የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) የመጨረሻ ዙር ማጣርያ ጨዋታ ከሱዳን ጋር ለሚያደርገው ፍልሚያ የሀገር ቤት ዝግጅቱን አጠናቆ ትናንት ምሽት ወደ ሊቢያ አቅንቷል።የሁለቱ ሀገራት ወሳኝ የቻን ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታም ታኅሣሥ 13 እና 16 ሊቢያ ቤንጋዚ ላይ ይካሄዳል፡፡
የዋልያዎቹ ጊዜያዊ ዋና አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ የደርሶ መልስ ጨዋታውንና የቡድኑን ዝግጅት በተመለከተ ከትናንት በስቲያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የተጫዋቾችን ጉዳት በተመለከተ አሠልጣኙ ባደረጉት ገለፃ፣ “ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ቸርነት ጉግሳ፣ መሐመድኑር ናስር፣ ቢንያም አይተን፣ ሬድዋን ናስር እና ፍሬዘር ካሳ በጉዳት ምክንያት አብረውን አይገኙም›› ብለዋል፡፡ እነዚህን ተጫዋቾች ይተካሉ ብለው ያሰቧቸውን ተጫዋቾች ጥሪ አድርገውም ሜዳ ላይ ጥሩ ነገር መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ተደጋግሞ የሚነሳውን የዋልያዎቹ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች ችግር በተመለከተ አሠልጣኙ በሰጡት ማብራሪያም፣ ‹‹ዘጠኝ ቁጥር ለመጠቀም እየሞከርን ነው ፤ ካሉትም የተሻለ ነገር ይሠራል ብለን የመረጥነውም ስንታየሁ መንግሥቱን ነው።›› በማለት ገልፀዋል፡፡
የአቋም መለኪያ ጨዋታን በተመለከተ “ከወዳጅነት ጨዋታ ጋር በተገናኘ በተወሰነ መልኩ ጊዜውም አጭር ነበር ፤ ራሳችንን ከማየት አንፃር፣ አሁን እየሠራን ያለው ‘ታክቲክም’ ከማየት አንፃር ከሃዋሳ ተስፋ ቡድን ጋር ጨዋታ አድርገናል።” ሲሉ አሠልጣኙ አጭር ገለፃ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሱዳን አቻው ጋር የሚያደርገውን የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ጨዋታውን በዝግ ለማድረግ መታሰቡን የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን በዚሁ መግለጫ ላይ ተገኝተው ተናግረዋል። ሁለቱም የደርሶ መልስ ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ በሊቢያ ቤንጋዚ የሚካሄድ ሲሆን፣ በመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ባለሜዳ እንደመሆና በዝግ ስቴድየም ለማድረግ መታቀዱን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
አቶ ባህሩ በንግግራቸው “ውድድሩ ሊቢያ ቤንጋዚ ላይ ነው የሚካሄደው፣ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በርካታ ሱዳናውያን በሊቢያ ኑራቸውን እያደረጉ እንደመገኘታቸው የሱዳን ቡድኖች በተለያዩ የካፍ ውድድሮች ላይ በሥፍራው በተጫወቱበት ወቅት ሱዳናውያን ተመልካቾች ሜዳውን ሞልተው የሚታዩበት እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እየወሰድን አቋማችን ጨዋታውን በዝግ ማድረግ ነው። አካባቢውን ምቹ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ከካፍ ጋርም ንግግሮች እያደረግን ነው። እኛ ባለሜዳ የምንሆንበት የመጀመሪያ ጨዋታን ግን በዝግ ማድረጋችን የማይቀር ነው። በዝግ ሲባል ግን አንድ መታወስ ያለበት ነጥብ የተወሰነ ያህል የተጋጣሚ ቡድን አባላትን ወደ መቶ ሊቆጠሩ የሚችሉ ነፃ ትኬቶች ሊሰጡ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል። በዚህ ደረጃ እኛም ውድድሩን እንፈልገዋለን። ማለፍም እንፈልጋለን፣ ለማለፍ ደግሞ ምቹ የሆነ አካባቢ ለቡድናችን መፍጠር አለብን። ስለዚህ ጨዋታው በዝግ የመሆን ዕድሉ የሰፋ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለፅ እንፈልጋለን። በቀጣይ እነርሱ ባለሜዳ በሚሆኑበት ጨዋታ ግን ተመልካች ሊኖር ይችላል።” ሲሉ ተናግረዋል።
በሀገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት የቻን ዋንጫ ዘንድሮ ለ8ኛ ጊዜ ሶስት በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት (ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ) ጥምረት ይስተናገዳል፡፡ ኢትዮጵያም በመድረኩ ለአራተኛ ጊዜ ለመሳተፍ ነው በማጣሪያው ሱዳንን የምትገጥመው፡፡
ኢትዮጵያ በመጀመርያው የመድረኩ ተሳትፎ የምድብ ማጣርያ ሶስት ጨዋታዎችን አድርጋ ያለምንም ነጥብ በአራት የጎል እዳዎች ነበር የተሰናበተችው፡፡ በ2016 ርዋንዳ አስተናጋጅ በነበረችበት ውድድር ዴሞክራቲክ ኮንጎ ለሁለተኛ ጊዜ ቻምፒዮን ስትሆን፣ የኢትዮጵያ ተሳትፎ በአንድ ነጥብ ከምድቧ በመሰናበት ነበር ያጠናቀቀችው። ከሁለት ዓመት በፊት በአልጄሪያ በተስተናገደው የቻን ውድድር ሶስተኛ ተሳትፎዋን ያደረገችው ኢትዮጵያ በተመሳሳይ አንድ ነጥብ ይዛ ከምድቡ ተሰናብታለች፡፡
ከምድብ ማጣሪያ ያልዘለለው የኢትዮጵያ የመድረኩ ተሳትፎ፣ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ለመሳተፍ በሚደረገው የማጣሪያ ጨዋታ ከዞኑ ጠንካራ ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችውና ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን ባረጋገጠችው ሱዳን ይፈተናል፡፡
የቻን ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር በሁሉም የአፍሪካ ዞኖች እአአ ከታኅሳስ 20-22 እና ከታኅሳስ 27-29/2024 ይከናወናሉ። ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምስራቅ፣ ምዕራብ 1 እና ምዕራብ 2 ዞኖች እንዲሁም ከማዕከላዊ በአጠቃላይ ስድስት የአፍሪካ ዞኖች የማጣሪያ ውድድራቸውን አሸንፈው በውድድሩ ለመሳተፍ ሀገራት ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም