
የክረምት ወቅት እየገባ ነው። በተቃራኒው ወቅቱ ከሀገራችን ሁኔታ በተለየ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ቅዝቃዜ እየቀነሰና ሞቃታማ እየሆነ የሚመጣበት ነው። በኢትዮጵያ ይህ ቀዝቃዛና እርጥበታማ ወራት ወሳኝ ሀገራዊ እንቅስቃሴን የሚካሄድበት ነው። በተለይ በግብርናው ላይ የክረምት ወር በኢትዮጵያ ወሳኝ ወቅት ነው። ሌላው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክረምት ጊዜ በስፋት እየተካሄደ የሚገኘው የዛፍ ችግኝ መትከል ነው። የክረምት ወራት በመጣ ቁጥር መንግሥት ሃብትን በማሰባሰብ፣ ማኅበረሰቡን በማነቃነቅ ችግኞች ይተከላሉ።
ዓለማችን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በርካታ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጠች ነው። በተለይ የአየር ንብረት ለውጥና የሙቀት መጨመር ምድራችንን በእጅጉ እየፈተናት ይገኛል። ይህንን አደጋ የሰው ልጆች መጋፈጥ ይኖርባቸዋል። በሀገራችን እያንዳንዱ ዜጋ በጋራ አካባቢውን መጠበቅ ይኖርበታል። ደኖች እንዳይመነጠሩ፣ ቸግኞች እንዲተከሉ መተባበር ይኖርበታል።
በሀገራችን ከቅርብ ግዜ ወዲህ የዛፍ ችግኞችን በመትከል አስደናቂ ለውጥ እየታየ ነው። ከኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴ ጀርባ ያለው አጣዳፊነት ትርጉም ሊገባን ይገባል። ዓለማችንን በአስፈሪ ፍጥነት የአየር ንብረት ለውጥ እያስተናገደች ትገኛለች። የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እና ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ችግኞችን በመትከል፣ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል እና ወደ ኦዞን ንጣፍ የምንልካቸውን በካይ ጋዞች በመቀነስ፣ ወንዞችን በመንከባከብ ችግሩን ለመቀነስ ካልሠራን የተለያዩ ጉዳቶችን እናስተናግዳለን። በመሆኑም መንግሥት የክረምት ወርን ተገን በማድረግ በሀገራችን የደን ሽፋንን የሚጨምሩ የችግኝ ተከላ ንቅናቄዎችን በሚያካሂድበት ወቅት በፍፁም ተነሳሽነት ተሳትፎ ልናደርግ ይገባል። ለመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን ላይ የደቀናቸው ስጋቶች ምንድን ናቸው? ዓለም አቀፍ ጥናቶችና ሪፖርቶች ምን ይላሉ? መፍትሄዎቹስ ምንድን ናቸው? በቀጣዮቹ ሀሳቦቼ ላይ ጥቂት ለማለት እወዳለሁ።
ሙቀት መጨመር
የዓለም ሙቀት እየጨመረ በመምጣቱ ከዓመት ዓመት ሪከርዶችን እየሰባበረ ይገኛል። በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች በከፍተኛ ሙቀት የተነሳ ሕይወታቸውን እያጡ የሚገኙ በርካታ ሰዎችም ተመዝግበዋል። በቅርብ ጊዜ የወጡ የአየር ንብረት ለውጥ ፓናል ግምገማ ሪፖርቶች እነዚህን አዝማሚያዎች የሚያሳዩ ናቸው። በዓለማችን ላይ ከሚመዘገቡ የሰው ልጆች ሞት ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥና ሙቀት መጨመር አንዱ ነው። የግብርና ምርቶች መቀነስ፣ የተፈጥሮ (የሰደድ እሳት) ጨምሮ በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል።
የአየር ንብረት ለውጥ የተፈጥሮ አደጋዎችን ያባብሳል። ለምሳሌ ሞቃታማ የሆኑ ውቅያኖሶች ኃይለኛ አውሎ ነፋሶችን ይፈጥራሉ። ይህም አስከፊ የሰደድ እሳትን ጨምሮ ሱናሚን የመሰሉ የባኅር ላይ ወጀቦች መፈጠር ምክንያት ይሆናሉ። በሌላ መልኩ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ አስከፊ ጎርፍ እና ሌሎች የአጭርና የረጅም ግዜ ጉዳቶችን ያስከትላል። በሀገራችን የሰደድ እሳት፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ ድርቅና ሌሎች መሰል የተፈጥሮ አደጋዎችን በተለያዩ ግዜዎች ማስተናገዷን አንደ ማስረጃ ልናየው እንችላለን።
ሌላው የአየር ንብረት ለውጥን በግዜ መከላከል ካልተቻለ የበረዶ ግግር መቅለጥ ከባሕር ሙቀት መጨመር ጋር ተዳምሮ የባሕር ከፍታ እንዲጨምር ያደርጋል። የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የዓለማችን ውቂያኖሶች ከፍታ ከአንድ ሜትር በላይ እየጨመረ ነው። በተመሳሳይ በዚህ ተግዳሮት ምክንያት የብዝሃ ሕይወት መመናመን እየደረሰ ነው። የኢትዮጵያን መልከዓ ምድር ጨምሮ በዓለማችን ላይ የሚገኙ የተለያዩ ሥነ-ምህዳሮች እየተፈቱ ነው። ብዙ ብርቅዬ ዝርያዎች ሊላመዱት ከሚችለው በላይ መኖሪያዎቻቸው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየተቀያየሩ ወይም እየጠፉ ናቸው። የብዝሀ ሕይወት እና ሥነ-ምህዳር አገልግሎቶች ኢንተርናሽናል ፓናል ዓለምአቀፍ ግምገማ ሪፖርት እንደሚያሳየው ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ዋናው ምክንያት ደግሞ የመኖሪያ አካባቢ መጥፋት (ብዙውን ጊዜ የደን መጨፍጨፍ) እና የአየር ንብረት ለውጥ ናቸው። ይህ ኪሳራ ንጹህ አየር፣ ውሃ፣ በሽታን መቆጣጠር የሚያስችል የተፈጥሮ አቅም የሚሰጡንን ሥርዓቶች እያዳከሙብን ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ ከምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ጋር በቀጥታ ይገናኛል። ድርቅ ያጠቃቸው ሰብሎች፣ ምርትን የሚያበላሽ ያልተጠበቀ ዝናብ እና ከፍተኛ ሙቀት የሚያስተጓጉለው የእንስሳት እርባታ ለዚህ ምክንያት መሆን ይችላሉ። የአየር ሙቀት መጨመር የውሃ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ የጮቄ ተራራን የመሰሉ ወንዞችን የሚመግቡ ወሳኝ የተራራ ምንጮች ይሟጠጣሉ። በምግብ እና በውሃ ላይ ያተኮሩ ጥናቶች የአየር ንብረት ለውጥ ረሃብን ከማምጣቱም ባሻገር በውስን ሀብቶች ላይ የተጠቃሚነት ግጭቶችን እያባባሰ ነው። ለምሳሌ የግብፅ በርሀ መሆንና በአካባቢ ጥበቃ ላይ በቂ ሥራ አለመሥራት በኢትዮጵያ ወንዝ ላይ ጥገኛ እንድትሆንና ፖለቲካዊ ንትርክ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።
ከላይ በምሳሌነት ያነሳሁትን በኢትዮጵያም ሆነ በዓለማችን ላይ የተደቀነውን ተግዳሮት ለመቋቋም የአየር ንብረትን ለውጥ መከላከል ይገባል። ለዚህ ደግሞ ችግኞችን መትከል እና መንከባከብ ይኖርብናል። ኢትዮጵያ ለደን ሽፋኗን እና ለተፈጥሮ ሀብቷ ልዩ ትኩረት ሰጥታለች። ችግኞችን መትከል እና ደኖቸን ከምንጣሮ መከላከል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት።
ዛፎች በተፈጥሮ በጣም ቀልጣፋ የካርቦንዳይ ኦክሳይድ (CO2) ቫክዩም ማጽጃዎች ናቸው። በፎቶሲንተሲስ አማካኝነት ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን (CO2) ይወስዳሉ። የተተከለው ዛፍ ሁሉ የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመዋጋት የተመዘገበ ወታደር ልንለው አንችላለን። ዛፎች የአፈር መሸርሸርን የሚከላከሉ ጠባቂዎች ናቸው። የዛፍ ሥሮች አፈርን እንደ ጠንካራ መረብ ያስራሉ። በተለይ በኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች ላይ ዛፎች በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው። ዛፎች ከሌሉ ከባድ ዝናብና ጎርፍ ውድ የሆነውን የአፈር ያጥባል። የአፈር መሸርሸር ደግሞ ወንዞችን ይዘጋሉ፤ ግድቦችን ጨምሮ መሠረተ ልማቶችን ይጎዳሉ፤ የተራቆቱ መልክዓ ምድሮችን ይፈጥራሉ። ይህንን ለመከላከል ዛፎች እንደ መልሕቅ ሆነው መሥራት ይችላሉ።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ቁርጠኝነት
ሀገራችን ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ቀውስ ጀርባ እና የዛፎችን ኃይል በመገንዘብ አመርቂ የመከላከል እርምጃ እየወሰዱ ካሉ ሀገራት ተርታ ትመደባለች። መንግሥት ለደን ልማት ያለው ቁርጠኝነት በእውነት የሚደነቅ እና ይበል የሚያሰኝ ነው። እ.ኤ.አ በ2019 የጀመረው የአረንጓዴው ሌጋሲ ኢኒሼቲቭ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው።
የተመዘገቡ ስኬቶቹም አስደናቂ ናቸው። በጥቂት ዓመታት ውስጥ በመላ ሀገሪቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለዋል። የተቀመጡ ግቦችን ማሟላት ብቻ ሳይሆን ከዚያም ያለፉ ሰኬቶች ተመዝግበዋል። በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎች የሀገራችን የመሬት ሆድቃ ሥር እየሰደዱ እያደጉ ነው። በያዝነው የክረምት ወቅትም ተመሳሳይ ሥራዎች እንደሚሠሩ ይጠበቃል። በአረንጓዴ ዘመቻው የመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የክልል ባለስልጣናት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ወታደር፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ማኅበረሰቦች በድጋሚ ተሳታፊ ለመሆን እየሠሩ መሆኑን ያገኘሁት መረጃ ያመለክታል። የሚተከሉት ችግኞች ከየአካባቢው ሁኔታ ጋር ተስማሚ የሆኑ የሀገር በቀል ዝርያዎች ለመትከል ቦታዎች እየተዘጋጁ ነው።
ይህ ንቅናቄ ችግኞችን ከመትከል በላይ ለሀገራዊ ደኅንነት እና ለዘላቂ ልማት መሠረት መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያ በፀረ የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፋዊ ትግል ላይ ያላትን የነቃ አቋም እያሳየች ነው። ለመጪው ትውልድ ጤናማ እና ጠንካራ ሀገር ለመተው ዜጎች ቁርጠኝነታቸውን እያሳዩ ነው። ለዚህ ትልቅ ተግባር ቅድሚያ በመስጠት፣ የችግኝ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ ሕብረተሰቡን በማስተባበር መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት እየወሰደ ይገኛል። ይህ እርምጃ የአካባቢ መራቆት (የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል) ለሚታገሉ ሌሎች ሀገራት አንፀባራቂ ምሳሌ ነው።
ከመትከል ባሻገር
በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዛፎችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየተተከሉ ይገኛሉ። ይህ በእጅጉ የሚያኮራ ጀግንነት ነው። ሆኖም ችግሩን ለመቅረፍ የተወሰደ የመጀመሪያ እርምጃ እንጂ የመጨረሻ መፍትሄ አይደለም። ዛፍ መትከል የመጀመሪያ የተስፋ እርምጃ ነው፤ ተንከባክቦ እስከ ጉልምስና (እድገቱን አረጋግጦ) ለቁምነገር ማብቃት ደግሞ የመጨረሻው ገብ ነው። ችግኞች ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው። በድርቅ፣ በእንስሳት፣ በተባይ፣ በበሽታ እና በሰዎች ግድየለሽነት ወይም ሆን ተብሎ በሚደርስ ጉዳት በቀላሉ ሊጠፉ ይችላሉ። ተክሎ ዞር ማለት ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማሳደግ ይገባል። መንከባከብ ካልቻልን ግን ሀብትን፣ ጉልበትንና ተስፋን ማባከን ነው የሚሆነው።
የዛፍ ችግኞች በተለይም በወሳኝ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት እና በደረቅ ወቅቶች ለማደግ ውሃ ያስፈልጋቸዋል። ችግኞችን ከከብት እና የዱር እንስሳት በአጥር ወይም በዛፍ ጠባቂዎች መጠበቅ እና ከእሳት እና ከሕገ ወጥ ድርጊት መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ይህንን ኃላፊነት መንግሥት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ መውሰድ አለበት።
የአየር ንብረት መከላከል እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በኢትዮጵያውያን በሁሉም ማኅበረሰብ ውስጥ ዘልቆ መግባት ያለበት ወሳኝ ግንዛቤ ነው። የአካባቢ ጥበቃ የመንግሥት ሥራ ብቻ አይደለም። የእያንዳንዱ ግለሰብ ተግባርና ኃላፊነት ነው። የምንተነፍሰው አየር፣ የምንጠጣው ውሃ፣ ምግባችንን የሚያበቅል አፈር እና ሕይወታችንን የሚቀርጸው የአየር ንብረት ነው። ይህ ረቂቅ ፅንሰ ሀሳብ አይደለም። ጤናማ የአየር ንብረት በዙሪያችን ካሉት መሬት እና ዛፎች ጋር በቅርበት የተሳሰረ የሕልውናችን መሰረት ናቸው።
በያዝነው የክረምት ወቅት
ችግኞቸን ለመትከል፤ የደን ሽፋን ቁጥርን ለመጨመር የያዝነው የክረምት ወቅት በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነው። ሆኖም በዓለማችን ላይ እየተስተዋለ ካለው የከፍተኛ ሙቀት መጨመርና የአየር ንብረት መዛባት አንፃር ሁሌም ቢሆን ቸግኖችን መትከልና መንከባከብ ያስፈልጋል። የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ጉዳቱ መጠነ ሰፊ እየሆነ ነው። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ከምንም በላይ ልዩ ትኩረት የሚሻው። በእርግጥ ክረምት በመጣ ቁጥር እየተመዘገበ የሚገኘው ስኬት የብሔራዊ ኩራት ምንጭ እና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው።
ይህንን የመንግሥት እና የዜጎች ጥምረት የታከለበት አርምጃ በሙሉ ልብ ማድነቅ ይገባል። የመንግሥትን ታላቅ ተነሳሽነት መውሰዱና ወደ ተግባር መግባቱ አንዲሁ እውቅና ሊሰጠው ይገባል። በዚህ የክረምት ወቅት የሚደረገው የችግኝ ተከላ ዘመቻ በጋለ ስሜት ሁሉም ዜጎች ሊሳተፉበት ይገባል። ነገር ግን አንድ ነገር ማስታወስ ይገባል፤ ችግኝ መትከል የመጀመሪያው እርምጃ ነው፤ እንክብካቤ ደግሞ ችግሩን እስከወዲያኛው ለመቅረፍ ዘላቂው መፍትሄ ነው።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በንቅናቄው መሳተፍ አለበት። ዛፎቹን እንደ ምልክት ብቻ ሳይሆን ለሕልውናችን እንደምንታገል መመልከት ይኖርብናል።
በዚህ ክረምት፣ እጆቻችሁ አፈሩን ሲነኩ እና ችግኞችን በምድር ላይ ሲያስቀምጡ ከዛፍ በላይ መትከላችንን ልናስታውስ ይገባል። ችግኞችን መትከል ተስፋን ፣ ጽናትን፣ ንፁህ አየርን ፣ የውሃ ደህንነትን ፣ ብዝሃ ሕይወትን እና የወደፊቷን የበለፀገች ኢትዮጵያን አንደመትከል ነው። ለዚህ ነው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው የምለው። የወደፊት ሕይወታችን የተመሰረተው ዛሬ በምናደርጋቸው ምርጫዎች በመሆኑ የክረምቱን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመን አስትንፋሳችንን እንትከል። ሰላም !!
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በሰው መሆን
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም