ፓኪስታን ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል እየሠራች እንደሆነ ተገለጸ

ፓኪስታን አሜሪካንን መምታት የሚችል ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል እየሠራች መሆኑ ተገለጸ፡፡ፓኪስታን እስካሁን የረጅም ርቀት ሚሳኤል አልነበራትም፡፡ ፓኪስታን የረጅም ርቀት ሚሳኤል ለመታጠቅ እየሠራች መሆኗን ተከትሎ ከአሜሪካ ጋር ግጭት ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡

አሜሪካ ፓኪስታን የረጅም ርቀት ሚሳኤል ለመታጠቅ መፈለግን በስጋትነት ያየችው ሲሆን ከድርጊቷ እንድትታቀብ በተደጋጋሚ እንዳሳሰበች ተገልጿል፡፡ ይሁንና ኢስላማባድ የረጅም ርቀት ሚሳኤል ማልማቷን መቀጠሏን ተከትሎ ከሰሞኑ አዲስ ማዕቀብ በፓኪስታን ላይ ጥላለች፡፡

ሮይተርስ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ፓኪስታን እያለማች ያለችው የረጅም ርቀት ሚሳኤል አሜሪካንን መምታት የሚችል ነው፡፡ አሜሪካ በሩሲያ፣ ሰሜን ኮሪያ እና ቻይና የረጅም ርቀት ሚሳኤል ስጋት ውስጥ ያለች ሲሆን ፓኪስታንም ይህን ሚሳኤል ከታጠቀች በአራተኛ ሀገር ስጋት ውስጥ ልትገባ ትችላለች ተብሏል፡፡

የፓኪስታን ባለሥልጣናት በበኩላቸው የረጅም ርቀት ሚሳኤል መታጠቅ የፈለጉት ከህንድ ሊሰነዘር የሚችልን ስጋት ለመመከት እንደሆነ ተናግረዋል፡ ፡ አሜሪካ ደግሞ የፓኪታን ሚሳኤል ርቀት ከእስያ ሀገራት የዘለለ ሊሆን እንደማይገባ መናገሯን ተከትሎ አለመግባባቱ እንደተፈጠረም ተገልጿል።

አሜሪካ ባልተጠበቀ መንገድ ጦሯን ከአፍጋኒስታን ካስወጣች በኋላ ከፓኪስታን ጋር ያላት ግንኙነት እየተሸረሸረ የመጣ ሲሆን በአንጻሩ ኢስላማባድ ከሩሲያ እና ቻይና ጋር የጠበቀ ወዳጅነት በመመስረት ላይ ትገኛለች ሲል አል ዐይን ዘግቧል፡

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You