
ዜና ትንታኔ
እሥራኤል በሶሪያ የምትፈፅመውን ጥቃት ቀጥላበታለች። የሀገሪቱ ጦር በደቡባዊ ሶሪያ በፈፀመው የአየር ጥቃት በሃማስ አባልነት የጠረጠረውን ግለሰብ መግደሉን ገልጿል። ጦሩ ባወጣው መግለጫ፣ ማዝራት ቤይት ጂን በተባለው አካባቢ በፈፀመው ጥቃት የሃማስ አባል እንደሆነ በጠረጠረው ግለሰብ ላይ ርምጃ መውሰዱን አስታውቋል። የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ተቋም በበኩሉ፣ በአካባቢው ተሽከርካሪን ዒላማ ባደረገ ጥቃት አንድ ሰው መገደሉንና ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን አስታውቋል።
የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ አል-ሻዕባኒ ጥቃቱን ‹‹የሶሪያን መረጋጋት የሚጥሱ የተቀናጁ ትንኮሳዎች›› በማለት የእሥራኤልን ጥቃት አውግዘዋል። ‹‹እነዚህ ድርጊቶች ሕገ ወጥ ቡድኖች አጋጣሚው ተጠቅመው እንዲያንሰራሩና ሶሪያን እንዲበጠብጡ ዕድል ይፈጥራሉ። ሶሪያ ዓላማዋን ግልጽ አድርጋ አሳውቃለች፤ እኛ መልሶ ግንባታ እንጂ ጦርነትን አንሻም›› ብለዋል።
ይህ የእሥራኤል ጥቃት አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሶሪያ ውስጥ የተፈፀመ ሁለተኛው ጥቃት ሆኗል። ከዚህ ጥቃት ቀደም ብሎ የእሥራኤል ጦር ዴራ በተባለው የሶሪያ ግዛት ውስጥ ጥቃት ፈጽሟል። በጥቃቱም ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። እሥራኤል በዴራ ጥቃት የፈጸመችው መነሻቸውን ከሶሪያ አድርገው ለተሰነዘሩብኝ የሮኬት ጥቃቶች ነው ብላለች።
ባለፈው ሳምንት ሁለት ሮኬቶች ከሶሪያ ወደ እሥራኤል የተተኮሱ ሲሆን፣ ይህም የበሺር አል-አሳድ መንግሥት ከወደቀ ወዲህ ከሶሪያ ወደ እሥራኤል የተሰነዘረ የመጀመሪያው ጥቃት ሆኖ ተመዝግቧል። ሮኬቶቹ እሥራኤል በተቆጣጠረችው የጎላን ተራሮች ላይ መውደቃቸውን ጦሩ የገለፀ ቢሆንም፣ ከሶሪያ በኩል የተሰጠ ማረጋገጫ የለም። ለጥቃቱ ‹‹የሰማዕቱ መሐመድ ዴይፍ ብርጌድ›› (Martyr Mohammed Deif Brigades) እና ‹‹የእስላማዊ ተጋድሎ ግንባር በሶሪያ›› (Islamic Resistance Front in Syria) የተሰኙ ሁለት ቡድኖች ኃላፊነት እንደሚወስዱ ገልጸዋል።
የእሥራኤል የመከላከያ ሚኒስትር እሥራኤል ካትዝ ለሮኬት ጥቃቶቹ የሶሪያን የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አሕመድ አል-ሻራን በቀጥታ ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፣ እሥራኤል ተገቢውን የአፀፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝተውም ነበር። በዚህም መሠረት እሥራኤል ዋዲ ያርሙክ በተባለው የደራ ግዛት መንደር የሞርታር ጥቃት ፈፅማለች።
‹‹የስድስቱ ቀናት ጦርነት›› በመባል ከሚታወቀው ከሁለተኛው የዓረብ-እሥራኤል ጦርነት (እ.አ.አ 1967) በኋላ እስራኤል ከጎላን ተራሮች ተጨማሪ ስፍራዎችን መቆጣጠሯን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እስከዛሬም ድረስ እንደሻከረ ዘልቋል። ለሩብ ክፍለ ዘመን ያህል በሥልጣን ላይ የቆየው የበሺር አል-አሳድ መንግሥት ከተወገደ ወዲህ ደግሞ እሥራኤል በሶሪያ ላይ የምትፈፅማቸውን ጥቃቶች አጠናክራ ቀጥላለች። በጥቃቶቹም አብዛኛዎቹን የሶሪያን ጦር መሣሪያዎች ከጥቅም ውጭ አድርጋቸዋለች። የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ተቋም ይፋ ባደረገው መረጃ፣ እሥራኤል ባለፉት አምስት ወራት በሶሪያ ላይ 61 ጥቃቶችን የፈፀመች ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 51 የሚሆኑት የአየር ጥቃቶች ናቸው ብሏል።
እሥራኤል ለምትፈፅማቸው ጥቃቶች ከምትሰጣቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ ሶሪያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የነበረው የጦር መሣሪያ ለደኅንነቷ ስጋት ይሆናሉ ባለቻቸው ታጣቂዎች እጅ እንዳይገባ የሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪም የሶሪያ መንግሥት ኃይሎች በድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የሚፈፀሙትን ግድያ ለመበቀል ከአንድ ወር ከግማሽ በፊት በሶሪያ ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ከባድ የአየር ጥቃት ፈፅማ ነበር።
የድሩዝ ማኅበረሰብ አባላት የሺአ እስልምና ተከታዮች ሲሆኑ በሶሪያ፣ በእሥራኤልና በሊባኖስ ይኖራሉ። እሥራኤል የማኅበረሰቡን አባላት እንደአጋሯ የምትቆጥራቸው ሲሆን፣ ብዙ ድሩዞች የእሥራኤል ጦር አባላት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል እሥራኤል የበሺር አል-አሳድን መንግሥት የገለበጡትን ኃይሎች ያሰባሰበውን የሶሪያን የሽግግር መንግሥት በበጎ አትመለከተውም። በአሕመድ አል-ሻራ የሚመራውን የሶሪያን የሽግግር መንግሥት ‹‹ከኢድሊብ ተነስቶ ደማስቆን በኃይል የተቆጣጠረው የሽብር ቡድን›› ብላ ሰይማዋለች።
እሥራኤል ሰሞኑን በሶሪያ ላይ የፈፀመቻቸው ጥቃቶች ሁለቱ ሀገራት መጀመሪያ በሦስተኛ ወገን በኩል፣ ቀጥሎም ፊት ለፊት ተገናኝተው ውጥረትን ስለማርገብ ከተወያዩ ከቀናት በኋላ መፈፀማቸው የሀገራቱን ግንኙነት ለማሻሻል የተጀመሩ ጥረቶችን የሚያጨናግፉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገልጿል። መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ኖሯቸው የማያውቁትና ከእሥራኤል ምስረታ ጀምሮ በጠላትነት የሚተያዩት ሁለቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ጎረቤት ሀገራት ከበሺር አል-አሳድ አገዛዝ መውደቅ በኋላ ግንኙነታቸው እንዲሻሻል ለማድረግ በወዳጆቻቸው በኩል አንዳንድ ጥረቶች ተጀምረው ነበር።
ሀገራቱ በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ለማርገብ ከአንድ ወር በፊት በሦስተኛ ወገን አደራዳሪ በኩል ተነጋግረው ነበር። በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አሸማጋይነት ተካሂዷል በተባለው በዚህ ቀጥተኛ ያልሆነው የሁለቱ ሀገራት ውይይት፣ ሁለቱ ሀገራት እ.አ.አ በ1974 የተፈራረሙት ስምምነት (The Agreement On Disengagement) ስለሚቀጥልበት ሁኔታ ተነጋግረዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት ደግሞ የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች ፊት ለፊት ተገናኝተው በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ለማርገብና በቀጣናው ተጨማሪ ግጭት እንዳይከሰት ለመከላከል ያለመ ውይይት አካሂደዋል። ዝርዝሩ ባይታወቅም በውይይቱ የእሥራኤልና የሶሪያ የፀጥታና ደኅንነት ባለሥልጣናት እንደተሳተፉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባለፈው ወር በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ሀገራቸው ቀደም ሲል በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩ ማዕቀቦችን እንደምታነሳ ማስታወቃቸው እና ከሶሪያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አሕመድ አል-ሻራ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
አሜሪካ ከሶሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማደስ እንደምትፈልግ ለአል-ሻራ የነገሯቸው ትራምፕ፣ ማዕቀቦቹን የማንሳት ርምጃ ተፈፃሚ እንዲሆን ለሶሪያ መንግሥት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠው ነበር። ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል ዋና ዋናዎቹ የሶሪያ መንግሥት ‹‹የአብርሃም ስምምነት››ን (Abraham Accords) በመቀበል ከእሥራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጀምር፣ አሸባሪ ፍልስጤማውያንን ከሀገሩ እንዲያስወጣ እና በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ለሚገኙ የእስላማዊ መንግሥት (ISIS) ማጎሪያ ማዕከላት ኃላፊነት እንዲወስድ የሚጠይቁ ናቸው።
በእርግጥ ‹‹የአብርሃም ስምምነት››ን ተቀብሎ ከእሥራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመጀመር ጉዳይ ለሶሪያ መንግሥት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ እንደሚሆንበት ተንታኞች ገልፀዋል። በተለይም ሶሪያ ‹‹የአብርሃም ስምምነት››ን እንድትቀበልና ከእሥራኤል ጋር መልካም ግንኙነት እንድትመሠርት የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ የፍልስጤማውያንን ጥያቄና ጥቅም የሚክድ በመሆኑ ቅድመ ሁኔታው ለዓረባዊቷ ሶሪያ እጅግ ከባድ ጥያቄ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ከሳምንት በፊት ደማስቆን የጎበኙት በሶሪያ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶማስ ባራክ በበኩላቸው፣ የእሥራኤልና የሶሪያ አለመግባባት ሊፈታ የሚችል በመሆኑ ሀገራቱ ውይይት እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርበው ነበር። በአሕመድ አልሻራ የሚመራውን የሶሪያን የሽግግር መንግሥት ያወደሱት እና እ.ኤ.አ በ2012 ተዘግቶ በነበረው የአሜሪካ ኤምባሲ ግቢ ውስጥ ተገኝተው የሶሪያን ሰንደቅ ዓላማ የሰቀሉት ባራክ፣ ‹‹በእስራኤልና በሶሪያ መካከል ያለው አለመግባባት መፍትሔ ሊያገኝ የሚችል በመሆኑ ሀገራቱ አለመግባባታቸውን ለመፍታት ንግግር መጀመር አለባቸው›› ብለዋል።
በእሥራኤልና በሶሪያ መካከል በሦስተኛ ወገን በኩል እና በቀጥታ የተደረጉት ውይይቶች እና ሀገራቱ መደበኛ ግንኙነት እንዲጀምሩ በአሜሪካ በኩል የቀረቡ ሃሳቦች ለብዙ አስርት ዓመታት ባላንጣ ሆነው የዘለቁትን ጎረቤቶች ግንኙነት ለማሻሻል አዎንታዊ ሚና እንደሚኖራቸው ተስፋ ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ውይይቶች ከተካሄዱም በኋላ እሥራኤል በሶሪያ የፈፀመቻቸው ጥቃቶች በውይይቶቹ የተሰነቀውን ተስፋ እንዳያጨልሙት ተሰግቷል። የሶሪያና የእሥራኤል መካረር መፍትሔ ሳያገኝ ተባብሶ ከቀጠለ በርካታ ተዋንያን የሚሳተፉባቸው ብዙ ግጭቶችን ለሚያስተናግደው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ተጨማሪ የፀጥታ ችግር መሆኑ አያጠራጥርም ሲሉ የፖለቲካ ምሑራን ይገልጻሉ።
በአንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም