ጠቆርቆር ብሎ የደመነውን ሰማይ ቀና ብሎ ለማየት አያስደፍርም። ነጎድጓዳማው ድምጽ በሰማይ አድማስ እየተደመጠ ማስፈራራቱን ቀጥሏል። በመብረቅ ብልጭታ የታጀበው የነጎድጓድ ድምጽ ከፊቴ ዞር በሉ፤ መጠለያችሁን በፍጥነት ፈልጉ… መልዕክት አንግቧል።
ሁሉም ሰው ይህንን መልዕክት ካለማንም መካሪና ተርጓሚ በራሱ ተረድቶታል። በየመንገዱ፣ በገበያ ስፍራ፣ በትራንስፖርት ጥበቃ…በሌላም በሌላም ቦታ የሚታየው ሁሉ በፍጥነት ወደ የመግቢያውና መጠለያው ይሯሯጣል። ከመጪው አስፈሪ ዝናብና ጎርፍ ለማምለጥም ለጊዜው መጠለያ ያለው ቦታም ያማትራል። በሰው ትርምስ የተጨነቀችው ከተማ በደቂቃዎች ሰው አልባ ሆናለች። አሁንም ጠንከር ካለው ነፋስ፣ ውሽንፍር እና በነጎድጓድ ድምጽ ታጅቦ ብልጭልጭ እያለ ሰላምን ከሚነሳው አስፈሪ መብረቅ ቀና ብሎ መሯሯጥ ምቾት አይሰጥም።
ይህን አስፈሪ የክረምት አመጣጥ አይተው ልጆቼ፣ ሃብት ንብረቴን ሳይሉ የመጣውን አስፈሪ የክረምት ወቅት ካለምንም መሸሻ ሳይወዱ በግዳቸቸው ለመቀበል የተዘጋጁ ወደ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚደርሱ ተፈናቃይ ወገኖቻችን በየመጠለያው አሉ። በየዳሱና ላስቲክ ቤቱ ኩርምት ብለው ተቀምጠዋል። ለልጆቻቸው ቆርሰው የሚያጎርሱ የእናት እጆች እርዳታ ጠባቂ፤ የሌላን እጅ ተመልካች፤ ሰጪ ሳይሆን ተቀባይ ሆነዋል። አርሶ አጉራሹ፤ አርብቶ አደሩ የወገን አለኝታ ወገኖቻችን ዛሬ የቤት እንስሳቶቻቸው ተበትነዋል፤ ሞፈር ቀንበራቸውን ሰቅለው ከማሳቸው ርቀዋል። የአዝመራው ወቅት ሊያልፈን ይሆን በሚል ስጋት ላይም ወድቀዋል።
ከሰል አቀጣጥለው፣ እንጨት አገፋፍጠው ትኩስ ትኩሱን እየተመገቡ ክረምቱን በሞቀ ጎጇቸው ማሳለፍ የለመዱ ወገኖቻችን ጸሀይና ሙቀት፣ ብርድና ቁር እየተፈራረቀባቸው በየመጠለያው ይገኛሉ። እኛ ደግሞ ባማረው ቤታችን ተቀምጠን፣ በልብስ ላይ ልብስ ደርበን፣ ሰውነትን የሚያሞቅ ሆድን የሚሞላ ምግብ በማማረጥ የክረምቱን አመጣጥ እንደአመጣጡ ለመቀበል የተዘጋጀን ብዘዎች ነን። ከቀያቸው ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ግን ይሄንን እያሰቡ አይደሉምና ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ልንደርስላቸው ይገባል።
መንግስት የዜጎችን ሰብአዊ መብት የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለበት። የተፈናቀሉ ዜጎችም እንዲቋቋሙ የማድረግም ግዴታ አለበት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የለውጡ አንደኛ አመት ሲዘከር በቀጣይ ለመስራት ቃል የገቡትም «የተፈናቀሉ ወገኖችን በፍጥነት እናቋቁማለን» ሲሉ ነው። ይሄ እንደ መንግስት ትክክል ነው፤ መሆንም አለበት። በፍጥነት ግን ከክረምት በፊት መተግበር አለበት፡፡
መንግስት ሁሉንም ነገር ያደርጋል፤ ለማድረግ አቅም አለው ብሎ ማሰብ ብቻ ደግሞ እንደ ዜጋ ተገቢ አይደለም። በመሆኑም ሁሉም ወገን ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በሚደረገው ሂደት የበኩሉን ድጋፍ መወጣት ይኖርበታል።
ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት በዋነኛነት ባለሀብቱ በገንዘቡ አስፈላጊውንና የአቅሙን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። በገንዘቡና በአይነት መርዳት ይገባዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የመንግስት ሰራተኛው በትንሹም ቢሆን ከደመወዙ በማዋጣት፣ በእውቀቱና በጉልበቱ በማገዝ አለኝታነቱን ማሳየት ተገቢ ነው።
እንዲሁም ተፈናቃዮች የሚገኙባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ከተፈናቃዩ ወገን ጋር ሆነው ቤቱን መልሰው በመስራት ኢትዮጵያዊነት ገፊነት ሳይሆን አቃፊነት መሆኑን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በዘመቻ መልክ በጉልበታቸውና በእውቀታቸው ታግዘው የተፈናቃዩን ቤት መልሰው በመስራት የወገን አለኝታ መሆናችሁን በተግባር የሚያስመሰክሩበት ወቅት አሁን ነው፡፡
ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ለሃምሳ ሰው ደግሞ ጌጥ ነው። ተፈናቃይ ወገኖችን የማቋቋሙ ስራ መንግስት ላይ ብቻ የምንጥለው ከሆነ ልክ እንደ ሀምሳው ሎሚ ሁሉ ሸክም መሆኑ አይቀርም። ስለዚህ ሁላችንም ተጋግዘንና ተረዳድተን ይሄንን የመንግስትን ሸክም ወደ ጌጥ መቀየር ይኖርብናል።
ተፈናቃዮችን ክረምቱ ከመግፋቱ በፊት መልሶ ማቋቋሙ ጠቀሜታው ብዙ ነው። አንደኛ ተፈናቃዩ ወገን በወቅቱ ወደ እርሻ ስራው ስለሚገባ በቀጣዩ ዓመት ተረጂዎች እንዳይኖሩ ወይንም ቁጥሩ በእጅጉ የቀነሰ እንዲሆን ያደርጋል። የሃገራዊ የግብርና ምርት መጠን እንዳይቀንስ ያደርጋል፡፡ ዜጎች በአዲሱ ዓመት ወደ መደበኛ የዕለት ተዕለት ስራቸው እንዲመለሱም መንገድ ይከፍታል። ይሄ እንዲሆን ግን በአሁኑ ወቅት ጠንከር ብሎ ካልተሰራና ተፈናቃዩ ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀዬው ተመልሶ በእርሻ ስራው ላይ ካልተሰማራ የባሰ ችግር የሚሆነው ለቀጣዩ ዓመት ነው። ይሄ ደግሞ ለተፈናቃዩ ህዝብ ብቻም ሳይሆን ከእነሱ የግብርና ምርቶችን ገዝቶ ለሚጠቀመው የከተማ ነዋሪዎችም ትልቅ ስጋት መሆኑ አይቀርም።
በመሆኑም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተፈናቃይ ወገኖቻችንን ለማቋቋም በሚደረገው ሂደት ላይ ተባባሪ መሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት። ተፈናቃይ ወገኖቻችንን የማቋቋሙ ጥረት ደግሞ ክረምቱ ገፍቶ ከመምጣቱ በፊት ሊሆን ይገባል።!
አዲስ ዘመን መጋቢት 29ቀን 2011