የሰው ልጅ የትውልድ ስፍራውን፣ የቆዳ ቀለሙን፣ ቤተሰቡን፣ ጾታውን ወይም መልኩን መርጦ አይወለድም። ነገር ግን የተሰጠውን ሁሉ ተቀብሎና ተጠቅሞ የሕይወቱን መንገድ መምረጥ ይችላል። ውሳኔው፣ አካሄዱ፣ እርምጃውና ሌላው ከዚህ የሚማሰለው የራሱ ምርጫዎች ናቸው። በዚህም ይጎድለኛል ከሚለው ይልቅ የተሰጠው ሲበልጥ፤ ከተሰጠው ደግሞ ሊያደርግ የሚችለው ይገዝፋል። የዛሬ እንግዳችን ወይዘሮ አዳነች ካሳ ይህንኑ ነው የሚነግሩን።
በምርጫቸው፣ በውሳኔያቸውና በእርምጃቸው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና አገራቸውን ማገልገል የቻሉ ሰው መሆናቸውን። በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል እሴቶችና ኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክተር ሲሆኑ፤ ከሕይወት ልምዳቸው ጨልፈው፤ በሙያና በሥራቸው ካሳለፏቸውና ከሚያውቋቸው ልምዶቻቸው ከፍለው፤ በትህትና እና በአክብሮት በተዋዙ ቃላት እንዲሁም የእኔነት ስሜት በሚነበብበት የመቆርቆር መንፈስ አጋርተውናል። እኛም እንዲህ አቀረብንላችሁ። መልካም ንባብ።
ባህልና አስተዳደግ
«ልጆቼ የምላቸውን አይሰሙም ብለሽ አትጨነቂ፤ ይልቁንም የምታደርጊውን ሁሉ ይከታተላሉና እሱ ያሳስብሽ» የሚል ብሂል አለ፤ ልጅ የቤተሰቡን ቃል ከሚሰማው በላይ ድርጊቱን ይከታተላል እንደማለት ነው። የወይዘሮ አዳነች ወላጆች ልጆቻቸውን ያሳደጉት እንደዚያ ነው። በተለይም ሥራ ወዳድና ሥራ አክባሪ አድርገው እንደቀረጿቸው ነው የሚያስታውሱት።
«ያደግሁበት ማኅበረሰብና ቤተሰቤ ስነምግባር ላይ ጠንቃቃ ነው። እያንዳንዱ እርምጃችን በጥንቃቄ ይደረጋል። የቤታችንም መሠረት ሥራ ነው። የታዘዝነውን ሥራ ሠርተን ካልጨረስን በቀር ሌሎች ሲበሉ እንኳ እንድንበላ አይፈቀድም ነበር። ከእምነትና ስነምግባር ጋር ተቆራኝተን አድገናል» ይላሉ ወደ አስተዳደጋቸው መለስ ብለው።
ይህ የሆነው ከአዲስ አበባ በ229 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ሆሳዕና ከተማ ነው። የአዳነች ቤተሰቦች በቤት ውስጥ ልጆቻቸውን በስነ ምግባር ለማሳደግ ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ያደረጓቸው ነገሮች ሁሉ የእነርሱ ምርጫዎች ነበሩ። ከዛ ባሻገር ግን ሕይወት በራሷ ልጆቻቸውን ሰፊ በሆነና በተለያየ ባህል ውስጥ እንዲያሳድጉ ረድታቸዋለች። ይህንንም ወይዘሮ አዳነች እንዲህ ይገልጹታል፤ «በሰፊ ባህል ውስጥ ነው ያደግሁት። የጉራጌ ባህልን ከነምግብ ዝግጅቱ አውቀዋለሁ። የአማራ ባህልን እያንዳንዱን በደንብ አውቃለሁ። በዛም ላይ በትውልድ ስፍራችን ምክንያት የሃዲያ ባህል፤ የመስቀል በዓል ከበራውንና ሌላውንም በሚገባ ተረድቼዋለሁ»
እናታቸው የቤት እመቤት ሲሆኑ፤ አባታቸው ደግሞ ከመንግሥት ሥራቸው በተጨማሪ በግብርና ሥራ ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ። ዘጠኝ ልጆችና በተለያየ ዝምድና አብረው እየኖሩ ቤተሰቡን ከሞሉት ጋር ያደጉት ወይዘሮ አዳነች፤ ለወላጆቻቸው ሁለተኛ ልጅ ናቸው። በዚህም እያንዳንዱ እርምጃቸው ለተከታዮቻቸው ፈለግ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ከታናናሾቻቸው አልፎም ወላጆቻቸውም የበኩር ልጆቻቸው አይተው አመለካከታቸውን እንዲቀይሩ ሆነዋል። ይህ እንዴት ሆነ? ቀጥለው ነግረውናል።
«አላገባም!»
«ብዙ ባሎች በቤተሰብ መጥተውልኝ ነበር።» አሉ፤ ለትምህርት የነበራቸውን ፍቅርና ከቤተሰብ ይታገሉበት የገጠማቸውን ታሪክ አስታውሰው። «ልጃችሁን ለልጄ» ባይ በዝቶ፤ «እገሌ ጥሩ ይሆንሻል፤ ብታገቢው ጥሩ ነው» ባይ መካሪና ተቆጪም ሞልቶ ነበር። የእርሳቸው ጎበዝ ተማሪ መሆን እንኳ ለቤተሰቡ ቁብ አልነበረም። እንደውም «ማንበብና መጻፍን ካወቅሽበት ብታገቢስ ምን ክፋት አለው?» አስባላቸው እንጂ። እናም አሻፈረኝ አላገባም ብለው በግልጽ የተሟገቱ ጊዜ፤ ኩርፊያን ጨምሮ በምግብ መከልከል ቅጣት ደርሶባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ያም ቢሆን ግን እርሳቸው ለቤተሰቦቻቸው ሁሌም የሚሉት ቃል አንድ ነው። «12ኛ ክፍልን እስክጨርስ ብቻ ታገሱኝ፤ ከዛ እሄዳለሁ። አሁን የማንም ጥገኛ መሆን አልፈልግም»
ከብዙ ሙግት፣ ትግልና ተግሳጽ በኋላ በመጨረሻ ወላጅ እናታቸው ልጃቸው ያልወደደችውን ልጓም እንዳይጫናት ቃላቸውን አሰሙ። «ተዋት የመረጠችውን ታድርግ» ሲሉ ፈቀዱ። ይህም ለታናናሾቻቸውም ተረፈ፤ ቤተሰቦቻቸውም ለልጆቻቸው የተሻለውን መንገድ መመልከት ቻሉ።
ያልታሰበው ውጤት
ጎበዝ ተማሪ የነበሩት ወይዘሮ አዳነች የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀረ። በዚህም ለበርካታ ቀናት ተከፍተው፤ ለብቻቸው ሆነው በውጤታቸውም ተበሳጭተው ቆዩ። ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገብቶ መማር ህልማቸው ነበርና፤ ከህልማቸው የቀሩ ስለመሰላቸውም ነው። ደግመው እንዲማሩና ፈተናውን በድጋሚ እንዲወስዱ ተጠይቀዋል፤ በዛ መልክ ጥቂት ከነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ገብቶ የተማረ ሰው አያውቁምና የሚሆን አልመሰላቸውም። ስለዚህም ተጽናንተው ወደ ደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገብተው ተማሩ፤ በዛም ቆይታቸው ዩኒቨርሲቲ ገብተው መማር አለመቻላቸው ይቆጫቸው ነበር። ቢሆንም በገቡበት መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም በከፍተኛ ማዕረግ ከመመረቅ አላገዳቸውም። ህልማቸውን ለማሳካትም ዳግም ተነሱ።
ስኬትን ፍለጋ
በ1978ዓ.ም ከደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም በጥሩ ውጤት ከተመረቁ በኋላ እዛው ደብረብርሃን አካባቢ በመምህርነት አገለገሉ። ቀጥለው ወደ ኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ገብተው ዲፕሎማቸውን ተማሩ። በልጅነት ሊገቡበት ይፈልጉት የነበረውና ተግተው የተማሩለት ዩኒቨርሲቲ የመግባት ህልማቸውን ከልባቸው አላወጡም። ይህ ደግሞ ወደ ስኬታቸው የሚጓዙበትን መስመር አመላከታቸው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመያዝ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። በዚያም በስነ ጽሑፍ ትምህርት መስክ ተመረቁ።
በርዕሰ መምህርነት እየሠሩ ትምህርታቸውን መቀጠል የሚሆን ያልመሰላቸው ወይዘሮ አዳነች ከመደበኛ የመምህርነት ሥራ ራሳቸውን ገድበው በትምህርት ዘርፍ ባለሙያነት እየሠሩ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ቀጠሉ፤ በሥነ ጽሑፍና ፎክሎር የትምህርት ዘርፍም በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ለመመረቅ በቁ።
የመምህርነት ቆይታ
ያኔ በህብረተሰብ ትምህርት መምህርነት ሲሰሩ «ያኔ ዲፕሎማ ያለው ሰው በመሥሪያ ቤቱ የሥራ ባልደረቦች ከተመረጠ ርዕሰ መምህር መሆን ይችላል። የተለየ ደመወዝ ኖሮት አይደለም፤ ግን ባለው ደመወዝ እገሌ ይስራልን ተብሎ ይመረጣል። እኔም በዛ ተመርጬ ኮከበ ጽባህ፣ የካና አብዩት ትምህርት ቤቶች በምክትል ርዕሰ መምህርነት ለሰባት ዓመታት ሰራሁ» ብለዋል የስራ ጅማሯቸውን ሲናገሩ።
ወይዘሮ አዳነች በድምሩ ወደ 27 የሚጠጉ ዓመታትን በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፤ በርዕሰ መምህርነት በሠሩባቸው በአንድኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻም ሳይሆን፤ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅም ለዓመታት በማታው መርሃ ግብር በሥነ ጽሑፍ መምህርነት ሠርተዋል። ታድያ ያኔ ከተማሪዎቻቸው በጣም የሚግባቡ፤ ጥሩ ግንኙነት ያላቸው መምህርት ነበሩ። «ውጤት በሰላምታ የለም» ይላሉ። እንዲህ ነው፤ ሰላምተኛ በመሆናቸው ለሁሉም ተማሪዎቻቸው ቅርበት አላቸው። የእነዛ ተማሪዎቻቸው ውጤት የታየ ጊዜ ነጥባቸው ዝቅ ያለባቸው ተማሪዎች፤ «ምነው መምህር፤ እኔኮ ሰላምተኛሽ ነኝ» ይሏቸዋል። እርሳቸው ግን «ውጤት በሰላምታ አላውቅም» ብለው ይመልሳሉ።
ከተማሪዎቻቸው መካከል ግን አንድ ተማሪ ነበረች፤ ዛሬም አይረሷትም። ፈተና አምልጧታል። ይህ የሆነው እናቷ በጠና ታመውባት እርሳቸውን ታስታምም ስለነበር ነው። እርሳቸውም ይህን ሳያውቁ የተማሪዎቻቸውን ውጤት ለትምህርት ክፍሉ ያስተላልፋሉ። ነገሩ ሁሉ ካለፈ በኋላ ያቺ ልጅ ወደእርሳቸው ትቀርብና፤ «እናቴን ሳስታምም የእርስዎ ፈተና አመለጠኝ። እናቴም ሳትድንልኝ ቀረች። በእርስዎ ፈተና ምክንያትም አንድ ዓመት እንድጨምር ተገደድኩ» አለቻቸው። ይህን ዛሬም ድረስ በሀዘኔታ የሚያስታውሱት የመምህርነት ቆይታቸው ገጠመኝ ነው።
«ሴት መምህራን፣ ሴት ትራፊኮች፣ ሴት ዳኞች…ወዘተ ሲለመኑ አይራሩም፤ ይጨክናሉ ይባላል» እርሶ እንዴት ያዩታል ለወይዘሮ አዳነች ያነሳሁት ጥያቄ ነበር። ይህ ነገር ለእርሳቸው አይዋጥላቸውም። «ሴት ተጠንቅቃ ሥራዋን ስለምትሠራ ነው። ሴት ጓደኝነት ፈጥራ ‘ችግር የለም አታስቡ’ አትልም» ይላሉ። ያንን ይዘው ነው ሴት ትጨክናለች የሚሉት። ትምህርት ሥራ ላይ ዋናው ውጤት ወይም ተማሪ ያመጣው ነጥብ ሳይሆን «ምን ያህል አነበብን? ወደ ትምህርት በገባንበት ጊዜ ውስጥ ምን ያህል አውቀናል? የትኛውን ሰዓት ለንባብና ለትምህርት አውለናል?» የሚለው መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።
ወደ ባህል የመሩ ጥናቶች
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሥነ ጽሑፍ ያጠናቅቁ እንጂ የመመረቂያ ሥራቸው ከባህል ጋር አስተዋውቆ በዛው እንዲቀጥሉም አድርጓቸዋል። የመጀመሪያ መመረቂያ ጽሑፋቸው የባህላዊ ጋብቻን መሠረት ያደረጉ አጭር ልብወለዶች ይዘት ትንተና ላይ ነበር። በዚህም በየባህሉ ያሉ የሰርግ ክዋኔ ዓይነቶችን አይተዋል። ከመተጫጨት ስርዓት ጀምሮ ማለት ነው። ይህ ጥናታዊ ሥራቸው ባህል ላይ ይበልጥ እንዲያነቡ አስገደዳቸው።
እርሳቸው ሲገልጹ፤ «ጥናታዊ ሥራው እንደውም ከሥነ ጽሑፍ ውጪ የሆነ ይመስል ነበር።» ብለዋል። በዛም ላይ መምህርና አማካሪያቸው የነበሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ባህል ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ሃሳብ ሰጥተዋቸዋል።
«ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን ለምን ባህል ላይ አታተኩሪም ይሉኝ ነበር። በዛው ሁለተኛ ዲግሪዬን በፎክሎርና ሥነ ጽሑፍ ስይዝ፤ ወደ ፎክሎር ያዘነበልኩት በእርሳቸው ግፊትና ሃሳብ ነው። የኢትዮጵያን አገር በቀል ባህል ልሥራ ብዬ የሃድያ ሴቶችን የቡድን ሥራ መሠረት ያደረገ ቁሳዊ ባህል ጥናት ለሁለተኛ ዲግሪዬ አጠናሁ። ፈልጌ ነበር የሠራሁት፤ ውጤቱም ጥሩ ሆነ» ይላሉ።
የመምህርነቱን ሥራ ትተው ሃሳባቸውን ወደ ባህል ለማድረግ የወሰኑትም ከዚህ በኋላ ነው። ምንም እንኳ ቴክኒክና ሙያ ላይ በርዕሰ መምህርነት የቅጥር ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ወደ ባህል አዘነበሉ። በዛም አዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ጥናትና ምርምር ከፍተኛ ባለሙያ ሆነው ተቀጠሩ።
የመንገድ ገጠመኝ
ጥናታዊ ሥራዎቻቸው ለመመረቂያ ነጥብ ማሟያ ብቻ የሠሯቸው አልነበሩም። ከአገር አገር እንዲንቀሳቀሱና በርካታ ልምዶችን እንዲቀስሙም የረዳቸው እንጂ። በባህልና ቱሪዝም ቢሮ መሥራት ከጀመሩ በኋላም በፌዴራሉ ወይም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በሚመራ የጥናት ቡድን ውስጥ ላቅ ያለ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ያገዛቸው ነበር። በዛም ብዙ ገጠመኞች እንዳሏቸው ያነሳሉ።
ብዙ ጊዜ ግን አገር አቋርጠው ሊያገኟቸው የሚሄዱ ለጥናት ግብዓት የሚሰጡ ሰዎች ቃላቸውን አለመጠበቅና አለመገኘት አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ያወሳሉ። ከዛ ባሻገር ደግሞ በሄዱባቸው አካባቢዎች የመብራት አለመኖር ወይም መጥፋት፤ ወንዝ ሞልቶ ካሰቡት ለመድረስ ቀናትን መጠበቅ በጊዜው የሚያበሳጭ ሲያልፍ ደግሞ ታሪክ ሆኖ የሚወራ ገጠመኝ መሆኑንም ያነሳሉ። «ባለሙያ ሆነን ስንሠራ መንግሥት እየመሰልናቸው የሚተቹንና የሚሰድቡን አሉ። ‘ዝም ብሎ ጥናት ምንድን ነው? ለምን መፍትሄ ሰጥታችሁ አትሠሩም?’ ብለው የሚያወግዙንም አሉ። ይህ በየክልሉ ይገጥማል፤ የወረቀቱ ባለቤት ሳይሆን የችግሩ መንስኤ የሆንን ይመስላቸዋል» ሲሉ ሁሌም የሚገጥማቸውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።
የትውልድ ቅብብል
ወይዘሮ አዳነች ካሳ አሁን በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል እሴቶችና ኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክተር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። በዛም ላይ የእናትነት ወግ አይተው፤ ቤተሰብ መሥርተው ከወላጆቻቸው የተረከቡትን ለልጆቻቸው አስረክበዋል፤ ታታሪነትንና ባህል አክባሪነትን። አሁን የአንዲት ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ እናት ናቸው። ሴት ልጃቸው የህክምና ባለሙያ /ዶክተር/ ስትሆን ወንዱ በአቪዬሽን ቴክኒሽያንነት እየሰራ ይገኛል።
የልጆቻቸውን አባት ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ ነው የተዋወቁት። ያኔ ታድያ ለትዳር ተሳስበው ሳይሆን የአሁኑ ባለቤታቸው ቀድሞ የታሪክ መምህራቸው ነበሩና ነው። ከዛም ዓመታት አልፎ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ተገናኙ። በዛም የገቡበትን ዓላማ ግብ ካደረሱ በኋላ በርካታ ዓመታት የቆየ ትውውቅ ወደ ፍቅር አድጎ በትዳር ተጣመረ። ወይዘሮ አዳነች ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለው ላመኑበት ጉዳይ ቅድሚያ ከመስጠት ወደኋላ የማይሉ ሴት ናቸው። ለዛም ነው፤ ከባለቤታቸው ድጋፍ በላይ የራሳቸው ጥንካሬ ትዳር መሥርተውም ሆነ ልጆች ወልደው ከመማር እንዲቆጠቡ ያላደረጋቸው።
«ከቤቴ አልጎድልም፤ ክፍተት እንዳይፈጠር እሠራለሁ። የሆነ ጉድለት ቢገኘኝ ‘ሴት የለ’ ስለሚባል የቤት ውስጥ ኃላፊነቴን እወጣለሁ። ልጆቼን ከማለባበስ ጀምሮ ትምህርታቸውን መከታተል ድረስ አለሁ። ልጆቼን እያስተማርኩ፤ አብረን እግራችንን ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ዘፍዝፈን እያጠናን ነው የተማርኩት» ይላሉ፤ ቤተሰብንና ትምህርታቸውን እንዲሁም ሥራቸውን አብረው ያስሄዱበትን መንገድ ሲናገሩ።
«በልመና አይሆንም»
የፈለጉትን ትምህርት ተማሩ፤ በፈለጉት ሙያ አገራቸውን ያገለግላሉ፤ ልጆቻቸውን ከጥሩ ደረጃ አድርሰው ከዛም በላይ እርሳቸውን ምሳሌ አድረገው የበረቱ በመሆናቸው ይኮሩባቸዋል። ግን ጉዞው ቀላል ሆኖ አልነበረም። እየተማሩ ቤተሰብ መምራት፤ ቤተሰብ እየመሩ ህልምን ለማሳከት መሄድ ቀላል እንደማይሆን ይናገራሉ።
«የቤተሰብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችም አብረው ፈተና መሆናቸው አይቀርም። የአገራችን እድገት ነገሮችን ያሳጠረ አይደለም። ዛሬ ለሚበላ እንጀራ ከትላንት በስቲያና ከዛ በፊት ነው ዝግጅቱ የሚጀምረው። አኗኗራችን የሚፈቅድ ስላልሆነ ይከብዳል» ይላሉ። ይህም ቢሆን እርሳቸው ግን ተወጥተውት አልፈዋል። ሴት ለራሷ ብቻ ብላ ሳይሆን ለልጆቿ መጠንከር እንዳለባትም አያይዘው ያነሳሉ። በትዳር አስፈላጊነት፤ በማኅበራዊ ኑሮ ጥቅም ላይ አይደራደሩም። እንደውም ያንን ሲያጸኑ እንዲህ ይላሉ፤ «ለመኖር ዋስትናችን ማኅበራዊ ትስስራችን ናቸው። እንደሰለጠነው ዓለም ሊረዳን የሚችል ተቋም የለም። ትዳርን፣ ቤትን፣ አካባቢን ማስቀየም አይቻልም። እስከቻልን ድረስ መሸከም አለብን»
ክብደቱ ከጸና እና ከአቃተ ግን የሚቀነሰውን እየቀነሱ ወደፊት መሄድ፤ ቅድሚያ ለሚያስፈልገው ቅድሚያ መስጠት ይገባል ባይ ናቸው። እናም በልበ ሙሉነት ሴቶች ራሳቸው መጠንከር እንዳለባቸውና በችሎታና በአቅማቸው፤ በችሎታቸው እንጂ በልመና የሚሆን ነገር የለም ይላሉ። እንደ ሴት ተጋፍቶ ማስቀረት የሚያስፈልገው፤ ከተሻሉ ሰዎች መካከል «እርሷ ከምትሆን’ኮ እገሌ ቢሆን» የሚለውን አስተሳሰብ እንደሆነ አስረግጠው ይናገራሉ።
የወይዘሮ አዳነች የስኬት ቁልፍም እዚህ ላይ ነው፤ ሁሉን ተሸክመዋል ከአቅማቸው በላይ ቢሆን እንኳ መቀነስ ያለባቸውን ለመቀነስ ዝግጁ ነበሩ። «ዘመድ ጥየቃ ወይም ቤተሰብ ጋር መሄድ ከሌለብኝ አልሄድም። ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ መስጠት፤ በዛም ላይ ባሉበት መስክ ምስጉንና ተጠሪ መሆን ያስፈልጋል። ሁሉም ቀድመን ልናደርግ ካሰብነው እንዲከተል ማድረግ አለብን» ብለዋል።
ሁለቱ ሙያዎች ሚዛን ላይ
መምህርት ሆነው እንዲሁም በባህል ዘርፍ ባለሙያነት አገልግለዋል፤ ወይዘሮ አዳነች። ከሁለቱ ሙያዎች አብልጠው የሚወዱት የትኛውን እንደሆነ እንዲመርጡ ጠየቅኳቸው። «የማይመረጥ ነገር አታስመርጪኝ» ነበር መልሳቸው። ሁለቱንም ሙያ አብዝተው ይወዳሉ፤ ሙያዎቹንም ያከብራሉ። ሁኔታቸውን ሳይ እንደውም ሁለት ሰው ቢሆኑ ሁሉንም በብቃት የመሥራት ፍላጎት ያላቸው ይመስላል።
ከእርሳቸው አንደበት ቃል በቃል ወስጄ ስለሙያዎቹ ልንገራችሁ፤ «የአገራችን ባህል ሰፊ ነው። ተሠርቶ የሚረካበት አይደለም፤ አያልቅም። የኢትዮጵያ ባህሎችና አገር በቀል እውቀቶች የኢትዮጵያን ሁለመና ተሸክመዋል። ሁሉም ማህበረሰብ የራሱ አካባቢ ትልቅ እውቀትና ባህል አለው። ብችልና ለብቻ የሚሠራ ቢሆን፤ ያንን ብቻ እያጠናሁና እየሠራሁ ብኖር ደስ ይለኝ ነበር።
«ማስተማርም እውዳለሁ። በትምህርት መስክ ደግሞ መምህራኑን ብለው እውቀት ለማግኘት ተማሪዎች ይመጣሉ። መምህሩ ከእነርሱ ብዙ ላይሻል ይችላል! ግን እነዛ የሚገባቸውን ሰጥቶ የሆነ ቦታ ደርሰው ማየት ትልቅ ነገር ነው። ማስተማር የሰው ልጅን መቅረጽ ነው። እንደውም ስርዓተ ትምህርታችን እያንዳንዱ ሰው በተፈጠረበት ባህል እንዲቀዳ የሚያደርግ እንዲሆን እጠይቃለሁ። በጥቅሉ ሁለቱም ትልልቅ ዘርፎች ናቸው። በእርግጥ ባህል ላይ ስሠራም የማስተማር ሥራ ነው የምሠራው። የግንዛቤ ለውጥ ላይ የሚሠሩ በመሆናቸው ሁለቱንም ሙያዎች አከብራለሁ። አበላልጬ መምረጥም አልችልም»
ያሳስበኛል
እንደዜጋ ሁሌ የሞራል ጉዳይ ያሳስበኛል ይላሉ። ትምህርቱም ሆነ የባህል ልማቱ፣ የጥበብ እድገቱ እንዲሁም ሌላው ሁሉ የሞራል ጉዳይ ነው በእርሳቸው እይታ። ይህም በስርዓትና በህግ ሊያዝ የማይችል መሆኑ የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል። የራስን እየናቁና ኋላቀር እያሉ የሌለን ዘመናዊ ማድረግ አያዋጣም፤ የተሠራበትን የማያውቅ ዜጋም በማንነት ቀውስ ውስጥ ገብቶ ጭራሽ ለገዛ አገሩ ጠላት እንደሚሆን ይናገራሉ።
በተለያየ አቅጣጫ ያዩትንና ጥናት በማድረግም በቅርበት የሚያውቁትን የመጤ ባህሎችን አሉታዊ ተጽእኖ አያይዘው በማንሳትም መንቃት የሚፈለግበት ጊዜ ላይ ነን ይላሉ። «የትኛውም ብልጽግና ቢኖረን ዋናው ሰዋዊ ልማት ነው። ሰዋዊ ልማት በትምህርትና ከፍተኛ ውጤት የሚመጣ አይደለም። በትምህርት ሰቃይ የሚባሉ ሰዎች ባልበዙበት ዘመን አገሪቱ ሞራል ነበረባት። አገራችንን የሚረከብ ዜጋን ለማምጣት የሞራል ጉዳይ ለሁሉም መሰረት ስለሆነ ያሳስበኛል» ሲሉም ከሃሳባቸው ያካፍላሉ።
መልዕክታቸውም ከዚህ ጋር ያገናኙታል። «ዘንግተው የቆረጡት ሲፈልጉት ይደርቃል» ይላሉ፤ ሰዎች በተለያየ ፈተና ውስጥ ሊገቡ፤ የተለያየ ጫና ሊኖርባቸውም ይችላል። ውሳኔቸውን በትዕግስት አድረገው አሸናፊ የሚሆኑበትን መንገድም በዛው መቀየስ እንዳለባቸው ያሳስባሉ። ስርቆትና የሰው ሀብትን የሚጸየፍ፤ ሠርቶ ራሱን የሚለውጥና ሞራል ያለው ትውልድ መገንባት ያስፈልጋል። ከብዙ ልምዳቸውና ከሕይወት ተሞክሯቸው ያካፈሉን ይህን ነው። ቀሪ ህልማቸው እንዲሳካ እየተመኘን ተሰናበትን። ሰላም!
ሊድያ ተስፋዬ