
እድሜ ትምህርት ቤት ነው። ዕድሜ ክፉና ደጉን ያሳውቃል፤ ከራስም አልፎ ለሌሎች መድህን ይሆናል። አዎ እድሜ የሰጣቸው ሰዎች ባለፉበት መንገድ፤ በወጡበት አቀበት እና በወረዱበት ቁልቁለት ልክ በርካታ ተሞክሮዎችን ይቀስማሉ፤የህይወትን ውጣ ውረድ ይገነዘባሉ።
እድሜ ጠገብ ሰዎች ከሕይወት በርካታ ቁምነገሮችን ስለሚማሩ ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች መካሪ እና ዘካሪ ይሆናሉ። የእነሱን ሕይወት አብዛኛውን ክፍል ስለኖሩ ሃሳባቸው እና ጭንቀታቸው በመጪው ትውድል እና በሀገሪቱ መጻኢ እድል ላይ ይሆናል። የወጣቱ ጉዳይ ያሳስባቸዋል፤የሀገሪቱ የሰላም እና የእድገት ጉዳይ እንቅልፍ ይነሳቸዋል። ከነሱ አለመመቸት የበለጠ የዜጎች ጉስቁልና እና መከራ ያሳስባቸዋል።
ስለዚህም ሀገር ሰላም እንድትሆን፤ በልማት እና በእድገት እንድትራመድ አብዝተው ይመኛሉ፤ ከልምዳቸው ያማክራሉ ፤በተቻላቸው መጠንም ይጸልያሉ፤ ለሀገራቸው በጎበጎውን ይመኛሉ። ቀሪውም ትውልድ እነዚህ የእድሜ ባለሃብቶች ረጅም ዘመን እንዲኖሩ ይመኛል፤ መኖራቸውን እንደ ጸጋ እና በረከት ይቆጥረዋል።
ሆኖም ሁሉም ሰው አንድ አይደለም እና ከስንዴ ማሳ ውስጥ አረም እና እንክርዳድ እንደማይጠፋው ሁሉ በእድሜያቸው ልክ የማይከበሩ፤ እድሜያቸውን ለምክር ሳይሆን ለጥፋት የሚያውሉ የእንጨት ሽበቶች እዚህም እዚያም አሉ። እነዚህ ሰዎች ከመቃብር አፋፍ ሆነው ጥላቻ እና ክፋትን የሚመክሩ ፤ከማስታረቅ ይልቅ ማጣላትን ስራዬ ብለው የያዙ፤ ከአብሮነት ይልቅ መለያየትን የሚሰብኩ ቁጥር ብቻ የሆኑ ሰዎች በዙሪያችን ይገኛሉ።
እነዚህ ጉዶች የወጣቱ ሕይወት አያሳስባቸውም፤ የሀገሪቱ እጣ ፋንታ አያስጨንቃቸውም። አፍላ ወጣቶች በጦርነት እና በግጭት ቢያልቁ ደንታ አይሰጣቸውም፤ የሀገር ገጽታ መበላሸትም አያሳስባቸውም። የእነሱ ዋነኛ ጭንቀት እና ትኩረት ልትበጠስ አንድ ሐሙስ የቀረችውን ሕይወታቸውን በሀጢያት ማስደሰት ነው። ወደ መቃብር የቀረበች ሕይወታቸውን ወደ ፈጣሪ በመመለስ ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ በቀረችው እንጥፍጣፊ ሰዓት ሀጢያት እቅፎ መሞትን ይመርጣሉ።
ከመቃብር አፋፍ ላይ የሚገኙት እነዚህ የእንጨት ሽበቶች ዛሬም በትላንቱ የሚኖሩ እና ሸፍጠኝነት፣ ሴረኝነት፣ ቂመኝነት፣ ጉልበተኝነትና ወገንተኝነትን ለወጣቱ ትውልድ መስበክ የሚዳዳቸው ናቸው። ሰሞኑንም በሰላም ስም ተሰባስበናል ከሚሉ ቡድኖች መካከል ላለፉት 50 አመታት እና ከዚያ በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ መከራ እና ስቃይ እንዲበረታ ሳይታክቱ የሠሩ ሰዎች ጭምር የሰላም አምባሳደር ሆነው መታየታቸው ለብዙዎቻችን ግርምትን ፈጥሯል። በተለይም እነዚህ የእንጨት ሽበቶች በፖለቲካ ስም ፖለቲከኞች ሆነው ላለፉት 50 አመታት ኢትዮጵያ የመከራ ግዜ እንድታሳልፍ ዋና ገጸ ባህሪ ተላብሰው ሲጫወቱ ኖረዋል። ዛሬም ይህ ትወና እንዲቀጥል ሲውተረተሩ አይተናል።
እነዚህ ፖለቲከኞች አዝጎች ናቸው። ከጊዜ ጋር የማይለወጡ፤ከወቅቱ ጋር የማይዘምኑ ችኮ ፖለቲከኞች በየስርቻው አሉ። ትላንት ብቻ እያላዘኑ ዛሬን መሻሻል የማይፈልጉ የትላንት እስረኞች የፖለቲካችን ጥቁር ቀለሞች ናቸው። ትላንት የሚዘምሩትን መዝሙር የዛሬውም ወጣት ሳያላምጥ እንዲውጥላቸው ይሻሉ፤ባስ ሲልም ዘመኑን ያልዋጀ የፖለቲካ ዕሳቤ ለመጋት ይሞክራሉ።
ለዘመናት ሲጨቁኑት እና ሲበዘብዙት ከኖሩትን ሕዝብ በኃይል ሲወገዱ ያለምንም እፍረት አይናቸውን በጨው አጥበው ለሕዝቡ ጠበቃ ነን ሲሉ ይደመጣሉ። አዳማጭ ጆሮ ካገኙም ያለፍንበትን የጨለማ ሕይወት ገነት አድርገው ለመሳል ይሞክራሉ። የእነሱ መንገድ የጻድቅ የሌላው ደግሞ የሰይጣን እንደሆነ በመለፈፍ ጥላቻን፤መጠፋፋትን፤መገፋፋትን ፤መወቃቀስን፤መወነጃጀልን በየሶሻልሚዲያው እና በየመድረኩ ሲሰብኩና ሲጠምቁ ይውላሉ።
ከአፋቸው እንኳን አንዲት በጎ ቃል ጠብ ሲል አይደመጥም። ችግሮች እንዲቃለሉ እና ሕዝቡ በሰላም እንዲኖር ከመሥራት ይልቅ ችግሮቹ ይበልጥ ጥልቀት እንዲኖራቸውና ስር እንዲሰዱ ያለመታከት ሲሠሩ ይታያሉ።
ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ያሉባት ሀገር ነች። ሥራ አጥነት፤የኑሮውድነት፤የባለሙያዎች ደመወዝ ዝቅተኛ መሆን፤አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ወዘተ እያሉ መደርደር ይቻላል። ሆኖም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ባለበት በዚህ ወቅት አንዳንድ ፖለቲከኞች ችግሮችን ከልክ በላይ በመለጠጥ ሕዝቡ ብሶት ውስጥ እንዲገባ ሲቆሰቁሱት ይታያሉ። ከላይ ያነሳናሳቸው ችግሮች ለዘመናት ያህል ሲንከባለሉ የመጡ እና ችግሮቹንም ለመቅረፍ ግዜ እንደሚያስፈልግ እየታወቀ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል በአንድ ጀንበር እንዲፈቱ ግፊት ሲደረግ ይታያል።
ሆኖም እነሱ ላለፉት 27 ዓመታት ያላሳኩትን ይልቁንም ወደ ባሰ ውስብስብ ድህነት የከተቱትን ሕዝብ በአንድ ጀንበር መፈወስ አለበት የሚል በመርዝ የተለወሰ መልዕክት በየማህባራዊ ሚዲያው ሲለፍፉ ይታያሉ። እነሱ ሥልጣን ላይ በነበሩባቸው በርካታ ዓመታት መፍታት ያልቻሏቸውን ችግሮች ዛሬ እንደምን በአንድ ጀንበር ችግሮቹን መቅረፍ ይቻላል?
ዛሬ ያሉት ችግሮች ላላፉት 27 ዓመታት ሆን ተብለው ኢትዮጵያን ለማዳከም በተሠሩ ሴራዎች የተፈጠሩ ችግሮች መሆናቸውን እናውቃለን። ኢትዮጵያ በመከፋፈል እና በልዩነት ውስጥ እንድትከርም በማድረግ በሂደትም ተዳክማ እንድትፈርስ በተሠራው ሴራ በርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ገብታለች። የብሄር ግጭት፤የኢኮኖሚ ቀውስ፤የኑሮ ውድነት፤የእዳ ጫና፤የፕሮጀክቶች መጓተት ወዘተ ጠርተን የማናቃቸው ችግሮች የተፈጠሩት እኮ ዛሬ መካሪ ሆነው በመጡት እድሜ ጠገብ ሰዎች አማካኝነት ነው። እነዚህ ሰዎች በእዚህ የእድሜ ማብቂያ ዘመናቸው ሃጢያታቸውን ተናዘው ፤እውነታውን ተናግረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ ሲገባቸው የትላንቱን መከራ ለመድገም መካሪ ሆነው ሲመጡ ከማየት የበለጠ የሚያበሳጭ ነገር የለም።
ሆኖም እድሜ ላላስተማራቸው ለእነዚህ የእንጨት ሽበቶች አንድ መልዕክት ማስተላለፍ እወዳለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ በዚህ ትውልድ አዲስ የለውጥ ፋና ተለኩሷል። አዲስ የሁለንተናዊ ብልፅግና ምዕራፍ ተከፍቷል። ይህ የለውጥ ምዕራፍ የተወሰኑ ግለሰቦች፣ የጥቂት ቡድኖች ወይም የሆነ አካባቢ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ምዕራፍ ነው።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የጎደለውን እየሞላን፤ ያነሰውን እየጨመርን፣ ያልተስማማንበትን እያቆየን፣ በተስማማንበት እየሠራን፤ በልዩነቶች ላይ ቆመን ሳንጋጭ፤ በተግባባንበት አብረን እየተጓዝን፤ ያልተግባባንበት ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ ሲኖር ምልዐተ ሕዝቡ በነፃነት ተወያይቶ እንዲወስንበትና የሕዝብን ድምጽ እያከበርን በመሄድ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ከማስረከብ ውጪ እንደቀድሞው የኋልዮሽ መጓዝ አይቻልም።
ያደጉ የምንላቸው ሀገራት ዛሬ ላይ የደረሱት ልዩነቶች ስለሌሏቸው አይደለም። ልዩነቶቻቸውን በማቻቻል፤ ልዩነቶቻቸውን ከግጭት በመለስ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ስለቻሉ ነው። ልዩነትም አንድነትም ተፈጥሯዊ ነው። የሰው ልጅ የመልክ፣ የእምነት፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የመኖሪያ አካባቢ፣ የአስተሳሰብ ልዩነት አለው። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የሚያደርጉት የሰውነት ጉዳዮችም አሉ። ወሳኙ ነገር ልዩነትን እንደ ጌጥ አንድነትን እንደ ማስተሳሰሪያ ኃይልና አቅም መጠቀሙ ነው።
አንጋፋ ነን የሚሉት ፖለቲከኞቻችን ትናንትን ለፖለቲካ ፍጆታቸው ሲያውሉት ይታያሉ፡፡ ሆኖም አሁን ባለው ትውልድ ዕሳቤ ትናንት ለነገ ዕንቅፋት መሆን የለበትም። ትምህርት እንጂ፣የትናንት ታሪክ የአብሮነት መገንቢያ እንጂ የልዩነት መነሻ እንዳይሆን መሥራት አለብን። እየተደማመጥን፤ እየተመካከርን፤ ለሃሳብና ለውይይት በራችንን ክፍት እያደረግን እንጓዝ። ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን እናጠንክር፤ ለሀገራችን መፃኢ ዘመን በጋራ እንትጋ። ከትናንት ይልቅ ጉልበታችንንና ጊዜያችንን በነገ ላይ እናውል። ይህ ነው የዚህ ትውልድ ትልቁ የቤት ሥራ።
ቀደምት ፖለቲከኞች ልዩነት ጌጥ ነው የሚለውን አባባል አያምኑበትም። ልዩነት በእኛ የተጀመረ ይመስል ከግዙፍ አንድነታችን ይልቅ ጥቃቅን ልዩነቶቻችን ላይ በማተኮር ለግጭትና አለመረጋጋት ሲዳርጉን ኖረዋል። ልዩነታችንንም ደርዝ ለመስጠት ዛሬን ትተው ትናንት ላይ ይቆዝማሉ። በምንቀይረው ዛሬና ነገ ላይ ማተኮር ትተው በማንቀይረው ትናንት ላይ ጊዜ ይፈጃሉ።
የኢትዮጵያን ትናንት ስንመለከተው ደግሞ የፖለቲካ ቁርሾ የበዛበት፤በረባ ባልረባው ሰዎች የሚጠፋፉበት፤ከንግግርና ውይይት ይልቅ ነፍጥ ማንሳት የሚመረጥበት፤ ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› በሚል ኋላቀርና በታኝ ትርክት ሀገር ስትማቅቅ የኖረችበት ነው። ይህ መጥፎ አካሄድ ደግሞ ዛሬን ጭምር ተጭኖት ይገኛል። የዛሬ ግጭትና አለመግባባት ብሎም ጥርጣሬና አለመተማመን ትናንት የተፈጠረ ነው። በአጠቃላይ የሀገራችን ፖለቲካ ጥንስሱ የተጀመረው ትላንትና ነው ማለት ይቻላል። ይህ ደግሞ ዛሬ መካሪ እና ዘካሪ ነን ብለው ብቅ ባሉት ዕድሜ የተጫናቸው ፖለቲከኞቻችን ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጥያቄ በይፋ ለውይይት ከቀረበ ሃምሳ ዓመታት ቢሞላውም ዛሬም የብሄር ጥያቄ ፋሽን ሆኖ ሁሉም ‹‹ብሄሬ ተነካ ››በሚል ፈሊጥ ነፍጥ ሲያነሳ ይታያል። የብሄር ጥያቄ መነሳት ከጀመረ ጀምሮ ሁነኛ መፍትሄ ሳያሠጥ በመቆየቱ አንዳንድ ጊዜም ከሀገሪቱ አቅም በላይ የሆኑ ጥያቄዎችን በብሄር ሽፋን በመጠየቅ ብጥብጥና ሁከት የሚጠምቁ ፖለቲከኛ ነን ባዮች በሚያስነሱት ወጀብ በኢትዮጵያ ምድር መከራ ወርዷል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አልቀዋል።
ኢትዮጵያን ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ሀገር ለማድረግ በጋራ መሥራት እየተቻለ፣ መለስተኛ ቅራኔዎችን ከመጠን በላይ በመለጠጥ በጠላትነት መተያየት ቀጥሏል። በኢትዮጵያ ምድር ኅብረ ብሔራዊ ሥርዓት መገንባት እየተቻለ፣ ዛሬም ብሄርንና ኢትዮጵያዊነትን ጽንፍ ለጽንፍ በመጎተት አሰልቺ ንትርክ ውስጥ እንገኛለን። ይህ መጓተት እንዲቀጥልም እነዚህ እድሜ ያልመከራቸው ፖለቲከኞቻችን ደባ ዛሬም ድረስ መቋጫ አላገኘም።
ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት ሀገር ናት። የሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ በሰጡበት በዚህ ወቅት የአዛውንቶችን ተረት ተረት ለማዳመጥ ጊዜው አይፈቅድም። ወቅቱ እንደቀድሞው በእንቶፈንቶ የሚታለፍበት ሳይሆን ነባር ችግሮችን ከስራቸው መንግሎ ለመጣል የሞት ሽረት ትግል የሚደረግበት ነው።
በአሁኑ ጊዜ የኑሮ ውድነቱ ፈተና ነው። የሥራ አጥነት ችግርም ጊዜ የሚሰጥ አይደለም። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይከፈል የቆየና እየተንከባለለ የመጣ የውጭ የዕዳ ጫና አለ። ጥራት ያለው የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ብዙ ጥረትን ይጠይቃል። በገጠርም ሆነ በከተማ የሚኖሩ በርካታ ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ።
ስለዚህም እነዚህን ተጨባጭ ችግሮች ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በትላንት ታሪክ ውስጥ ተዘፍቆ በችግር አዙሪት ውስጥ መኖርን የሚመርጥ ትውልድ የለም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋስትና ያለው ሰላምና ልማት ያስፈልገዋል። ለዚህም ሲባል ሁሉን አካታች የሆነ ሰላማዊ ንግግርና ድርድር ለማድረግ ሀገር አቀፍ ምክክር ለማድረግ ጥረት በመደረግ ላይ ነው። ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ ችግሮቻችንን በማስወገድ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ዕድል ይሰጠናል። በተለይም ትናንት ላይ ተቸንክረው ፖለቲካን በሴራ እና በተንኮል እየጠነሰሱ መኖር ለሚሹ ወገኞች አካሄዱ ላይዋጥላቸው ይችላል። ሆኖም ሀገር ወዳድ ለሆንን ዜጎች ግን ከምክክርና ውይይት ውጪ አማራጭ የለንም።
ስለዚህም እድሜ ጠገቦቹ ፖለቲከኞቻችን ዘመኑን ሊዋጁ ይገባል። በትላንት በሬ ያረሰ የለም እና ከዛሬ ጋር እራሳቸውን ሊያስታርቁ ይገባል። ዛሬም እንደ 60ዎቹ ሀገርን በሸፍጥ፣ በሴራ፣ በቂም እና በቡድንተኝነት መምራት አይቻልም። ይህንን ሀቅ ፖለቲከኞቻችን እድሜያቸው ሊመክራቸው ይገባል። ስለዚህም እንጨትም ሽበት ያወጣል እና የሰጣቸውን እድሜ ትውልድን ለመምከር እና ለማነጽ ሊያውሉት ይገባል።
በአሊሴሮ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም