የምግብ ደህንነት ለጤናማ ሕይወት

ምግብ የሚለው ስያሜ እንደ ሥነምግብ ባለሙያዎች ብያኔ የተለያየ ትርጉም ቢሰጠውም ሁሉም የሚስማሙበት ሀሳብ ምግብ ማለት ማንኛውም የሚበላ እና የሚጠጣ ለሰው ልጅ እድገት እና ጤናማ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያግዝ ከእንስሳት አልያም ከእጽዋት የሚገኝ እንደሆነ ነው። ይህ የሰው ልጆች ሕይወትን የሚወስነው ምግብ በተለያየ ምክንያት ሊበከል ይችላል፡፡ ብክለቱ ደግሞ ከእርሻ እስከ ጉርሻ በሚደርስ የምግብ ሰንሰለት ውስጥ የሚከሰት እንደሆነም የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ይህ ብክለት በተለምዶ የምግብ መመረዝ በመባል ይታወቃል። የዘርፉ ምሁራን ደግሞ የምግብ ወለድ በሽታ ይሉታል።

ይህ በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የጤና ስጋት ነው። በቁጥር ስናስደግፈውም እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ 600 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በምግብ ወለድ በሽታዎች ይጠቃሉ። በየዓመቱ ከ420 ሺህ በላይ ሰዎች ይሞታሉም። ምግብን ተከትሎ ከ200 በላይ የተለያዩ በሽታዎች እንዳሉና መንስኤያቸው ምን ምንድነው፣ ለመከላከል ምን ያስፈልጋል፣ ሕክምናው ምንድነውና መሰል ነገሮችን በተጨማሪም እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተሠሩ ያሉ ተግባራት ምን ይመስላሉ የሚሉትን በማንሳት በዛሬው ዓምዳችን የምናስነብባችሁ ይሆናልና ተከተሉን።

የምግብ ወለድ በሽታዎች መንስኤ

እነዚህ በሽታዎች የሚመጡት ጎጂ ባክቴሪያዎችን፣ ቫይረሶችን ወይም ጥገኛ ተውሳኮችን የያዘ የተበከለ ምግብ በመመገብ ነው። መዘዙ ከቀላል ምቾት ማጣት እስከ ከባድ የጤና ችግሮች ሊደርስ ይችላል። ሰዎች የተበከሉ ምግቦችን ወይም መጠጦችን በመውሰዳቸው ከቀላል የጨጓራ እስከ ከባድ የሥርዓተ- ምግብ ችግር ሊያቀጋጥማቸው ይችላል።

መንስኤዎችን፣ ምልክቶችን እና የመከላከያ ስልቶችን መረዳት ደግሞ በምግብ ወለድ በሽታ የመያዝ እድልን ለመቀነስ ወሳኝ ነው። ከዚህ አንጻርም ከመንስኤያቸው ጀምረን እንመልከታቸው። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በምግብ ወለድ በሽታዎች ዋነኛ መንስኤዎች ተብለው የሚጠቀሱት ረቂቅ ተሕዋስያን ናቸው። ተገቢ ያልሆነ የምግብ አያያዝ፣ በምግብ ዝግጅት እና በማከማቸት ወቅት ደካማ ንፅህና ወደ ብክለት ሊያመራ ይችላል። የተለመዱ የባክቴሪያ በሽታ አምጪ ተሕዋሲያንም እንዲሁ የችግሩ መንስኤ ይሆናሉ።

ቫይረሶችና ጥገኛ ተውሳክ ወይም ኢንፌክሽኖችም ለምግብ መበከል ችግር ናቸው። የተበከለ ውሃን ወይም በደንብ ያልበሰለ ስጋን መውሰድም ሌላው በመንስኤነት የሚጠቀስ ነው። የኬሚካል ብክለት የሚከሰተው ፀረ-ተባይ መድሃኒቶችን በአግባቡ አለመጠቀም ወይም የኢንዱስትሪ ብክለት በመኖሩ ምክንያትም ምግቦች ሊበከሉ ይችላሉ። አንዳንድ እንደ እንጉዳዮች እና የባሕር ምግቦች ያሉ በተፈጥሮ የሚገኙ መርዛማ ንጥረ ነገሮችም የበሽታው መንስኤ የመሆን እድል አላቸው።

የምግብ ወለድ በሽታ ምልክቶች

ምልክቶቹ እንደ መንስኤዎቹ ይለያያሉ። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ ማስቀመጥ፣ የሆድ ሕመም እና ትኩሳት በዋናነት የሚታዩ ናቸው። ችግሩ ከባድ ሁኔታ ላይ ከደረሰ ደግሞ የነርቭ ምልክቶች ወይም የሥርዓተ-ምግብ መዛባት ሊያጋጥም ይችላል። የሕመሙ ምልክቶች የሚታዩት ደግሞ ከተመገቡ በኋላ ከሰዓታት ሊጀምር ይችላል። ቆይታውም ቀናትን ሊወስድ ይችላል።

የምግብ ወለድ በሽታዎችን የመከላከያ ዘዴዎች

ረቂቅ ተሕዋስያን ለመከላከል ትክክለኛውን የምግብ ሙቀት መጠበቅ እና የንጽህና አያያዝ ልምዶችን ማዳበር ያስፈልጋል። ኬሚካሎች በግብርና ወይም በማሸግ ወደ ምግብ ሊገቡ ይችላሉ። ስለሆነም ይህ እንዳይሆን ትክክለኛ ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ ነው። በአጠቃላይ የምግብ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል ከግለሰቦች እስከ ተቆጣጣሪ አካላት የሚደርስ ሥራዎች መከናወን አለባቸው። ለአብነት ግለሰቦች የግል ንጽህናቸውን በአግባቡ ሊጠብቁ ይገባል። ደህንነቱ ያልተጠበቁ ምግቦችን እና ያልበሰሉና ቶሎ ለብክለት የሚጋለጡ ምግቦችን አለመመገብ ይኖርባቸዋል።

እንደ ኢንዱስትሪ አይነት ተቋማት ደግሞ የምግብ ማከማቻ እና ዝግጅታቸው ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን ይኖርበታል። የሙቀት መቆጣጠሪያውን ለምግቡ ምቹ ማድረግ አንዱ ነው። ምግቦች ሲዘጋጁ ተሻጋሪ ብክለት እንዳይፈጠርም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል። ተቆጣጣሪ አካላት ደግሞ ሁሌም ክትትልና ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር አስተማሪ ርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋቸዋል። ይህንንም ከምግብ ደህንነት ደረጃዎች አንጻር እያዩ መሆን ይኖርበታል።

የምግብ ወለድ በሽታዎች ምርመራ እና ሕክምና

የምግብ ወለድ በሽታዎችን ለይቶ ማወቅ የታካሚውን ታሪክ፣ የምልክት ግምገማ እና የላብራቶሪ ምርመራዎችን ያጠቃልላል። የጤና እንክብካቤ አቅራቢዎች ለበሽታው መንስኤ የሆነውን የተለየ በሽታ አምጪ ለመለየት የሰገራ ናሙና ሊጠይቁ ይችላሉ። በአንዳንድ ሁኔታዎች የኢንፌክሽኑን መጠን ለመገምገም የደም ምርመራዎች እና የምስል ጥናቶች አስፈላጊ ሊሆኑ ይችላሉ።

በምግብ ወለድ በሽታዎች ላይ የሚደረግ ሕክምና ብዙውን ጊዜ ምልክቱን በመቆጣጠር እና በመከላከል ላይ ያተኩራል። . በባክቴሪያ ለሚመጡ ኢንፌክሽኖች አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ። የፀረ-ቫይረስ መድሃኒቶች ለቫይረስ ኢንፌክሽን አስፈላጊ የሚሆኑበት አጋጣሚም አለ። ይሁን እንጂ ሁሉም የምግብ ወለድ በሽታዎች መድሃኒት አይፈልጉም። ምክንያቱም ሕክምናው እንደ በሽታው ክብደት እና አይነት ይወሰናል። እናም አብዛኛዎቹ ቀላል ጉዳዮች እረፍትን ጨምሮ በድጋፍ ሰጪ እንክብካቤ ይፈታሉ። ከዚህ አንጻር ታዲያ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምን ተሠራ ከተባለ ጥቂቶቹን እናንሳ።

የከተማ አስተዳደሩ ሥራውን የጀመረው ከግንዛቤ መፍጠር ነው። ምክንያቱም የምግብ መበከል ጉዳይ ወይም የምግብ ወለድ በሽታ መንስኤ ከእያንዳንዱ ሰው ጓዳ የሚመነጭ ነው። ስለዚህም እያንዳንዱን መንስኤና ቀድሞ የመከላከል ዘዴውን በሚገባ መገንዘብ አለበት። ለመፍትሄውም ከግለሰብ የጀመረ ሥራ የግድ ነው። እናም ከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነት በሰጠው የአዲስ አበባ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን በኩል ‹‹እኔም ለጤናዬ ባለስልጣን ነኝ›› የሚል የጋራ ፎረም አቋቁሞ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል። በትብብር የመሥራቱን ሁኔታም እያፋጠነ ነው።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን የምግብ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ነጋሽ ስሜ እንደሚሉት፣ የምግብ ጉዳይ የመኖርና አለመኖር ጉዳይ ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ የእኔ ነው ብሎ ካልሠራበት በአንድ አካል እንቅስቃሴ ብቻ መፍትሄ የሚያገኝ አይደለም። ስለዚህም ጉዳዩ የግለሰቦች የመንቀሳቀስና ለምግብ ጉዳይ እንደሚሰጡት ትኩረት የሚለካ ነው። በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ከብዙ አቅጣጫ የምግብ ወለድ በሽታዎች ይከሰታሉ። አንዳንዴ በቸልተኝነት፣ አንዳንዴ ያላግባብ ለመበልጸግ፣ አንዳንዴ ደግሞ እኔን አይንካኝ እንጂ በማለት አለያም ደግሞ በንጽህና ጉድለትና በቦታ ጥበት ምክንያት ዜጎችን ወደ ችግር የመክተት ዘመቻ ውስጥ ይገባል።

በኢኮኖሚ ችግር ሳቢያም በሽታዎቹ የሚፈጠሩበት ሁኔታ ብዙ ነው። እናም ይህንን መፍትሄ ለመስጠት ከተቆጣጣሪ አካሉ በተጨማሪ ሌሎች የሚመለከታቸውም አካላት ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል። ከሁሉም በላይ ግን ራስ ወዳድነትን ማጥፋት ያስፈልጋል። ዛሬ የእኛ ልጅ የተበከለውን ባይበላ የእኛ ዘመድ ምግቡን አግኝቶት በበሽታ እንዲማቅቅ ይሆናል። ስለዚህም ‹‹እኔም ለጤናዬ ባለስልጣን ነኝ›› የሚለው መርህ የሁሉም ድርሻ መሆን ይገባዋል ሲሉም ያስረዳሉ።

ባለስልጣኑ ከክልልም ሆነ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ጋር በስፋትና በቅርርብ እየሠራ ስለመሆኑ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በተለይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በስፋት እንዲሠራ የሆነበት ምክንያት ስፋት ያለው ሕዝብና አገልግሎት ስለሚሰጥበት እንደሆነ ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉእመቤት ታደሰ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ምግብ በሕይወት ለመኖር የግድ ነው። በዚህም ባለስልጣኑ በምግብና ጤና ነክ ዘርፎች ላይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ለማድረግ በርካታ የቁጥጥርና ድጋፍ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በተለይ አምራቹ ማኅበረሰብ ችግሩን ለመቅረፍ የድርሻውን እንዲወጣ ከማስቻል አንጻር ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።

አሁን አሁን ከተላላፊ በሽታዎች ይልቅ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በሀገራችን በስፋት እየተስተዋሉ ብሎም ሞትን እያስከተሉ ይገኛሉ። ለእነዚህ በሽታዎች መስፋፋት ደግሞ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን አለመከተል ትልቁን ድርሻን ይይዛል። ለጤናማ አኗኗር ደግሞ መሰረቱ ጤናማ አመጋገብ እንደሆነ ማንም ይረዳዋል። ይሁንና አሁን አሁን ላይ የታሸጉ ምግቦችን አብዝቶ መጠቀም እየተለመደ በመምጣቱ ጤናማ አመጋገባችንን እያዛባው ይገኛል። ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎችም ተጋላጭ እያደረገን ነው። የታሸጉ ምግቦች ጤንነታችንን የሚያሳቡበት ምክንያት የተለያየ ነው። የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት፤ አንዱና ዋነኛው የምግቦቹ አቀማመጥ ሁኔታ ነው። በተለይ የታሸጉ ምግቦች የሙቀትና የቅዝቃዜ መጠን የተመጣጠነና ደህንነቱን የሚጠብቅ ካልሆነ አደጋው የከፋ ነው። እስከ ካንሰር የሚደርስ ችግርም ያስከትላሉ።

ለፀሀይ ተጋላጭ የሆኑ ምግቦች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሳያልፍ ወደ ሻጋታነት ብሎም ወደ መርዛማነት እንደሚቀየሩ የሚያነሱት ወይዘሮ ሙሉመቤት፣ ባለስልጣኑ የምግብ ነክ ምርቶችን የፀሀይ ተጋላጭነት ለመከላከል በስፋት እየሠራ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። የፀሀይ ተጋላጭነትን የመከላከሉ ሥራ የምግብን ደህንነት ከማስጠበቅ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤና ከመጠበቅ አኳያ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እየተወጣ ያለው ማኅበራዊ ኃላፊነት መሆኑንም ይጠቁማሉ።

ወይዘሮ ሙሉ እመቤት፤ ከአፍላቶክሲን ጋር የተያያዘ የምግብ ደህንነት ስጋትን ከግብርናው እስከ ኢንዱስትሪው በአግባቡ ሊሠራበት ይገባልና ይህ እንዲሆንም ባለስልጣኑ በጥብቅ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ዘርፉን ሲመራ ቆይቷል። በዚህ ቁጥጥር ደግሞ በበጀት ዓመቱ በቁጥጥር እንዲሁም በጥቆማ በተገኘ መረጃ 933 የሚሆኑ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል። ይህም 767 የሚሆኑት ላይ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ 164 ተቋማት ላይ ጊዜያዊ እሸጋ፣ ሁለት ተቋማት ደግሞ ከተፈቀደላቸውና ከተሰጣቸው የብቃት ማረጋገጫ ውጪ ሲሠሩ በመገኘታቸው ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ሆኗል። በተመሳሳይ ከፀሐይ ተጋላጭነት አንጻርም ምርቶቻቸውን አደጋ ውስጥ የሚከሰቱ 65 ተቋማት ታሽገው የማስተካከል ሥራ ተከናውኗል። 410 የሚደርሱት ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ያስረዳሉ።

እንደ ወይዘሮ ሙሉ እመቤት ማብራሪያ፤ የምግብ ጉዳይ ከትንባሆ አንጻርም የሚታይ ነው። እናም ባለስልጣኑ ትንባሆን በማስጠቀምና በማስጨስ ምክንያት ተቋማት ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። ይህም 25 ተቋማት ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው፣ 35 ተቋማት ደግሞ የማሸግ ሥራ የተሠራባቸውና 65 ተቋማት የገንዘብ ቅጣት የተደረገባቸው ናቸው። በተጨማሪም ግምታቸው ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የትንባሆ ምርቶችና መጠቀሚያ መሳሪያዎች ተወርሰው እንዲወገዱ ተደርጓል። በአጠቃላይ በ10 ወራት ውስጥ ከ35 ሺህ በላይ የምግብና ጤና ነክ ምርት አምራቾች፣ አከፋፋይና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ቁጥጥር ተደርጓል።

በየትኛውም ሥራ ላይ እርምጃ መውሰዱ ብቻ መፍትሄን አያመጣም የሚሉት ሥራ አስኪያጅዋ፣ ከእርሻ እስከ ጉርሻ ያለውን የምግብ ደህንነት ለማረጋገጥ አበረታችና እውቀት የሚያስጨብጡ ተግባራትን ማከናወን ያስፈልጋል። በዚህም ባለስልጣን መሥሪ ያቤቱ በርካታ የግንዛቤ ሥራዎችን ሠርቷል፣ አሁንም እየሠራ ይገኛል። ከዚያም ሻገር የሚሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው። ይህም የሠሩ የሚበረታቱበትን እድል መፍጠር ሲሆን፣ አምራቾችን፣ አከፋፋዮችንና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን እንደ ሀገር በወጣው የምግብ ደህንነት ደረጃ አንጻር ተመዝነው በውጤታቸው እውቅና እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህ ደግሞ ለተሸላሚዎች ቀጣይነት ያለው ሥራ እንዲያከናውኑና የበለጠ ለመሥራት እንዲታትሩ የሚያደርግ ነው። በተጨማሪም በተቃራኒው ወገን ያሉትንና ችግር ያለባቸውን ተቋማትም ለማስተማር የሚበጅ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

ወይዘሮ ሙሉ እመቤት፤ በመጨረሻም የምግብ ደህንነት ጉዳይ የሁሉም የሕይወት ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም ሰው ችግሩን ተከትሎ የሚመጡ በሽታዎችንና ሞትን ለመቀነስ መረባረብ እንዳለበት አስገንዝበዋል። በተለይም አምራቹና አገልግሎት ሰጪው ማኅበረሰብ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You