
አዲስ አበባ፡– በአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አማካኝነት ከተለያዩ ተቋማትና የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ የጤና ቁጥጥር ፎረም መቋቋሙ የመዲናዋን የጤና እክል መንስኤዎች ለመከላከል አስችሏል ሲሉ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የምግብና ጤና ነክ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ እስጢፋኖስ ጌታቸው አስታወቁ፡፡
አቶ እስጢፋኖስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት መጀመሪያ በማዕከል፣ በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እና በክላስተር “እኔም ለጤናዬ ባለሥልጣን ነኝ” በሚል መሪ ቃል የጤና ቁጥጥር ፎረም ከተመሠረተ በኋላ 6ሺህ 139 አባላትን በማፍራት በርካታ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል፡፡
የፎረሙ አባላት በሚሰጡት ጥቆማ የተለያዩ የተበላሹ፣ ጊዜ ያለፈባቸው የምግብና የመጠጥ ምርቶች እንዲሁም ሕገወጥ መድኃኒቶች ኅብረተሰቡ ዘንድ ደርሰው ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት እንዲሁም የጤና እክል ከመፍጠራቸው በፊት በመወገዳቸው የኅብረተሰቡን ጤና ማስጠበቅ መቻሉን አንስተዋል፡፡
ከኅብረተሰቡ እና ከባለድርሻ አካላት የሚመጡ እውነተኛ ጥቆማዎች መጨመራቸውን፤ አመልክተው፤ በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ ስለጤናው ግንዛቤ እየተፈጠረ በመሆኑ ለፀሐይ የተጋለጡ ምግብና መጠጦች ሲወገዱ ተባባሪ በመሆን ክንውኑ እንዲሳለጥ አስችሏል ብለዋል፡፡
የፎረሙ አባላት ባደረጉት እንቅስቃሴ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በአብዛኛው እንዲፈቱ እያደረጉ ስለመሆናቸውም አንስተዋል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች በአጥፊዎች ላይ በተወሰዱ የተለያዩ የእርምት ርምጃዎች የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደተቻለም ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማን ከትንባሆ ጭስ ነፃ የማድረግ የቁጥጥር ኢኒሼቲቭ ላይ የፎረሙ አባላት ባደረጉት ከፍተኛ ተሳትፎ የትምባሆ ቁጥጥር ኢኒሼቲቭ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት መቻሉን ዳይሬክተሩ ገልጸው፤ በዚህም ሙሉ በሙሉ ከትምባሆ ነፃ የሆኑ ትምህርት ቤቶች፣ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች፣ የወጣት ማዕከላት፣ የሕዝብ መዝናኛዎችና ሕዝብ በጋራ የሚጠቀምባቸው አደባባዮች ቁጥራቸው መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ ከትምባሆ ጭስ ነፃ በመሆን ሞዴል የሆኑ የንግድ ተቋማትን በመለየት እውቅና የመስጠትና የማበረታታት ሥራ ስለመሠራቱም ገልጸዋል፡፡
የጤና ቁጥጥሩ ፎረሙ በየአደረጃጀቱ በቀጣይ አራት ወራት አመርቂ ሥራዎችን ለማከናወን የተለያዩ ዋና ዋና የጤና ቁጥጥር ተግባራትን አቅጣጫ አስቀምጦ የሚንቀሳቀስ መሆኑን አቶ እስጢፋኖስ ገልጸው፤ የከተማዋ ነዋሪዎችም ለፎረሙ እንቅስቃሴ ተባባሪ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡
በስሜነህ ደስታ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም