ክልሉ ሁሉም ሕጻናት ትምህርት የሚያገኙበት ሁኔታ ፍትሐዊ እንዲሆን እየሠራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፡– በከተማም ሆነ በገጠር የሚገኙ ሕጻናት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የሚያገኙበት ሁኔታ ፍትሐዊ እንዲሆን እየሠራ መሆኑን የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የሲዳማ ክልል ምክትል አስተዳዳሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በሪሶ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ጊዜ በሲዳማ ክልል ከ200 ሺህ በላይ ሕጻናት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት እየተማሩ ይገኛል፤ እነዚህም በአመዛኙ በከተማ የሚገኙ ናቸው። በገጠርም በከተማም የሚኖሩ ሕጻናት የትምህርት ተደራሽነትን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያገኙ እየተሠራ ነው።

በየትኛውም የክልሉ አካባቢዎች ልጆች እኩል እንክብካቤ እና ደረጃቸውን የሚመጥን የትምህርት ማእከል ሊቀርብላቸው እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በተለይ በገጠር የሚገኙ ሕጻናት በቅድመ አንደኛ ትምህርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

ተማሪዎች 12ኛ ክፍል ሲደርሱ ለውጤታቸው ማነስ አንዱ መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች መካከል ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ ያሉ ክፍተቶች መሆናቸው በዳሰሳ ጥናት መመልከት እንደተቻለ ጠቅሰው፤ ሕጻናት ጥሩ የእውቀት መሠረት እንዲኖራቸው ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ በእንክብካቤ እና በነፃነት ማስተማር እንደሚገባ በመረዳት ወደ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል፡

ቀደም ሲል የሲዳማ የትምህርት ተሐድሶ በሚል ንቅናቄ ሕጋዊ ማሕቀፍ በማስያዝ ሀብትን ከተለያዩ ምንጮች አሰባስቦ ወደ ሥራ መገባቱን በመጥቀስ፤ በእዚህም የመጀመሪያው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶችን በገጠር ማስፋፋት መሆኑን አመልክተዋል።

በክልሉ ከ200 ሺህ በላይ ሕጻናት በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ በክልሉ ካሉት 37 የወረዳና ከተማ መስተዳድር መዋቅሮች 24ቱ በተሟላ ሁኔታ አጠናቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን እና ለእዚህም እውቅና መሰጠቱን ገልጸዋል። ደረጃቸውን የጠበቁ መማሪያ ቦታዎች እና የአስተማሪዎች ማረፊያ እንዲሁም የመጫወቻ ቦታዎችን በማሟላት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም ጠቅሰዋል።

ሁሉንም ማህበረሰብ በማነቃነቅ በርካታ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰው፤ መንግሥት የማስተባበር ሥራ በመሥራት ባለሀብቶች፣የመንግሥት ሠራተኞች እና ማህበረሰቡ ባደረጉት ተሳትፎ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ባይዳረስም አበረታች ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርትን በሁሉም ወረዳዎች ተደራሽ እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል።

በትውልድ ለትምህርት ንቅናቄ የነባር ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል እና የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሆነ በማመልከት፤ ጎን ለጎን የመምህራንን ቁጥር የማስፋትና አቅም የመገንባት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ወላጆች ሕጻናትን ለማስተማር ብዙ ገንዘብ ያወጡ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ በተስፋፉት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በነጻ የሚያስተምሩበት ሁኔታ በመመቻቸቱ ወላጆች እፎይታ ማግኘታቸውን አስረድተዋል። ሕጻናቱም ተገቢውን ክህሎት እና እንክብካቤ ስለሚያገኙ ቀጣዩ የትምህርት ሂደት ቀላል እንዲሆን ይረዳቸዋል ሲሉ አመልክተዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You