ከተፈጥሮ የምንማረው – ትዕግስት፣ ሚዛናዊነት እና ፅናት

ተፈጥሮ በድንቅ ነገሮች የተሞላች ናት። እንዴት መኖር እና ማደግ እንዳለብን የምታሳየን አስተማሪ ጭምር። የተፈጥሮን ዓለም ለማየት የተወሰነ ጊዜ ከወሰድን በሕይወታችን ውስጥ ሊረዱን የሚችሉ ጠቃሚ ትምህርቶችን መማር እንችላለን። ከተፈጥሮ የምናገኛቸው ሶስት ቁልፍ ትምህርቶች ትዕግስት፣ ሚዛናዊነት እና ፅናት ናቸው። ከዚህ እንደሚከተሉት በዝርዝር እንመለከታቸዋለን።

  1. ትዕግስት

ተፈጥሮ በጭራሽ አትቸኩልም፣ ግን ሁሉም ነገር ይከናወናል። አንድን የዛፍ ፍሬ ተመልከት፤ ሲተክል በአንድ ጀምበር ወደ ዛፍ አያድግም። ሙሉ በሙሉ ለማደግ ሳምንታት፣ ወራት ወይም ዓመታትን ይወስዳል። ዘሩ ለመብቀል ጊዜ ይፈልጋል፣ ሥሮቹ በጥልቀት ማደግ አለባቸው፣ ዛፉም ቅርንጫፎቹን በቀስታ ወደ ሰማይ መዘርጋት አለበት።

ይህ የተፈጥሮ ቁምነገር ፍሬው ይደርስ ዘንድ ጊዜ እንደሚወስድ ያስተምረናል። ትልቅ ነገር ማሳካት ከፈለግን ታጋሽ መሆን አለብን። ሕይወት የራሷ ፍጥነት አላት። መቸኮል ብዙ ጊዜ አይረዳም። ለምሳሌ ቢራቢሮ እድገቱ እንዲጨርስ ጊዜ በኮኮናት ውስጥ ቀናትን ያሳልፋል። ኮኮኑን በጣም ቀደም ብለው ለመክፈት ከሞከሩ ቢራቢሮው በሕይወት ሊተርፍ አይችልም። በመሆኑም ለሕልሞችህ መሳካት ታገስ። ሕልምህ እውን እስኪሆን ግዜውን እመነው።

እዚህ ጋር ሌላም ምሳሌ ልጨምርልህ አንድ ገበሬ ዘር ዘርቶ ሰብል ለመሰብሰብ ወራት ይጠብቃል። አርሶ አደሩ ምንም ያህል ሰብል በፍጥነት እንዲያድግ ቢፈልግ ሂደቱን ማፋጠን አይችልም። ፀሐይ በየቀኑ ትወጣና ትጠልቃለች። ነገር ግን በዝግታ እና ያለማቋረጥ ትሰራለች። በችኮላ የሚሆን ነገር የለም።

ትዕግስት ከሚያሳዩት ምርጥ ምሳሌዎች አንዱ የቀርከሃ ዛፍ ነው። ቀርከሃ በምትተክልበት ጊዜ በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ብዙ እድገት ላታይ ትችላለህ። በዚህ ጊዜ ቀርከሃው ከመሬት በታች በጠንካራ ሥሮች እያደገ ነው። ነገር ግን አንድ ጊዜ ከመሬት በላይ ማደግ ከጀመረ በጣም በፍጥነት ለውጡን ታየዋለህ።

ይህ አንድ ውጥን ስኬታማ ለመሆን ጊዜ እንደሚወስድ ያስተምረናል። በአንድ ነገር ላይ ጠንክረህ እየሰራህ ከሆነ እንደ አዲስ ክህሎት መማር ወይም ሙያ መገንባት አሊያም ለማደግ ጊዜ መስጠት ይኖርብሀል። መቸኮል አይጠቅምም። ተስፋ ቆርጦ በጣም ቀደም ብሎ ማቆም ማለት ደግሞ ውጤቱን በጭራሽና መቼም ላታየው ትችላለህ። በመሆኑም እድገትህ አዝጋሚ ቢመስልም ታጋሽ ሁን። ትላልቅ ውጤቶች ብዙ ጊዜ ይወስዳሉ!!

  1. ሚዛን

በተፈጥሮ ውስጥ ሁሉም ነገር የተገናኘ ነው። ወንዞቹ ዛፎቹን ይመግባሉ፣ ዛፎቹ ለእንስሳት ቤት ይሰጣሉ፣ እንስሳትም ብዙ እፅዋትን ያበቅላሉ። የዚህ ሚዛን አንዱ ክፍል ከጠፋ አጠቃላይ ስርዓቱ ይጎዳል። ለምሳሌ ብዙ ዛፎችን ከቆረጥን እንስሳት ቤታቸውን ያጣሉ። እና አፈሩ ውሃ ሊይዝ አይችልም። ሚዛኑ ተዛባ ሕልውናህ አደጋ ገጠመው ማለት ነው።

ይህ ሚዛን በሕይወታችን ውስጥ የመስማማትን አስፈላጊነት ያሳየናል። ሥራ ላይ ብቻ አተኩረን እረፍትን መርሳት አንችልም። ሁል ጊዜ መስጠት ወይም ሁል ግዜ መቀበል አንችልም፤ በጭራሽ ትክክል አይሆንም። በግንኙነታችን፣ በጤናችን እና በስሜታችን ውስጥ እንኳን ሚዛን ያስፈልጋል። በመሆኑም ሚዛናዊ ሕይወትን ኑር። ጠንክረህ ሥራ፣ ግን ደግሞ እረፍት አድርግ። ሌሎችን ተንከባከብ ነገር ግን ለራስህም ግዜ ስጥ።

ሚዛናዊነትን የሚያስረዳን ሌላም ምሳሌ እዚህ ጋር ማቅረብ ይቻላል። ይህ ምሳሌ በተፈጥሮ ውስጥ ሁሉም ነገር ተስማምቶና ሚዛኑን ጠብቆ መኖር እንዳለበት ያሳየናል። ለምሳሌ የምግብ ሰንሰለቱን አስበው። ሣር ይበቅላል፤ እንደ አጋዘን ያሉ እንስሳት ደግሞ እፅዋትን ወይም ሣር ይበላሉ። እንደ አንበሳ ያሉ ሥጋ በል እንስሳት ሚዳቋን ይበላሉ። አንበሳው ሲሞት ሰውነቱ ወደ አፈር ይመለሳል፤ ይህም አዲስ ሣር እንዲያድግ ይረዳል። ይህ ዑደት ሁሉንም ነገር ሚዛናዊ ያደርገዋል።

ሰዎች ይህን ሚዛን ሲያውኩ – ለምሳሌ እንስሳትን በማደን ወይም አየሩን በመበከል ተፈጥሮ ይጎዳል። ወንዞች ይደርቃሉ፣ እንስሳት ቤታቸውን ያጣሉ፣ እና ሰዎች እንኳን እንደ ጎርፍ ወይም የምግብ እጥረት ያሉ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል።

ሌላው የተፈጥሮ ሚዛን ምሳሌ የቀንና የሌሊት ዑደት ነው። ቀን ወይም ሌሊት ብቻ ቢሆን ኖሮ አስበው እስኪ። ለማረፍ ጊዜ ስለሌለ እንደክማለን እና እንጨነቅ ነበር። በተመሳሳይም ሕይወት ሥራን እና ዕረፍትን፤ ደስታን እና ሀዘንን፤ መስጠትን እና መቀበልን ሚዛናዊ እንድንሆን ያስተምረናል። ስለዚህ ሁሉንም የሕይወትህን ክፍሎች ማመጣጠን ተማር።

  1. ፅናት (የመቋቋም ችሎታ)

ፅናት (መቋቋም) ማለት ከችግሮች የማገገም ችሎታ ማለት ነው። ተፈጥሮ በጥንካሬ ምሳሌዎች የተሞላ ነው። ከአውሎ ነፋስ በኋላ ዛፎችን ተመልከት፤ ብዙዎቹ ይንበረከኩ ይሆን እንጂ አይሰበሩም። አውሎ ነፋሱ ካለፈ በኋላ እንደገና በቁመታቸው ይቆማሉ። ሌላው ምሳሌ በረሃ ነው። ምንም እንኳን እንደዚህ ባለ ደረቅ እና አስቸጋሪ ቦታ ሕይወት ለመትረፍ መንገድ ታገኛለች። ካክተስ (የበረሀ አትክልቶች) ውሃ ያከማቻሉ፣ እንስሳት በቀን ውስጥ ይደበቃሉ፤ እና ተክሎች ከመሬት በታች ውሃ ለማግኘት ጥልቅ ሥሮች ያሳድጋሉ። ሕይወት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ችግሮች፣ ኪሳራዎች እና ውድቀቶች ያጋጥሙናል። ነገር ግን እንደ አውሎ ነፋሱ ዛፍ ወይም በበረሃ ውስጥ እንዳለ ቁልቋል፣ መላመድ እና መቀጠል እንችላለን። ስለዚህ ሕይወት ሲከብድ በርትተህ ቆይ። ታጠፍ ነገር ግን አትሰበር። ተግዳሮቶች ምንም ቢሆኑም ማደግህን ቀጥል።

ይህንን በደንብ የሚያስረዳ ሌላ ምሳሌ ልጨምርልህ። መቻል (የመቋቋም ችሎታ) ማለት አስቸጋሪ በሆኑበት ጊዜም እንኳን ጠንካራ መሆን ማለት ነው። ተፈጥሮ በጥንካሬ ምሳሌዎች የተሞላ ነው። በከተማው የእግረኛ መንገድ ስንጥቆች ውስጥ ስለሚበቅል ትንሽ ተክል አስብ። የበለጸገ አፈር የለውም፤ የሚንከባከበው አትክልተኛም አያገኝም፤ ነገር ግን ይበቅላል። ሰዎች ሲረግጡት እንኳን ወደኋላ መቆሙን ይቀጥላል።

ሌላው ምሳሌ የሳልሞን ዓሶች ነው። እነዚህ ዓሳዎች ከጥልቁ የባሕር ስርቻ ተነስተው እንቁላሎቻቸውን ለመጣል ወደ ላይ ይዋኛሉ። ጉዞው ረጅም እና ብዙ አደጋዎች የተሞላ ቢሆንም እነሱ ግን ጉዞውን አያቋርጡም። ምክንያቱም ሕይወት መቀጠል አለበት። ታዲያ ብዙዎቹ ወደ መዳረሻቸው ይደርሳሉ፤ ዓላማቸውንም ከግብ ያደርሳሉ። የማይታመን ጥንካሬ እና ቁርጠኝነት ያሳያሉ። ዘራቸውም ይቀጥላል።

ጫካ እሳት ሲነድ፣ እዚያ የሕይወት መጨረሻ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አዳዲስ ተክሎች ማደግ ይጀምራሉ። ከእሳቱ የሚወጣው አመድ አፈሩ እንዲበልጽግ ይረዳል። ይህም ጫካው ከበፊቱ የበለጠ ጠንካራ ሆኖ እንዲመለስ ያስችለዋል። ይህ የሚያስተምረን ሕይወት ምንም ያህል ከባድ ቢሆን መትረፍ እና ከዚም በላይ (እንዲያውም) ማደግ እንደምንችል ያስተምረናል። አስቸጋሪ ጊዜያት እንድንጠነክር እና እንድናድግ ሊረዳን ይችላል። ስለዚህ ፈተናዎች ሲመጡ ተስፋ አትቁረጥ። ጠንካራ ሁን እና ወደፊት ቀጥል።

  1. ተስማሚነት

ተፈጥሮም ከለውጥ ጋር እንድንስማማ ያስተምረናል። እንደ ዋልታ ድቦች ያሉና በአንታርቲካ ውስጥ ያሉ እንስሳትን ተመልከት። በብርድ ሙቀት ውስጥ እንዲሞቁ ለማድረግ ወፍራም ፀጉር አላቸው። በአንጻሩ በበረሃ ውስጥ ያሉ ግመሎች ውሃ የሚያጠራቅሙ ጉብታዎች እና ዓይኖቻቸውን ከአሸዋ የሚከላከሉ ረጅም ሽፋሽፍቶች አሏቸው። በክረምት ወራት ብዙ ዛፎች ኃይልን ለመቆጠብ ቅጠላቸውን ያራግፋሉ። ፀደይ ሲመጣ፤ አዲስ ቅጠሎችን ያበቅላሉ። ይህ ከተለያዩ ሁኔታዎች ጋር እራሳችንን እንዴት ማስተካከል እንዳለብን ያሳየናል።

በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ የማያቋርጥ ነው። ወደ አዲስ ከተማ ልንሄድ፣ አዲስ ሥራ ልንጀምር ወይም ያልተጠበቀ ፈተና ሊያጋጥመን ይችላል። እንደ እንስሳት እና ዛፎች ለመኖር እና ስኬታማ ለመሆን መላመድ አለብን። ስለዚህ ተለዋዋጭ እና ሕይወት በሚፈልግበት ጊዜ ለመለወጥ ዝግጁ ይሁኑ።

  1. የቡድን ሥራ

ተፈጥሮ በጋራ የመስራትን ኃይል ያስተምረናል። ጉንዳኖች ፍጹም ምሳሌ ናቸው። እነሱ ጥቃቅን ናቸው። ነገር ግን በቡድን ስለሚሰሩ ትልቅ ነገር ተሸክመው ይንቀሳቀሳሉ። አብረው ቤት ይሠራሉ፣ ምግብ ይሰበስባሉ። ይህ ብቻ አይደለም፤ ግዛታቸውንና ለጥቃት የመጣ ጠላትን በጋራ ይከላከላሉ። ንቦች ሌላ ምሳሌ ናቸው። ተባብረው ቀፎ አዘጋጅተው ማር ይሠራሉ። እያንዳንዱ ንብ የሚጫወተው ሚና አለው። በእንስሳት ዓለምም ቢሆን አዳኞች እንደ አንበሳ በቡድን እያደኑ ብዙ አዳኞችን ይይዛሉ። ይህ የሚያሳየን ተባብሮ መስራት ብቻውን ከመስራት የበለጠ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ነው። በመሆኑም የቡድን ሥራ ተግባራትን ቀላል እና የበለጠ ስኬታማ እንደሚያደርግ ከተፈጥሮ ተማር። ከሌሎች ጋር መተባበርን እሴትህ አድርግ።

ማጠቃለያ

ተፈጥሮ ጥበበኛ አስተማሪ ናት። በትዕግስት ትክክለኛውን ጊዜ እስኪመጣ እንድንጠብቅ ታስተምረናለች። ሚዛናዊ ሕይወትን እንድንመራ እና በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳን ጠንካራ እንድንሆን በምሳሌዎች ታሳየናለች።

ተፈጥሮ ውድ የትምህርት ሣጥን ነው። በዛፎች አዝጋሚ እድገት ፣በምግብ ሰንሰለት ሚዛን፣ ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚተርፉ እፅዋት እና እንስሳት የመቋቋም ችሎታ፣ ወቅቶችን በመለዋወጥ እና በጉንዳን እና በንቦች በቡድን በመስራት ትምህርት ወስደህ የራስህን የሕይወት መንገድ እንደምትገነባ እወቅ።

ተፈጥሮን በመመልከት፣ እንዴት በተሻለ ሁኔታ መኖር እንደምንችል እና በተረጋጋ አእምሮ የሕይወት ፈተናዎችን መጋፈጥ እንዳለብን ማወቅ እንችላለን። ስለዚህ በሚቀጥለው ጊዜ አንድ ዛፍ፣ ወንዝ ወይም ትንሽ አበባ ስትመለከት ትንሽ ጊዜ ወስደህ ተከታተል። ለተፈጥሮ ልብህ ክፍት ይሁን፤ ይህ ኡደት ምን ትምህርት ነው የሚያስተምረው? የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ ጠይቅ። ተፈጥሮ ሁልጊዜ ትናገራለች። ከኛ የሚጠበቀው ማስተዋል፣ ማዳመጥ ልቦናን ክፍት ማድረግ ብቻ ነው።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You