የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት የዓባይ ግድብ ከ13 ዓመታት የግንባታ ሂደት በኋላ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል። ግድቡ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ጥያቄ ሲመለስ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ በረከቶችንም ይዞ ይመጣል። በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ከጨለማ ሕይወት እንደሚያወጣው ሁሉ በጨለማ ለሚጓዘው የኢትዮጵያ ስፖርትም የራሱን በረከቶች ይዞ ከተፍ እንደሚል ማሰቡና በዚያው ልክ መዘጋጀት ተገቢ ይሆናል።
ግድቡ ከኃይል ማመንጨት ባሻገር የሚኖረው ትልቅ ጥቅም ከቱሪዝም ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ቀደም ሲል ተነግሯል። ለዚህም መንግስት ምቹ የቱሪዝም መስህቦችን በአካባቢው ለመፍጠር የተለያዩ ንድፎችን እንደሚያዘጋጅ ይፋ አድርጎ ነበር። የግሉ ባለሀብትም አካባቢውን በማልማት ሊፈጥር የሚችለው ልዩ የቱሪዝም መዳረሻ በጉጉት የሚጠበቅ ይሆናል።
የቱሪዝም ነገር ሲነሳ ኢትዮጵያ ካልተጠ ቀመችባቸው እምቅ ሀብቶች አንዱ የስፖርት ቱሪዝም ነው። በዚህ ረገድ የዓባይ ግድብ ለስፖርት ቱሪዝም መስፋፋት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ከሌሎች አገራት ተሞክሮ በመነሳት መመልከት ይቻላል። የዓባይን ግድብ ከስፖርት ጋር ማገናኘት አሁን ላይ የማይታሰብ ነገር ሊመስል ይችላል። ግን ቅንጦትና ዓለም ላይ የሌለ አዲስ ነገር አይደለም።
እንደ ዓባይ አይነት ግድብ የገነቡ በርካታ የዓለም አገራት ግድቦችን ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ወይም ለግብርናና ለመስኖ ሥራዎች ብቻ አይደለም የሚጠቀሙባቸው። ከስፖርት በተለይም ከውሃ ስፖርቶች ጋር በተያያዘ እንደ ዓባይ አይነት ግድቦች ጥቅም ላይ ሲውሉ ማየት የተለመደ ነው። ግድቦች ለውሃ ስፖርቶች ምቹ ናቸው። ዋናው ነገር አጠቃቀሙን ማወቅ ነው።
መንግስት የዓባይ ግድብን ከቱሪዝም ጋር ለማያያዝ በሚያደርገው ጥረት ግድቡንና ግድቡ ያለበትን አካባቢ ለስፖርት ቱሪዝም ከማዋል አኳያ የታሰቡ ፕሮጀክቶች ስለመኖራቸው በግልፅ የተቀመጠ ነገር የለም። ያም ሆኖ ግድቡ ከስፖርት ቱሪዝም ጋር በተያያዘ ይዞት የሚመጣው ትልቅ እድል በቀላሉ የሚታይ አይደለምና ከወዲሁ ማሰቡ ብልህነት ነው፡፡
ከስፖርት ባሻገር
ስፖርት ሁልጊዜም ለሰዎች እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ አካል ነው። የተለያዩ ሕብረተሰቦችን በአንድ ላይ በማሰባሰብና አንድነትን በማጠናከር ረገድ ስፖርት የማይተካ ሚና አለው። በዘመናችን ግን ስፖርት ለአንድ አገርና ማኅበረሰብ ከዚህም የተሻገረ ጥቅም እንዳለው እየታየ ይገኛል።
ስፖርት ሁለት አካላትን (ቡድኖችን) ከማፎካከር ባለፈ ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳው እየገዘፈ መጥቷል። ይህ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖውም በቀጥታ በዘርፉ ተሳታፊ የሆኑ ስፖርተኞችን ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ያሉ ግለሰቦችን፣ ማኅበረሰብንና አገርንም ጭምር በተለያየ መንገድ የመጥቀም ትልቅ አቅም ማዳበሩ ነው።
ጥቅሙን ቀድመው የተረዱና ተግተው የሰሩበት እንደ እንግሊዝ አይነት አገራት ሌላውን ሳይጨምር በተወዳጁ እግር ኳስ የፕሪሚየር ሊግ ውድድራቸው ብቻ ከጠቅላላ ሀገራዊ ገቢያቸው አንድ አራተኛውን የመሸፈን አቅም እንዲኖረው አድርገዋል። ይህ እግር ኳስ ባደገባቸው ሀገራት ያለ ሀቅ ቢሆንም እግር ኳስ ያላደገባቸው አገራት ፊታቸውን ወደሌሎች ስፖርቶች አዙረው ከቱሪዝም ጋር በማቆራኘት የማይነጥፍ ሀብት ፈጥረው ይገኛሉ።
ስፖርትና ቱሪዝም
ኢትዮጵያ ካልተጠቀመችባቸው እምቅ አቅሞች አንዱ ግን የስፖርት ቱሪዝም ነው። የስፖርት ቱሪዝም በዓለም ኢኮኖሚ እያሳደረ የሚገኘው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ገቢ ከማስገኘት እና ቱሪስቶችን ከመሳብ እስከ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር እና የሕብረተሰቡን ጤና ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የስፖርት ቱሪዝም በዓለም ኢኮኖሚ እድገት ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
በ2022 የዓለም የስፖርት ቱሪዝም 587.87 ቢሊየን ዶላር እንዳመነጨ የሚጠቁሙ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ይህ አሀዝ ከ2023-2030 በ17.5 በመቶ እየተመነደገ እንደሚሄድ ይተነብያሉ። በ2022 የውሃ ስፖርቶችን ጨምሮ በውሃ አካላት ላይ የሚደረጉ የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች እንደ ዓለም 156.9 ቢሊየን ዶላር ኢኮኖሚ ማመንጨት እንደቻሉ የሚገልፁ ጥናቶች ደግሞ በመጪዎቹ አስር ዓመታት 2032 ድረስ የ845.8 ቢሊየን ዶላር ኢኮኖሚ መፍጠር እንደሚችሉ ያስቀምጣሉ።
ከዚህ ውስጥ የውሃ ስፖርቶች ብቻ ከ2022- 2027 ድረስ በየዓመቱ 4.8 በመቶ እያደጉ 7.4 ቢሊየን ዶላር የማመንጨት አቅም እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል። ይህም የስፖርት ቱሪዝም የሀገራትን ብሎም የዓለምን ኢኮኖሚ ያቀጣጥላል ተብሎ ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል።
የውሃ ስፖርቶችና የስፖርት ቱሪዝም
የተለያዩ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፣ ከ2021 አጋማሽ ጀምሮ በመላው ዓለም 41 ሚሊየን ሰዎች ከውሃ ስፖርቶች ቱሪዝም ጋር በተያያዘ ወደተለያዩ አገራት አቅንተዋል። ይህ በየዓመቱ 182 በመቶ እያደገ ሄዶ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በውሃ ስፖርት ቱሪዝም ከአንድ አገር ወደ ሌላው የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር 117 ሚሊየን እንደሚደርስ ይጠበቃል። ይህም በመላው ዓለም የውሃ ስፖርት ቱሪዝም ምን ያህል ተፈላጊ እየሆነ እንደመጣ ማሳያ ተደርጎ ይቀርባል፡፡
ከዚሁ ከውሃ ስፖርቶች ቱሪዝም ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ሰፊ የሥራ እድሎች እንዳሉ ሆኖ ስፖርቱ የሚፈልጋቸው ቁሳቁሶችን ማምረትና መሸጥ በከፍተኛ ሁኔታ መጧጧፉ ሌላው ቁልፍ የኢኮኖሚ መሰረት ነው። በውሃ ስፖርቶች ከትንንሽ እስከ ትልልቅ ጀልባዎች፣ ከስፖርተኞች አልባሳት እስከ ደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶች በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው፡፡
በውሃ ስፖርቶች ቱሪዝም ላይ የሚሰሩ አገራት እነዚህን ቁሳቁሶች የሚያመርቱ የተለያዩ ፋብሪካዎችን ገንብተዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ የሚያንቀሳቅሱት መዋዕለ ንዋይ ብቻ ሳይሆን የሚፈጥሩት ሰፊ የሥራ እድልም ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ እነዚህን የፋብሪካ ውጤቶች የውሃ ስፖርቶች በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በጅምላም ይሁን በችርቻሮ ለተጠቃሚዎች የሚያቀርቡ ከትልልቅ እስከ ትንንሽ ድርጅቶችም በርካታ ናቸው፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት የውሃ ስፖርት ቱሪዝም ቢፈጠር እንኳን ስፖርቱ የሚፈልገውን ቁሳቁስ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ላይፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ያም ሆኖ ቁሳቁሶችን ከውጪ አገራት በማስመጣት የሚፈጠረው የሥራ እድልና ገበያ እንደሚኖር ማሰብ ይቻላል፡፡
የዓባይ ግድብና የስፖርት ቱሪዝም አቅም
የሰው ልጅ በቆዳው ላይ ያለውን የደም ፍሰትን እና የላብ መጠንን በመጨመር የሙቀት መጠንን የመላመድ ልዩ ችሎታ አለው። የሰው ልጅ አካላት በቀዝቃዛ ሁኔታዎች ውስጥ የመላመድ ችሎታቸው በጣም አናሳ ነው፣ ይህም የክረምት ወቅት ቀዝቃዛ አካባቢዎች ላይ የውሃ ስፖርት ቱሪዝምን ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎችን ቁጥር በእጅጉ እንዲቀንሱ ያደርጋል።
በዚህ ምክንያት ቀዝቃዛ አገራት ወይም አካባቢዎች ተመራጭ አይደሉም። ስለዚህ ስፖርቱን ማዘውተርና በስፖርቱ መዝናናት ምርጫቸው የሆኑ ሰዎች ሙቀት ያለባቸውን አገራት ለመምረጥ ይገደዳሉ። የዓባይ ግድብ የተገነባበት ሥፍራ በዚህ ረገድ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያለበት እንደመሆኑ ከተሰራበት ተመራጭ የሚያደርገውን የተፈጥሮ ፀጋ ታድሏል።
የዚህ ስፖርት ወዳጅና አዘውታሪ የሆኑት በብዛት ያደጉት አገራት ዜጎች ናቸው፡፡ እነዚህ የውጪ አገር ዜጎች ወደ ተለያዩ አገራት ጎብኚዎች ሆነው ሲሄዱ የተለያዩ ሥፍራዎችን ከመጎብኘት ባሻገር እንደ ውሃ ስፖርቶች አይነት የተለያዩ ጀብዶችን/adventure/በመፈፀም ይበልጥ እንደሚዝናኑ በብዙ አጋጣሚዎች መመልከት የተለመደ ነው።
የኢትዮጵያን ቱሪዝም ወደ ላቀ ደረጃ እንዳያድግ እንቅፋት ከሚሆኑበት ምክንያቶች አንዱ ለጎብኚዎች ምቹ የሆኑ ሥፍራዎች አለመኖራቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የጎብኚዎች ቆይታ ለአጭር ጊዜና የተገደበ ይሆናል፡፡ ይህም የውጪ ጎብኚዎች ይዘው የመጡትን የውጭ ምንዛሬ ብዙም ሳይጠቀሙበት ይዘው እንዲመለሱ እንደሚያደርጋቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ እንደ ውሃ ስፖርቶች አይነት ጎብኚዎችን ለረጅም ቀናት እንዲቆዩ የሚያደርጋቸው መዳረሻዎች ለዚህ ችግር እንደ አንድ መፍትሄ የሚሆኑበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ጎብኚዎች ለዚህ የሚሆን መሰረተ ልማትና ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚሹ ግን ግልፅ ነው።
የአዳዲስ ውሃ ስፖርቶች ውልደት
የስፖርት አይነቶች በተለያዩ አገራት የሚፈጠሩት እንደየአካባቢው መልክአ ምድር፣ እምቅ አቅምና ወዘተ ነው። ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት የታደለች ብትሆንም እንደ አገር የሚዘወተሩ የውሃ ስፖርት አይነቶች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው ለማለት እንኳን የሚያስደፍሩ አይደሉም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታወቀውና የሚዘወተረው የውሃ ስፖርት አይነት በተለያዩ ሆቴሎች በትንንሽ ገንዳዎች ውስጥ የሚከናወኑትና በኦሊምፒክ መድረኮች በኮታ የምንሳተፍባቸው ብቻ ናቸው።
ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት የሚሆነው በሌሎች አገራት የሚዘወተሩ የውሃ ስፖርቶች የሚፈልጉት ምቹ የውሃ አካል አለመኖር ሊሆን ይችላል። በበርካታ አገራት የውሃ ስፖርቶች አይነታቸው ቁጥር ስፍር የለውም። በውሃ አካላት ላይ እና ውስጥ ተከፋፍለው የሚካሄዱ የስፖርት አይነቶች ብቻ ተቆጥረው አያልቁም።
ከ250 ኪሎ ሜትር በላይ የሚንጣለለው የዓባይ ግድብ ሌላውን ትተን በውሃ አካላት ላይ የሚካሄዱ ነገር ግን በኢትዮጵያ ተሞክረው የማያውቁ በትንሹ ከሃያ የማያንሱ የውሃ ስፖርቶች እንዲፈጠሩ የማድረግ አቅም ይኖረዋል። ከተለመደው የጀልባ ውድድር አንስቶ አሳ እስከ ማጥመድ እንዲሁም ሌሎች በግልና በቡድን የሚካሄዱ የመዝናኛና የውድድር የውሃ ስፖርቶችን መፍጠር ይችላል።
በኦሊምፒክ መድረክ ውድድር የሚካሄድባቸው የውሃ ስፖርቶች (swimming, diving, water polo, rowing, sailing, canoe flatwater, canoe slalom, artistic swimming, marathon swimming, and surfing) በስፋት ይታወቃሉ፡፡ የዓባይ ግድብ እነዚህ ስፖርቶች በኢትዮጵያ እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይቻለዋል፡፡ ከነዚህ ስፖርቶች የተወሰኑት ላይ እንካን ጥናት አድርጎ በሂደት እንዲለመዱና እንዲዘወተሩ ማድረግ የሚቻልበት እድል ዝግ አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር መነሻ ይኖረዋል፣ መቼም በነዚህ ስፖርቶች አሁን ላይ በኦሊምፒክና በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ወርቅ የሚያፍሱ አገራት ከስፖርቶቹ ጋር አብረው ተፈጥረው አይደለም፡፡
በሆኑ አጋጣሚዎችና ሁኔታዎች ስፖርቶቹን ተላምደው፣ አጎልብተውና ሰርተውበት ነው ለትልቅ ደረጃ የበቁት፡፡ ለእኛም አዳዲስ ስፖርቶችን ከመሞከር የሚከለክለን ነገር የለም። ካለመሞከር መሞከር ሁሌም ይሻላል። መጀመሪያ እኛ ካለን አቅምና ሁኔታዎች ተነስቶ በጥናቶች ላይ በመመርኮዝ ስፖርቶቹን ማስተዋወቅ፣ በሂደትም የማላመድና የማጎልበት ብሎም በፕሮፌሽል ደረጃ የማምጣት ጉዳይ ይመጣል።
እንደ አሜሪካ ያሉ አገራት በኦሊምፒክ በርካታ ወርቆችን ጠራርገው የሚወስዱት በውሃ ስፖርቶች ነው፡፡ ያም አልበቃ ብሏቸው ዳንሶቻቸውን ጭምር በኦሊምፒክ ስፖርት እንዲካተቱ ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ኢትዮጵያ በሌሎች በተለመዱና ለረጅም ዓመታት በሚዘወተሩ ስፖርቶች ውጤታማነት ላይ ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩም አዳዲስ ነገሮችን መሞከሩ ክፋት የለውም፡፡ በእጃችን ያሉትን ተጠቅመን ውጤታማ አልሆንም ማለት በአዳዲስ ነገሮች አይሳካልንም ማለት አይደለም፡፡ ምናልባትም አብረውን ከከረሙት ይልቅ በአዳዲሶቹ ተክነን እንገኝ ይሆናል፡፡ ይህም በአትሌቲክስ፣ ብስክሌት ወዘተ ብቻ የተወሰነውን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ተሳትፎ በሂደት ወደ ተጨማሪ ስፖርቶች ለማሳደግ በር የሚከፍት ነው።
የክልሉ ስፖርት መነቃቃት
የዓባይ ግድብ የተሰራበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከዚህ ቀደምም ይሁን አሁን በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው በኩራት ያውለበለቡ በርካታ ከዋክብት የፈለቁበት ነው። ያም ሆኖ ክልሉ አሁንም ድረስ በስፖርት መሰረተ ልማቶች እዚህ ግባ የሚባል ነገር የለውም።
ይህም ክልሉ ያለውን የስፖርት እምቅ አቅም በተገቢውና በሚፈለገው መንገድ አውጥቶ እንዳይጠቀም አንዱ እንቅፋት እንደሆነ በድፍረት መናገር ይቻላል። ያም ሆኖ አሁንም ድረስ ከዋክብት ስፖርተኞች በራሳቸው ልፋትና ጥረት ከዚያ ክልል ተነስተው በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስም እየገነቡ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ስትመለስ የዋልያዎቹ ወሳኝ የአጥቂ መስመር ተጫዋች የነበረው ሳላሀዲን ሰዒድ መነሻው ከዚሁ ክልል አዋራማ ሜዳዎች ነበር።
ሳላሀዲን ወርቅ ከሚፈልቅበት ክልል ተነስቶ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ተፅእኖ በመፍጠር ስሙን በወርቅ ቀለም የፃፈ ኮከብ ነው። ሳላሀዲን በዚህ ደረጃ የሚጠቀስ በክልሉ ብሎም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ይቀመጥ እንጂ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዛሬም ድረስ በርካታ ሳላዲኖች መኖራቸውን ወደ ሥፍራው ተጉዞ መንገድ ዳር በአዋራማ ሜዳዎች ኳስ ሲያንከባልሉ የሚውሉ ታዳጊዎችን መመልከት በቂ ነው።
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በእግር ኳስ ብቻ አይደለም የታደለው፣ በአትሌቲክሱም ከኦሊምፒክ እስከ ዓለም ቻምፒዮና ብሎም እስከ አፍሪካ ጨዋታዎች በወርቅ የደመቁ ከዋክብት የፈሩበት ሥፍራ ነው። ኢትዮጵያ በ2016 የሪዮ ኦሊምፒክ አንድ የወርቅ ሜዳሊያ ብቻ ስታስመዘግብ በባዶ እጅ ከመመለስ የታደገችን ወርቃማዋ አትሌት አልማዝ አያና የዚሁ ክልል ፍሬ ነች።
አልማዝ ሪዮ ኦሊምፒክ ላይ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ስታጠልቅ ለ23 ዓመታት ያልተደፈረውን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን በማንከት ጭምር ነው። በዚያው ኦሊምፒክ በ5ሺ ሜትር ሌላ ወርቅ ለማጥለቅ ተቃርባም ለጥቂት ነበር የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነችው። አልማዝ ከኦሊምፒክ ባሻገር ከዓለም ቻምፒዮና እስከ የግል የማራቶን ውድድሮች አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ኩራት የሆነች አትሌት ነች።
የአልማዝን ፋና ተከትላ በቅርቡ በአትሌቲክሱ ዓለም ገናና ስምና ዝና እየገነባች የምትገኘው ኮከብ አትሌት ፅጌ ዱጉማም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማሕፀን የወጣች ናት። ይህች ጥቁር እንቁ ዘንድሮ ግላስጎው በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የ800 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ክልሉ ከረጅም እስከ አጭር ርቀት ሩጫ ትልቅ አቅም እንዳለው በተግባር አረጋግጣለች። ከዚህ ታሪካዊ ድሏ ከሳምንታት በኋላ ወደ ጋና አክራ ፊቷን በመመለስ በአፍሪካ ጨዋታዎች በርቀቱ ያስመዘገበችው የወርቅ ሜዳሊያም የቅርብ ጊዜ ትውስታና ሌላ ታሪክ ነው።
ከእግር ኳስ እስከ አትሌቲክስ የጀገኑ እነዚህ አትሌቶች ከቤኒሻንጉል ክልል የተገኙት በራሳቸው ልፋትና ጥረት እንጂ በተመቻቸ መንገድ ተጉዘው አይደለም። ክልሉ አሁንም ድረስ ያለውን የስፖርት አቅም አውጥቶ እንዲጠቀም የሚያግዙ መሰረተ ልማቶች የሉትም። በግልም ይሁን በመንግስት ስር የሚገኙ የተለያዩ የስፖርት ክለቦችንም ፈልጎ ማግኘት አዳጋች ነው። በአሶሳ ከተማ የተጀመረው ትልቅ ስቴድየም እንኳን ለአስራ አምስት ዓመታት ግንባታው የት እንደደረሰ ዛሬም ድረስ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም።
ስፖርት የሚያድገውና የሚስፋፋው በከተማ ነው። ከተሞች ባደጉ ቁጥር የስፖርት መሰረተ ልማቶች ብሎም የስፖርት ክለቦች እያደጉ መሄዳቸው የማይታበይ ሀቅ ነው። የዓባይ ግድብ መጠናቀቅ እንደ አገር ይዞ የሚመጣው ፋይዳ እንዳለ ሁሉ ግድቡ የሚገኝበትን ክልል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ማሳደጉ እንደማይቀር ከወዲሁ መገመት አያዳግትም። ክልሉ አደገ፣ ከተሞች ተስፋፉ ማለት ደግሞ ስፖርቱም የእድገቱ ተቋዳሽ የሚሆንበት እድል ጠባብ አይደለም። ይህም በተመቻቹና ዘመናዊ በሆኑ መንገዶች ብዙ ሳላሀዲን ሰኢዶችን፣ በርካታ አልማዝ አያናዎችን ማፍራት የማይቻልበት ምክንያት እንደማይኖር አመላካች ነው።
ልዑል ከካምቦሎጆ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም