መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባሮችን እያከናወነ ይገኛል። ከእነዚህ ተግባሮች መካከል ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ እየተከናወነ ያለው ስራ ይጠቀሳል፡፡ በዚህም ለመስኖ ልማት ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
ይህን ተከትሎም በሀገሪቱ በብዛት ከሚታወቁት የመኽርና የበልግ ምርት ወቅቶች ባሻገር የበጋ መስኖ ግብርናን በማስፋፋትና ለአርሶ አደሩ አዲስ የሥራ ባሕል በማስተዋወቅ በምግብ እህል ራስን ለመቻል ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ እስከ አሁንም በተከናወነው ተግባርም ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ በማስቀረት የስንዴ ፍላጎቷን መሸፈን ችላለች፡፡ ከውጭ ከማስገባት ወጥታ ወደ መላክ የተሸጋገረችበትን አስደማሚና ተስፋ ሰጪ ውጤት ላይ ደርሳለች፡፡
መንግስት ለመስኖ ልማት በሰጠው ትኩረት የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን በማቋቋም እየሰራ ይገኛል፡፡ ሚኒስቴሩ የሀገሪቱን የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ ለመስኖ ልማት ለማዋል በመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ይሰራል፡፡
የመስኖ መሰረተ-ልማትን ለማስፋፋት በተለይም ከለውጡ በፊት ከፍተኛ በጀት የወጣባቸው ፕሮጀክቶች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተጀምረዋል፤ ይሁንና አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች ከአስር እስከ አስራ አምስት ዓመት የሚሆን እድሜ አስቆጥረውም ዛሬም ድረስ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ መግባት አልቻሉም፤ ይህም በሕዝብ ዘንድ ቅሬታ እያስነሳ ቆይቷል፡፡
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ የህዝብ ቅሬታ ሲያስነሱ የነበሩ ግንባታቸው ከተጀመረ በርካታ አመታትን ያስቆጠሩ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የአሠራር ማሻሻያዎችን ማድረጉን በቅርቡ አሳውቋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ10ኛ መደበኛ ስብሰባውን በቅርቡ ባካሄደበት ወቅት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡ በወቅቱም የምክር ቤቱ አባላት ከመስኖ ፕሮጀክቶች አንጻር የሚታዩ ችግሮች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎንና አስተያየቶችን ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች አቅርበዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል፤ ምርትና ምርታማነትን በማሳደጉ ሂደት በመስኖ ልማቱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ምን እየተሠራ ነው? አብዛኛዎቹ የመስኖ ፕሮጀክቶች ብዙ ጊዜ ፈጅተዋል፤ ይህንን ችግር ለመፍታት ምን ተስፋ ሰጪ ነገሮች ላይ ተደርሷል? የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ከለውጡ በፊት በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በደቡብ ወሎ ዞን ፎገራ ወረዳ የሚሰራው የርብ የመሶኖ ግድብ አንዱ ነው፤ ግድቡ ከተጀመረ አስራ አምስት ዓመታትን ቢያስቆጥርም ፕሮጀክቱ ካለመጠናቀቁም በላይ አፈጻጸሙ በጣም ዝቅተኛ ነው፤ በምግብ ራስን በመቻሉ ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የተባለው ይህ የመስኖ ግድብ አሁን የካናል ክለሳ ተደርጎለታል፤ ይህ ደግሞ የተፋሰሱን አቅጣጫ በመቀየሩ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብ ለሚያቀርበው ቅሬታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምን ምላሽ አለው ? የሚል ጥያቄም ቀርቧል፡፡
ለኦሞ ኩራዝ መስኖ ፕሮጀክት ማጠናቀቂያ እየተባለ በምክር ቤቱ በየጊዜው በጀት ቢቀርብም፤ አሁንም በተባለው ልክ ስራው እየሄደ አይደለምና መቼ ነው ፕሮጀክቱ አልቆ ሪቫን የሚቆረጠው? በትላልቅ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች ላይ የአፈጻጸም ችግሮች እንዳሉ በተደጋጋሚ በምክር ቤቱ ሲነሳ ኖሯል፤ አሁንስ የታየ ለውጥ አለን? ምክር ቤቱ በጀት ያጸደቀላቸውን ፕሮጀክቶች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሥራቸው እንዳይጀመር የማድረግ ስልጣን አለው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሀብት የፈሰሰባቸውና 120 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች የቅድመ አዋጭነት ጥናት ሳይካሄድባቸውና ዲዛይናቸው ሳያልቅ ሥራቸው የተጀመረ በመሆኑ በወቅቱ ተጠናቀው አገልግሎት መሰጠት ሳይችሉ ቀርተዋል፤ ሥራቸውን ከ50 በመቶ በላይ ያልገፉት አንዳንዶቹም የዲዛይን ክለሳ እየተደረገላቸው የተጀመረው ሥራ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡
በአጠቃላይ በመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች ላይ የሚታየውን ችግር ከስር መሰረቱ ለመፍታት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስቀድሞ ችግሮችን የመለየትና ለችግሮቹ የሚሆን መፍትሔ የማስቀመጥ ሥራ ሲሠራ እንደቆየም ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በዚሁ መሰረት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ለማመላከት ሞክሯል፡፡
ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ፕሮጀክቶቹ ውሳኔ የሚያገኙበትና ወደ ግንባታ የሚገቡበት መንገድ ግልጽ የሆነ ፍኖተ-ካርታ የሌለው ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፤ ፕሮጀክቶቹ መነሻቸው ምንድን ነው? ከተጀመሩስ በኋላ ምን አይነት የአሠራር መንገድን የመረጡ ናቸው? ውሳኔ ከተሰጣቸው በኋላ ወደ ፕሮጀክት የሚገቡበት ሥርዓት ምን ይመስላል? ለሚሉት ግልጽ የሆነ ፍኖተ-ካርታ ሳይቀመጥ፤ አንዳንዴ ከክልል፣ አንዳንዴ ከምክር ቤት አንዳንዴም ከግል ፍላጎት በመነሳት ፕሮጀክቶች ሲሠሩ እንደነበር አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት ግልጽ የሆነ የአሠራር ሥርዓት ( ፍኖተ-ካርታ) ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ከቀደመው ችግር መረዳት እንደተቻለም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
በፕሮጀክቶች ዲዛይን እና የግንባታ ሂደቶች ላይ የነበሩ ችግሮችም ለፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያት እንደነበሩ መታወቁን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በፊት በተቋማት ወይም በኤክስፐርት ፍላጎት የዲዛይን ሥራ እየተሠራ በአሰራር ወጥነት እና በጥራት ደረጃው ላይ ችግር ተፈጠሯል፤ በዚህ የተነሳ በግንባታም ሂደት የሚፈጠሩ ጉድለቶችን ማረም አዳጋች እንደሆነ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታትም የፕሮጀክት ዲዛይንና ጥራትን ለማስጠበቅ የሚረዱ 30 የሚሆኑ ደረጃዎችን/ስታንዳርዶችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ማዘጋጀት እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡ የጨረታ ግዢው ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲካሄድ የሚያስችሉ ስታንዳርዶች ስለመቀረጻቸውም አስረድተዋል፡፡ ስታንዳርድ ዝግጅቱ በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ አልቆ በቀጣይ ዓመት ሥራ ላይ የሚውል እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቶች እየፈረሱ እንዳይሰሩ መከተል ያለባቸው ሂደት አለ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሂደትን ካልተከተሉ ግን በተባለው ወጪ፣ ጊዜና ጥራት መሰረት ሊጠናቀቁ አይችሉም ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል የአዋጭነት ሥራ ሳይሠራ፤ የዲዛይን ሥራ ይቀድም ነበር፤ የዲዛይን ሥራ ሳያልቅም ግንባታዎች ይጀመሩ ነበር፤ እነዚህ ሂደቶች አስቀድመው በቅደም ተከተል ሳይከናወኑ ከቀሩ የፕሮጀክቶች ሥራ መቋረጡ ወይም ዲዛይናቸው መቀየሩ እንደማይቀር አስረድተዋል፡፡
የፕሮጀክቶች ዲዛይን ለምን ተቀየረ? ወይም ለምን ዘገዩ? በሚል የምክር አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች ከላይ የጠቀሷቸውን ነጥቦች በምክንያትነት አስቀምጠዋል። በአሁኑ ሰዓትም አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች የዲዛይን ክለሳ እየተደረገላቸው ናቸው የሚባለውም በእነዚህ ምክንያቶች እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ለጊዜ መራዘም ለወጪ መጨመር፣ ለጥራት መጓደል ምክንያት የሆነው ቀደም ሲል የነበረው የዘፈቀደ ሥራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም ከዚህ በኋላ ፕሮጀክቶች የቅድመ አዋጭነትም የአዋጭነትም ጥናት ተደርጎላቸው፣ የተሟላ ዲዛይን ተሠርቶላቸው፣ አስፈላጊው በጀት ተመድቦላቸው ወደ ሥራ ይገባል እንጂ እንደከዚህ ቀደሙ በተባለላቸው ጊዜ ላይጠናቀቁ በዘፈቀደ አይጀመሩም ብለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ እንደሚበላሽና እንደማይሠራ እየታወቀ የሚጀመር ፕሮጀክት እንደማይኖርም አስረግጠው ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ወደ ግንባታ የተሸጋገሩና ወደኋላ መመለስ የማይችሉ ወይም በሥራ ላይ ያሉ የዲዛይን ክለሳ ተደርጎላቸው ግንባታቸው እንዲፋጠን ይደረጋል ብለዋል፡፡ ሂደቶችን ሳይከተሉ ከግማሽ በላይ የተከናወኑ ፕሮጀክቶች ግን ማስተካከል የሚቻለውን ብቻ በማስተካከል እንዲጠናቀቁ ይደረጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ እስከ አሁንም 11 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች የተጀመሩና ከግማሽ በላይ የሄዱ ስለሆነ ማቆም ስለማይቻል፤ በዚያው ሂደት በተፋጠነ መልኩ ለማስጨረስ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ግን በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ነው ያስረዱት፡፡
ተገቢውን ሂደት ሳያልፉ በጨረታ ግዢ ላይ የነበሩ ቢያንስ ግንባታቸው ያልተጀመረ ፕሮጀክቶች አካሄዳቸው መስተካከልና መታረም ስላለበት የአሠራር ሥርዓቱ ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ እንዲቋረጡ ስለመደረጉም ተናግረዋል፡፡
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ እንደ ሽኒሌ፣ አንገር፣ ጉደር የታችኛው፤ የመሳሰሉት ፕሮጀክቶች ከየት ተነስተው የት እንደሚደርሱ ግልጽ አመላካች ነገር ስለሌላቸውና ብዙም የግንባታ ሂደትን ስላልገፉ በፍጥነት የዲዛይን ለውጥ ተደርጎላቸው፤ ለግንባታ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተውላቸው ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ለፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያት ተብሎ የተለየው የበጀት ችግር ነው፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአሁኑ ሰዓት በስራ ላይ ያሉ 120 ቢሊየን ብር የሚገመት ዋጋ ያላቸው ፕሮጀክቶችን እየፈጸመ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ እነዚህን ፕሮጀክቶች ከኮንትራክተሮች ጋር ባለው ውል መሰረት በዚህ ዓመት ሠርቶ ለማስረከብ 40 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ነባር ፕሮጀክቶችን እንዲያጠናቅቅ የተመደበለት 8 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረው ለጊዜው ሀገሪቱ ያላትን አቅም መሰረት ባደረገ መልኩ ይከናወናል ብለዋል፡፡ ከአስር እና አስራ አምስት ዓመት በላይ ስማቸው ሲጠራ የነበረ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ቅደሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
ብዙ ሀብት ፈሶባቸው፣ ህዝብ እያለቀሰባቸው ለረዥም ዓመት የተቀመጡ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እና ለህዝቡ ተስፋ ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ አቅምንና የተመደበውን ሃብት አውቆ በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ከማዋል ይልቅ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መጀመር እንደችግር የተለየ ነው ሲሉም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፤ ‹‹የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች በተቻለ ፍጥነት ልዩ ትኩረት ሰጥተንና አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርገን፤ የተመደበልንን በጀት በትክክል ለፕሮጀክቱ ከተጠቀምን ቢያንስ በዚህ ዓመት የሚያልቁ ፕሮጀክቶችን ማሳየት እንችላለን›› ብለዋል፡፡
በተለያየ ጊዜ ጨረታ ሲወጣባቸው የነበሩና ወደ ግንባታ ያልተቀየሩ ሶስት የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ጨረታቸው እንዲቋረጥ ስለመደረጉም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ትክክለኛ ሂደትን ያልተከተሉ ስምንት የጥናትና ዲዛይን ፕሮጀክቶችም ጨረታቸው እንዲቆም መደረጉን ጠቅሰው፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች በአዲሱ አሰራር መሰረት ተቃኝተው በቀጣይ ዓመት እንደሚጀመሩም ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ በአራተኛ ደረጃ የተለየው ችግር ከአቅም ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ በተደረገው ፍተሻ ለፕሮጀክቱ የሚመጥኑ ተቋራጮች አለመኖራቸውን ማወቅ ተችሏል፡፡ የኮንትራትና የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓታቸው በጣም ዝቅተኛ የሆነ፤ በሚገባው ልክ ሞራልና ኢነርጂ ኖሯቸው ለመጨረስ የማይሠሩ፤ አልፎ አልፎም ፕሮጀክቶችን መኖሪያ ቦታቸው ያደረጉ ተቋራጮች ስለመኖራቸው ታውቋል፡፡
እንዲህ አይነት ኮንትራክተሮች መኖራቸውን ሚኒስትሩ ለፕሮጀክቶች መጓተት እንደ ምክንያት አስቀምጠዋል፡፡ ይህ ችግር በትኩረት ታይቶ መስተካከልና መታረም አለበት ሲሉም ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡
እንደ መገጭ፣ የታችኛው ጉደር እና ኦሞ ኩራዝን የመሳሰሉት ፕሮጀክቶች እንዲህ አይነት ችግር የተስተዋለባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የእነዚህ ፕሮጀክቶች ኮንትራክተሮች ውላቸውን እንዲያቋረጡ ስለመደረጉም ጠቅሰዋል፡፡ የጉደር መስኖ ልማትና የፈንታሌ መሰረተ ልማት ኮንትራክተሮች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው እያንዳንዱ ሥራቸው በየቀኑ ክትትል እየተደረገበት እንዲሠሩ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል የሚታየው የአቅም ውሱንነት ተገምግሞ የማስተካከያ ርምጃዎች እንደተወሰደም አስታውቀዋል፤ እነዚህን ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚመራ ተቋም ያለው አደረጃጀትና አሠራር ክፍተት እንዳለበት መገምገሙን ጠቅሰው፤ ተቋሙ ፕሮጀክቶችን በቦታው ተገኝቶ እንደ ባለቤት እለታዊ ክትትልና ግምገማ ማድረግ እንዲችል የአሰራር ለውጥ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
እስከ አሁን የሚሠሩት ፕሮጀክቶች ባለቤታቸው በቅርበት ሳይኖር የሚሰሩ ነበሩ ሲሉም አስታውሰው፤ ይህንን ችግር ለመፍታትም የፕሮጀክት ፕሮግራም ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም ተደርጓል ብለዋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ተጠሪነቱ ለሚኒስትሩ ሆኖ እስከ ፕሮጀክቶች ጣቢያ ድረስ ሙያተኞችን መድቦ እለታዊ ክትትል እንደሚደርግ አብራርተዋል፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በስድስተኛ ደረጃ የተለየው የግብዓት አቅርቦት ችግር ነው፤ በተለይም ሲሚንቶ እና ነዳጅ ትልልቅ ግንባታዎች ትልልቅ ማሽነሪዎችን የሚጠቀሙ እንደመሆናቸው ከፍተኛ የነዳጅ ፍጆታ ይጠይቃሉ፤ ያልተቆራረጠ የሲሚንቶ አቅርቦትም ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተናብቦ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ የሚያገኙበት አሰራር ተዘርግቷል፤ ይህን ተከትሎም ፕሮጀክቶች በተፋጠነ ሁኔታ መራመድ የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ከካሳ ክፍያ ጋር የተያዙ ሂደቶች ለፕሮጀክቶች መዘግየት እንደ ችግር የተለዩ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ከዚህ አንጻር ክልሎች የካሳ ጉዳይ ራሳቸው እንዲጨረሱ የወጣው ህግ በቀጣይ ሥራዎች ላይ ሊኖር የሚችልን ጫና እንደሚቀነስ ጠቁመዋል፡፡ የሀገሪቱ ሰላምና ጸጥታ የቆየበት ችግርም ሌላው ተግዳሮት መሆኑን አመላክተው፣ ሀገራዊ ጥቅማቸው ከፍተኛ የሆነውን የመስኖ ፕሮጀክቶች ሁሉም ዜጋ እንደ ራሱ ሃብት ተመልክቶ ሊጠብቃቸው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
በአጠቃላይ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዳይሆኑ ያረጋቸው የአዋጭነት ጥናትና የተሟላ ዲዛይን ስራ ያልተሰራላቸው መሆን፤ የተቋራጮች የአቅም ውሱንነት፣ የበጀት እጥረት፤ የግብዓት አቅርቦት ችግር፣ ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንደሆኑ አመልክተው፣ አዲሱ የአሠራር ሥርዓት ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡ ይህም ቀጣዩ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም የተሻለ ለውጥ እንደሚኖረው ዶክተር አብርሃም አስረድተዋል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም