
“ቤት ሳጥብ፣ ሳጸዳ ጡቴና እንባዬ እኩል እየፈሰሰ ከውሃው ጋር እወለውለው ነበር፤ እጣ ክፍሌ ሳይሆን አይቀርም አይለፍልሽ የተባልኩ ይመስል ከልጅነት እስከ ዕውቀት የመከራ ካባ ስደርብ ነው የኖርኩት” አለችኝ ። የዛሬ እንግዳዬ ጸሃይ በቀለ። መንታ መንታ የሚወርድ እንባዋ የአፍንጫዋን ተረተር ተከትሎ ከደረቷ ማሳ ኩሬ እየሠራ ።
ጸሀይ አዲስ አበባ በተለምዶ ‹‹ሳሪስ ሃምሳ ስድስት›› ከሚባል አካባቢ ከአባቷ አቶ በቀለ ገመዳና ከእናቷ ከወይዘሮ ሸጌ በዳኔ በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ አመተ ምህረት በወርሃ መጋቢት አስራ ሁለት ነው የተወለደችው። ጸሃይ ለአባቷ የመጀመሪያ ልጅ ስትሆን ከአባቷ በፊት ሌላ ትዳር የነበራቸውና ኋላም ባላቸው ሲሞቱ የእሷ አባት ጋር በአንድ ጣሪያ ስር ላደሩት እናቷ ሰባተኛ ፍሪያቸው ናት። በዚህ የመነሻ ወጋችን የመጀመሪያ ልጅ በመሆንሽ መቅበጥን ነው ወይስ ፈተናን ያተረፍሽው? በማለት ጥያቄ አቀረብኩላትና በአጭር ያልወሰንነውን ረጅም ልባችንን አንቅተን ሰፊ ጨዋታችንን መሰለቅ ያዝን።
ወላጅ አባቷ የመኖርን ትርጉም ያወቁባት በመሆኗ “አፈር አይንካሽ” ብለው ሊያሳድጓት ብዙ ኳትነዋል። ከእጅ ወደአፍ የሆነው ኑሯቸው ግን አካሏ ሳይጠና፣ መንፈሷ ሳይሰላ ገና በአስራ ሶስት አመቷ ለጉልበት ስራ ሊዳርጋት ግድ ሆነ። አባት እንባቸውን ወደውስጥ ጠጥተው ከንፈራቸውን ከመምጠጥ በቀር ምንም ሊያደርጉላት አልቻሉም፤ “እግዜር ሲቆጣ በዝናብ ምን ያመጣ” ነውና ተረቱ ችግሩን ሲያከፋው ደግሞ ጎጇቸውን ባቆሙበት በአደይ አበባ ድርጅት ውስጥ ክፉ አደጋ ገጠማቸው።
አንድ ቀን የዕለት ስራቸውን በማከናወን ላይ ሳሉ በድንገት አንድ እጃቸውን ማሽን ቆረጣቸው። ይህኔ ድንግዝግዝ ህይወታቸው የባሰ ጨለመባቸው። ውሎ አድሮ የድርጅቱ ሃላፊዎች በተቋሙ ክሊኒክ በተቆጣጣሪነት እንዲሰሩ ዕድሉን ሰጧቸው። ሆኖም የቤታቸው ነገር ግን አልሞላ፣አልጠረቃ አላቸው። ቆይተው ግን ሚስታቸው የዘየዱትን የመሸታ ስራ ሳይወዱ በግድ ተቀበሉና ውል የበዛበትን የኑሯቸውን ሽንቁር ለመድፈን የህብረት እጆቻቸውን አጣመሩ።
ፀሀይ‹‹ እነ አራዳ ጪሱ›› በአሲድ በሚጉመጠመጡበት፣ ጥርሳቸውን በጩቤ በሚፍቁበት፣ ዘፈን ጨርሰው በዜና በሚደንሱበትና ውሃ ጠብሰው በሚበሉበት በሚባልላት መሃል አዲስ አበባ እየኖረች ከከተሜነቱ ርቃ በገጠሩ ያኗኗር ዘይቤ ተቃኘችና የድርሻዋን ሃላፊነት ለመወጣት ብልሃትን ማማተር ያዘች። ከቦሌ ቡልቡላ ማዶ የተንጣለሉ የርሻ ማሳዎች ከሃሳቧ ገቡ። በእነሱ ነፍሷ ያረፈ ቢመስላት ወደስፍራው አቅንታ ሰዎቹን አናገረችና በሚሰጧት ጎመን ፋንታ በአረም ልትውልላቸው ቃል አሰረች።
ወዲያው ኩበት በመልቀም እየሸጠች እናቷን መደገፍ ጀመረች፤ ከዚሁ ጎንም መንገድ ዳር ተቀምጣ የተቀቀለ ድንች መሸጥ ያዘች። ፀሀይ ከቤት ያሰናዱትን ጠላና ሙልሙል ዳቦና ቆሎ መያዝ ስራዋ ሆነ። በየግዜው ከጠጅ ቤት ሌላ የቀን ሰራተኞች ይገኙበታል በተባለ ስፍራ ሁሉ እየዞረች ታጣራለች።
በእንዲህ መልኩ ኑሮን እየገፋች ሳለ በሚያውቋት ሰዎች በኩል ቡና ቦርድ ለመቀጠር በቃችና የቀን ትምህርቷን ወደማታ በማዞር የገደም ዳሜ ጥረቷን ቀጠለች። ይሁን እንጂ ቀለሙ ላይ እምብዛም ነበረች። ይህን የተገነዘቡት አባቷ ከፍሬ ህይወት ትምህርት ቤት አስወጥተው ወደ ስብስቴ አስገቧት። ልቧ የተከፈለው ጸሃይ ግን የቤተሰቦቿን ጉሮሮ ለመድፈን ወዲያ ወዲህ መራወጥ ግድ አላትና በተፈለገው ልክ በትምህርቱ ሳትዘልቅ ቀረች።
አፍላነት ሲደርስ፣ ወዳጅ ሲፈራ፣ በሰው ምክር አለማደር የወጣትነት አንዱ ባህሪ ነው። ወጣ ወጣ ማለቷን ያልወደዱላት አባቷ ከቤት አስወጧት፤ ገላጋይ ገብቶ ወደቤት ብትመለስም የሸፈተ ልቧ መርጋት አልቻለምና ጉዞ ለመጀመር ስትሰናዳ አስራ ስምንት አመት ያልሞላው መታወቂያ ማውጣት እንደማይችል ሲነገራት ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ስድስት አመተ ምህረት እድሜዋ ላይ ሁለት አመት በመጨመር መስፈርቱን አሳክታ በወሬ ያጠገባትን እሾሃማውን ወርቅ በሰፊ መዳፏ ልትዘግን ለጋ ሞራሏን አበርትታ ተስፋ ባዘለ ልብ አድማሱን አቋረጠች።
ጥቂት ቆይታ በሩቅ የምትሰማው የስደት አለም ነፍስና ስጋ ሰርቶ ከልቦናዋ ቢሳል ለመሄድ በእጅጉ ቋመጠች። አባቷ “ቃሌን ተላልፈሽ ትተሽኝ ብትሄጂ በሰቀቀን እሞትብሻለሁ፤ እወቂው ቶሎ ብትመለሺ እንኳን በህይወት አታገኚኝም”ሲሏት ለግዜው የመሄድ ጉጉቷን ገታችው። ከአባቷ ጋር የፈጠረችው አለመግባባት ግን መልሶ ሆድ አስባሳትና ለመተው ያለችውን የስደት ህይወት ዳግም ናፈቀች።ወዲያው ትምህርቷን ከዘጠነኛ ክፍል አቋርጣ ወደቤሩት ተጓዘች።
ጸሃይ የቤሩትን ምድር ጫማዋ እንደሳመ ብልጭልጭ ሰማይ ብትመለከትም ለሷ ግን ባቢሎናውያንን የከለለና በጽልመት የተሸመነ የሰይጣን ብሉኮ ነበር የመሰላት። “ወይ ድንግርግር ተጓዝ ያለው እግር” የሚሉት አባባል ካጥንቷ ዘልቆ ተግባሩን ሲገልጥላት የከፋ ህይወት እንደተደነቀረባት ተረዳች። ሁሉንም ፈተና እንዳመጣጡ በጽናት ለመጋፈጥ ስነልቦናዋን አዘጋጅታ “ኖር” አለችው።
የተቀበለቻት አሰሪ ምላጭ የዋጠች ከመሆኗ በላይ “ኢትዮጵያውያን ሲገናኙ ተያይዘው ከኮንትራት ቤት ይጠፋሉ” የሚል ወሬ ሰምታለችና ከሰው አይን ሸሽጋ ነበር የምታኖራት፤ ቢሆንም ግን በየአስራ አምስት ቀኑ ወደሃገር ቤት ስልክ እየደወለች ከቤተሰቦቿ ጋር ስለምታገናኛት ይህን እንደተስፋ ቆጥራ በመጽናናት ጥርሷን ነክሳ መስራቷን ቀጠለች። ዳሩ ምን ይሆናል የሴትዮዋ እልህ ከትዕግስቷ አቅም ተሻግሮ ነገሩ ሁሉ ከበዳት። እያደር ባይተዋርነቱ ቢከብዳት ለወሰዳት ኤጀንሲ “አቤት” አለች “ተፈራርመሽ እስከመጣሽ ድረስ ሁኚ እንደምትልሽ መሆን ግዴታሽ ነው” የሚል መልስ ምላሽ ተሰጣት። አንጀቷ ደበነ፣.ውስጧ አረረ።
“ያውና ይታያል ያገሬ ሰማይ፣
እንዲህ ሆዴ ቆርጦ መጥቻለሁ ወይ።”
ስትል አንጎራጉራ ሶስት የመከራ አመታትን ፉት አደረገቻቸው። “ይግረምህና የቡና ሙቀጫ ይመስል ከራሷ እናት ቤት አልፋ ከባሏ እህት ቤትም ጭምር እንድሰራ ታውሰኝ ነበር” አለች የሚወርድ እንባዋን ባይበሉባዋ እየሞዠቀች።
እንደ ዕንጩጭ በቆሎ ያርመጠመጠቻቸው አይኖቿ ያረገዙትን የዕንባ ዘለላ ሲዘረግፉት ብሶት የሞላው ታሪኳም አብሮ ተግተለተለ። ጊዜዋን አድርሳ ወደ እናት ምድሯ ለመመለስ ጓዟን ስትሸክፍ የእስራኤልና ሶሪያ የጦርነት አውድማ ተፋፍሞ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ሆነ። ሸሽተው ቤሩት የከተሙትን ሶሪያውያንን እስራኤል እየተከተለች “በለው” ስትል በባለቤትነት የተረከባቸው ኤጀንሲ በሎንቺና ጠቅጥቆ ለጥቂት ከሞት አፋፍ አስመለጣቸው። እንዲህ ባይሆን ጸሃይ ያለችበት መኪና የሶሪያን ድንበር እንደረገጠ በሰከንዶች ልዩነት የእስራኤል ሰራዊት ድልድዩን ሰብሮት ነበር።
“ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል” የሚሉት ተረት አቆንጅቶ ያሳያትን ስደት ስትቀምሰው እንደኮሶ ጎምድዶ ቢያንገሸግሻትም ከመከራው በላይ “ምን ይዤ ነው የምመለሰው?” የሚለው ጭንቀት እንደረመጥ ይፈጃታል። በስፍራው ያሉ ወገኖች ርሃብና ጥሙ አይሎ ከሰውነት ተራ ሲያወጣቸው ለኢትዮጵያ መንግስት ያሉበትን ሁኔታ አሳወቁና ከክፍያ ነጻ አውሮፕላን ልኮ ለሃገራቸው ምድር አበቃቸው።
ጸሃይ እትብቷ የተቀበረበትን ቀዬ ስትረግጥ ደስታዋ እጥፍ ድርብ ሆነ። ይህ ስሜት ግን ከሁለት ወር መዝለል አልቻለም። ምክንያቱ ደግሞ ይሳሱላት የነበሩት ወላጅ አባቷ በማረፋቸው ነበር። ትኩረቷን ሰብስባ በከፈተችው ሱቅ እየሰራች ለመተዳደር ብትሞክርም ከአባቷ እልፈት ጋር ቀልቧ አብሮ ተገፏልና ዳግም ለስደት ተነስታ የባህሬንን አየር ማገች፤ ይሁን እንጂ አሁንም የተሻለ የስራ ዕድል ሳይገጥማት ቀረ።ይህኔ ታዲያ
“እህህ ይላል ያሰሩት ፈረስ፣
ሳር ባይጥሉለት የልቡ ባይደርስ።”
ያስብላት ያዘ ። ከምድር ዳርቻ የሰፋው ሰማይ ጠቀሱ ፎቅ በውስጡ የሰገሰጋቸውን ክፍሎች ለማጽዳት ቆማ መዋልና ማደሯ ጤናዋን ሲያናጋው አሰሪዋን የሰው ሃይል እንድትጨምር ተማጸነች። አሰሪዋ ግን ሰው ከመጨመር ይልቅ ገንዘብ ልትጨምራት እንደምትችል አሳወቀቻት። “ዞሮ ለህክምና ሊወጣ ምን ያደርግልኛል? እምቢ ካልሽኝ እንግዲያውስ ሸኚኝ” አለችና አንድ ወር እንኳን በቅጡ ሳትደፍን ወደኢትዮጵያ ተመለሰች።
ፀሀይ ሌላ ፈተና ገጥሟት ነበር። የአሰሪዋ ጎረምሳ ልጅ ያለፍላጎቷ ሴትነቷን የመከራ ማቅ ሲያለብሰው ለመከልከል አልሞከረችም። “መኖር ደጉ ብዙ ያሳያል፤ ነገሮች ከመሆናቸው አስቀድሞ የመማር ልምዱ ቢኖረኝ ኖሮ” አለች ሳግ እየተናነቃት። የባህሬኑን ጉዞ የቱንም ያህል የኢኮኖሚ ጥቅም አታግኝበት እንጂ ለአዲስ የህይወት ምዕራፍ ማለትም የልጅ አባቷን ለማግኘት ምክንያት ሆኗታል።
መልሽው ኤርፖርት ውስጥ ወዲያ ወዲህ እየተንቆራጠጠች የምትልከው ሰው ስትፈልግ ከጸሃይ ጋር ተዋወቁና የዛሬ ባለቤቷን የስልክ አድራሻና የሚሰጠውን እቃ አቀበለቻት። ሃገር ቤት እንደገባች አደራ የተባለችውን ንብረት ለማቀበል በተሰጣት ቁጥር ደውላ መልዕክቷን አደረሰች። ከዕቃው ጋር ልቧን ጭምር ለመቀበል የቋመጠው አዲስ ቆይቶ የፍቅር ጥያቄ አከለባት፤ ጸሃይ ግን ሃሳቡን በሆዷ እንደያዘች በባህሬኑ ጉዞ የሻከረ ህልሟን ለማለዘብ ዳግም ወደኳታር አቀናች።
ኳታርም ቢሆን ባሰበችውና በጠበቀችው ልክ አልሰመረላትም። አንድ አመት ብትቆይም ፤ እንደባህሬኑ ሁሉ ቆይታዋን ያደበዘዘው ያሰሪዋ ባለቤት ሚስቱ ወጣ ስትል እግሯን ተከትሎ የጸሃይን የመኝታ በር ሰብሮ በመግባት ሊደፍራት በብርቱ ታገላት። ይህም በህይወቷ ተስፋ እንድትቆርጥ ምክንያት ሆኖ ጊዜዋ ሳይደርስ ውሏን አቋርጣ ለመመለስ ተገደደች።
ሃገሯ እንደገባች በይደር ያቆየችውን የአዲስን የፍቅር ጥያቄ አንስታ ከእህቷ ጋር መከረች። እህት ይሁንታዋን ሰጠቻትና የትዳር ሽርጉዱን አጧጧፉት። ይሁን እንጂ አጨራረሱ አላማረም።
“ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም፣
ፍቅሬ ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም።”
እንደሚሉት ዘፈን አይነት ሆነ። እናቷ ሸጌም ቢሆኑ በትዳሩ ደስተኛ አልሆኑም። ከአዲስ ጋር ሶስት ጉልቻ ከመመስረታቸው በፊት “እንዲህ ነኝ፤ ይህ አለኝ” ሲላት የቆየው ሁሉ የማይጨበጥ እውነት ሆነ። ፀሀይ “አሁን ማን ይሙት ብሯን ብሎ እንጂ ይህን መሳይ ቆንጆ ታገኘው ነበር?” የሚለውን የሰውን ሃሜት ሰምታለችና ትዳሯ እንዳይፈርስ ጎንበስ ቀና ትል ጀመር። ያግዘኛል ብላ ተስፋ በማድረግ በወዳጆቿ በኩል እንጨት ፋብሪካ ብታስቀጥረውም ሀሳቧ አልተሳካም። አቅል የሚያስት ሱሱ ቤቷን ሲመነሸው በትግስት ልትይዘው ጣረች፤ መፍትሄ ቢመስላት ፀነሰች። እሱ ግን በተቃራኒው ውጭ ማደር ጀመረ። ይባስ ብሎ ገንዘብ. የጋብቻ ቀለበታቸውንና ከአረብ አገር ያመጣችውን ወርቅ ሰርቆባት ጠፋ። ጸሃይ የናቷ ህልም ነፍስና ስጋ ሰርቶ በቁመና ስታየው መጪው ህይወቷ አስፈራትና እስከማበድ ደረሰች።
ባሏ ይህ ብቻ አልበቃውም። ሽማግሌ ሰብስቦ “ሱዳን ለመሰደድ ነበር አወጣጤ፤ ነገር ግን አልሆነልኝም” ሲል ዋሸ ።እውነቱን ብታውቅም ልጇ ያለአባት እንዳያድግ አስባ ይቅር አለችው። ቆይታ ግን ለውጥ አጣችበትና እስከወዲያኛው በፍቺ ተለያዩ ። በዚህ መሃል ከስድስት አመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የሄደችባት የቤሩቷ አሰሪዋ ደውላ ስትጠራት ለልጇ ማሳደጊያ የሚሆናት ጥሪት ለማበጀት ዳግም ተነስታ ተጓዘች።
ከሶስት አመታት ቆይታ በኋላ አገር ቤት ስትመለስ እህቶቿን አስተባብራ ማለፊያ ሪስቶራንት ብትከፍትም ጤናዋ ላይ እክል ገጠማት። ሰራተኛ በመቅጠር ዳቦ ቤት ከፈተች። ይህን ጊዜ ጥረቷን ያዩ ደንበኞቿ ቁርስ ቤት እንድትጀምር ወተወቷት። እነሱ እንዳሏት ሆና ሞከረችው ። ውሎ አድሮ ለክስረት የተዳረገው ሪስቶራንት ቢዘጋም ብርቱ ናትና ከአንድ ደንበኛዋ ጋር ‹‹ሎሚ ለሁለት›› ብለው ምግብ ቤት ጀመሩ።
ይህም ቢሆን ባሰበችው ልክ አልቀጠለም። ከባልንጀራዋ ሲለያዩ ጥርሷን ነክሳ ያስቀጠለችው ስራዋ አሁን ላይ ከራሷ አልፎ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ችሏል። የነገ ህልሟን በጠየኳት ጊዜ ወደፊት ሆቴሉን በተሻለ ለማሳደግ እንደምታስብ ገለጸችልኝ። እኔም ምኞቷ ይሰምር ዘንድ ተመኝቼ ጽሁፌን ቋጨሁ።
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም