አገራዊ ኃላፊነት በመሸከም የሰሩ ናቸው። ይሄ ልፋታቸው ጥንካሬና ታታሪነታቸው የክብር ዶክትሬት አስገኝቶላቸዋል። በተለይ በወባ የሚሞቱ ሰዎችን በመታደግ እና ስርጭቱን ለመግታት በተሰራው ስራ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢ በ1990 ዓ.ም ወባ የሰውን ሕይወት እየቀጠፈ ነበር። ችግሩ በ1990 ዓ.ም. ላይ ጎልቶ ይውጣ እንጂ፣ ከ1980 አጋማሽ ጀምሮ መባባሱ አልቀረም። የበረሃ በሽታ ማለትም ቆላ አካባቢ የሚከሰተው ወባ በደጋማ አካባቢዎችም መታየት ቀጠለ።
ይሄን ጊዜ እንዴት? ወገኔን ለምን? ወንድምና እህቴን ብለው ኢትዮጵያውያንን ወገኖቻቸውን ከሞት ለመታደግ ወሰኑ፤ ለራሳቸውም ቃል ገቡ « በወባ የሚሞት ሰው አይኖርም። ለዚህ ደግሞ ጠንክሬ እሰራለሁ» ብለው በ1990 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበርን መሠረቱ። በወባና በተለያዩ ጤና ነክ ጉዳዮች ላይ መሥራት ከጀመሩ እነሆ21 ዓመታትን አስቆጥረዋል፤ የዛሬው የ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› እንግዳችን የክብር ዶክተር አበረ ምሕረቴ። ቀሪውን የህይወት ጉዟቸውን እንዲህ ከአንደበታቸው አድምጠን ለንባብ አዘጋጅተነዋል። መልካም ንባብ!
ልጅነት ሲታወስ
የተወለዱት በቀድሞ አጠራሩ በጎጃም ክፍለ ሀገር በማቻከል ወረዳ የልርይ በሚባል መንደር ነው። የወታደር ልጅ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ አበረ ምህረቴ ከወላጅ እናታቸው ስመኝ መብራቴና ከወላጅ አባታቸው ምህረቴ የተመኝ በ1946 ዓ.ም ሰኔ 8 ቀን ተወለዱ። በስድስት ወራቸው ደብረ ማርቆስ ወላጆቻቸው ይዘዋቸው ገቡ። ኑሮአቸውን በጀመሩበት በደብረ ማርቆስ ከተማም እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም አስኳላ ገብተው ከቀለም ትምህርት ጋር ትውውቅ አደረጉ።
አባታቸው አቶ ምህረቴ የተመኝ የወህኒ ቤት ፖሊስ በመሆናቸው የተለያዩ ቦታዎች ይቀየሩ ነበር።የቅያሬው ምክንያት ደግሞ ዕድገት ወይም ለስራ ተፈልገው ሳይሆን ቅጣት ነበር። በንጉሱ ጊዜ ማንኛው ባለስልጣን ከሸዋ ነበር የሚሾመው ይህ ደግሞ አቶ ምህረቴን አያስደስታቸውም። ይህ ብቻ ሳይሆን የማዕረግ ዕድገትም ለማግኘት ለሹማምንቶቹ ጉቦ መስጠትም እንዲሁ አቶ ምህረቴን የሚያጋጫቸው አንዱ ምክንያት ነበር። እሳቸው ማንኛውም ሰው በስራው ማደግና መመስገን እንጂ በገንዘብ (በጉቦ) ማደግ አለበት ብለው አያምኑም ነበር። በዚህም ምክንያት ከአለቃቸው ጋር መስማማት አልቻሉም።
ሌላኛው ችግር ደግሞ አቶ ምህረቴ የዋህ ናቸው፤ ሌባ አይወዱም ነገር ግን ሽፍታ ያደንቁ ነበር። ስለዚህም ሽፍታ ታስሮ ሲመጣ እንደ ሌባ አያዩም ነበር። ታዲያ ይህንን የተረዱ ሽፍቶችም የአቶ ምህረቴን የዋህነት በመጠቀም ጠላ ጠጥተን እንምጣ፤ ለሽንት እያሉ በመውጣት በዚያው ይጠፉ ነበር።በዚህም ምክንያት አባታቸው የቅጣት አይነት ይፈራረቅባቸው ነበር፤ ከቅጣቱ መካከል ደግሞ ዝውውር አንዱ ነው፤ በዝውውሩ ማንኛውም ዓይነት መጓጓዣ የማይገባበት እና ለኑሮ አመቺ ያልሆነ ቦታ ነበር የሚላኩት፤ ለዛ ነው የያኔው ታዳጊ አበረም የተቆራረጠ እና ያልተረጋጋ የትምህርት እና የልጅነት ህይወት እንዲኖራቸው የሆነው። አቶ አበረም የስድተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አስኪጨርሱ ድረስ አባታቸው ሶስት ጊዜ ወደ ሞጣ ተቀይረዋል። አለቃው እንደገና ለአራተኛ ጊዜ ሊቀይራቸው ሲል የአቶ ምህረቴ የስራ ባልደረቦች ወደ አለቃው በመግባት እባክዎ ልጆቹ ተሰቃዩ፤ የተረጋጋም ትምህርት መማር አልቻሉም ቢያንስ ለመጓጓዣ እና ለትምህርት የሚመች ቦታ መድባቸው በማለት ተማጸኗቸው።አለቃውም ወደ ገጠሩ የአገሪቱ ክፍል አባታቸውን ሊመድቧቸው የነበረውን ትተው መጓጓዣ የሚገባበት ፍኖተ ሰላም ከተማ አዛወሯቸው።
በዚሁ ከተማም መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ፍኖተ ሰላምም ከሄዱ በኋላ አቶ ምህረቴ ያው በሽፍታ ላይ ያላቸው አቋም ባለመቀየሩ እዚያም ለአንዱ ሽፍታ በመፍቀዳቸው እና በመጥፋቱ ያለዕድሜያቸው ጡረታ እንዲወጡ ሆነ፤ ይህ ደግሞ በቤተሰቡ ላይ ችግር ይዞ መጣ።
አቶ አበረም ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሲሸጋገሩ አባታቸው ስራ አልነበራቸውም። በዚህም ምክንያት በጣም ተቸግረው ስለነበር የዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን ሊያቋርጡ ነበር። በወቅቱ መምህራን በራሳቸው ወጪ የተወሰነ ተማሪን በመርዳት ያስተምራሉ የሚል መረጃ ሰሙ። እናም መምህራኖቹን እንዲደግፏቸው መጠየቅ ጀመሩ። አቶ አበረ መምህራኖችን ለድጋፍ በሚጠይቁበት ጊዜ ሁሉም መምህራኖች የሚደግፉት ተማሪ እንዳላቸው እና ጊዜውም እንዳለፈ ነገሯቸው፤ በዚህም ተስፋ ቆረጡ፤ ትምህርቱን አቋርጠው ለመመለስ ያላቸው ሁለት ሳምንት ነበር። ታዲያ አንድ ቀን የፈረንሳይ ቋንቋ አስተማሪያቸው ኢብ ለቦኘክ አስተምሮ ሲወጣ ተከትለው ወጥተው ችግራቸውን ነገሩት። መምህሩም ልክ እንደሌሎቹ መምህራን እንደማይችል ነገራቸው። እሳቸውም ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እንደማያዩት ሊያቋርጡ እንደሆነ አስረዷቸው። ያኔ መምህሩ በሳምንት ሁለት ሁለት ብር እሰጥሃለው ተማር አሏቸው። እሳቸውም በጣም ደስ አላቸው። ትምህርታቸውን ቀጠሉ። በሂደትም በወር አስራ ሁለት ብር ይሰጣቸው ጀመር። እንዲህ እንዲህ እያሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
የእድገት በህብረት ዘመቻ
ለአገራቸው ከሰሩት አንዱ የእድገት በህብረት ዘመቻ እንደሆነ አቶ አበረ ያወሳሉ። በዘመቻው ብዙ ተማሪ ደስተኛ ባይሆንም አቶ አበረ ግን በፍቃደኝነት ወደው ፈቅደው በመሄድ በተመደቡበት ቦታ ታሪክም የማይሽረው፤ ነዋሪውም የማይረሳው ስራ ሰርተዋል። የመጀመሪያው ስራቸው የመሰረተ ትምህርት ማስተማር ሲሆን ይህንንም በሚገባ ተወጥተውታል። ሌላኛው ደግሞ የመሬት ይዞታ ትምህርት አስተምረዋል፤ በጉልበትም ቢሆን የምንጭ ውሃ የማጎልበትም ስራ ሰርተዋል። አቶ አበረ ዘመቻውን ሲዘምቱ እንዲሰሩ የተላኩት የመሰረተ ትምህርቱን ብቻ ቢሆንም በፍላጎት ስለሆነ የሄዱት ለውጥም አመጣለው ብለው ስላሰቡ ሁለገብ ሆነው አገልግለዋል። ኮሚቴ በመሆንም ትልልቅ ስራዎችን ማሰራታቸውን ሲያስታውሱ ዛሬ ድረስ ደስታ ይሰማቸዋል።
የትዳር እና የሥራ ህይወት
ጊዜ ፈቃዱ ሆኖ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል አዲስ አበባ ገቡ። የደረሳቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ የሳይንስ ትምህርት ክፍል ነበር። ነገር ግን አንድ የፈረንሳይ መምህራን ኮሌጅ የሚባል መምህራንን በፈረንሳይኛ ቋንቋ በመምህርነት በዲግሪ የሚያስመርቅ ተቋም የአቶ አበረን ቀልብ ሳበ። ምክንያቱም ያኔ ኮሌጁ ለተማሪዎች በወር ሃምሳ ብር ይሰጥ ነበር። ይህ ደግም ለአቶ አበረ ያለምንም ችግር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያደርጋቸዋል። በዚህም የተነሳ ኮሌጁን ሊቀላቀሉ ችለዋል። ከኮሌጁም በፈረንሳይኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማግኘት የፈረንሳይኛ ቋንቋ መምህር በመሆን ወደ ስራ አለም ተቀላቀሉ።
ሶስት ጉልቻ የመሰረቱት የዘር ሐረጓ ከአደሬ ከሚመዘዘው ወይዘሮ ማሪያ አብዱልቃድር ነው። በትዳር ቆይታቸው ሁለት የአብራካቸው ክፋዮች ማፍራት ችለዋል። አቶ አበረ ለመሰረቱት ጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማህበር ዋነኛውን ሚና የተጫወቱት ባለቤታቸው እንደሆኑም ይናገራሉ።
የጸረ ወባ ማህበር ምስረታ
አገር ሰላም ብለው የመምህር ህይወታቸውን እየመሩ ሳለ ወባ ህዝቡን እየጨረሰ መሆኑን መስማት ጀመሩ። በወቅቱ የነበሩ መሪዎች ለፖለቲካ ፍጆታቸውም ብለው በግልጽ የተከሰተው ችግር ምን እንደሆነ አይነገርም ነበረ። ታዲያ በአቶ አበረ አነሳሽነት በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በመሰብሰብ በእለቱ እርሳቸውን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ሆነው በመነጋገር የተለያዩ ጥናት በማድረግ ለማህበር ምስረታ መሰረት ጣሉ። ከዛ በኋላ ነው ለአቶ አበረ ፈታኝ ጊዜ የሆነባቸው። እርሳቸው ኮሚቴ ሆነው መመረጥ አይፈልጉም ምክንያቱም በወቅቱ ሁለት ስራ በተሻለ ገቢ ይሰራሉ፤ ከተመረጡ ደግሞ ቢያንስ አንዱን ስራ መተው ሊገደዱ ነው። መስራች ከሆነው ጓደኛቸው ጋር በመሆን የማይመረጡበትን ዘዴ አበጅተው እና መክረው ስራ አስፈጻሚ ወደሚመረጥበት አዳራሽ ቢገቡም ሊሆን አልቻለም፤ ተመረጡ። በዚህም መሰረት መጀመሪያውኑ እንደፈሩት አንዱን ስራቸውን አቋርጠው ለማህበር ህልውና ቀኝ እጅ ሆነው ቀጠሉ።
ታዲያ በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢ በተለይ በአቶ አበረ የትውልድ ቦታ እና ከተማ ደግሞ ይበልጥኑ ወባ የሰውን ሕይወት እየቀጠፈ መጣ። ችግሩ በ1990 ዓ.ም. ላይ ጎልቶ ይውጣ እንጂ፣ ከ1980 አጋማሽ ጀምሮ መባባሱ አልቀረም። የበረሃ በሽታ ማለትም ቆላ አካባቢ የሚከሰተው ወባ በደጋማ አካባቢዎችም መታየት ጀመረ። በሰሜኑ በተለይም ጎጃም የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ የሚታወቀው ወባ ተስፋፋ። ቀድሞ ከባህር ወለል ከ1 ሺህ 500 በላይ የማይከሰተው ወባ ከባህር ወለል በላይ እስከ 2 ሺ መከሰት ጀመረ። ሰዎች በብዛት መታመምና መሞት ጀመሩ። ወደ ሐኪም ቤት የሄዱ እንኳን አይድኑም ነበር። በመሆኑም በ1990 ዓ.ም. ከሚያዚያ እስከ ሰኔ በነበሩት ወራት በጎጃም ደንበጫ በሚባል ከተማ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ብቻ በቀን እስከ 12 ሰው ይቀበር እንደነበር ያስታውሳሉ። ከደንበጫ አዲስ አበባ የመጣ ሰው ደንበጫ ላይ ሕዝቡ እያለቀ መሆኑን ሲነግራቸው ‹‹መንግሥት ሕዝቡን ሊጨርስ ነው›› ብለው መነሳታቸውን ያስታውሳሉ። ለዚህም የባለቤታቸው አስተዋጽኦ ቀላል አልነበርም። ‹አንተ ለሕዝብ ምን አድርገሃል› ስትላቸው፣ እውነት ነው በማለት ጥቂት ጓደኞቻቸውንና ዘመዶቻቸውን አሰባስበው ደንበጫ ላይ በወባ የሚያልቀውን ሰው ለማዳን መነሳታቸውን ይናገራሉ። አቶ አበረ ምሕረቴ በ1990 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበርን መሥርተው በወባና በተለያዩ ጤና ነክ ጉዳዮች ላይ መሥራት ከጀመሩ 21 ዓመታትን አስቆጥረዋል። ወባ በተለይ በደንበጫ አካባቢ ያደረሰውን እልቂት ለማርገብና ብሎም ለወደፊቱ ለመቆጣጠር ነበር። በደንበጫና በሌሎች አካባቢዎች በወባ ዙሪያ ስራ ለመስራት የመጀመሪያ እንቅስቃሴያቸውን ጀመሩ።
ሁሉንም ጎጃም ባያጠቃልልም አዊ፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃምና ባህር ዳር ልዩ ዞን ላይ ትኩረት አድርገው ነበር። ሥፍራዎቹ ደጋማ ቢሆኑም ወባ ከፍተኛ እልቂት ያደረሰበት ነበር። በባህር ዳር ደንበጫ፣ ጫጫ፣ ይልማና ዴንሳ፣ ቡሬ፣ ቋሪት ወረዳዎች፤ በምሥራቅ ጎጃም ሸበል በረንታ፣ ሞጣ ወረዳዎችን ጨምሮ 29 ወረዳዎች በወባ ተጠቅተው ነበር። አለማቸው ሕዝቡን ከሞት ማዳን ነው። ምዕራብ ጎጃም ዞን ትኩረት የሚሻ ስለነበር ከአካባቢው ጤና ቢሮ መረጃ ሰብስበው ገንዘብ በማፈላለግ፣ መድኃኒት ገዝተውና ባለሙያ አሰባስበው ገበያ ላይ ሳይቀር መመርመርና ሲታመሙ መድኃኒት መስጠት ጀመሩ።
የሕክምና ባለሙያዎችም በየጤና ጣቢያ እየገቡ ዕገዛ አደረጉ። ለውጥ መታየትና ብዙዎችም መዳን ጀመሩ። ዓላማችን ሕዝብን ከሞት ማዳን ነበር። በእኛ ግምትም ከ180 ሺ በላይ አደጋ ላይ የነበረ ሕዝብ አድነናል። ችግሩ ከግንዛቤ እጥረት የመነጨም ስለነበር መጻሕፍትና በድምፅ የተቀረፀ ማስተማሪያ ጭምር በማዘጋጀትና በጎ ፈቃደኞችን ከዩኒቨርሲቲ አሠልጥነን በማሰማራት ህዝቡን ከሞት የመታደጉን ስራ ሰራን።
1990 ዓ.ም. መጨረሻ ተቋቁመው 1991 ዓ.ም. ክረምት ላይ 2 ሺ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አሠልጥነው በኢትዮጵያ አሰማርተዋል። በ1992 ደግሞ 1 ሺ 500 አሠልጥነው ተመሳሳይ ስራ እንዲሰሩ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። በ1993 ዓ.ም. በኤድስ ዙሪያ የሚሠሩ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገንዘብ እየከፈሉ ማሰማራት ስለጀመሩ እነርሱ ማቆማቸውን ያወሳሉ። በዚህም ምክንያት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ፊታቸውን በማዞር በጎጃም በሚገኙ 23 ትምህርት ቤቶች ያሉ ተማሪዎች ለሁለት ክረምት ኅብረተሰቡን እንዲያስተምሩ አድርገዋል። ወጣቶች፣ እድሮች፣ የሴት ማኅበራት አደራጅተው በወረዳ ደረጃና በቀበሌ ፀረ ወባ ኮሚቴ እያዋቀሩ ዘመቻ አካሂደዋል። ዘመቻው የመንግሥት ድጋፍ ነበረው። በሥፍራው የነበረውን ጭንቅ የገላገለም ነበር።
በስራቸው መካከል ግን ከአየር ትንበያ ጋር በተያያዘ እክል ገጥሟቸው ነበር። ከተለያዩ ወረዳዎች የሚመጣው የወባ ሪፖርት ከአየር ንብረቱ ጋር አልጣጣም እንዳላቸው ያስታውሳሉ። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሲያጤኑ፣ ለሥራ ሌላ አካባቢ ሄደው የሚመለሱ ይዘውት የሚመጡት የወጪ ችግር መሆኑን ደረሱበት።
ከዚህ በኋላ ለሥራ የሚወጡ ሰዎች እንዲመዘገቡ ሲመለሱ ምርመራ እንዲያደርጉ ተደረገ። ከአንድ ቀበሌ ለሥራ የወጡ 182 ሰዎች ሲመለሱ መርምረው፣ 78ቱ ላይ ወባ አግኝተዋል። መጀመሪያ ላይ አጎበር ተጠቃሚውም 15 በመቶ ነበር። አጎበር የሚጠቀም፣ የሌለው፣ እያለው የማይጠቀም እያሉ በር ላይ በቀለም ምልክት በማድረግ የተጠቀሙት ዘዴ 93ነጥብ7 በመቶው አጎበር እንዲጠቀም አስችሏል። ይኼንን በሠሩባቸው አካባቢዎች በወባ ምክንያት ሞት የለም። እስካሁንም 200 ትምህርት ቤቶች ላይ ሠርተዋል። ለሥራቸውም የሃይማኖት አባቶችንም ተጠቅመዋል።
አቶ አበረ እና ማህበራቸው በወባ ስራ ላይ ብቻ አልተጠመዱም፤ ይልቁኑ የኅብረተሰብን ደህንነት መጠበቅ፣ ደህንነቱ በተጠበቀ አካባቢ እንዲኖር፣ ለመኖሪያ ምቹ የሆነ አካባቢ መፍጠርና ኅብረተሰቡም ይኼንን ማግኘት አለበት የሚለውን ዓላማ በማድረግም ታላቅ ስራ ሰርተዋል። አቶ አበረ ሲናገሩ “ለዚህ በጤናው ዘርፍ መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ። አንደኛው ዕውቀት ነው። የእኛ ሕዝብ መሠረታዊ የጤና ግንዛቤ እጥረት አለበት። ስለሆነም ይኼንን መለወጥ ይገባል። ወባ፣ ኤችአይቪ፣ የግልና አካባቢ ንፅህና፣ ሥነ ተዋልዶ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ መሠራት አለበት። ለምሳሌ ወባና ኤችአይቪን ብንወስድ ለወባ አካባቢን ንፁህ ማድረግ፣ ከአቆረ ውኃ መጠበቅና ቤትን በንፅህና መያዝ አለብን። ለኤችአይቪም ቢሆን የግልና የአካባቢ ንፅህና ብሎም የሥነ ተዋልዶ ጤና መጠበቅ ግድ ነው። ስለሆነም የተቀናጀ የጤና ፕሮግራም የጀመርነው ቀድመን ነው።”ይላሉ።
በአገር አቀፍ ደረጃ የማስተማሪያ ጽሑፎችን ለየክልሉ አሰራጭተዋል። በድምፅ የተቀረፀ የ60 ደቂቃ ካሴት አዘጋጅተው አገር አቋራጭ አውቶቡሶች በቀን ቢያንስ አንዴ እንዲከፍቱ፣ በሻይ ቤቶችም እንዲደመጥ አድርገዋል። በቪዲዮ የተደገፈ ትምህርት አዘጋጅተው አርሶ አደሩን ማወያየት የማስተማሪያና የማሳወቂያ መንገዳቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ፈታኙ ጊዜ
«የሰው ፊት ይፋጃል» የሚል አባባል ሰምተናል። አቶ አበረም የሰው ፊት ማየት ከባድ ነው ይላሉ።ለማህበሩ ገንዘብ ለማፈላለግ የሚያደርጉት ጥረት እጅግ ፈታኝ እና አስከፊ እንደነበር ይናገራሉ። ይህንን ተቋቁመን እንኳ ለመጠየቅ የሄድንበት ቦታዎች ላይ የምናገኘው ምላሽ ተስፋ አስቆራጭ ይሆናል። በዚህ መልኩ እርዳታ የመጠየቁ ሂደት የተጓዘው ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ነበር። ከዛ ሌላ አዲስ አበባ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እየጠየቁ ነበር ስራውን የሚሰሩት።
ሌላው ህብረተሰቡ ወባ በሽታን እንደ በሽታ አለመቀበሉ ሌላኛው ችግር ነበር። ከዛ ይልቅ የፈጣሪ መቅሰፍት ነው፤ ተስቦ ነው እና የመሳሰሉትን ስያሜ መስጠት አለ። ይሄ ደግሞ ከአቶ አበረ እና ጓደኞቻቸው ጋር ከመተባበር ይልቅ ወደ ባዕድ አምልኮ እና የሀይማኖት ቦታዎች በመሄድ ለጉዳት እንዲዳረጉ አድርጓል። ይህንን የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ለመቀየር የሄዱበት ርቀት እና ያስከፈላቸው ዋጋ አሁን ድረስ እጅግ ከባዱ ጊዜ ብለው አንዲያስታውሱት አድርጓቸዋል።
ስኬት
መጋቢት 12 ቀን 1991 ዓ.ም. የገቢ ማሰባሰቢያ አዘጋጅተው 523 ሺ ብር አገኙ። በወቅቱ ብዙ ገንዘብ ነበር። ከውጭም በዶላር ይላክላቸው እንደነበር ይናገራሉ። ያኔ እርሳቸውም ከአዲስ አበባ ሲወጡ የሆቴልና የትራንስፖርት ይከፈልላቸው ነበር እንጂ ነፃ አገልጋይ ነበሩ።
በአማራ ክልል በክረምት ውኃ መሻገር የማይቻልባቸው አካባቢዎች አሉ። በመሆኑም በርካታ ቦታዎች ላይ የብረት ድልድይ ሠርተዋል። ሁለት የወጣት ማዕከላት በደንበጫና በዳንግላ ከተማ አስገንብተዋል። በደንበጫ ቤተ መጻሕፍት፣ ባህር ዳር ላይ ክሊኒክ ገንብተዋል። ለኅብረተሰቡ ይጠቅማሉ የሚባሉ ነገሮች ላይ ሁሉ ይሰማራሉ። ጊኒዎርም ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርገዋል። ሬሽሚኒያስስ (በአንዳንድ አካባቢ ቆንጥር ይባላል) ማለትም አፍንጫ ላይ የሚቆስለው ላይ ትምህርት ሰጥተዋል።
ለወባው መስፋፋት ምክንያቱ ምን እንደነበር በተቀናጀ መልኩ ማጥናት እና ማጤን ጀምረዋል፤ አንዱ ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ ነበር። በአገር ውስጥ የሜትሪዎሎጂና የወባ ባለሙያዎች ቢኖሩም፣ ተገናኝተው አይናበቡም ነበር። ስለዚህ ማኅበሩ አዲስ እንቅስቃሴ ጀመረ። ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሁለቱን በማገናኘት እንዲወያዩና አብረው እንዲሠሩ አደረጉ። ከፈረንሣይ ድርጅት ጋር በመሆንም በድሬዳዋ፣ ሐዋሳ፣ ጅማ አዊና ባህር ዳር ላይ ስድስት የሙከራ ጣቢያ አድርገው የሜትዎሮሎጂና የሕክምና ባለሙያዎች እየተገናኙ መረጃ እንዲለዋወጡ፣ ወባ ሊከሰት ይችላል አይችልም የሚለውን እንዲተነብዩ ማድረግ ጀመሩ ጥሩ ውጤት አገኙበት።
ላለፉት አራት ዓመታት ከግማሽ ከአሜሪካ ሳውዝ ዳኮታ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የአማራ ክልልን የትንበያ ሥራ ለብቻ አጥንተዋል። በጥናቱ የ45 ወረዳዎችን ተሞክሮ ወስደው በየሳምንቱ የወባን ሁኔታ መተንበይ የሚያስችል ሥርዓት ዘርግተዋል። ሥራውን እንዲቀጥሉበት ለባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ለክልሉ ጤና ቢሮ አስረክበዋል። የባህሪ ለውጥ ላይ መሥራት አለብን ብለው ስለሚያምኑ ወባን በተመለከተ የአቻ ለአቻ ትምህርትም አላቸው። የባህሪ ለውጥ ካመጣን፣ በፖለቲካው እና በአገራችን ዕድገት ላይ ለውጥ እንደሚመጣም ያምናሉ። “አዕምሮአችን ላይ ለውጥ ካላመጣን፣ አሁን ባለን አያያዝ ለውጥ አናመጣም። ልጆቻችን ላይ መሥራት አለብን። ልጆች ወላጆችን መቀየር ይችላሉ። ላለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ ወረዳዎች የአቻ ለአቻ ትምህርት እየሰጠን ነው። ማኑዋልም ተዘጋጅቷል። በዚህ ለውጥ ዓይተናል።”ሲሉ አቶ አበረ ይናገራሉ።
እውቅና
አቶ አበረ ከተለያዩ ድርጅቶች ከሚደረግላቸው ሽልማት በላይ ሁሌም የሚያስደስታቸው ከህዝቡ የሚቀበሉት ምስጋና ነው። ይሄ ደግሞ ይበልጥ እንዲሰሩ ብርታት ሆኗቸዋል። ያም ሆኖ ደግሞ ይሀው ለልፋትህ የሚላቸው አላጡም። ምክንያቱም ስራቸው ያስመሰግናልና ነው። ከጣና አዋርድ የዋንጫ ሽልማት፣ ከቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ እጅ የምስክር ወረቀት እንዲሁም ባሳለፍውነው ዓመት ደግሞ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት አግኝተዋል። እኛም ዕድሜ፣ ጤናና ተጨማሪ ስኬት እንዲበዛላቸው ተመኘን። ገና ብዙ ስራ መስራት አለባቸውና ለብርታቱም ጉልበት እንዲሆናቸው ፈጣሪን ተማጸንን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2011
አብርሃም ተወልደ