– ባንኩ አንድ ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ሰብስቧል
አዲስ አበባ፡- እኤአ በ2023/24 የሂሳብ ዓመት አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 282 ቢሊዮን ብር መድረሱን የአዋሽ ባንክ አስታወቀ። ባንኩ አንድ ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መሰብሰቡን ጠቁሟል፡፡
የአዋሽ ባንክ አክሲዮን ማህበር የባለአክስዮኖች 29ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ትናንት በአዲስ አበባ አካሂዷል። የአዋሽ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጉሬ ኩምሳ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ አዋሽ ባንክ እኤአ በ2023/24 የሂሳብ ዓመት አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 282 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
አዋሽ ባንክ አ.ማ በ2023/24 የሂሳብ ዓመት 10 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አስመዝግቧል ያሉት አቶ ጉሬ ፤ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የብር አንድ ነጥብ 06 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ተመዝግቧል ብለዋል።
በዓመቱ ውስጥ ባንኩ 45 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡን ጠቅሰው፤ የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ ብር 232 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል።
የባንኩ አጠቃላይ የብድር መጠን 183 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ደርሷል ያሉት ሰብሳቢው፤ በሂሳብ ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ገቢ 36 ነጥብ 58 ቢሊዮን ብር ተመዝግቧል ብለዋል። ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ አንድ ነጥብ 52 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
በሂሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን ብር 282 ቢሊዮን መድረሱን ጠቅሰው፤ የባንኩ የቅርንጫፍ ቁጥር 947 መድረሱን ገልጸዋል።
አጠቃላይ የደንበኞች ብዛት 12 ነጥብ 41 ሚሊዮን በላይ መሆኑ የገለጹት ሰብሳቢው፤ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ11ሺ በላይ የደረሰ ሲሆን የተከፈለ የካፒታል መጠኑ ደግሞ ከ20 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል ብለዋል።
ባንኩ የተለየዩ ስትራቴጂዎችን በመቀየሰ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን አመልክተው፤ ቦርዱ በዓመቱ የሀገሪቱን የፋይናንስ ሕግና የብሔራዊ ባንክ መመሪያዎችን በጠበቀ መልኩ የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ማጽደቁን ገልጸዋል።
ባንኩ ለህብረተሰቡ የባንክ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ በኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና አካባቢዎች ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
አዋሽ ባንክ ዘመናዊ አዲስ የዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ ለመገንባት 10 ሺህ 500 ካሬ ሜትር መሬት በሊዝ መረከቡን ገልጸው፤ ለህንጻው ግንባታ የፕሮጀክት ቢሮ ተቋቁሞ የግንባታውን ዲዛይን ለማሠራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም