በመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ ያንፀባረቁ ኮከቦች

የኦሊምፒክና መላ አፍሪካ ጨዋታን ፅንሰ ሃሳብ አንግቦ የሚካሄደው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተቋርጦ በመቆየቱ ብዙዎች ይቆጫሉ። አንዱ የቁጭታቸው ምክንያት ደግሞ እንደ ሀገር ተተኪ ስፖርተኞችን ማግኘት የሚቻልበት እድል በመቅረቱ ነው። በእርግጥም በዓለም ቻምፒዮናና በኦሊምፒክ መድረኮች ዛሬም ድረስ ጠንካራ ተፎካካሪና ሜዳሊያዎችንም ማስመዝገብ የቻለው አትሌት ኃጎስ ገብረህይወት፣ በኦሊምፒክ ኢትዮጵያን መወከል የቻለችው ብስክሌት ጋላቢዋ ሀድነት አስመላሽን የመሳሰሉ አትሌቶችን ያፈራው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታ መሆኑ ሲታሰብ ቁጭቱ የተጋነነ አይደለም።

መላ ኢትዮጵያ ጨዋታ ከእነዚያ ዓመታት መቋረጥ በኋላ ዘንድሮ ተመልሶ ለ6ኛ ጊዜ በጅማ ሲካሄድ አሁንም በበርካታ ስፖርቶች ሀገርን በዓለም መድረክ ሊወክሉ የሚችሉ አትሌቶችን ማፍራት እንደሚችል አሳይቷል። ለእዚህም ፉክክር ከተደረገባቸው 26 የስፖርት ዓይነቶች በበርካቶቹ ማንፀባረቅ የቻሉ ወጣት ኮከቦች ማሳያ ናቸው።

በዘንድሮው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በየውድድር ዓይነቱ በርካታ ተስፈኛ ኮከቦች ቢታዩም፤ በቦክስ ስፖርትና በውሃ ዋና ድንቅ ብቃት ያሳዩ ወጣቶች የብዙዎችን ቀልብ በመሳብ መነጋገሪያ ሆነዋል።

በአስሩ ቀናት የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ ድንቅ ብቃት በማሳየት በደርዘን የሚቆጠር የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለው የውሃ ዋና ተወዳዳሪ በልዩነት ይጠቀሳል። ይህ የውድድሩ ክስተት የሆነ አትሌት በኮምቦልቻ ከተማ የተወለደው ተምኪን ጌታቸው ይባላል፡፡ አስራ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ብዙዎችን አስገርሟል። በውድድሩ የተሳተፉ በርካታ ክልሎች የእዚህን ወጣት ያህል የወርቅ ሜዳሊያ መሰብሰብ አልቻሉም።

የውሃ ዋና ስፖርትን በኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ የጀመረው ወጣቱ ዋናተኛ ተምኪን ጌታቸው፤ በአማራ ክልል ከታዳጊዎች እስከ ዞን ውድድሮች በመሳተፍ ያለውን አቅም በሚገባ አሳይቷል፡፡ በቅርቡ በተደረገው የመላ አማራ ጨዋታዎች ድንቅ ብቃቱን በማሳየት ክልሉን ለመወከል የበቃው ተስፈኛ የውሃ ዋና ተወዳዳሪ፤ የጅማው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይም ክስተት ሆኖ ጎልቶ እንዲወጣ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮለታል። ተምኪን ከተወዳደረባቸው 13 የውሃ ዋና ስፖርቶች 12 የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል፤ በአንድ ውድድር ደግሞ የብር ሜዳሊያ በማግኘት ታሪክ ሠርቷል፡፡

ኢትዮጵያ ስኬታማ ባልሆነችበት የስፖርት ዓይነት ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚፈልግ የገለጸው ተምኪን፤ በተለይ በኦሊምፒክ መድረክ የሀገሩን ስም ማስጠራት ትልቁ ግቡ መሆኑንም ይናገራል፡፡ ከእዚህ በፊት በአህጉርና ዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያን መወከል የቻሉ ዋናተኞችን ያፈራችው ኮምቦልቻ አሁን ደግሞ ተምኪን ጌታቸውን በመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ አማካኝነት አስተዋውቃለች። የዘንድሮው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታ ከተምኪን ጌታቸው በተጨማሪ ሌላኛው ከኮምቦልቻ የተገኘው አብዱ ሁሴንንም አበርክታለች። አብዱ በውሃ ዋና ስፖርት 9 የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ሌላኛው የውድድሩ ክስተት ሲሆን፤ አማራ ክልል በውድድሩ ካስመዘገባቸው ሜዳሊያዎች 50 በመቶ የሚሆነው ወርቅ የተገኘው በውሃ ዋና ስፖርት ነው። ለእዚህ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ደግሞ ሁለቱ ወጣት ዋናተኞች ናቸው።

ሌላኛው የመላ ኢትዮጵያ አንፀባራቂ ኮከብ ደግሞ የተገኘው ከወደ አዲስ አበባ ሲሆን፤ እሱም በቡጢ ፍልሚያ ተወዳዳሪዎቹን ያንቀጠቀጠው የ15 ዓመቱ ታዳጊ ቦክሰኛ ዳግማዊ አንዱዓለም ነው።

የወደፊቱ ተስፈኛ የቡጢ ተፋላሚ ዳግማዊ ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ኮልፌ ሲሆን፤ ወደ ቦክስ ስፖርት የገባው ገና በታዳጊነቱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ አርዓያ የሆነው ደግሞ በኦሊምፒክ ተሳትፎው የሚታወቀው ቦክሰኛ አጎቱ አዲሱ ጥበቡ ነው።

ታዳጊው ዳግማዊ በ9 የፉክክር መድረኮች ተሳትፎ 6 ወርቅ በማምጣት ከእኩዮቹ በርቀት የተቀመጠ ስፖርተኛ ሆኗል። በመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ ሦስት ጨዋታዎችን አድርጎ ሁሉንም በማሸነፍ ለአዲስ አበባ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል።

“ሕልሜ በኦሊምፒክ ላይ ተሳትፌ ለሀገሬ የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣት ነው፡፡” ይላል ዳግማዊ የወደፊት ተስፋውን ሲናገር። “እስካሁን ድረስ ኦሊምፒክ ላይ በቦክስ ስፖርት ለኢትዮጵያ የትኛውም አትሌት ሜዳሊያ አላመጣም እኔ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሆን እፈልጋለሁ ፡፡” በማለት ሕልሙ እሩቅ እንደሆነ ይናገራል።

ዳግማዊ የቦክስ ስፖርት ፍቅሩ ከቤተሰብ በተለይም አርዓያ ከሆነው አጎቱ በኦሊምፒክ ተሳታፊ የፈለቀ ቢሆንም፤ ታዳጊው ቦክሰኛ ግን ሕልሙ ከአጎቱ ከፍ ባለ መልኩ ሀገሩን ማስጠራት እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን ነው።

ሕልሙን ለማሳካት እየጣረ እንደሚገኝ የገለጸው ዳግማዊ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርትቶ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ በመሳተፍ ልምድ ማግኘት እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን ስፖርቱ ትልቅ ትኩረት እንደሚፈልግ አስረድቷል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You