
ኢትዮጵያ እያደገች ነው። በእዚህም በርካታ የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል። ከእዚህ ቀደም በቤተሰብ አባላት ይከወኑ የነበሩ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለመሥራት ባለሙያ መፈለግ እየተለመደ መጥቷል። ለእዚህም የከተሞች መስፋትን ተከትሎ የሥራ ቦታና የመኖሪያ አካባቢዎች መራራቃቸው፣ እሱን ተከትሎ ሰዎች በመንገድ ረዥም ጊዜ ማሳለፋቸውና እቤት ውስጥ የሚያሳልፉት ጊዜ ውስን መሆን ከምክንያቶቹ መሐል ይገኙበታል።
እናቶቻችን ለመግዛት ሰው አየኝ አላየኝ ብለው ይሸማቀቁባቸው የነበሩት የባልትና ውጤቶችን መግዛት አሁን የተለመደ ሆኗል። በእዚህም በትልልቅ ሱፐርማርኬቶችም ሆነ ራሱን ችሎ የባልትና ውጤቶችን መመልከት አዲስ መሆኑ ካከተመ ሰነበተ። አንድ ሴት ባለሙያ ለመባል ወይም በማህበረሰቡ ተገቢውን ክብር ለማግኘት የግድ ማዋቅ ወይም መከወን አለባት ተብለው ይታሰቡ የነበሩ ነገሮች አሁን ከገበያ ይሸመታሉ። እንጀራ፣ የተነጠረ ቅቤ፣ የወጥ ቅመሞች፣ በቅርቡ ደግሞ ወጥም ከእዚህ ዝርዝሮች ተርታ ተመድቧል።
ታዲያ እነዚህን አማራጮች ከገበያ ከመግዛት ባሻገር ቋሚ የቤት አጋዥ በመቅጠር ማሠራት እንዲሁም ተመላላሽ ወይም ለአንድ ጊዜ ሥራዎችን ሠርቶ የሚሄድ ሰው መቅጠር የተለመደ ነው። ችግሩ የሚመነጨው እዚህ ላይ ነው። ሙያ የሌለው ሰው የማይችለውን ሙያ እችላለሁ ብሎ እንዲቀጠር እንዲሁም ጊዜ ያመቸው ሰው ያሻውን ምርት አሽጎ እንዲሸጥ ሁኔታው ይፈቅድለታል። ደህና ባለሙያን ከሌሎች መለየት ከባድ ሆኗል። አንድ የቤት ሠራተኛ መቅጠር የፈለገ ሰው በሰው ወይም በደላላ ያገኛት ልጅ ሁሉንም የቤት ሙያዎች አጠናቃ እንደምትችል ትናገራለች።
ለእዚህ የሚቀርብ ማስተማመኛ የለም፤ የሀበሻ ሁሉንም፤ እንዲሁም የፈረንጅ የተወሰኑትን እንደምትችል ትዘረዝራለች። ብቃት እንዳላት ትናገራለች። በእዚህ ሂደት የመጣች የቤት ሠራተኛ እንዳለችው ሁሉንም የመቻል ወይም በቀላልነቱ የተነሳ የወንደላጤ ምግብ እንደሆነ የሚነገርለት እንቁላል ሳንዱችንም ያለመቻል እኩል እድል አላት። ለአብነት የባልትና ውጤቶችንና የቤት ሠራተኞችን ጉዳይ አነሳን እንጂ ይህ እውነታ ለአብዛኞቹ የትምህርት ዝግጅት ለማይጠየቅባቸው የሙያ መስኮች ተመሳሳይ ነው።
በሀገራችን በአብዛኛው መደበኛ የትምህርት ዝግጅት ለማይጠየቅባቸውና በልምድ ለሚሠሩ የሙያ ዘርፎች ብቁ ባለሙያዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ነበር:: የባለሙያዎቹን ክህሎት የሚያረጋግጥ ሕጋዊ ማስረጃ የለም ነበርና እችላለሁ ያለውን ሁሉ ከማመን ወይም ስለእነሱ የሚመሰክር ሁነኛ ሰውን እማኝነት ከመጠቀም ውጪ ምርጫ አልነበረም::
ብቁ የሆኑትም ባለሙያዎች አካባቢያቸውን ቢቀይሩ የተሻለ እድል የሚያገኙ ቢሆን እንኳን ለሥራቸው እማኝ የሚሆን መስካሪ ካለበት አካባቢ መራቅን ብዙም አይደፍሩም:: ብቃቱ ቢኖራቸው እንኳን አዲስ አካባቢ ሄደው በሙያቸው ብቃት እንዳላቸው ለማስመስከር ጊዜ ይወስዳል:: ጭራሹንም ቀጣሪ ላይኖር ይችል ነበር::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ይህንን የሚቀይር አሠራር ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል። በልምድ የተገኘ ሥራን እውቅና የሚሰጥ አሠራር ተጀምሯል። በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በልምድ የተገኘ ብቃት ያለው ሰው ክህሎቱ ተመዝኖ እውቅና የሚያገኝበት ሁኔታ ተመቻችቷል:: እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ፤ አንድ ባለሙያ ሙያውን እንዴትና ከየት አመጣው የሚለው ከግምት ውስጥ ሳይገባ ለሙያው የሚያስፈልገውን ክህሎት ይዞ ከተገኘ ለሙያው ብቁ መሆኑን የሚገልጽ እውቅና ይሰጠዋል።
በሀገራችን ካሉ በርካታ ሙያዎች በርካታ ባለሙያዎችን እንዳቀፉ የተለዩ ከ60 በላይ ሙያዎች የመመዘኛ መስፈርቶች እንደተዘጋጀላቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መረጃ ያሳያል። ከእነዚህ ሙያዎች ተጨማሪ ሙያዎች ላይ የመመዘን ጥያቄ ከቀረበ የመመዘኛ መስፈርቶች እንደሚዘጋጁ ተመላክቷል። ሆኖም በወጡት የሙያ መመዘኛ መስፈርቶች ተመዝነው ብቁ መሆናቸው የተረጋገጡ ሰዎች ብቃታቸው ካልተረጋገጠ ባለሙያዎች የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር አልተዘረጋም።
በእርግጥ በከተማ ደረጃ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ትልልቅ ድርጅቶች በተሠራ የተግባቦት ሥራ ሠራተኞቻቸውን ማስመዘናቸውንና የበቁ ሠራተኞች የተሻለ ቦታ ማግኘታቸው ተሰምቷል። በሌሎች መደቦች በልምድ አስፈላጊው የብቃት ደረጃ ላይ የደረሱ ባለሙያዎች በምዘና ማረጋገጫ ማግኘታቸው ከሕሊና እርካታ የዘለለ ጥቅም ሊያገኙበት ይገባል።
ያ ሲሆን ባለሙያዎች ያገኙትን ልምድ ለማስመዘን ይበረታታሉ። አሠሪዎችም የተሻሉ ባለሙያዎችን ከመሐላ በዘለለ የሚያገኙበት አሠራር ይኖራል። ለእዚህም በልምድ የተገኘ ሥራን እውቅና የሚሰጥባቸው የሙያ መስኮች ሊሰፉ ስለእውቅና አሰጣጡ ባለሙያዎችም ሆነ ቀጣሪዎች መረጃ የሚያገኙበት አሠራር ሊዘረጋ ይገባል። ይህ ሲሆን ሀገር እያደገች ስትሄድ ከሚፈጠሩ የሥራ እድሎች የሚጠቀሙ ዜጎች ይበዛሉ። ካልሆነ ሰው “ብቃቱ አለኝ እችላለሁ” ብሎ የሚሰማራባቸው የሙያ ዓይነቶች ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች ተገቢው ክህሎት ባልኖራቸው ቁጥር የተከፈቱ የሥራ እድሎች ተመልሰው ወደ መታጠፍ ይሄዳሉ። በተደጋጋሚ አስፈላጊው ክህሎት አለኝ የሚሉ ሰዎችን እየቀጠረ ያሠራ ግለሰብ፤ በተጨባጭ እነዚህ ባለሙያዎች አስፈላጊው ክህሎት ባልኖራቸው ቁጥር በተጣበበ ጊዜም ቢሆን ሥራዎቹን ራሱ ለመከወን ሊወስን ይገደዳል።
ከእዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ሥራዎች በቀላሉ ቢታዩም ሥራውን በማይችል ሰው መከወናቸው ጉዳቱ ለሀገርም ይተርፋል። ለአብነት የእንስሳት እርድን ማየት ይቻላል። በፊት የቤት እንስሳት እርድ ሲፈጸም ብልት መበለትም ሆነ ቆዳ መግፈፍ ቤተሰብ በጋራ የሚከውነው፤ በእዚህም ልምድ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገርበት ሂደት ነበር። አሁን ግን ዘመኑ የሩጫ ሆኗልና እርድ በዘመናዊ ቄራ ወይም ሰፈር ውስጥ በሚገኙ ባለሙያዎች የሚከወን ተግባር ሆኗል።
በቆዳ ሀብቷ ለምትታወቅ ሀገራችን ታዲያ የእንስሳት እርድ ትርጉሙ ከቤተሰብ ማእድ ይዘላል። በተገቢው መልኩ የተከናወነ እንስሳ እርድ ቆዳ ለሀገር የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል። ግን አሁን ባለው ሀቅ በተለይ በበዓላት ሰሞን ገንዘብ ማግኘት ያማረው ሁሉ ቢላ ይዞ “አራጅ አራጅ” እያለ ይዞራል። ታዲያ ያለእውቀቱ በሙያው የተሰማራ አራጅ ቆዳውን ከጥንቃቄ ጉድለት ስለሚበሳሳው የዶላር ማግኛ የነበረው ቆዳ ገዢ አጥቶ የአካባቢ በካይ ወደ መሆን ይሸጋገራል።
ለቆዳ ምርት ጥራትና ውጤትም የአራጁ ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ፤ የዘርፉ ምሁራን በእርድ ላይ የሚሰማሩም ተገቢው ክህሎት ሊኖራቸው እንደሚገባ ይመክራሉ። ምክራቸው አለፍ ሲልም የእንስሳት እርድ መከናወን ያለበት ተገቢው ክህሎት ባላቸው ሙያተኞች ብቻ መሆኑን ይናገራሉ።
ታዲያ በልምድ የተገኘ ሥራን እውቅና መስጠት መሰል ሙያዎች ላይም የሀገር ሀብትን ከብክነት ለመታደግ ይጠቅማል። በልምድ የተገኘ ሥራን እውቅና መስጠት ይበል የሚያሰኝ ግን አሁንም በጅምር ያለ ሥራ ነውና ተጠናክሮ በርካታ የሙያ መስኮችን አቅፎ፣ እውቅና ያገኙ ሙያተኞች የሚጠቀሙበት አሠራር ተዘርግቶ፣ በሙያተኞችም ሆነ በአሰሪዎች ዘንድ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
ከትዝታ ማስታወሻ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም