አዲስ አበባ፡- የብልፅግና ፓርቲ ስኬቶችን ለማስቀጠልና ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ አበክሮ እንደሚሠራ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል “የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ትናንት ተከብሯል።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ፤ ብልፅግና በሃሳብ ልዕልና የሚያምን፤ ኢ-ፍትሃዊነት፣ አግላይነት፣ የነጠላ ትርክት የበላይነትና ሌሎች ችግሮችን በሃሳብ ልዕልና ለመፍታት በፅኑ መሠረት ላይ የተመሠረተ ፓርቲ ነው።
ያልተገራ ስሜትና ፅንፈኝነት የሚገራው፤ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው፣ የሕዝብ ኑሮ የሚሻሻለው፣ ብሔራዊ ጥቅም የሚከበረው፣ የጥራትና የኢፍትሀዊነት ችግሮች የሚቀረፉት፣ ማህበራዊ ፍትህ የሚነግሰው በሃሳብ ልዕልና ብቻ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ፓርቲው ስር የሰደዱ ሀገራዊ ችግሮችን በመቅረፍ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ሕልም ሰንቆ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
“መዳረሻችን ሁለንተናዊ ብልፅግና፤ አንድነት፣ ሕብረ ብሔራዊነትና አካታችነት ነው” ያሉት አቶ አደም፤ ሁሉም ሰው በደስታና በክብር የሚኖርበት፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና ማህበራዊ መስኮች በሁሉም ለሁሉም በሆነ አግባብ ስኬት ለማረጋገጥ እየተጋን ነው ብለዋል።
በጋራ ከሠራን ሀገራዊ ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚቻልም የፓርቲው የአምስት ዓመታት ጉዞ በተግባር ማሳየቱን ነው ያስረዱት።
በበሳልና ብቁ መሪ፣ በቁርጠኛ አመራርና አባላት እንዲሁም በሕዝብ ድጋፍ ታጅቦ በፈተናዎች ሳይዛነፍ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።
የፖሊቲካ ምህዳር ማስፋት መቻሉ፣ የአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ መጀመሩ፣ እውነተኛ ፌዴራሊዝም እየተገነባ መሆኑ፣ ምርታማነትን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ዕውን ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች ከስኬቶቹ መካከል በዋቢነት ገልፀዋል።
በኢኮኖሚ መስኮች በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በኮሪደር ልማት የተመዘገቡ ስኬቶች እንዲሁም በማህበራዊ መስኮች የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የተከናወኑ የማህበራዊ አገልግሎት ተግባራትን ጠቅሰዋል።
በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ረገድም በዓለም መድረክ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ ወዳጅ ሀገራት ማብዛትና የብሪክስ አባልነትን ለአብነት አንስተዋል።
በአጠቃላይ ብልፅግና በተመሠረተ በጥቂት ዓመታት ውስጥ መልከ ብዙ ስኬቶች ያስመዘገበ ፓርቲ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።በቀጣይም ስኬቶችን ለማስቀጠልና ሀገራዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ አበክሮ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም