በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶ ደሮችን የፋይናንስ ተደራሽነት ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በአነስተኛ ማሳ ለሚያመርቱ አርሶ አደሮች የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽነት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ትናንት ሲካሄድ እንዳሉት፤ ግብርናው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው። ለዚህም መንግሥት የዘርፉን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ርምጃዎችን እየወሰደ ነው። በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን የፋይናንስ ተደራሽነት ማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሠራባቸው ሥራዎች መካከል መሆኑን አንስተዋል።

የተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ አካታችና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እየተተገበረ መሆኑንም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በስንዴ ልማትና በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሮች የተገኙ ውጤቶች በምግብ ራስን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት ማሳያ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ለግብርና ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ መሆኑንም አብራርተዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በየዓመቱ የምትተክላቸው ችግኞች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ካላቸው ሚና ባለፈ በምግብ ራስን ለመቻል የሚሠሩ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመው፤ በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የዜጎችን የአመጋገብ ሥርዓት ለማሻሻል እያስቻለ ነው ብለዋል።

በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶና አርብቶ አደሮች ለአየር ንብረት ለውጥ የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን የጠቀሱት ግርማ (ዶ/ር)፤ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ ርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። በዚህም ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ አርሶና አርብቶ አደሮች የፋይናንስና የኢንሹራንስ አቅማቸውን የበለጠ እንዲያጠናክሩ በማገዝ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል ።

የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽነት የበለጠ ለማጠናከር የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን የማጠናከር ተግባራት እየተከናወኑ ነው። አካታች የፋይናንስ ሥርዓት በመዘርጋት የገጠር ልማትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዲዮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የግብርና ፋይናንስና የኢንሹራንስ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አንስተው፣ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ አርሶና አርብቶ አደሮችን የፋይናንስና የኢንሹራንስ አቅማቸውን የበለጠ እንዲያጠናክሩ ለማድረግ የጀመረችው ተግባር አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

የግብርና የዘርፉን ቀጣይነት ያለው የፋይናስ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ አነስተኛ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል። የግብርና ዘርፉ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች የአጀንዳ 2063 ለማሳካት ያስችላል ያሉት ተወካዩ፤ በዚህም ቀጣይነት ያለው ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በተጨማሪም የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ሰላምን ለማስፈንና በሁሉም መስክ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ያግዛል። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

የውይይት መድረኩ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የልማት አጋሮች እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ናቸው።

በፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You