
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በቀዳሚነት ከምትጠቀስባቸው ጉዳዮች አንዱ የቀንድ ከብት ሀብት ነው:: የቀንድ ከብት በብዛት መኖሩን ተከትሎ፤ በቆዳ ምርት ቀዳሚ የመሆን እድል አግኝታለች:: ይሁንና ቆዳን ወደ ውጭ በመላክ ገናና መሆን ያለባት ኢትዮጵያ፤ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የቆዳ ውጤቶችን እንካችሁ ብትልም በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል::
ይህንን ሃሳብ በመደገፍ በሀገሪቱ ባለው አቅም ልክ የዘርፉ ሀብት ጥቅም ላይ አልዋለም የሚል ግምገማ መኖሩ ተገቢ መሆኑን ያነሱት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ናቸው:: ሚኒስትሩ በዘርፉ ተለዋዋጭ የደንበኞች ፍላጎት መኖሩ፣ ተፈላጊ ተብለው የተመረቱ ምርቶች ቶሎ ፋሽን የሚያልፍባቸው መሆኑ፣ ዓለም ላይ ከቆዳ ወደ ሴንቴቲክ የመዞር ዝንባሌ መታየቱ፤ አዳዲስ ፍላጎቶችና ምርቱን ወደ ዓለም ገበያ ለማስገባት የሚወጡ መስፈርቶች ከሀገሪቱ አምራቾች ጋር አለመጣጣም ዘርፉ ላይ ተጽእኖ መፍጠራቸውን አብራርተዋል::
በተጨማሪ ኮቪድና የጸጥታ ችግር በዘርፉ የጎላ ተጽእኖ አሳድረዋል ሲሉ የገለፁት ሚኒስትሩ፤ በዚህ እና በተለያዩ ምክንያቶች አሁንም ድረስ ቆዳ እየተጣለ መሆኑን አመልክተዋል:: ዘርፉ ላይ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን አስታውሰው፤ ስትራቴጂ ማሻሻል፣ በዘርፉ የተሻሉና ሞዴል ሊሆኑ የሚችሉ ኢንዱስትሪዎችን መለየት እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል::
በቀጣይም ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ኢንዱስትሪዎች ከተናጠል ድጋፍ ባሻገር፤ በጋራ መደገፍ የሚያስችል የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል በዘርፉ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል:: ይህን ተከትሎ አሁን ተጽእኖ በመቋቋም ተዘግተው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች እየተከፈቱ ይገኛሉ ብለዋል::
የቆዳ ውጤቶች ምርምር ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዙልፋኪር አባጆቢር በበኩላቸው፤ ከ2012 ዓ.ም ወዲህ ወደ ውጭ የሚላከው የቆዳ መጠን የመቀነስ አዝማሚያ የታየበት መሆኑን ይናገራሉ:: ዘርፉ በሚፈለገው ልክ ያልተሻገረበትን ሁኔታ ለመለየት በ2015 ዓ.ም ጥናት መጠናቱን ጠቅሰው፤ በጥናቱ ከሌላው ዓለም አንጻር የሀገሪቱ የቆዳ ፋብሪካዎች የተበታተኑ መሆናቸው ተለይቷል:: እንዲሁም በቆዳ ኢንዱስትሪ ላይ የግብዓት አቅርቦት ችግር መኖር፣ በዘርፉ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የአመራር ውስንነት መታየት፤ የቆዳ ፋብሪካዎች ከአካባቢና ከማህበራዊ ጉዳይ አንጻር ማሟላት ያለባቸው የዓለም አቀፍ መስፈርት ቢኖርም፤ ጥናቱ በተጠናበት ወቅት አለማሟላታቸው መታወቁን ተናግረዋል::
ዘርፉ በፋይናንስ አቅርቦት ረገድም ክፍተት እንዳለበት የሚያነሱት አቶ ዙልፋኪር፤ ከመሥሪያ በጀትም ሆነ ከውጭ ምንዛሬ አንጻር ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል:: የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ በሀገሪቱ በተተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚክ ሪፎርም መልስ እያገኘ ቢሆንም፤ የመሥሪያ ካፒታል እጥረት አሁንም አለ ብለዋል:: በተመሳሳይ የቆዳ ምርቶችን ከማስተዋወቅ አንጻርም እጥረት መኖሩን አስታውሰዋል::
በዘርፉ የቆዳና ሌጦ አቅርቦት አንዱ ችግር መሆኑን ያነሱት ሥራ አስኪያጁ፤ ከአቅርቦቱ በተጨማሪ የሚቀርበው ቆዳና ሌጦ የጥራት ሁኔታ አሳሳቢ ነው ብለዋል:: የቁም እንስሳቱ ላይ ካለው የጥራት ችግር ባሻገር ከታረደም በኋላ ቆዳው ፋብሪካ እስኪደርስ በሰው የሚፈጠሩ የጥራት መጓደሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል::
“የእንስሳት አራጆቹ አብዛኛው ትኩረት ስጋ ላይ በመሆኑ ቆዳና ሌጦው ላይ የሚደርስ ጉዳት ብዙም ግድ አይሰጣቸውም” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በተለይ ቄራ አካባቢ በርካታ እርድ ላከናወነ ማበረታቻ እንዳለው በማንሳት፤ በዚህም ባለሙያዎቹ ብዙ እርድ ለማከናወን ሲፈጥኑ የቆዳና ሌጦው ጥራት ሊጎድል ይችላል ብለዋል::
“ቆዳ ፋብሪካ ብዙ ውሃ ይጠቀማል:: አንድ ኪሉ ግራም ያለቀለት ቆዳ ለማውጣት ከ35 እስከ 40 ሊትር ውሃ ይፈሳል:: በተመሳሳይ አንድ ሺህ ቶን ቆዳ ወደፋብሪካ ቢገባ፤ ከዛ ውስጥ ሁለት መቶ ኪሎ ብቻ ቆዳ ይሆናል:: የተቀረው በፈሳሽ መልክ እንደሚወገድና ይህም በተገቢው መልኩ ካልተያዘ በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ የሚኖረው መሆኑን አስረድተዋል::
ከ90 በመቶ በላይ እርድ በሰው ጓሮ እንደሚከናወን ያነሱት አቶ ዙልፋኪር፤ በሰው ጓሮ የታረዱት እንስሳት ቆዳና ሌጦ ተሰብስቦ ወደ ኢንዱስትሪዎች እስኪደርስ ችግር መኖሩን አንስተዋል:: ለዚህም የግብይት ሥርዓቱ የሚከናወንባቸው ደንቦችና መመሪያዎች አሉ:: ሆኖም ጉዳዩ ያልተፈታ የባለቤትነት ጥያቄ እንዳለበት አብራርተዋል::
ግብርና ሚኒስቴር ጉዳዩን ወደ ንግድ ሚኒስቴር እንደሚገፋው በማንሳት፤ ንግድ ሚኒስቴር በተመሳሳይ ጉዳዩን ወደግብርና ሚኒስቴር እንደሚመራ ጠቅሰዋል:: በግብይት ዘርፍ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሦስቱ ሚኒስትር መሥሪያቤቶች መነጋገራቸውን በማንሳት ያለውን ችግር ለመፍታት እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል::
እንደ አቶ ዙልፋኪር ማብራሪያ፤ ቆዳ ፋብሪካዎች በምርት ሂደት ከአካባቢ ጥበቃ አንስቶ ማሟላት ያለባቸው 17 መስፈርቶች አሉ:: ይህንን አሟልተው ሲገኙ ሌዘር ወርኪንግ ግሩፕ (LWG) የምስክር ወረቀት ያገኛሉ:: በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ይህንን መስፈርት ያሟላና ሰርተፍኬት ያለው ፋብሪካ አልነበረም::
ሰርተፍኬቱን ማግኘት በዓለም ገበያ ላይ ሰብሮ ለመግባት ጠቃሚ ነው:: ይህን ሰርተፍኬት የማግኘት ሂደት በሌሎች የቆዳ ፋብሪካዎች ላይም መቀጠል አለበት የሚሉት አቶ ዙልፋኪር፤ በአሁኑ ወቅት ስድስት ፋብሪካዎች ሰርተፍኬቱን ማግኘት ችለዋል:: ከእነዚህ ውስጥ አራቱ በወርቅ ደረጃ ሲሆኑ፤ ሁለቱ በብር ደረጃ ያገኙ መሆናቸውንም አመላክተዋል::
ሰርተፍኬት ያገኙ ፋብሪካዎች ምርቱ አልቆ ገበያ ላይ ሲያቀርቡ የዓለም ሸማቾች ሼልፍ ላይ የሚያዩት የቆዳ ውጤት ከቆዳው መነሻ ጀምሮ ደህንነቱ በተጠበቀና አካባቢ ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ እንደተመረተ ይረዳሉ:: ይህ ገበያው ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉ ገልጸዋል::
የቆዳ ምርት ከግብርና ልማት ተነስቶ በመጨረሻ ምርት እስከሚሆን ረዥም ሰንሰለት መጓዙ የዘርፉ ሌላኛው ፈተና መሆኑን አስታውሰው፤ ይሁንና ጉዳዩ ከእንስሳት ሀብት ልማት ጋር ስለሚገናኝ ግብርና ሚኒስቴር ለእንስሳት ስጋና ወተት በማሰብ የሚሠራው ሥራ ለቆዳና ሌጦ ምርት ጥራት ይጠቅማል:: ለዚህም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ የሚሠራበት ሁኔታ ተፈጥሯል ይላሉ::
ሌሎችንም ችግሮች ለመቀልበስ ይቻል ዘንድ የአስር ዓመት ዕቅድን የመከለስ ሥራ ተሠርቷል:: በእዚሁ ላይ እስከ 2025 ዓ.ም ተግባራዊ በሚሆነው ዕቅድ ላይ ከላይ ጀምሮ እስከ ወረዳ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተወያይተዋል:: በጥናት የተለዩት የዘርፉን ችግሮች እና በእቅድ የተቀመጡትን ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል:: በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወነው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተዘግተው የነበሩ ስድስት የቆዳ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተደርጓል:: የቆዳ ዘርፉ ላይ ከ60 እስከ 70 በመቶ አቅም ያላቸው ሰባት የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ተለይተው በውጭ ንግድ ላይ የሚገጥማቸው ችግር እየተፈታ ይገኛል ብለዋል::
እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በተለይ ከሃይል አቅርቦት ጋር ተያይዞ የነበረባቸው ችግር ቅድሚያ ተሰጥቶት የተሻለ የሃይል አቅርቦት እንዲኖራቸው እየተሠራ ነው:: በዚህ ሂደት በሞጃ አካባቢ የሚገኙት ኢልኮና አዲስ አበባ የተሰኙ ፋብሪካዎች የሃይል አቅርቦት ችግራቸው መፈታቱ በዘርፉ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል ሲሉም ተናግረዋል::
የተሻለ የአመራረት ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ለእዚህም ህንድ ሀገር ከሚገኝና በዘርፉ ረዥም ዓመት ካስቆጠረ የቆዳ ምርምር ማእከል ጋር በመሥራት እነሱ ተግባራዊ ያደረጉትን ቴክኖሎጂ ወደሀገር ውስጥ ለማምጣና በሀገሪቱ የቆዳ ፋብሪካዎች የእውቀት ሽግግር ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል::
ከቆዳ ተረፈ ምርት ኮላን በማምረት ለጫማ ሥራ ግብአት እንዲሆን ማድረግ መቻሉን የሚናገሩት አቶ ዙልፋኪር፤ ለቆዳ ማለስለስ ሂደት ግብአት የሚሆን ፕሮቲን ፊለር የተሰኘ ኬሚካልን ከተረፈ ምርት ማምረት መቻሉንም ይገልጻሉ:: የቆዳ ተረፈ ምርትን ወደ ጠቃሚ ነገር ለመቀየር ከቻይና የቆዳና ጫማ ምርምር ኢንስቲትዩትና የህንድ ማዕከላዊ የቆዳ ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር ግንኙነት በመፍጠር በቆዳ ምርት ሂደት ላይ የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም የሚያመርቷቸው ምርቶች ተለይተዋል:: በዚህ ሂደት የተገኙ ተሞክሮዎች በተወሰኑ ቆዳ ፋብሪካዎች ላይ ተግባራዊ መደረግ መጀመራቸውንም አስረድተዋል::
የአዞ ቆዳ በተፈጥሮ እራሱ ላይ ዲዛይን ስላለው ለቦርሳና ለጫማ ተፈላጊ መሆኑን የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ ከአዞ ቆዳ የተሠራ ምርት ዋጋው በሦስትና በአራት እጥፍ እንደሚበልጥ ይናገራሉ:: ይህንን ከግምት በማስገባት ምርምር የተሠራ ሲሆን፤ ከአርባምንጭ የአዞ ቆዳ በማምጣት በኢንስቲትዩቱ ቆዳው ተስተካክሎ ወደ ቆዳ ፋብሪካዎች እንዲደርስ ተደርጓል:: በዚህ ሂደትም ኬሬዥ ኢትዮጵያ የሚባል ፋብሪካ የአዞ ቆዳ ቦርሳዎች ለሀገር ውስጥ ለውጭ ገበያም ማቅረቡንና ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰዋል::
የቆዳ ፋብሪካዎች ከነበረው ተሞክሮ ለመውጣት ያለመፈለግ ሁኔታና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያለመቀበል ሁኔታ ይታይባቸዋል ያሉት አቶ ዙልፋኪር፤ አሁን በኢንስቲትዩቱ የሚመጡ ምርጥ ተሞክሮዎችን እያዩና ገበያውም እየገፋቸው ሲመጣ የመቀበል አዝማሚያ እያሳዩ መሆኑን ጠቅሰዋል::
የአቶ ዙልፋኪርን ሃሳብ በማጠናከር በዘርፉ ለውጥ መኖሩን የሚናገሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ በበሉላቸው፤ የአምራች ዘርፉ ውጤታማነት የሚለካው በማምረት አቅም መሆኑንና በዛም መሻሻል መኖሩን ተናግረዋል:: ለአብነትም በ2015 ዓ.ም የቆዳ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም 31 ነጥብ 4 እንደነበር በማስታወስ፤ አሁን ወደ 45 ነጥብ 7 ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል::
በ2015 ዓ.ም 58 በመቶ የነበረው የጫማና ቆዳ ውጤቶች የማምረት አቅም አጠቃቀም በአሁኑ ወቅት ወደ 63 በመቶ ከፍ ብሏል:: ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እያዳንዱ ፋብሪካ የጎደለው ምን እንደሆነ የሚለይበትና መፍትሄ የሚፈለግበት አሠራር መፈጠሩን አስታውሰው፤ በተጨማሪ የተደረጉ ሥልጠናዎች፣ ድጋፎች ለውጥ ማምጣታቸውን አመላክተዋል::
እንደሚኒስትሩ ገለጻ፤ በሀገሪቱ የቆዳ አምራቾች ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች እያመረቱና በዓለም አቀፍ ትላልቅ ከተሞች መሸጫ ሱቅ እየከፈቱ ውጤታማ እየሆኑ ነው:: ይሁንና በተለይ የመንግሥት ተቋማት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ምርት የመግዛት ፍላጎት የላቸውም:: በዚህ የተነሳ ሚኒስቴሩ ጣልቃ በመግባት ከሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲገዙ ጫና እያደረገ ይገኛል::
ተቋሞቹ ወጪን ምርት አስበልጦ የመመልከት ሁኔታ ይታይባቸዋል:: ለዚህም የግዢ መስፈርቶቹ ላይ ለሀገር ውስጥ አምራቾች ይልቅ የውጪዎቹን የሚጋብዙ ሁኔታዎችን ያስቀምጣሉ:: ለአብነትም ለሀገር ውስጥ አምራቾች አነስተኛ ጊዜ በመስጠት ለውጭዎቹ ረዥም ጊዜ የመስጠትና መሰል ሁኔታዎች መኖሩ ይስተዋላሉ:: የመንግሥት ተቋማት ከፍተኛ ግዢ የሚፈጽሙ ከመሆኑ ጋርና የሀገር ውስጥ አምራቾችን ከማበረታታት ረገድ ዘርፉ ትኩረት ይፈልጋል::
ቄራ ላይም ሆነ ከቄራ ውጭ እርድ በሚፈጸምባቸው ቦታዎች የሚያርዱ አካላት የሰለጠኑ መሆን አለባቸው በሚል የማሰልጠኛ መሣሪያዎች እየተዘጋጁ ናቸው ብለዋል:: በዚህም እስካሁን ወደ መቶ የሚጠጉ መሰልጠናቸውንና በቀጣይም ያልሰለጠነ አራጅ ሥራ ውስጥ መግባት የለበትም የሚል አቋም መኖሩንም አንስተዋል::
እርድ ላይ ከቆዳ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት፤ ችግሩን ለማስወገድ ቆዳም ዶላር መሆኑን በማስረዳት ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር ትክክለኛ የአስተራረድ ሁኔታዎችን ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል::
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩም በተመሳሳይ ለቆዳ ኢንዱስትሪው ስኬት ከእንስሳት ርባታ አንስቶ እስከመጨረሻ ያለውን የእሴት ሰንሰለት ተከትሎ ድጋፍ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል:: በዚህ ሂደት ግብርና ሚኒስቴር፣ የግብይት ሥርዓቱን በመከታተልና በመደገፍ ድርሻ ያለው የንግድ ሚኒስቴር፤ ቆዳውን ተቀብሎ የሚያስፈልገውን ሥራ ሠርቶ ለገበያ በማውጣት ደግሞ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ድርሻ አላቸው:: በዚህ ላይ የሚጠበቅባቸውን እየሠሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል::
በቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም