በፉክክሮች እየተገባደደ የሚገኘው የሠራተኞች የበጋ ወራት ውድድር

ካለፈው ጥር አንስቶ እየተካሄደ የሚገኘው የሠራተኞች የበጋ ወራት ውድድር በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች በሚደረጉ ጠንካራ ፉክክሮች ታጅቦ እየተገባደደ ይገኛል። በአስር የስፖርት ዓይነቶች የበርካታ ተቋማት ሠራተኞችን እያፎካከረ የሚገኘው የበጋ ወራት ውድድር በእዚህ ወር መጨረሻ አካባቢ በተያዘለት መርሃ ግብር መሠረት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን(ኢሠማኮ) የስፖርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ካሳ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ዮሴፍ ገለጻ፤ ውድድሮቹ በደማቅ ፉክክር ታጅበው እየተገባደዱ ነው። በ2ኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ የሚደረጉ ፉክክሮች በጥሎ ማለፍ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በተመሳሳይ በ1ኛ ዲቪዚዮን ደግሞ ሰባት ሰባት ጨዋታዎች ተደርገው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ነው የሚቀራቸው። ይህም በእዚህ ሳምንት በጎፋ ሜዳ ይደረጋል። በ1ኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ ቡድኖች ተቀራራቢ ነጥብ ስላላቸው በተመሳሳይ ሰዓት ነው ቀጣዩን ጨዋታ የሚያካሂዱት።

“እግር ኳሱ አጓጊ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው” ያሉት አቶ ዮሴፍ፤ በበጋ ወራት ውድድሮቹ በቤት ውስጥ ስፖርቶችም ፉክክሮች እየተገባደዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በቤት ውስጥ ስፖርቶች ዘንድሮ ጥሩ በርካታ ቡድኖች ተሳታፊ ከመሆናቸው በተጨማሪ ጠንካራ ተፎካካሪዎችም በርክተዋል። “ትልቁ ችግራችን ጨዋታዎችን የምናካሂድበት የሜዳ እጥረት ነው” ያሉት አቶ ዮሴፍ፤ ውድድሮችን ለማካሄድ ሜዳ በልመናና በተቋማት በጎ ፍቃድ እንደሚያገኙ ገልጸው፤ ቀጣይ 2018 ግን ይህ የሠራተኛው ስፖርት ችግር ከተቀረፈ የተሻለ ውድድር ማዘጋጀት እንደሚቻል ተናግረዋል።

የሠራተኛው ስፖርት የዘወትር ጥያቄ የሆነውን የሜዳ እጥረት መፍትሔ ለመስጠት ኢሰማኮ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ይሁን እንጂ አሁንም ተገቢ መልስ አላገኘም። አቶ ዮሴፍ “የሠራተኛው ስፖርት ትልቁ ችግር የሜዳ ነው፤ የተሳታፊዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ለማስተናገድ እንቸገራለን” የሚሉትም ከችግሩ አሳሳቢነት በመነሳት ነው። ከእዚህ ባሻገር የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም ፌዴሬሽኖች ዳኞችን በመመደብ ለሠራተኛው ስፖርት ጥሩ እገዛ እያደረጉ እንደሚገኙ አቶ ዮሴፍ አስረድተዋል።

በሠራተኛው ስፖርቶች ንቁ ተሳታፊ ከሆኑ ተቋማት አንዱ የሆነው የኢትዮ ቴሌኮም የቤት ውስጥ ስፖርቶች አሠልጣኝና አስተባባሪ ጋሻው ካፍቲመር እንደሚናገሩት፤ ተቋማቸው በበጋ ወራት የሠራተኛ ውድድሮች እስካሁን በቤት ውስጥ ስፖርቶች ውጤታማ እየሆነ ነው። የተሻለ ውጤት ይዞ እንደሚያጠናቅቅም ተስፋ አድርገዋል። ከእዚህ በፊት ከነበረው አኳያ ዘንድሮ የተሳታፊዎች ቁጥር መጨመሩ ፉክክሩ ጠንካራ እንዲሆን አድርጓልም ይላሉ። “አንዳንድ ቡድኖች ዘግይተው ነው የተመዘገቡትና ፉክክሩን የተቀላቀሉት፤ ይህ እናገኛለን ብለን ያሰብነውን ውጤት እንዳናገኝ ቢያደርግም እንደ አጠቃላይ ግን ጥሩ የፉክክር ጊዜ እያሳለፍን እንገኛለን። በጊዜ ቢሆን ራሳችንን የተሻለ አጠናክረን እንቀርብ ነበር” የሚሉት አቶ ጋሻው፤ ዘግይተውም ቢሆን ውድድሩን የተቀላቀሉት ጠንካራ ቡድኖች የተሻለና ቤተሰባዊ የስፖርት እንቅስቃሴ እንዲታይ ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም የስፖርት እንቅስቃሴ የሚደገፍ በሠራተኛ ማህበሩና በማኔጅመንቱ መሆኑን በመጥቀስም፤ ይህም ምንም ዓይነት የቁሳቁስም ሆነ የሎጀስቲክ ችግር እንዳይገጥማቸው ማድረጉን ያስረዳሉ። ለእዚህም የሁለቱ አካላት ተናቦ በጋራ መሥራት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ይላሉ። በሠራተኛው ውድድሮች ከሞላ ጎደል በሁሉም ስፖርቶች ተሳታፊ መሆናቸውን በመናገርም፤ ወደፊት ደግሞ በእቅድ ደረጃ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የተቋሙ ሠራተኞች መካከል የውስጥ ውድድር የማድረግ ሃሳብ እንዳለ ገልጸዋል።

የሠራተኛው ስፖርት አዘጋጅ ኮሚቴው በሚያደርገው ጥረት ምንም እንከን ሳይኖር ጠንካራ ውድድር መፍጠር መቻሉን የተናገሩት አቶ ጋሻው፤ በእዚህ ሁሉ የስፖርት ዓይነት በርካታ ውድድሮች እየተካሄዱ የጎላ ስህተት እንዳልተፈጠረና ይህም ፉክክሮች ይበልጥ ጤናማና የወዳጅነት ስሜት የተላበሱ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል።

የመከላከያ ኮንስትራክሽን የቮሊቦል ተጫዋች የሆነችው ዓለሚቱ አዲሱ በርካታ ጠንካራ ቡድኖች ተፎካካሪ መሆናቸውን ትናገራለች። “ሠራተኛው ላይ ያለው የስፖርት ፍላጎት ደስ የሚል ነው፣ ከሥራ ሰዓት ውጪ እየተዝናናን ጤናችንን እንድንጠብቅ የሠራተኛው ስፖርት እድል ፈጥሮልናል” የምትለው ዓለሚቱ፤ የሠራተኛው ውድድር ከእዚህ በፊት በስፖርት ያለፉና አሁን ሥራ ላይ የሚገኙ ሰዎችም ከስፖርት እንዳይርቁ አደርጓቸዋል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች በሠራተኛው ስፖርት ውስጥ መኖራቸውም ፉክክሮችን ደማቅና የተሻሉ እንዲሆኑ ማድረጉን ተጫዋቿ ተናግራለች።

በቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You