በሰው ሠራሽ ደሴት ላይ እየተገነባ የሚገኘው ግዙፉ አውሮፕላን ማረፊያ

ቻይና በሰው ሠራሽ ደሴት ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፉን የአውሮፕላን ማረፊያ እየገነባች እንደሆነ ተገለጸ፡፡ አዳዲስ ፈጠራዎችን በማስተዋወቅ እና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመገንባት በዓለም ቀዳሚ የምትሆንበትን አዲስ ፕሮጀክት እየገነባች ትገኛለች፡፡

ሀገሪቱ በዓለማችን ግዙፍ በተባለው ሰው ሠራሽ ደሴት ላይ በግዝፈቱ ተወዳዳሪ አይኖረውም የተባለውን አየር ማረፊያ እውን ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምራለች። አራት ትላልቅ የአውሮፕላን መንደርደርያዎችን እና ማረፊያዎችን ይይዛል የተባለው የደሴት ላይ አውሮፕላን ማረፊያ 900 ሺህ ስኩየር መሬት ላይ ያረፈ የመንገደኞች ማስተናገጃ (ተርሚናል) ይይዛል ተብሏል፡፡

በሂደት 20 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ለመሸፈን ያቀደው የደሴት አውሮፕላን ማረፊያ (ኤርፖርት) የሆንግኮንግ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እና የጃፓኑን ካንሳይ ኤርፖርት በመብለጥ ቀዳሚ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በዓመት 80 ሚሊዮን መንገደኞችን እና 540 ሺህ በረራዎችን የሚያስተናግድ አቅም ይኖረዋልም ተብሏል።

ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች በሚኖሩበት ዳሊያን በተሰኘ ከተማ ላይ የሚገነባው አውሮፕላን ማረፊያ ለጃፓን እና ደቡብ ኮርያ ካለው ቅርበት አንጻር ከፍተኛ የትራንስፖርት መናኸሪያ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

በከተማዋ ለ100 ዓመታት ያገለገለው የዳሊያን ጆሽዊዢ ኤርፖርት ለበርካታ ጊዜ ማስፋፍያ ቢደረግለትም አሁን ላይ ያሉትን ደንበኞች ወይም ተጓዦች ማስተናገድ የሚችልበት አቅም ላይ እንደማይገኝ ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና መሀንዲስ ሊ ያንግ ግንባታው በውሃ ላይ እንደመገንባቱ እንዲሁም ከሚሸፍነው ቦታ ስፋት አንጻር ውስብስብ የኮንስትራክሽን ቅየሳዎችን ቢፈልግም መሳካቱ እንደማይቀር ተናግረዋል፡፡

ኤርፖርቱን ለመገንባት እኤአ በ2003 የቦታ መረጣ እና የማሳያ ሥራ የተጀመረ ቢሆንም ግንባታው የተጀመረው ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው፡፡ አዳዲስ አውሮፕላን ማረፊያዎች የቻይና የአቪዬሽን እድገት ማሳያ ቁልፍ አካል ናቸው። ሀገሪቱ አሜሪካን በመብለጥ የዓለማችን ትልቁ የአየር መጓጓዣ ገበያ ማዕከል ለመሆን በመንገድ ላይ ነች ነው ያሉት።

ዳክሲንግ የተባለው የቤጂንግ ሁለተኛ ግዙፍ አውሮፕላን እኤአ በ2019 ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን የቻይና ባለሥልጣናት ሀገሪቱ የአየር ትራንስፖርት ፍላጎትን ለማሟላት እኤአ በ2035 450 አየር ማረፊያዎች እንደሚያስፈልጓት መናገራቸውን የዘገበው አል ዐይን ነው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You