አፍሪካውያን በምዕራብ አፍሪካ በኩል ያለውን ስደት በአግባቡ የተረዱ አይመስሉም:: በርግጥ በአሁኑ ወቅት ስደቱ አዲስ አይደለም:: በአንዳንድ የአፍሪካ ህትመቶች ላይ ምዕራብ አፍሪካ አካባቢ ያለውን ችግር ከመፍታት ይልቅ መስደብ ይቀናቸዋል:: አካባቢው ኋላቀር ነው ተብሎም ይታሰባል:: አፍሪካውያን ያለውን ችግር ለመፍታት ጠንካራና ምክንያታዊ የሆነ ሥራ መስራት ከተቻለ የነበሩ ችግሮችን መፍታት ይቻላል:: የማስተካከያ እርምጃው የሚታዩ ችግሮችን ከመቀነስ ባሻገር እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ምን እንደሆኑ ለመለየት ያስችላል::
በዚህም በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ ርብርብ ያስፈልጋል:: በአካባቢው የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት አፋጣኝ መፍትሄዎች ይጠበቃሉ:: ከላይ የተቀመጠው መንደርደሪያ መነሻ የሆነው በቅርቡ ሲኤን ኤን በጋና ያለውን የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ በማስመልከት የሰራው ዘጋቢ ፊልም ነው:: ዘጋቢ ፊልሙ በጋናውያን የፖለቲካ ሰዎች አጋዥነት የተሰራ ሲሆን ቤቲ ሜናሳህ፣ ሳሙኤል ኦኬሬ፣ ካዊሚ አጋሪማን የተለያዩ ፅሁፎችን ለአልጀዚራ አዘጋጅተው ልከዋል:: በዚህ በተያያዘ አካሄድ ‹‹ በጋና ምንም አይነት የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ መኖር የለበትም›› በሚል ዘመቻዎች እየተደረጉም ነው::
በምዕራብ አፍሪካ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በተለይ በጋና በለውጥ ላይ የሚገኝ ነው:: የአገሪቱ መገናኛ ብዙሀን እና የአገሪቱ ባህልን መሰረት በማድረግ ሜኒሳህ፣ ኦክዬሬ እና አጋሪማን የበኩላቸውን ለመወጣት ጥረት እያደረጉ ነው:: ነገር ግን እነሱ እያዘጋጁ ያለው ፅሁፍ ምን ያክል በአገሪቱ የተፈጠረውን የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ያስቀረዋል የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ ነው:: ጸሐፊዎች በዋናነት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያሳዩት ያልተገባ እንቅስቃሴ እና የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀን በምዕራብ አፍሪካ ያሉትን ችግሮች አጋነው የሚያቀርቡበት መንገድ ትክክል አለመሆኑን ጠቅሰዋል:: በተያያዘም በጋና ያለውን የህፃናት የጉልበት ብዝበዛና ሽያጭ ለማስቆም በተለይ በቮልታ ሀይቅ አካባቢ ያለው ሁኔታ ላይ ትኩረት ሰጥተዋል::
በተጨማሪም የህፃናት ንግድና የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ በቮልታ ሀይቅ አካባቢ የተበራከተ ቢሆንም አሳማኝ መረጃዎችን ለማቅረብ ሜኒሻ፣ ኦክያሬ እና አግራማን ተቀባይነት ያለው ሀሳብ ማቅረብ ያስፈልጋቸዋል:: በህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ በህፃናት ሽያጭና ንግድ ላይ ትክክለኛ መረጃ አለማግኘት በአካባቢው ያለውን ችግር ለመፍታት አዳጋች አድርጎታል:: የጋና ባለስልጣናት ጠንካራ ሥራ መስራት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ በየአካባቢው ምን ያክል ህፃናት እንደሚገኙ መረጃ መያዝ ይጠበቅባቸዋል:: እያንዳንዱ ህፃን ተለይቶ ከተመዘገበ በኋላ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን መደረግ አለበት:: ምክንያቱም ህፃናቱ ከጉልበት ብዝበዛ፣ ከባርነትና ከሽያጭ ነፃ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ማስቀመጥ አይቻልም::
በህፃናት ጉልበት ብዝበዛና በህፃናት ባርነት መካከል ልዩነቶች እንዳሉ በአክቲቪስቶች ሲነገር ይደመጣል:: መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ምሁራን የጉልበት ብዝበዛ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል እና በአገሪቱ ባህል ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ይናገራሉ:: ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ሲተረጉመው ‹‹ ህጻናትን ያለ ዕድሜያቸው ሥራ ማሰራት አቅማቸውንና መብታቸውን የሚነካ በመሆኑ አካላቸውንና አዕምሯቸውን የሚጎዳ ድርጊት ነው›› ይላል:: በተጨማሪም የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ አለ የሚባለው ህጻናት በባርነት ሲገዙ መሆኑንም ያስቀምጣል::
ተቀማጭነቱን በእንግሊዝ ያደረገው ዓለም አቀፉ የፀረ ባርነት ተቋም እንደሚለው፤ የህፃናት ባርነትና የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ልዩነት ቢኖራቸውም ጉዳታቸው ግን ተመሳሳይ ነው:: የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ለህፃናት ጉዳት ከማምጣት ባሻገር ዕድገታቸውና ትምህርታቸው እንዲገታ ያደርጋል:: የህጻናት ባርነት ሲባል ግን ለአንድ ሰው ጥቅም ሲባል የህፃናቱን ጉልበት መበዝበዝ ነው::
እነዚህ ሀሳቦች ላይ ውይይት ሲደረግ መታወቅ ያለበት በተለያዩ አገራት ባህል መሰረት ህፃናት ቤተሰቦቻቸውን በቤት ውስጥ ሥራ ማገዝ ግዴታቸው ነው:: አንዳንዴም ህፃናት በኢኮኖሚ ቤተሰባቸውን ለመደገፍ የተለያዩ ገንዘብ አምጭ ሥራ ላይ ይሰማራሉ:: ሁሉንም ሊያስማማ የሚችለው ግን ህፃናት መስራት የሚገባቸው አካላቸውና አዕምሯቸው ላይ ጉዳት የማያመጡ ሥራዎች ላይ ነው:: አሁን እያከራከረ ያለው ጉዳይ ግን ህፃናት ቤተሰባቸውን ለመርዳት ወይም ለማገዝ ምን አይነት ሥራ መስራት አለባቸው የሚለው ነው:: ህፃናቱ በምንም ዓይነት ምክንያት ጉልበታቸውን ማባከን እንደሌለባቸው አቋም የያዙ አካላትም አሉ::
ሜኒሻ፣ኦኬሬ እና አጋሪማን በአገሪቱ ባህል መሰረት ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት አድርገዋል:: በጋና ባህል መሰረት ህፃናት ቤተሰቦቻቸውን በሥራ መርዳት ግዴታ አለባቸው:: በተለይ ደግሞ በድህነት ውስጥ የሚገኝ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ህፃናት ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ ላይ መሰማራት ግዴታቸው ይሆናል:: ድህነት ባመጣው ችግር ህፃናት ለሥራ እንዲሸጡ አድርጓቸዋል:: በገንዘብ የተሸጠ አንድ ህፃን ገዥውንም ቤተሰቡንም በገንዘብ መደገፍ ይጠበቅበታል:: ይህም ሁኔታ ሽያጭና ባርነትን ያሳያል::
ይህን ሁኔታ በቀላሉ መግለፅ አይቻልም፡ አብዛኛዎቹ ልጆቻቸው የተሸጡባቸው ቤተሰቦች ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩና በግዴታ እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ የገቡ ናቸው:: ከፍተኛ ገንዘብ በመቀበል ልጆቻቸውን ወደ ሩቅ ቦታ የሚልኩ ቤተሰቦች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል:: በአብዛኛዎቹ ህፃናት በዓሳ አጥማጅነት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ:: ሌላኛው በጋና ድህነት እየጨመረ እንዲመጣ ያደረጉ ብዙ ነገሮች አሉ፤ በተለይ በሀይቅ ዳርቻ የሚኖሩ ሰዎች ላይ:: የመጀመሪያው ያልተጠና የሊብራል ገበያ ከፍተኛ የሆነ የዓሳ ገበያው ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ ነው:: ለዚህም በዓሳ አጥማጆች ላይ ከፍተኛ የሆነ ሥራ ጫና እንዲመጣ አድርጓል:: የአየር ፀባይ መለወጥ እና በየአካባቢው የሚገኙ ውሃዎች መበከል የዓሳ ምርቱ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል:: በዚህ ምክንያት አብዛኛው ቤተሰብ ልጆቹን ወደ ሌሎች ቦታዎች በመላክ የጉልበት ሥራ ሰርተው ገንዘብ እንዲልኩ እያደረገ ይገኛል::
በጋና ከሚገኙ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች መካከል ይህን ጉዳይ በቮልታ ሀይቅ አካባቢ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መድረሱን ባወጣው ሪፖርት ገልጿል:: እንደዚህ አይነት ድርጅቶች ገንዘብ በማሰባሰብ ህፃናትን ነፃ ለማውጣት እናቶችን በማሰባሰብ፣ ስልጠና በመስጠትና ብድር በማቅረብ ለገንዘብ ብለው ልጆቻቸውን እንዳይሸጡ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው:: አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በምዕራብ አፍሪካ ነዋሪዎች ላይ የተጋነነ መረጃዎች በማቅረብ ህዝቡን የሚቀሰቅሱበትን መንገድ ሲከተሉ ይስተዋላል:: ነገር ግን ድርጅቶቹ የሚያወሩትን ያክል ችግሮች አልተባባሱም ይላሉ::
አሁን ያለው ጉዳይ የአንድ ግለሰብ ወይም ባህል አይደለም:: ነገር ግን በጋና ያለው ድህነት ምን ያክል ደረጃ እንደደረሰ ማሳያ ነው:: ባለስልጣናትና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የአገሪቱን ባህል በማጣቀስ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ህፃናት ቤተሰባቸውን ለመርዳት መስራት አለባቸው ብለው ይከራከራሉ:: ነገር ግን በራሳቸው ልጆች ላይ እንዳይደርስ ይከላከላሉ::
ባህል የተቀመጠ ቀመር አይደለም:: ጋናውያን የተሳሳቱ ባህሎችን የማሻሻል መብት አላቸው:: ጋናውያን በህፃናት ሽያጭና ጉልበት ብዝበዛ ጉዳይ ብሄራዊ ውይይት ማድረግ አለባቸው:: በውይይቱ የህፃናት መብቶች የሚጠበቁበት ሁኔታ ላይ መንግሥት እና የሚመለከታቸው ከማህበረሰቡ የተውጣጡ ሰዎች ለውጥ አምጭ ሥራ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል:: ህፃናት በምንም ዓይነት መንገድ እራሳቸውን ለማኖር ሥራ ላይ መሰማራት የለባቸውም:: ሥራ ላይ የሚሰማሩ ከሆነ ግን አገሪቱ ወድቃለች ማለት ነው::
ሜናሽ፣ ኦኬሬ እና አጋሪማን እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ትክክል ነው:: በተለይ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሀን እየዘገቡበት ያለው መንገድ ትክክል አለመሆኑን መቃወማቸው አግባብነት አለው:: ጉዳትን ለመቀነስ ተብሎ የአገሪቱ ባህልና እሴቶች እንዳይናዱ ጥንቃቄ መደረግ አለበት:: በቮልታ ሀይቅ አካባቢ ያለው ጉዳት፣ ጉልበት ብዝበዛ እና ድህነት አጠቃላይ አገሪቷን የሚገልፅ አይደለም::
መርድ ክፍሉ