በፍቅር አጋሩ መጠጥ የጽንስ ማቋረጫ እንክብል ‘የጨመረው’ አሜሪካዊ በግድያ ወንጀል ተከሰሰ

የፍቅር አጋሩ ሳታውቅ መጠጧ ላይ የጽንስ ማቋረጫ እንክብል ጨምሯል የተባለው አሜሪካዊ በግድያ ወንጀል ተከሰሰ። ጀስቲን አንቶኒ ባንታ የተባለው ግለሰብ ለቀድሞ ፍቅረኛው ፕላን ሲ የተባለውን የጽንስ ማቋረጫ መድኃኒት ሳታውቅ እንደሰጣት ግለሰቧ መክሰሷን ተከትሎ ነው ባለፈው ሳምንት አርብ በቁጥጥር ስር የዋለው። በግለሰቡ ላይ ለወራት የዘለቀ ምርመራ መደረጉን የቴክሳስ ግዛት ፖሊስ ገልጿል።

ግለሰቧ ስለ ማርገዟ ስትገልጽለት ጽንሱን እንድታቋርጠው እና ወጪውን ለመሸፈን ፈቃደኛ መሆኑን የተናገረ ሲሆን፤ እሷ በበኩሏ ልጁን መውለድ እንደምትፈልግ ነግራዋለች። በአንዲት ዕለትም በአንድ ካፌ ውስጥ ከተገናኙ በኋላ ከፍተኛ ደም መፍሰስ አጋጥሟት ወደ ድንገተኛ ሕክምና እንደተወሰደች እና ከጥቂት ቀናት በኋላ ልጇን ማጣቷን ፖሊስ ገልጿል። ጀስቲን ማስረጃዎችን በማበላሸት ጭምር ክስ እንደተመሠረተበት የፓርከር ካውንቲ የፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ፖሊስ እንዳስታወቀው፤ ግለሰቧ ለሕክምና በሄደችበት ወቅት የስድስት ሳምንት ነፍሰ ጡር መሆኗን እና ሕጻኑ ጤናማ እንደሆነ ጠንካራ የልብ ምት እንዳለው ተነግሯት ነበር ብሏል። “በእዚያችው ዕለት ተጎጂዋ ሪፖርት  እንዳደረገችው ጀስቲን ጋር በአንድ ካፌ ውስጥ መገናኘታቸውን ነው። እናም እሷ ሳታውቅ ወይም ሳትፈቅድ የጽንስ ማቋረጫ እንክብል መጠጧ ላይ እንደጨመረባት ጥርጣሬ እንደገባት ተናግራለች“ ሲል ፖሊስ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

በተጨማሪም ማርገዟን በምትገልጽለት ወቅት የፕላን ሲ ጽንስ ማቋረጫ እንክብል በኦንላይን እንዲገዙ ሃሳብ አቅርቧል ተብሏል። ፖሊስ ጀስቲንን ካናገረው በኋላ ስልኩን ወስዶ ባደረገው ምርመራ “ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ መረጃዎች” እንዲጠፉ መደረጋቸውን ተመልክቷል። በአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የአይቲ ባለሙያ የሆነው ተከሳሹ ስልኩን በርቀት ሆኖ በመቆጣጠር መረጃዎችን በሙሉ በማጥፋት ስልኩ ባዶ እንዲሆን ማድረጉን መርማሪዎች ያምናሉ።

ግለሰቡ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል እንዲሁም መረጃዎችን በማድበስበስ ወንጀል ክስ ባለፈው ሳምንት ተመስርቶበታል። ቴክሳስ በከባድ የጤና ሁኔታ ምክንያት ካልሆነ ጽንስ ማቋረጥ የሚከለክል ገዳቢ ሕጎችን ደንግጋለች። ግዛቲቷ በአውሮፓውያኑ 2022 ጽንስ ለሚያቋርጡ ግለሰቦች የፍትሐ ብሔር እና የወንጀል ቅጣቶችን የሚያስከትል ሕግ አጽድቃለች። ከእዚያ በፊት የነበረው ሕግ የጽንሱ የልብ ምት ከተሰማ በኋላ ጽንሱን ማቋረጥ የሚከለክል ቢሆንም ነገር ግን ለድንገተኛ ሁኔታዎች ፍቃድ ይሰጥ እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You