እንደ መነሻ …
ከዓመታት በፊት አገሯን ለቃ ስትርቅ ብዙ ምክንያቶች ነበሯት፡፡ ባለቤቷን በሞት አጥታለች፣ አቅም ጉልበት አንሷታል፡፡ ሕይወት ለእሷ በብቸኝነት፣ መልከ ብዙ ነበር፡፡ ሁለቱ የሙት ልጆች ከእናታቸው ብዙ ይሻሉ፡፡ ባለችበት፣ በኖረችበት ቦታ ሕይወት አልተመቻትም፡፡
አንዳንዴ ሀሳቧ ወንዝ ተሻግሮ ይሄዳል፡፡ አሁን አርሶ የሚያበላ፣ ጎተራ የሚሞላ አባወራ ጎኗ የለም፡፡ በሴት አቅሟ ጎደሎውን መሙላት፣ ስብራቱን መጠገን አልሆነላትም፡፡ ሁሌም ውስጠቷ መዳረሻዋን እያሳያት ነው፡፡ ከቀዬዋ መራቅ፣ ከአገሯ መውጣት መፍትሄ እንደሆነ ገብቷታል፡፡ ሀሳቡን ፈጽሞ መተው አልፈለገችም፡፡
ትውልዷ ጎጃም ገጠር ውስጥ ነው፡፡ ከብቸኛ አለፍ ከምትል አንዲት የጎጥ መንደር፡፡ ሙሉ ጌታነህ ልቧ ለመንገድ ከተነሳ ቆይቷል፡፡ ባገር በቀዬው መቆየትን አትሻም። ከተማ ገብታ ኑሮዋን መቀየር ሕይወቷን መለወጥ አለባት፡፡ ሁለቱ ልጆቿ ለምግብ እንጂ ለሥራ አልደረሱም፡፡ ሙሉ ይህ አልጨነቃትም፡፡ የአዲስ አበባ ሰው ጥሩ ነው ሲባል ሰምታለች፡፡ ሰርታ ማ ደር ራሷን ማሸነፍ አያቅታትም፡፡
ከቀናት በአንዱ ሙሉና ሁለት ልጆቿ መሀል አዲስ አበባ ራሳቸውን አገኙት፡፡ ለግዜው ተቀባይ ዘመድ አላጡም፡፡ ውሎ አድሮ ግን እንግድነቱ ቀረ፡፡ እናት ለእሷም ለልጆቿም ጉሮሮ መስራት፣ መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ እግሮቿ ርቀው ተጓዙ፡፡ አቅሟ የሚችለውን ያህል አላጣችም፡፡ ትከሻዋ የቀንሥራውን ሸክም ለመደው፡፡ ውሎዋ ቢከብድም ከሰዎች ተዋወቀች፡፡ ከብዙዎች ተግባባች፡፡
ሙሉ የከተማ ሕይወት እንዳሰበችው ሆኖ አልቀለላትም። የቤት ኪራዩ፣ የዕለት ወጪው፣ የውጣውረድ ድካሙ ይለያል። ሁሉን እንደአመጣጡ ችላ ጊዚያትን ተሻገረች፡፡ እያደር ደግሞ እያንዳንዱን ጉዳይ ለመደችው፡፡ ከተሜነት ተዋሀዳት፣ ወዳጅ፣ ዘመድ፣ ጓደኛ፣ ጎረቤት አፈራች፡፡
መፍትሔ -ለብቸኝነት …
አሁን ሙሉ የአዲስ አበባ ሰው ሆናለች፡፡ ኑሮ ከብዶ ሕይወት ቢያስጨንቃትም እጆቿ ለጓዳዋ ጎዶሎ አላነሱም። እንደአቅሟ ራሷን አሸንፋ ታድራለች፡፡ ልጆቿ በዕድሜ ትንንሾች ናቸው፡፡ ከጎኗ ሆነው ሊያግዟት፣ ሊደግፏት አይችሉም፡፡ ከፍ ብለው ራሳቸውን እስኪችሉ ከጉያዋ አይወጡም፡፡
ለሙሉ የአዲስ አበባ ኑሮዋ ችግር ብቻ አልሆነም፡፡ በፈተናዎች መሀል ያወቀችው ጎልማሳ ለቁምነገር አስቧታል። እሷም ብትሆን ብቸኝነቱን አትሻውም፡፡ ከጎኗ የሚቆም፣ ‹‹አለሁሽ›› የሚል የትዳር አጋር ቢኖራት ትወዳለች፡፡ ለጋብቻ ያሰባት ሰው እሷን ብቻ ወዶ ልጆቿን አልጠላም፡፡ በአንድ ጎጆ መኖር ሲጀምሩ ለሁሉም ልቡ ፈቀደ፡፡
አሁን የሙሉ ቤተሰብ በቁጥር አንድ ጨምሯል፡፡ ችግር ከስሩ ባይነቀልም ሕይወት ከትናንቱ የተሻለ ነው፡፡ ከአንድ ትከሻ በሁለት እጅ መሰራቱ ጎዶሎዎችን ሞልቷል፡፡ ከትናንት ዛሬ ተሽሎም ሀሳብ በእኩል ተከፍሏል፡፡ ሙሉ ትዳር ከያዘች ጥቂት ግዚያት በኋላ የተወለደው ልጅ ለጥንዶቹ የጋራ ሕይወት ማሰሪያ ሆነ፡፡ በቤቱ ኑሮ ባይሞላም ፍቅር አልጎደለም። ሕይወት እንደትናንቱ ቀጥሏል፡፡ ግዜ እየቆጠረ፣ ዓመታት እየነጉዱ ነው፡፡ ትልልቆቹ የሙሉ ልጆች በዕድሜ ማደግ፣ መለወጥ ጀምረዋል፡፡ ይህ እውነት ዓይምሮቿውን አብስሎ ብዙ ያሳስባቸው፣ ያስጨንቃቸው ይዟል፡፡ የመጀመሪያ ልጇ ወጣት እየሆነ ነው፡፡ እስከዛሬ በቤተሰብ ስር ኖሮ፣ ይተዳደር ነበር፡፡ አሁን ግን ማንንም ማስቸገር እንደሌለበት አምኗል። በአቅሙ በቀን ሥራ እየዋለ የላብ የጉልበቱን ይዞ ይገባል፡፡
ታናሽ እህቱ አስራ አራት ዓመት ሆኗታል፡፡ እድሜዋ ለሥራ ባይደርስም ቤተሰብ መሀል መቀመጡ ከብዷታል፡፡ ከእናቷ ተነጥላ ሰው ቤት ሰራተኛ ከሆነች ሰንብታለች፡፡ ሙሉ ሁሌም የልጆቿ ሕይወት ያሳዝናታል፡፡ እንደ እኩዮቻቸው ተምረው፣ ተመችቷቸው ቢኖሩላት ምኞቷ ነበር፡፡ ጥሩ ከመመኘት ሌላ ግን አንዳች ማድረግ አይቻላትም፡፡ ድህነት ዛሬም ከአጠገቧ አልራቀም፡፡ በየግዜው በችግር ትፈተናለች፡፡
ወይዘሮዋ ከአዲሱ ትዳር አጋሯ የወለደችው ሶስተኛ ልጅ አድጎላታል፡፡ አባቱ በቅርብ አለና ስለእሱ ጎዶሎ አስባ አታውቅም፡፡ ቢገኝም፣ ቢጠፋም ፈገግታው ተስፋው ነው። አባትነቱ ያኖረዋል፡ እስትንፋሱ ያሳድረዋል፡፡ ሙሉ የሴት ልጇ ነገር ሁሌም ዕንቅልፍ እንደነሳት ነው፡፡ ያለዕድሜዋ ከጎኗ ርቃ የሰው ቤት ሰራተኛ መሆኗ ጭንቀት ጥሎባታል። ለዚህ ምክንያቱ ማጣት፣ መንጣቷ መሆኑ ሲገባት ሀዘኗ ይበረታል፡፡ አንዳች ማድረግ አልቻለችምና በነገሮች እውነታ አብዝታ ትቆጫለች፡፡
አራተኛው ልጅ …
አስራሶስት ዓመት ያስቆጠረው ትዳር ከነጥንካሬው ዘልቋል፡፡ ክፉ ደግ ቀናት ችግር ከደስታን አስከትለው እየተጓዙ ነው፡፡ የቀን ሰራተኛው አባወራ በሕንጻ ግንባታው ሲባትል፣ ሲደክም ይውላል፡፡ የቤት ኪራዩ፣ የዕለት ወጪና ጉርስ ከክብደቱ አልቀለለም፡፡ ዛሬና ነገ እንደትናንቱ በችግር ተጨባብጠው እያለፉ ነው፡፡
ኑሮ ለውጥ ባይኖረውም ሕይወት እንደቀድሞው ቀጥሏል፡፡ ሙሉ አራተኛውን ልጅ አርግዛለች፡፡ በችግሯ ላይ ሌላ ሆድ መምጣቱ ቢያሳስባትም አልተማረረችም፡፡ የሆነውን ሁሉ በምስጋና ተቀብላ ኑሮን ቀጥላለች፡፡ ነገሮች ቢከብዱም፣ ስለኑሮ መንገዶች ቢጠቡም ዛሬ እንደትናንቱ እያለፈ ነው፡፡
ነፍሰጡሯ ወይዘሮ መውለጃዋ እስኪደርስ እረፍት ይሉትን አታውቅም፡፡ ለቤት ለጓዳዋ፣ ለትዳር ልጆቿ ለመድረስ የአቅሟን ትለፋለች፡፡ ከቀን ሥራው መለስ ብላ እንጀራ እየጋገረች ትሸጣለች፡፡ እንዲያም ሆኖ የሕክምና ክትትሏን አትረሳም፡፡ ቀጠሮ ባላት ቀን ሀኪሟ ፊት ትቀርባለች፡፡ ምክር ተቀብላ፣ ቀጣዩን ቀጠሮ ወስዳ በወሩ ትመለሳለች፡፡
ሙሉ እስካሁን ከሀኪሟ የሰማችው የጤና ችግር የለ። ውስጧ ፍጹም ሰላም ነው፡፡ ያማራትን ትበላለች፡፡ እንዳሻት ትሰራለች፣ ትራመዳለች፡፡ ግዜ ተቆጥሮ ዘጠነኛው ወር ስትገባ ግን እስካሁን ሆኖባት የማያውቅ አዲስ ጉዳይ ለጆሮዋ ደረሰ፡፡ በሆዷ ያለው ጽንስ ችግር ያለበት መሆኑ ተነገራት፡፡
ይህ እውነት በችግር ተፈትና ላለፈች እናት እጅግ ከባድ የሚባል ነበር፡፡ ሙሉ ዘጠኝ ወር ሙሉ ያለ አንዳች ስጋት ማለፏን ታውቃለች፡፡ አሁን ላይ ተከስቷል የተባለው ችግር ለእሷ መልስና መፍትሔ የለውም፡፡ ወይዘሮዋ ከነበረችበት ጤና ጣቢያ ለተሻለ ሕክምና ወደ ሌላ ሆስፒታል ስትደርስ የመውለጇ ቀኗ ደርሶ ነበር፡፡
ያለ ፈገግታ …
በሆስፒታሉ ልጇን ወልዳ የታቀፈችው እናት ሙሉ ደስታ አይሉት ሀዘን ወረራት፡፡ ሕጻኑ ላይ የሚታየው ችግር አስቀድሞ የተረጋገጠው ሕመም ስለመሆኑ ተነግሯታል፡፡ ስሜት አልባውን እውነት ያለፈገግታ ተቀበለችው፡፡ በአስቸኳይ ከሆስፒታሉ ወጥታ ወደ ሌላ ሆስፒታል እንድትላክ ሆነ፡፡ ለጥቂት ግዚያትን አልጋ ይዛ የልጇን ጤንነት ተከታተለች፡፡
የሕጻኑ ችግር በእርግዝና ወቅት ተገቢውን የፎሊክ አሲድ ካለመውሰድ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር የጤና እክል ነው፡፡ በጽንስ ግዜ የነርቭ ዘንግ ክፍተትና የጭንቅላት ውሀ መቋጠር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ይህ ክስተትም በሳይንሳዊ ስሙ ‹‹ ስፓይና ቢፊዳ እና ሀይድሮሴፋለስስ›› በመባል ይጠራል፡፡
ችግሩ ባብዛኛው መኖሩ የሚታወቀው በእርግዝና የመጨረሻዎቹ ግዚያት በመሆኑ አስቀድሞ መፍትሔ ለመውሰድ ዕንቅፋት ይሆናል፡፡ በምርመራ ከታወቀ በኋላም በርካታ እናቶች ጽንሱ እንዲወገድ ባለመፈለጋቸው ከችግሩ ጋር የሚወለዱ ሕጻናት ቁጥር በርካታ ነው፡፡ የሙሉ ልጅ የጤና ችግርም ጀርባው ላይ ክፍት ሆኖ መወለዱ ነበር፡፡
ይህ እውነት ከታወቀ በኋላ ሕጻኑ በተወለደ በአንድ ወሩ የቀዶ ሕክምና ተደረገለት፡፡ እንደታሰበው ሆኖ ግን እናትና ልጅ ወደ ቤታቸው አልሄዱም፡፡ ሕፃኑ በጭንቅላቱ ላይ የተፈጠረው ኢንፌክሽን ለከፋ ሕመም ዳርጎ ያሰቃየው ያዘ፡፡ የታዘዘለት መድሀኒት የኪስ አቅምን ይፈትናል፡፡ የአንዷ ኪኒን ዋጋ በባልና ሚስቱ ኪስና ቦርሳ የሚሞከር አይደለም፡፡
በወቅቱ በሰዎች እገዛና በወዳጅ ዘመድ ድጋፍ የሕጻኑ ጤና ተመልሶ ቆየ፡፡ እናት ሙሉ የሆነበትን ሳትቆጥር ‹‹እፎይ! ››አለች፡፡ ፈጣሪዋንም አመሰገነች፡፡ ይህ መልካም ስሜት እምብዛም ሳይርቅ ሌላው አጋጣሚ ሆነ፡፡ ትንሹ ልጅ በልቡ ላይ የጤና ችግር እንዳለበት በሀኪሞች ተረጋገጠ፡፡
ትንሹ ልጅ ዕድሜው ከፍ እያለ ነው፡፡ በሰላም እዚህ መድረሱ ለሙሉ ሰላም ለግሷል፡፡ የአንድ ዓመት ልደቱን ከማክበሩ በፊት ግን እናት ከእሱ ማየት የምትሻውን አንድ እውነት እየናፈቀች ነው፡፡ እንደ እኩዮቹ ልጇ ‹‹ ዳዴ …. እያለ እንዴሄድ ወድቆ እንዲነሳ ትሻለች፡፡ ‹‹ወፌ ቆመች ማለት ትፈልጋለች፡፡
እናት ግዜውን አስልታ በየቀኑ መዳህ፣ መጓዙን ጠበቀች። በልጇ ላይ አንዳች ለውጥ አልታየም፡፡ ራሷን ሸንግላ በሌላም ቀን ጠበቀችው፡፡ ሕጻኑ እንደ እኩዮቹ ዕቃ ይዞ አልተነሳም። ‹‹ዳዴ… እያለ አልተጓዘም፡፡ ከመሬት እንዳኖረችው፣ ቁጭ እንዳለ ውሏል፡፡ እናት ልቧ ስብር፣ ድቅቅ ሲል ተሰማት። የሕመሙ ምክንያት እግሮቹን አደንዝዞ እንደማያራምደው ታውቃለች፡፡ እሷ ግን ተስፋ ሳትቆርጥ ስትጠብቀው፣ መራመዱን ስትናፍቀው ቆይታለች፡፡
የጣራው ሥር ችግር እንደቀጠለ ነው፡፡ እናት አቤል ልጇ ባይራመድም አንደበቱ በመናገሩ ደስ ይላታል፡፡ የእሱ አይነት ምክንያት ካላቸው ሕጻናት አንዳንዶቹ አለመራመድን ጨምሮ የመናገርና፣ የማየት ችግር እንዳለባቸው ታውቃለች፡፡ ከእነሱ ጋር ልጇን ስታወዳድር ምስጋናዋ ያመዝናል፡፡ አቤል በዊልቸር ተቀምጦ መንቀሳቀስ፣ እንደልቡም ማውራት መጫወት ይችላል፡፡ ይህን ስታይ ደጋግማ ‹‹ተመስገን›› ትላለች፡፡
ስሜት አልባ እግሮች ….
ትንሹ አቤል አንደበቱ ተፈቶ መግባባት ይችላል፡፡ ከወገቡ በታች ያለ አካሉ ግን አንዳች ስሜት የለውም፡፡ ይህ እውነት አንዳንዴ ባስገራሚ አጋጣሚዎች ያልፋል፡፡ እንዲህ በሆነ ግዜ ከአቅም በላይ ውስጥን ይረብሻል፡፡ በቅርብ ግዜ በእሱ ላይ የተከሰተው አጋጣሚም ይኸው ነው፡፡ አቤል ሕመሙ ሳይሰማው ሌሎች ቀድመው ላወቁለት ጉዳት ተዳርጓል፡፡
በዚህ ቀን አቤል እንደሌላው ግዜ በዊልቸሩ ተቀምጦ ሲጫወት ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ድንገት ዞር ሲል በገጠመው ጉዳት ግን እግሮቹ ላይ የከፋ ስብራትን አስተናግዷል፡፡ የዚህ ስብራት ሕመም ግን ቀድሞ ለእርሱ ተሰምቶት አላለቀሰም፣ እግሮቹ ተሰብረው ማበጥ መታመማቸው የታወቀው ቅድሚያ በእናቱ እይታ፤ ቀጥሎም በሕክምና ምርመራ ነበር፡፡
ምሽቱን እናቱ ትኩሳቱ ቢያግላት እጆቿን ሰዳ ዳበሰችው፡፡ ያየችውን እውነት ማመን አልቻለችም፡፡ ዳይፐሩን ስትፈታ አጥንቱ ስፍራውን ለቆ ቆዳው ብቻውን እየዋለለ ነው። ይህ ሁሉ ሲሆን በሕጻኑ ላይ አንዳች ለውጥ አልታየም። በሞቀ ዕንቅልፍ ውስጥ ምቹ እረፍት ላይ ነበር፡፡ ሀኪም እጅ ገብቶ መፍትሄ አስኪያገኝም ዘና ብሎ ሲስቅ ሲጫወት ቆይቷል፡፡
አቤል ከወገቡ በታች ያለ አካሉ ሕይወት አልባ ነው፡፡ መቼም ቢሆን በእሳት ቢቃጠል፣ ቢደበደብና ቢሰበር አንዳች አይሰማውም፡፡ በፎቶግራፍ የቀረውን የትንሹን ልጅ ምስል አስተዋልኩት፡፡ ከወገቡ በታች ያለ አካሉ ሙሉ ለሙሉ በጀሶ ታስሯል፡፡ ሲበላም፣ ሲጠጣም ተኝቶ እንደሆነ አጫወተችኝ። እናት ይህን ባነሳች ቁጥር በዓይኖቿ ውሀ ይሞላሉ፡፡ ጉዳቱን የተሸከመው ትንሹ ልጅ ግን ገጽታው ከእሷ ይቃረናል፡፡ ፊቱ በፈገግታ ብሩህ ሆኖ እየተነበበ ነው፡፡
ሌላው ፈተና…
ወይዘሮዋ በኑሮና ሕይወቷ ዋጋ መክፈሏ ቀጥሏል። ቀድሞ ሮጦ የሚያድረው ባለቤቷ በሕንጻ ሥራ ላይ በደረሰበት የመውደቅ አደጋ ለከፋ ችግር ተዳርጎ ከአልጋ ውሏል፡፡ ይህ ክፉ አጋጣሚ ሌላ ፈተና ደርቦም ጫናውን በእሷ ትከሻ አሳርፏል፡፡ ዛሬ ሙሉ የቤቱና የቤተሰቡ ኃላፊነት ያሳስባታል፡፡ ለቤት ኪራይና ለዕለት ጉርስ ለልጁ ዳይፐርና ለሕክምና የሚያስፈልገው ወጪ ከእሷ ትከሻ አያልፍም፡፡
በየቤቱ እየዞረች እንጀራ መጋገር፣ ልብስ ማጠብ፣ የተገኘውን ሥራ መከወን ግዴታዋ ነው፡፡ ሕጻኑ እግሩ ከመሰበሩ በፊት ለሥራ ስትወጣ እያዘለችው ነበር፡፡ ልብስ ስታጥብ፣ እንጀራ ስትጋግር አጠገቧ ታስቀምጠዋለች፡፡ ልብሱ ንጹህ ካልሆነ ብዙዎች ይጠየፉታል፡፡ በዚህ ሰበብ ሥራውን እንዳታጣ አብዝታ ትጠነቀቃለች፡፡
አንዳንዴ የቅርብ ዘመዶቿን ታገኛለች፡፡ ጥቂቶቹ ውስጧን ለመስበር ፈጣን ናቸው፡፡ በጨዋታቸው መሀል የእሷ ልጅ ምክንያት የእግዜር ቁጣ መሆኑን ይጠቁሟታል፡፡ ንግግራቸው አስከፍቷት ስታለቅስ አያዝኑላትም፡፡ ‹‹የልብሽን ክፋት አይቶ እሱን ሰጠሸ ››ሲሉ ይዘባበቱባታል፡፡
ሙሉ ሴት ልጇ ‹‹ራሴን ልቻል›› ብላ ከራቀቻት ቆይቷል፡፡ ስለእሷ ሕይወትና ኑሮ ሁሌም ትብሰለሰላለች፡፡ ትልቁ መማር ሲገባው በቀን ሥራ መድከም መልፋቱ ያሳዝናታል፡፡ የባለቤቷ ካልጋ መዋል ደግሞ ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ ትንሹ አቤል አሁን ክፉኛ ተጎድቷል፡፡ አራት ዓመቱ ቢያልፍም መቼም በእግሩ አለመራመዱ ልቧን ይሰብረዋል፡፡ የዕድሜ ልክ ዳይፐር ተጠቃሚ ነውና የወጪው ጉዳይ የየእለት ሀሳቧ ነው፡፡
ሙሉ በሥራና ልጆች በማሳደግ ጉልበቷ ደክሟል። በየቀኑ የምታጥበው ልብስ ከድካም በላይ ነው፡፡ አንዳንዴ እህል ባፏ ሳይዞር ስታጥብ ትውላለች፡፡ ባዶ እጅ ከባዶ ሆድ ይዛ በድካም እያዞራት፣ ቤት ስትገባ ባዶቤት እሷን የሚናፍቁ ነፍሶች ይጠብቋታል፡፡ ወጪ እንጂ ገቢ የሌለው ኑሮዋ አሰልቺና አድካሚ ነው፡፡
እሷ ስለልጇ መኖር አትሆነው የለም፡፡ ዛሬ ግን ሁሉም ያቃታት፣ የተሳናት ይመስላል፡፡ የቤት ኪራይ ከአቅሟ በላይ ሆኗል፡፡ የዕለት ጉርስ እያሳሰባት፣ እያስጨነቃት ነው። ወይዘሮዋ ባዶቤትን ለብቻ መምራት ያንገዳግዷት ይዟል፡፡ አሁን የሚረዷት፣ የሚያግዟትን እጆች ትሻለች፡፡ ስለነገ ዛሬን ዋጋ የምትከፍለው እናት ሙሉ ጌታነህ፡፡
መልካምሥራአፈወርቅ
፣አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም