አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የፀረ- ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ።
በኢትዮጵያ ምግብና የመድኃኒት ባለሥልጣን መድኃኒት ደህንነት ክትትልና የህክምና ሙከራ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ አስናቀች አለሙ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች ደህንነቱ የተጠበቀ የሕክምና ሂደቶችን ለማረጋገጥና ለተለያዩ የሕክምና ሂደቶች ወሳኝ ሚና አላቸው። የውጤታማ ፀረ- ተህዋሲያን መድኃኒቶች እጥረት የሕክምና አገልግሎቶችን በማወክ በተለይ የታካሚዎች ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል ለአካል ጉዳት ከፍ ሲል ለሞት ይዳርጋል።
ፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በተህዋሲያን መላመድም የበሽታ አምጪ ጀርሞችን ለማስወገድ ጥቅም ላይ የሚውሉ መድኃኒቶች አቅም ሲፈተን የሚከሰት ነው። በሰዎች፣ በእንስሳትና በእፅዋት ላይ መድኃኒቶችን ያለ አግባብ መጠቀምም መድኃኒቶች በተህዋሲያን በቀላሉ እንዲላመዱና በሽታ ፈዋሽነታቸውን እንዲያጡ ያደርጋል።
‹‹በኢትዮጵያም የፀረ- ተህዋሲያን መድኃኒቶች በተህዋሲያን መለመድ ችግር አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ ደርሳል›› ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ፣ በችግሩ ምክንያት በሀገሪቱ በዓመት ከ106 ሺ በላይ ሰዎች ለህልፈት እንደሚዳረጉ በጥናት መረጋገጡንም አስታውቀዋል። ይህም ከፍተኛ የሚባል የሞት ቁጥር መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር የጤና፣ የግብርና እና የአካባቢ ጥበቃን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ የጋራ ስትራቴጂ ተቀርፆ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህም የግንዛቤ ፈጠራ፣ የቅኝት ሥራዎች፣ የመድኃኒት ጥራትና ደህንነት እና የግልና አካባቢ ንፅህናን ማስጠበቅ እንዲሁም ከመድኃኒት አግባብአዊ አጠቃቀም ጋር የተዛመዱ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
ችግሩን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ መሆኑንና መንግሥታትም ምርምር ላይ ኢንቨስት ማድረግን ጨምሮ መረጃዎችና ስልቶችን መለዋወጥ አለባቸው›› ብለዋል።
በሀገር ደረጃ ችግሩን ለመከላከልም፣ በተለይ በጤና እንክብካቤና በግብርና ላይ ፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች አጠቃቀምን በተመለከተ ጥብቅ ደንቦችን መተግበርና ፀረ- ተህዋሲያን መድኃኒቶች ተጠያቂነት ባለው አጠቃቀም ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የግልና የአካባቢ ንፅህናና ጤናን መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፀረ- ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት ከህዳር 9 እስከ 15 ‹‹እናስተምር፣ እናሳውቅ፣ አሁን እንተግብር›› በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል።
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በተህዋሲያን መላመድ ምክንያት እኤአ በ2019 በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም