ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢውን ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነት አለበት!

ሁሉም ነበር ተገማች መሆን ባልቻለበት ባለንበት ዘመን፤ ያለ ባሕር በር የሀገርን እጣ ፈንታ የተሻለ አደርጋለሁ ብሎ መናገር አይደለም ሀገርን ባለችበት ሁኔታ ማስቀጠል ይቻላል ብሎ ማሰብ አደጋን በሀገር እና በሕዝብ ላይ ከመጋበዝ የሚተናነስ አይደለም። የአደጋው ስሌትም ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና አዳጊ ኢኮኖሚ ላላቸው ሀገራት የከፋ እንደሚሆን ይታመናል።

የባሕር በር ጉዳይ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ከወደብ ፣ ከወጪ እና ገቢ ንግድ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ብቻ አይደለም። በእርግጥ አሁን ላይ በንግዱ ዓለም ካለው ከፍተኛ ፉክክር እና ተወዳዳሪነት አኳያ የወደብ ጉዳይ በአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ወደብ አልባ መሆን በራሱ ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ ሊያስከትል የሚችለው ስጋት ከህልውና ጋር ሊተሳሰር የሚችል ነው።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ወደብ ያላቸው ሀገራት ወደብ ከሌላቸው ሀገራት የ10 ከመቶ የኢኮኖሚ ብልጫ ይኖራቸዋል። ይህ ብቻ በራሱ ወደብ የሌላቸው ሀገራት ኢኮኖሚ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚኖረው ተፎካካሪነት ላይ የቱን ያህል ፈተና እንደሚሆን ብዙም ለመገመት የሚከብድ አይደለም።

በተለይም የሀገራቱ የወጪ ንግድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊኖረው በሚችለው ተወዳዳሪነት ላይ ተገማች የ10 በመቶ ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀርም። ይህ አሀዝ ከፍተኛ ፉክክር እያስተናገደ ባለው የዓለም ገበያ ላይ ሊኖረው የሚችለው የገበያ ስልት ትርጓሜ ለሀገራቱ ኢኮኖሚ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑ የማይቀር ነው።

በሀገር ውስጥ ንግድ ላይም ቢሆን የሚፈጥረው የዋጋ ግሽበት ፣ የዜጎች የመግዛት አቅም የሚያዳክም ነው። ከእዚህ ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችለው ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በራሱ ሀገራቱ የሰከነ እና የተረጋጋ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረት ላይ ትልቅ ፈተና ነው።

ከእዚህም ባለፈ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የባሕር የንግድ መስመርን ተከትሎ ሊኖር ከሚችል ጂኦ ፖለቲካል ተጽእኖ ፈጣሪነት የተገለሉ ናቸው። ከተጽእኖ ፈጣሪነት ይልቅ ተጽእኖ ተሸካሚ ናቸው። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራቸውን ተሰሚነት የሚያደበዝዝ ነው። ከእዚህ ጋር በተያዘው ሊያስተናግዱት የሚችለው ተጽእኖ እንደ ሀገር ባላቸው ህልውና ላይ ቀልሎ የሚታይ አይደለም።

በተለይም የጂኦ-ፖለቲካ ተጽእኖ ፈጣሪነት በአዲሱ ዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ካለው ሰፊ ስፍራ አኳያ፤ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና የወሊድ ምጣኔ ያለበት ማህበረሰብ ይዞ ተጽእኖ ተቀባይ ሆኖ እንደ ሀገር መቀጠል የሚታሰብ አይሆንም፤ ነገን በተስፋ የሚጠብቅ ማህበረሰብ መፍጠር አይቻልም።

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና አዳጊ ኢኮኖሚ ላላቸው ፤በብዙ ፍላጎቶች የተጽእኖ አቅሙ ሁለንተናዊ ከሆነው የቀይ ባሕር ከ60 ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ ለሚገኙ ሀገራት ችግሩ ተጨባጭ የህልውና ጉዳይ መሆኑ የማይቀር ነው። ይህን ያህል ሰፊ ሕዝብ ይዞ ተጽእኖ በበዛበት ቀጣና፤ በተዘጋ በር ውስጥ እንደ ሀገር መቀጠል በራሱ ትልቅ ፈተና ነው።

ችግሩ እንደሀገር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም ለማፈላለግ ለሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ተግዳሮት መሆኑ የማይቀር ነው። በቀጣናው ጥቅም ያላቸው ሀገራትም ቢሆኑ ጥቅማቸውን በዘላቂነት ለማስቀጠል ሀገሪቱ ከባሕር በር ጋር በተያያዘ ያነሳችው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል።

ሀገሪቱ ለዘመናት በእጇ የነበረውን፣ የተፈጥሯዊ ማንነቷ አካል የሆነውን የባሕር በር በብዙ ሴራዎች ያለአግባብ ከእጇ ተነጥቃለች። በጉዳዩ ዙሪያ ፍትሕን የሚጠይቅ ፣ ስለ ብሔራዊ ጥቅሞቿ የሚሞግት መንግሥት አጥታ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የችግሩ ሰለባ ሆናለች።

በእነዚህ ሦስት አስርት ዓመታት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በብዙ ትጋት ተከታታይነት ያለው ከፍተኛ እድገት ቢያስመዘግብም፤ በሀገሪቱ ያለው የሕዝብ ቁጥር ከእጥፍ በላይ አድጓል። ይህም ከባሕር በር አልባነት ጋር ተዳምሮ፤ በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን የኢኮኖሚ እድገት ትርጉም አደብዝዞታል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ የጀመረችው ከራሷ አልፎ ለቀጣናው ፣ ከእዚያም ተሻግሮ ለመላው አፍሪካውያን ወንድም እህቶቻችን መነሳት ሊሆን የሚችለው ድህነትን ታሪክ የማድረግ የመደመር የለውጥ ጉዞ ስኬታማ ሊሆን የሚችለውም ቀድሞ ለሀገሪቱ የህልውና ጉዳይ የሆነው የባሕር በር ጉዳይ አዎንታዊ ምላሽ ስታገኝ ነው።

ለጥያቄዋ አግባብ ያለው ምላሽ ለመስጠት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የታሪክ ፣የሕግ እና የሞራል ግዴታ አለበት። ጥያቄው እንደ ሀገር በግፍ ያጣችውን የባሕር በር በሰላማዊ እና ፍትሐዊ መንገድ ማግኘት ነው። ለጥያቄው ምላሽ መንፈግ ሀገሪቱን እና የሕዝቦቿን ነገዎች ማጨለም፣ እንደ ሀገር እና ሕዝብ ያላቸውን ዘመናት የተሻገረ ህልውና ስጋት ውስጥ መጣል እና ለቀጣናው ሰላም ትኩረት መንፈግ ይሆናል!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You