ማዕከሉ በቀን በአማካይ አንድ ሺህ ሊትር ወተት እያመረተ ነው

አዲስ አበባ፡- አቃቂ የእንስሳት ልህቀት ማዕከል በቀን አማካይ አንድ ሺህ ሊትር ወተት እያመረተ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሽጉጤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የእንስሳት ልህቀት ማዕከሉ በአማካይ በቀን ከዘጠኝ መቶ እስከ አንድ ሺህ ሊትር ወተት እያመረተ ይገኛል።

ማዕከሉ ከዚህ ቀደም በልማት ምክንያት የተነሱ አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም የተገነባ ፕሮጀክት መሆኑን በማንሳት፤ አርሶ አደሩ ከዚህ በፊት በግብርና ዘርፍ የነበረውን ልምድ ይዞ እንዲቀጥል በማድረግ፤ ችግር የመፍታት ሥራ እየሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ከመልሶ ማቋቋም እና ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ የዝርያ ማዕከል እንዲሆን በረጅም እና በመካከለኛ ጊዜ እቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ይህም የወተት ምርትን ከማሳደግ አንጻር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የዝርያ ማዕከል ለማድረግ የተፈለገበት ትልቁ ዓላማ የተሻለ ወተት የሚሰጡ ጊደሮችን ለማግኘት እንደሆነም ጠቅሰዋል። ከዚህ አንጻር በምርምር የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱትን ዝርያዎች ለማግኘት ለእንስሳት ምርምር ማዕከላት ጥያቄ ማቅረባቸውን ኮሚሽነር ባዩ  አመላክተዋል።

በወተት ልማት፣ እንስሳት የማደለብ እና የዶሮ እርባታ ሥራዎች በዋናነት የሚሠሩ ሲሆን፤ በአንድ መሥሪያ ቦታ ወይም ሼድ 15 ሰዎች ተደራጅተው እየሠሩ እንደሆነ ተናግረው፤ በዚህም አጠቃላይ በማዕከሉ ለ600 ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

በማዕከሉ ከ35 ሺህ በላይ ዶሮዎች እንዳሉ የተናገሩት ኮሚሽነሩ፤ በቀን 35 ሺህ እንቁላል፤ በወር ደግሞ አንድ ሚሊዮን እንቁላል የሚመረት መሆኑን እንዲሁም፤ በማዕከሉ የመሸጫ ሱቅ በማዘጋጀት አንድ እንቁላል በ10 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መኖ ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉና የመኖ ዋጋ መወደዱ፤ ወደ ጎረቤት ሀገራት ሱዳን እና ጅቡቲ እንቁላል ኤክስፖርት መደረግ መጀመሩ እና ፍትሐዊ ያልሆነ የንግድ ሥርዓት መኖሩ የእንቁላል ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።

ማዕከሉ እንቁላል በ10 ብር እየሸጠ ያለው በርካታ ድጋፍ ስለሚደረግለት እንደሆነ ተናግረዋል። በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ የመንግሥት ሼዶች እና በግለሰብ ደረጃም እንቁላል የሚያመርቱ ግለሰቦች ቢበዛ አንድ እንቁላል ከ13 ብር በበለጠ ዋጋ እንደሚሸጡ ጠቅሰው፤ ነገር ግን ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መልኩ በሱቆች አካባቢ ዋጋ የማስወደድ ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ከማዕከሉ በተጨማሪ ካዛንቺስ አካባቢ በተመጣጣኝ ዋጋ እንቁላል እና ወተት እየቀረበ ሲሆን፤ በቀጣይ በሌሎች የመዲናዋ አካባቢዎችም ቦታ በማፈላለግ ምርቶችን የማቅረብ እቅድ እንዳላቸው ኮሚሽነሩ አመላክተዋል።

በዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You