣት አዘው ነበር። ይሁንና ኮቪድ ቻይናን አስጨንቋት ስለነበር መዘግየት አጋጠማቸው። ይህ ከፕሮግራም ውጪ እንዲሆኑ አስገድዷቸው እንደነበር ጠቅሰው፤ ያ ፈተና እንዳልበገራቸው ይናገራሉ። መሠረታዊው ጉዳይ ግን ሲጀምሩ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ እርግጠኛ መሆናቸው እንደነበሩ ያስረዳሉ።
እሳቸው እንደሚያስረዱት፤ በሌላ በኩል ኮንክሪቱን ሲሠሩ ለአምስት ዓመታት ማፒ ከተሰኘ የጣሊያን ድርጅት የግንባታ ኬሚካል ሲገዙ ቆይተዋል። ይህ ኬሚካል አምራች ድርጅት እ.አ.አ በ1930 የተቋቋመ ነው። 5ሺህ ዓይነት ምርቶችን በማቅረብ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ አቶ ዘላለም ኬሚካል ከመጠቀም ባለፈ ከአንድ ዓመት ወዲህ የማፒን ድርጅት ሁሉንም ምርቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ለማቅረብ ብቸኛ ተወካይ ሆነው ተስማምተው እየሠሩ ነው።
አዲስ አበባ ቃሊቲ አካባቢ ማከማቻ ያላቸው ሲሆን፤ ድርጅቱ ለሥራው ጣልያን ሀገር ድረስ ሄደው ሥልጠና የወሰዱ የውጭ አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች እንዳሉ ይናገራሉ። ከዚህ ምርት አንፃር ዋና ሥራቸው መሸጥ ብቻ መሆኑን አስታውሰው፤ መሸጥ ከጀመሩ አንድ አመት ብቻ ማስቆጠራቸውን ይጠቅሳሉ። በሂደት እነዚህንም ምርቶች አገር ውስጥ የሚገኝ ጥሬ ዕቃን በመጠቀም ወደ ማምረት ለመግባት ማሰባቸውን ይናገራሉ።
በሥራቸው ሂደት እንደችግር ሊገለፁ የሚችሉ ነገሮችን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ ለአንድ ሀገር ዕድገት ዘላቂ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ መንደፍ አስፈላጊ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚወጡ ህጎች በየጊዜው ባይቀያየር ጥሩ ነው። መጀመሪያ ከአምስት ዓመት በፊት ካምፓኒውን ሲያቋቁሙ የነበሩ ሕጎች እና መመሪያዎች አሁን ካሉት ጋር የተለያዩ ናቸው። የመመሪያዎች መቀያየር በሥራዎች ላይ ትልቅ እንቅፋት የሚፈጥር መሆኑን ያስረዳሉ።
ጥሬ ዕቃ ከውጭ ከማስገባት አንፃር ፍራንኮ ቫሉታ ላይ ያለውን አሠራር ብቻ መመልከት ይቻላል። እሳቸው እንደሚናገሩት፤ ከሶስት ጊዜ በላይ ህጉ ተቀያይሯል። አንዴ ሲፈቀድ በእሱ መሥመር ሲሠሩ መልሶ ይቆማል። ቆመ ሲባል ደግሞ መልሶ ይጀመራል። ለሶስት ወር ከተሠራበት በኋላ መልሶ ይቆማል። ይህ ሥራዎችን ተረጋግቶ ለመሥራት እንዳይቻል ምክንያት ሆኗል። በተለይ ይህ ቀጥታ ከውጪ መጥቶ ለሚሸጠው ምርት ሳይሆን ጥሬ ዕቃን አምጥቶ አምርቶ ለመሸጥ እንቅፋት የሚፈጥር ነው። ምክንያቱም ጥሬ ዕቃው ከሌለ ማምረት አይቻልም። ከዚህ ውጪ ይህን ያህል ሥራቸውን እና ዕድገታቸውን አጓተው የሚያስብል ትልቅ ችግር የለም።
አቶ ዘላለም ከማህበራዊ ኃላፊነት አኳያ ድርጅታቸው እየተወጣ ያለውን ሚና በተመለከተ ሲገልፁ፤ ካምፓኒው ያለው ቦሌ ክፍለ ከተማ ነው። ለበዓላት እና በተለያዩ ጊዜያት በክፍለ ከተማው እና በሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች በሚዘጋጁ የምገባ ፕሮግራሞች ላይ ይሳተፋሉ። ለአቅመ ደካማዎች ቤት በመሥራት እና ለወረዳ 1 ሕንፃ ግንባታ ግብዓት በመሥጠት ተሳትፈዋል።
ዓመቱን ሙሉ ለማህበረሰቡ በሚሠሩ በጎ ሥራዎች ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ ከእነርሱ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የሥራ ዕድልም ሆነ በሚያደርጉት ድጋፍ በጣም ደስተኞች መሆናቸውን እና ፈጣሪያቸውን እንደሚያመሰግኑ ይጠቁማሉ።
ኢትዮጵያ ብሎም አጠቃላይ የአፍሪካ አገራት ብዙ ሥራ ሊሠራባቸው የሚችሉ መሆናቸውን በመጠቆም፤ ወደ አደጉት አገራት ከማምራት ይልቅ አፍሪካ ውስጥ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ። በተለይ ኢትዮጵያ ተምረው ውጪ ሔደው እየሠሩ ያሉ ኢትዮጵያውያን፤ ያስተማረቻቸውን ሀገራቸውን ለማገልገል ሀገራቸው ላይ ቢሠሩ መልካም ነው ሲሉ መክረዋል። ሀገር ላይ መሥራት የጋራ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለራሳቸው በቂ ዕውቀት ያለው ባለሙያ ባለባቸው ሀገራት ተቀጥሮ ከመሥራት ወይም ያደጉት አገራት ውስጥ ሆኖ ከብዙዎች ጋር ለመወዳደር ከመሰቃየት ሀገር ውስጥ መሥራት የተሻለ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም