
አሜሪካና ቻይና የንግድ ስምምነት መፈራረማቸውን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል። ትራምፕ በዋይት ሃውስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ “ከቻይና ጋር ስምምነት ተፈራርመናል” የሚል አጭር መረጃ ተናግረዋል።
ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የዋይት ሃውስ ባለሥልጣን በበኩላቸው፤ የትራምፕ አስተዳደርና ቻይና የጄኔቫውን ስምምነት ለመተግበር የሚያስችል ማሕቀፍ ላይ ተነጋግረው መስማማታቸውን ገልጸዋል። ማሕቀፉ ቻይና ወደ አሜሪካ በሚገቡ ልዩ ማዕድናት ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ እንድታነሳ የሚያስችል እንደሆነ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።
አሜሪካ እና ቻይና ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ አንዳቸው በሌላቸው ምርቶች ላይ የጣሉትን ታሪፍ ለ90 ቀናት ለመቀነስ ከስምምነት ደርሰው እንደነበር ይታወሳል። ሁለቱ ኃያላን ሀገራት እዚህ ስምምነት ላይ መድረሳቸው የተገለጸው በስዊዘርላንድ በዝግ ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው። ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ከጣሉ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የሀገራቱ ውይይት፤ ሁለቱም ሀገራት የጣሉትን ታሪፍ በ115 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ተስማምተው ነበር።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ 145 በመቶ ታሪፍ ሲጥሉ፤ ቤጂንግ በምላሹ ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ 125 በመቶ ታሪፍ ጥላለች። በስምምነቱ መሠረት አሜሪካ በቻይና ምርቶች ላይ የጣለችውን ታሪፍ ለ90 ቀናት ወደ 30 በመቶ ዝቅ ስታደርግ፤ ቻይና በአሜሪካ ምርቶች ላይ የጣለችው ታሪፍ ደግሞ እንዲሁ ለተመሳሳይ ቀናት ወደ 10 በመቶ ይቀንሳል።
ከጄኔቫው ንግግር በኋላ የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ጃሚየሰን ግሪር ከቻይናውያን አጋሮቻችን ጋር የደረስንበት ስምምነት አሜሪካ ያለባትን አንድ ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር የንግድ ጉድለት ይቀንሳል ብለዋል። በእርግጥ ቤሰንት የንግግራቸው ትኩረት ውጥረት ማርገብ ላይ እንደሆነና ውይይቱ ትልቅ የንግድ ስምምነት እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው ይታወሳል።
የአሜሪካንና የቻይናን ውይይት “ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የሚደረግ ጉዞ” ሲሉ ያደነቁት የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ፤ ሁለቱም ሀገራት ውጥረቶችን የሚቀንሱ፣ የሚታየውን ሁኔታ የሚያድሱ እና በባለብዙ ወገን የግብይት ሥርዓት ላይ ያላቸውን እምነት በማጠናከር ተግባራዊ መፍትሔዎችን በማዘጋጀት ግስጋሴያቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበው ነበር።
ይሁን እንጂ ከስምምነቱ መፈረም ጥቂት ሳምንታት በኋላ ሁለቱም ወገኖች ስምምነቱ እየተጣሰ ነው በሚል ሲወነጃጀሉ ታይተዋል። ትራምፕ፤ ቻይና ስምምነታቸውን እየጣሰች እንደሆነ እና ቻይና በበኩሏ የጣሰችው የስምምነት አካል እንደሌለ በየፊናቸው ገልጸው ነበር።
በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለው የንግድ ጦርነት የተካረረው ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ታሪፍ መጣላቸውን ተከትሎ ነው። ሁለቱ የዓለም ባለግዙፍ ምጣኔ ሀብት ባለቤቶች የገቡበት የንግድ ጦርነት በፋይናንስ ገበያው እና በዓለም ላይ ግሽበትን ያስከትላል የሚል ፍርሀት ቀስቅሶ ቆይቷል።
ቻይናና አሜሪካ ካላቸው ግዙፍ የንግድ ልውውጥ አንጻር የታሪፍ ውሳኔው የሀገራቱን ንግድ ሊጎዳው እንደሚችል በተደጋጋሚ ሲገለጽ ነበር። ባለፈው ዓመት አሜሪካ የ438 ቢሊዮን ዶላር ምርት ከቻይና ያስገባች ሲሆን፤ ቻይና ደግሞ 143 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ከአሜሪካ ሸምታለች። በእዚህም አሜሪካ ከቻይና ጋር በምታደርገው የንግድ ልውውጥ የ295 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ጉድለት ገጥሟታል። አሜሪካ ከቻይና የምታስገባቸውን ምርቶች ከሌሎች ሀገራት በአጭር ጊዜ ለመተካት መቸገሯ አይቀርም። ቻይናም ብትሆን ለምጣኔ ሀብቷ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የውጭ ንግዷ በታሪፍ ጫና ውስጥ ሲወድቅ ቀላል የማይባል ፈተና እንደሚገጥማት ግልጽ ነው።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከተለያዩ ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጋቸውን ያሳወቁት ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ገደማ ነው። ሀገራቱ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት በሀገራቱና በአሜሪካ መካከል የንግድ ድርድሮች እየተካሄዱ ነው።
ትራምፕ ለታሪፍ ጭማሪው የሚያነሷቸው ምክንያቶች ከአደንዛዥ መድኃኒቶችና ከሕገ ወጥ ስደተኞች እንዲሁም ከንግድ ሚዛን ኢ ፍትሐዊነት ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ጎረቤቶች ካናዳና ሜክሲኮ ሕገ ወጥ ስደተኞችና እንደፌንታኒል (Fentanyl) ያሉ አደገኛ መድኃኒቶች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ቁጥጥር አያደርጉም የሚለውን የመረረ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ከእዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ “አሜሪካ በጎረቤቶቿና በሌሎች የሩቅ ሀገራት ለበርካታ ዓመታት ስትበዘበዝ ኖራለች፤ በሀገራቱና በአሜሪካ መካከል ያለው የንግድ ሚዛን ኢ ፍትሐዊና አሜሪካን የጎዳ ነው” የሚል አመለካከት አላቸው።
ከሌሎች ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለው ቀረጥ አሜሪካውያን ሸማቾች የሀገር ውስጥ ምርቶችን እንዲገዙ እንደሚያበረታታ፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚያሳድግ እንዲሁም የሚሰበሰበው የታክስ መጠን እንዲጨምር እንደሚያደርግ ይከራከራሉ።
በእርግጥ አሜሪካ በዓለማችን ትልቁ የንግድ ጉድለት ያለባት ሀገር ናት። እኤአ የ2023 መረጃዎች እንደሚሳዩት፤ የሀገሪቱ የንግድ ጉድለት ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ነው። ሀገሪቱ በ2024 ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በነበራት የንግድ ልውውጥ ደግሞ የ213 ቢሊዮን እንዲሁም ከቻይና ጋር በምታደርገው የንግድ ልውውጥ ደግሞ የ295 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ጉድለት ገጥሟታል። ትራምፕ ይህንን የንግድ ጉድለት “ግፍ” ሲሉ ጠርተውታል። በአጠቃላይ ይህ የንግድ ጉድለት የመጣው ከአሜሪካ ወደ ሌሎች ሀገራት የሚላኩ ምርቶች ከፍተኛ ታሪፍ ስለሚጣልባቸው እንደሆነ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያምናሉ። መላውን ዓለም ያስገረመውን የታሪፍ ውሳኔ ይፋ ያደረጉትም ይህን የንግድ ጉድለት ለማስተካከል አስበው ነው።
“መዝገበ ቃላት ውስጥ ካሉ ቃላት መካከል በጣም የምወደውና ደስ የሚያሰኘኝ ‘ታሪፍ (Tariff)’ የሚለው ቃል ነው” ብለው የተናገሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ የታሪፍ ጭማሪ የአሜሪካን አምራች ኢንዱስትሪ ለመጠበቅና ምርትን ለማሳደግ ይጠቅማል ብለው ያምናሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ግን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በየጊዜው ይፋ የሚያደርጓቸው የታሪፍ ጭማሪዎች ለዋጋ ንረት፣ ለምጣኔ ሀብት መዳከምና ለዓለም አቀፍ የንግድ ጦርነት እንደሚያስከትሉ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። እንደባለሙያዎቹ ማብራሪያ፤ የታሪፍ ጭማሪው ለአሜሪካውያን ሸማቾች የምርቶች ዋጋ እንዲንር ያደርጋል፤ በሌሎች ሀገራትም የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም