ባሕላዊ እና መደበኛ ፍርድ ቤቶች ተደጋግፈው መሥራታቸው የፍትሕ ሥርዓቱን አፈጻጸም አሻሽሏል

አዲስ አበባ፡- ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጋር ተደጋግፈው መሥራታቸው የክልሉ የፍትሕ ሥርዓት አፈጻጸም እንዲሻሻል አስችሏል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ጋዛሊ አባሲመል አስታወቁ።

43ኛው ዙር “ጉሚ በለል” ፤ “ባሕላዊ ፍርድ ቤት ለባሕላዊ ፍትሕ” በሚል መሪ ሃሳብ የጥናት ውጤትን መሠረት ባደረገ ውይይት በትናንትናው እለት በኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ተካሂዷል።

በመርሃ-ግብሩ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ጋዛሊ አባሲመል፤ ክልሉ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችለውን አዋጅ ቁጥር 240/2013 በማጽደቅ ሥራ ላይ እንዲውል ከአደረገ ወዲህ፤ በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጎን እየሠሩ የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት ውጤታማ እንዲሆን አግዘዋል።

በአንድ ሀገር አስተዳደር ውስጥ ትኩረት ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አንዱ በሕዝቦች መካከል ፍትሕን ማስፈን ነው ያሉት አቶ ጋዛሊ፤ ይህም የሰው ልጆች ኑሮ እና አኗኗር ዋስትና እንዲኖረው ያስችላል ብለዋል። የሰዎች በጋራ የመኖርና አብሮ የመዝለቅ ሁኔታ ስኬታማ የሚሆነውም በመካከላቸው ትክክለኛ ፍትሕ ሲሰፍን እንደሆነ ተናግረዋል።

በኦሮሞ ባሕል መሠረት በአንድ ሰው ላይ የሆነ ሕገ ወጥ ድርጊት ሲፈጸም በግለሰቡ እንደተፈጸመ ብቻ ተደርጎ ሳይሆን የሚታመነው፤ በፈጣሪና በምድሪቱ ላይ የተፈጸመ መጥፎ ድርጊት ተደርጎ ነው የሚታየው ብለዋል። ስለሆነም ጥፋቶች ሲከሰቱ የሰው ሕግ ብቻ ሳይሆን የፈጣሪም ሕግ ተጥሷል ተብሎ እንደሚታመን አቶ ጋዛሊ አስረድተዋል። ይህ ባሕላዊ አሠራር እውነትን ፈልፍሎ በማውጣት ፣ በሰው እና በሰው፣ በጎሳ እና በጎሳ በሰውና በምድሪቱ፣ በሰውና በፈጣሪ መካከል እርቅ እንዲወርድ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

እንዲህ ዓይነቱ ባሕላዊ እሴትም በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ፣ ክብርና ተቀባይነት እንዳለው ገልጸው፤ ባሕላዊ ሥርዓቱን መለስ ብሎ ማየትና ማስቀጠሉ ለፍትሕ መስፈን ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ አመልክተዋል። ይህም ለምርጫ የሚቀርብ ሳይሆን፤ የትውልዱ ግዴታ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በመደበኛው የፍርድ ሥርዓት ሰዎች የሚዳኙት እና ፍትሕ የሚያገኙት በተጻፈ ሕግ ነው፤ በፍርድ ሂደትም የተሻለ ምስክር ወይም ጠበቃ ያለው አሸናፊ ይሆናል ያሉት አቶ ጋዛሊ፤ በባሕላዊ ፍርድ ቤት ግን ከእንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ይልቅ አሸናፊ የሚያደርጉት ታማኝነት፣ እውነትና ፈጣሪን መፍራት መሆናቸውን ተናግረዋል። በክልሉ ሁለቱም የፍርድ ሥርዓቶች ጎን ለጎን የሚተገበሩ በመሆናቸው የፍትሕ ሥርዓቱ እየተሻሻለ መምጣቱን አቶ ጋዛሊ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል የሕግ ማሠልጠኛ እና ምርምር ተቋም የሕግ አሠልጣኝና የጥናታዊ ጽሑፉ አቅራቢ አቶ ሚልኪ መኩሪያ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በኦሮሚያ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች ወደ ሥራ ከገቡ ገና የሦስት ዓመት እድሜ ያላቸው ናቸው። እስከ አሁን በክልሉ ከ6ሺህ 900 በላይ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመዋል። በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ300ሺህ በላይ ጉዳዮችን ተመልክተዋል።

በሦስቱም ደረጃ የሚገኙ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ከባሕላዊ ፍርድ ቤቶች በ15ሺህ መዝገብ ብቻ ብልጫ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በርካታ ሰዎች ወደ ባሕል ፍርድ ቤቶች እየቀረቡ የመዳኘት ልምድ እያዳበሩ መምጣታቸውን አቶ ሚልኪ ተናግረዋል።

“ጉሚ በለል” የገዳ ሥርዓት አካል በሆኑ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ በተለያየ ጊዜ የሚደረግ ወይይት ነው፤ “ባሕላዊ ፍርድ ቤት ለባሕላዊ ፍትሕ” በሚል በትናንትናው እለት የተካሄደው ጉሚ በለል 43ኛው ዙር ሲሆን ፤ መድረኩ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥናትን መሠረት ያደረገ ውይይት የተካሄደበት ነው።

መርሃ ግብሩን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እና የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን፤ በመርሃ-ግብሩ ላይ ከተለያዩ ከዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የሕግ ምሁራን ፣ ባለሙያዎች፣ የገዳ አባቶችና ሀደ ስንቄዎች እንዲሁም አርቲስቶች እንደተገኙበት ታውቋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You