ሀገራዊ ትልሞችን ለማሳካት እምቅ ጸጋዎችን አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- ሀገራዊ ትልሞችን ለማሳካት በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በአገልግሎት እና በሌሎች ዘርፍ ያሉ እምቅ ጸጋዎችን አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

ወይዘሮ ሙፈሪሃት ባለፉት አምስት ወራት በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት እንዲሁም በኢንዱስትሪ ሰላማዊ ግንኙነት ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ትናንት ውይይት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ትልሞችን ለማሳካት በተለያዩ ዘርፎች ያሉ እምቅ ጸጋዎችን አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል።

የወጣቶችን የፈጠራ አቅም ለማበልጸግ የሚያስችሉ በርካታ ፕሮግራሞች ተነድፈው ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰው፤ የሥልጠና ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በውጭና በሀገር ውስጥ የሚሰማሩ ዜጎች ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ በተከተለ መንገድ ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ እየተሠማሩ እንደሚገኙ ገልጸው፤ በቀጣይም ለወጣቱ ክህሎት መር ሥልጠና የመስጠትና የሚታዩ ክፍተቶችን ወደ እድል የመቀየር ሥራ ይሠራል ብለዋል።

በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በስፋት እየተሠራ ነው ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪሃት፤ በዚህም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከውጭ የሚገቡ ማሽኖችን በሀገር ውስጥ መተካት ተጀምሯል ብለዋል።

በቀጣይ በክልሎች ያሉ ሀብቶችን በመጠቀም የዜጎችን ተጠቃሚነትና የሀገርን ልማት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ገልጸዋል።

ባለፉት ጊዜያት በተሠሩ ሥራዎች ስድስት የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት የአይ ኤሶ ስታንዳርድ በማሟላት እውቅና ማግኘታቸውን አውስተው፤ የተቀሩት ተቋማት ዓለም አቀፍ ደረጃን እንዲይዙ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል።

ይህም የተጀመረውን የተቋም ግንባታ ሥራ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉ እንዲሆኑ እየተሠራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ባለፉት አምስት ወራት በክልሎች በተከናወኑ ተግባራት አውጥቶ መጠቀም የሚገባው እምቅ ሀብት እንዳለ መገንዘብ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይህንንም ለማሳካት ለወጣቱ ክህሎት መር ሥልጠና የመስጠትና የሚታዩ ክፍተቶችን ወደ እድል የመቀየር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You