አዲስ አበባ፡- አካባቢን ከብክለት ለመከላከል የወጡ ሕጎች፣ መመሪያዎችና አዋጆች የሕዝብና የሀገርን ደህንነትና ተጠቃሚነት በሚያጎለብትና ዘመኑን በዋጀ መልኩ እንዲሻሻሉ እየተደረገ መሆኑን የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ። ሕጎችን ከማሻሻል ባሻገር ለውጤታማ ተፈፃሚነታቸው ከወትሮ በላቀ መልኩ እንደሚሠራም አመለከተ።
የባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ አካባቢን ከብክለትና ከብክነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጡ ሕጎች፣ መመሪያዎች፣ አዋጆች በርካታ ቢሆኑም አካባቢን ከብክለት በመከላከል ረገድ ክፍተት ያለባቸው ናቸው። እነዚህ የወጡ ሕጎች ዘመኑን በሚዋጅና አካባቢን ከብክለት በሚከላከሉ መልኩ እንዲሻሻሉ እየተደረገ ነው።
እንደ ሀገር ከግንዛቤ ባሻገር የሕጎች ተፈፃሚነት ላይ ክፍተት ስለመኖሩ ያመላከቱት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ከዚህ ቀደም የወጡ በተለይም ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችንና አዋጆች መሻሻል ከፍ ሲል ወቅቱን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መቀየር እንዳለባቸው መታመኑን ገልፀዋል።
ይህን ተከትሎም በቅርቡም ‹‹ሁለት ረቂቅ አዋጆችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርተዋል›› ያሉት ኢንጂነር ለሊሴ፣ ከእነዚህ ረቂቅ አዋጆች አንዱም የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ በተለይም አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችን መከልከልን የሚያካትት ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው አዋጅ ግልፅነት የጎደለውና ለአፈፃፀም አዳጋች ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው፣ ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ይህን የሚቀይርና አማራጭ የሆኑ ምርቶችን ለህብረተሰቡ ማቅረብን የሚያበረታታ እንደሆነም አስገዝበዋል።
ከፕላስቲክ ባሻገር የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማም አዋጅም ማሻሻያ እንደተደረገበት ያመላከቱት ኢንጂነር ለሊሴ፣ አዋጅ ቁጥር 2009/2002 ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረና በተለይም የህብረተሰቡን በሚፈለገው መልኩ ማእከል ያደረገ እንዳልነበረ አስገንዝበዋል።
ይህን አዋጅ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ማቀራረብ ብሎም ማስማማት የግድ ሆኖ በመገኘቱ የአዲስ ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን ያመላከቱት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ይህ ረቂቅ አዋጅም የሕዝብ ደህንነትና ተጠቃሚነት ማእከል ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
ይህ ረቂቅ አዋጁ የልማት ፕሮጀክቶች የሚኖራቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ በማጎልበትና አሉታዊ ተፅዕኖችን በመቀነስ ከተቻለም በማስቀረት ከአካባቢው ጋር ተስማሚ፣ በማኅበረሰቡም ዘንድ ተቀባይ ሆነው ዘላቂ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ በማድረግ ረገድ የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በቀጣይም አካባቢን ከብክለትና ብክነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጡ ሕጎች፣ መመሪያዎች፣ አዋጆችን በሚመለከት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማጎልበት ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመው፣ ሕጎችን ከማሻሻል ባሻገር ለውጤታማ ተፈፃሚነታቸው ከወትሮ በላቀ መልኩ እንደሚተጋም አስታውቀዋል።
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ስድስት ክፍሎች እና 28 አንቀጾች ያሉት የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረቂቅ አዋጅ፣ በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ከረጢት መጠቀም፣ ማምረት እና ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት በገንዘብ እና በእስራት የሚያስቀጣ ድንጋጌ የተካተተበት ነው። በረቂቅ አዋጁ መሠረት የፕላስቲክ ከረጢት የተጠቀመ ወይም ለመጠቀም ይዞ የተገኘ ማንኛውም ሰው ከአምስት እስከ አስር ሺህ ብር ገንዘብ እንደሚቀጣ ያስቀምጣል።
በተመሳሳይ የፕላስቲክ ከረጢት ማምረት፣ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ ለገበያ ማቅረብ፣ መሸጥ ወይም ለንግድ ዓላማ ማከማቸት ከሃምሳ ሺህ ብር በማያንስና ከሁለት መቶ ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም