የዕንቁ መንገድ- የጂኦቱሪዝም እሳቤ

እንቁ ሙሉጌታ አብርሀም ይባላል። በኢትዮጵያ የቱሪዝምና የማዕድን ዘርፍ ላለፉት 30 ዓመታት አገልግሏል። ‹‹በዓለም ትታይ ኢትዮጵያ›› የአስጎብኚ ድርጅት በመመስረት የኢትዮጵያን የመስህብ ሀብቶች እያስጎበኘ ይገኛል። በተለይ በስነ ምድር ሳይንስና በከርሰ ምድር ሀብት ጥናት እና በጂኦ ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ አለው። የጂኦ-ቱሪዝም በኢትዮጵያ በፖሊሲ ተደግፎ ተግባራዊ እንዲሆን፤ የአገሪቱ ሀብቶች ለዓለም እንዲተዋወቁ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ከሚገኙ አንጋፋ ባለሙያዎች ቀዳሚው ነው። ለዛሬ የዝግጅት ክፍላችን ” የሕይወት ገፅታ ” አምድ እንግዳችን አድርጎታል።

ትውልድ እና እድገት

እንቁ ሙሉጌታ ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ነው፤ ግዜው ደግሞ 1963 ዓ.ም። ቤተሰቦቹ ትምህርትን የመቀበል እድሜ ላይ ሲደር በመኖሪያ አካባቢያቸው (መስቀል ፍላወር) ወደሚገኝ ‹‹ፒተር ፓን›› የሚባል መዋለ ሕፃናት አስገቡት። እናቱ ወይዘሮ መፅሄት ተፈራና አባቱ መቶ አለቃ ሙሉጌታ አብርሀም ለትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጡ ነበሩ። ትምሀርት ወዳድ መሆናቸው ደግሞ ለዛሬው የእንቁ የሙያ መንገድን የጠረገም ነበር።

በመዋለ ሕፃናት ትምህርት ቤት ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ ሲከታተል ቢቆይም አባቱ መቶ አለቃ ሙሉጌታ በደርግ የአውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው ወደ ጎጃም (ደብረ ማርቆስ) ተሹመው በመሄዳቸው ምክንያት ቤተሰቡ አዲስ አበባን ለመልቀቅ ተገደደ። እንቁም የአዲስ አበባን የከተማ ኑሮ ከሁለት ወንድሞቹ ጋር ሆኖ ተሰናበተ።

ባለታሪካችን ‹‹ከዘመናዊው የመዋለ ሕፃናት ትምህርት ወደ ቄስ ትምህርት ቤት ገባሁ›› ይላል በወቅቱ የሕይወት አቅጣጫው የተቀየረበትን አጋጣሚ ሲያስረዳ። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያውያንን አብሮነት፣ ፍቅርና መተሳሰብ በገጠሪቱ ክፍል የተማረበትና ልዩ ስብዕናን የገነባበት እንደነበር ይናገራል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው ንጉስ ተክለሀይማኖት አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እውቀት ለማስታጠቅ የተቀበለው ነበር። በአዲስ አበባ ያገኘው እውቀት ቋንቋ ላይ እንዲጎብዝ ሲያግዘው፤ በጎጃም ከተማረው የቄስ ትምህርት ጋር ተዳብሎ ጠንካራውን፣ ትምህርት ወዳዱን እንቁ ፈጠሩ።

የስብዕና ግንባታ

እንቁ ዛሬም ድረስ ለተሰማራበት ሙያው ወዳድነት መሰረት የሆነው እና ስነ ምግባሩን በመልካም የቀረፀው የልጅነት አስተዳደጉ ነው። በግዜው ከመምህራኖቹ ከቤተሰቦቹ ልዩ ድጋፍ ማግኘቱ በእጅጉ እረድቶታል። በተለይ ኢትዮጵያዊ እሴት እና ባሕሉን በሚያከብር ማሕበረሰብ መካከል የመኖር እድል ማግኘቱ አስቸጋሪ የሕይወት አጋጣሚዎችን እንዲቋቋም አድርጎ ቀርፆታል።

በጊዜው በደርግ መንግሥት ምክንያት በኢትዮጵያ የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ስላልነበር ገና በልጅነቱ ነበር አባቱን በሞት የተነጠቀው። ይህ አጋጣሚ የእንቁ የልጅነት የፈተና ወቅት ነበር። መንግሥት እራሱ የሾማቸውን አባቱን ወደ እስርቤት አስገብቶ ለሞት ከዳረጋቸው ወዲህ ለአጭር ወቅትም ቢሆን የልጅነት ጊዜውን አዋክቦታል። አጋጣሚው የባሕሪ ለውጥ ከማምጣት አንስቶ ትኩረቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመውሰድ ታግሎት ነበር። ነገር ግን የእናቱ፣ የዘመዶቹ እንዲሁም የአካባቢው ማሕበረሰብ ጠንካራ ክትትል የማይሰበረውን እንቁ ሰርተው በትምህርቱ እና በባሕሪው ጠንካራ የሆነውን ማንነቱን ገነቡ። ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት አንስቶ ዩኒቨርሲቲ አስኪገባ ድረስም በቀለም ትምህርት ከፍተኛ ውጤት የሚያመጣ ልጅ ሆነ።

የሕይወት ዝንባሌ

እንቁ ለቀለም ትምህርት ካለው ዝንባሌ ውጪ በሌሎች ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ ነበር። ገና በ14 ዓመቱ በወቅቱ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለምን ተከትሎ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ በሚተላለፉ የሞስኮ ራዲዮ (የአማርኛ ድምፅ ዲፓርትመንት)፣ የምስራቅ ጀርመንና የቡልጋሪያ ስርጭቶች ላይ በንቃት ይሳተፍ ነበር። ርዕዮተ ዓለሙን የተመለከተ ፅሁፎችን በመፃፍ ይላላክ ነበር። በተሳትፎው የትምህርት እድሎችን (በእድሜው ማነስ ምክንያት ባይሳካም)፣ የሌኒን ዓርማ ያለው ባጅ እና ሌሎች ሽልማቶቸን ያሸንፍ ነበር።

እንግዳችን የሆነው የዛሬው የስነ ምድር እና ቱሪዝም ባለሙያ በታዳጊነት ዘመኑ ለየት ያለ ዝንባሌም ነበረው። ይህ ፍላጎት ለተፈጥሮ ያለው ልዩ ተመስጦና ቁርኝት ነበር። ከታዳጊነቱ ጀምሮ የተለያየ ቀለማት ያላቸው አፈሮችን አመጣጥ፣ አፈጣጠር ለማወቅ ጥረት ያደርግ ነበር። ከዚያም ባለፈ ራቅ ወዳለው ወደ አያቶቹ መንደር ሲያቀና በተራሮችና ጉብታዎች ላይ የሚያስተውላቸው በየዘመን የተፈጠሩ የአፈር አይነቶችንና አቀማመጣቸውን ይመለከት ነበር፤ በፌስታል ለናሙና በመውሰድ የአፈጣጠር ሚስጢራቸውን ለማወቅ ጥረት ያደርገ እንደነበር ያስታውሳል።

‹‹በምኖርበት አካባቢ ከነበረው ከባሕሉ፣ ከኑሮ ዘይቤና እሴቶች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ነበረኝ›› የሚለው እንቁ ሙሉጌታ፤ ይህ ተፈጥሮና ሕዝብ ላይ ልዩ ዝንባሌን እንዲያዳብር መሰረት እንደሆነው ይገልፃል። አሁንም ያልተለየውን ጥብቅ የተፈጥሮና የመልከዓ ምድር ወዳጅነት በጠንካራ መሰረት ላይ የታነፀውም በያኔው የልጅነት ዘመኑ ነው። አስተዳደጉ ዛሬም የሚመነዝረው የእውቀት፣ የስነ ምግባርና የማሕበራዊ እሴት ዝንባሌን አጎናፅፎታል።

ከፍተኛ ትምህርት

መምህራን እንቁን ጨምሮ ሁሉንም ተማሪዎች እንደ ልጆቻቸው የሚመለከቱ ትጉህ ነበሩ። በጊዜው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመግባት ከባድ ጥረትና እውቀትን ይጠይቅ ነበር። ይህንን ጉብዝና እንዲያገኙ አስተማሪዎች ከ8ተኛ ክፍል ጀምሮ ክትትልና ድጋፍ ያደርጉላቸው ነበር። በዚህ ምክንያት እንቁ ከራሱ ጥረት ጋር ተዳምሮ ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ ነጥብ አመጣ። ውጤቱ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መራው።

አዲስ አበባ ገና በልጀነቱ ጥሏት ወደ ጎጃም ቢያቀናም ቂም የያዘችበት አትመስልም። ለትምህርት ተመራጭ የሆነው ዩኒቨርሲቲ ሳያቅማማ ነበር እንቁን የተቀበለው። እርሱም ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ልጅነት ከተማው በመግባት የስነ ምድር (Geol­ogy) ጥናት ትምህርት ክፍልን ተቀላቀለ። ይሄኔ ነበር በልጅነቱ የነበረው የአፈረና የመልከዓ ምድር አፈጣጠር የማወቅ ጉጉት በሳይንሳዊ እውቀት የተደገፈውና እውን የሆነው። ‹‹ልጅህን በሄድክበት መንገድ ምራው ይከተልሃል›› የሚለው አባባል ለቤተሰቦቹና እንደራሳቸው ልጅ ቆጥረው ላሳደጉት ነዋሪዎች በተግባር የተገለጠ ነበር።

በ1982 ዓ.ም ጀምሮ የስነ ምድር ጥናት ትምህር ክፍልን የተቀላቀለው የዛሬው የሕይወት ገፅታ እንግዳችን ለአራት ዓመታት በፍላጎት የመረጠውን ትምህርት በውጤታማነት ተከታትሏል። ይሁን እንጂ የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት፣ የተማሪዎች አመፅና አለመረጋጋት ቆይታውን አልጋ በአልጋ አላደረጉትም። በጊዜው የኢሕአዴግ መንግሥት (የለውጥ ስርዓት መምህራን ለምን ተባረሩ በሚል ተቃውመሀል በሚል) ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ለሶስት ወራት አስሮት ነበር። ይህ ጊዜ ፖለቲካን ይበልጥ እንዲርቅና ወደሚወደው የስነ ምድር ጥናት ትኩረት እንዲያደርግ ሌላ ገፊ ምክንያት ሆነው።

በከፍተኛ ትምህርት ቆይታው ሙሉ ትኩረቱን የስነ ምድር ጥናት ላይ አድርጎ በልጅነት አዕምሮ ለሚያነሳቸው ሀሳቦችና ጥያቄዎች ምላሽ ያገኝ ነበር። ትምህርቱም ይበልጥ ሙያውን እንዲወደው እና የሕይወት መንገዱን በዚያው ዙሪያ እንዲቀይስ በር የከፈተለት ነበር።

እንቁ በአዲስ አበባ ዩነቨርሲቲ የመጨረሻው ዓመት ሲደርስ በተጨማሪነት ከቀድሞው ሲቲቲአይ ከአሁኑ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት በቱር ኦፕሬተርነት በዲፕሎማ ተመረቀ። ከዋናው ትምህርቱ ጋር እንዳይጋጭ መምህራኑ ከኢንስቲቱዩቱ ጋር በመነጋገር ትልቅ ድጋፍ አድርገውለታል። በስነ ምድር ጥናትና በቱር ኦፕሬተር ባለሙያነት መመረቁ ዛሬ ላይ ያልተጠበቀ የሙያ ግጥምጥሞሽና ጥምረት እንዲፈጠርም ምክንያት ሆነ። መልክ እየያዘ የመጣው የልጅነት ሕልሙ የሁለት ሙያ ባለቤቶች አድርጎት ወደ ስራ ሕይወት እንዲገባ መንገዱን ጠረገለት። በባሕል፣ እሴት፣ በሃይማኖት፣ በጠንካራ ስነ ምግባር የታነፀው እንቁ አገርን በእውቀቱ ለማገልገል የሚያስችል አቅምን ገነባ።

እውቀትን ወደ ተግባር

የእንቁ ሙሉጌታ የዓመታት ትልም እውን ሊሆን ግዜው ፈቀደ። በትምህርት የታገዘው የስነ ምድር ጥናትና የቱር ኦፕሬተር ሙያ መሬት የሚነካበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ፅንሰ ሀሳብን እና ሙያዊ እውቀትን ለማሕበረሰብ ሁለንተናዊ እድገት የማዋል ግዴታ በወጣቱ የስነ ምድር ተመራማሪ ላይ ወደቀ። ለታመነለት ሙያ ሙሉ ግዜውን ለመስጠት ያላቅማማው እንግዳችን ለጥቂት ወራት ስራ ለመቀጠር አማትሮ በመጨረሻም ማረፊያውን አገኘ።

ለመጀመሪያ ጊዜ በውጪ ንግድ እረዳትነት በጀነራል ታፈሰ አያሌው (የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስኪያጅ የነበሩ) አማካኝነት ተቀጠረ። እርሳቸው የአገር ውስጥ ወኪል ሆነው ይሰሩበት ለነበረው ‹‹ሊፍት ኤር›› የተባለ አስጎብኚ ድርጅትም (የስነ ምድር ጥናት የሚያደርግ ካምፓኒን የሚያካትት ነበር) የመስራት አጋጣሚው ተፈጠረ። በዚህ ግዜ ጎብኚዎችን ወደ መስህብ ስፍራዎች ከመውሰድ አንስቶ በማዕድን ምርምር ላይ በአስተባባሪነት የመስራትን እድል በአንድ ግዜ ማግኘት ቻለ። ከዚያን ግዜ አንስቶ እንቁና የዓለም መልከዓ ምድር ጥብቅ ወዳጅነት ፈጠሩ። የኢትዮጵያን የመስህብ ስፍራዎች ጨምሮ የከርሰ ምድር ሀብት የሚገኘባቸው ጓዳ ጎድጓዳዎች ጋር ተዋወቀ።

የእንቁ መዳረሻ – ቱሪዝምና ስነ ምድር

በ1988 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የገባውና ‹‹ሀንት ኦይል›› በሚል ስያሜ የሚታወቅ ነዳጅ አፈላላጊ ካምፓኒ አስተባባሪ ሆኖ መስራት ጀመረ። የስነ ምድር ጥናት ባለሙያ መሆኑ ማዕድን ላይ እንዲሳተፍ ሲያደርገው ቱር ኦፕሬተር መማሩ ደግሞ ሎጅስቲኩንም ደርቦ እንዲይዝ ያስመረጠው ነበር። በዚህ ምክንያት በስራው የረጅም ዓመት ልምድ ባይኖረውም በአለቆቹ ወዲያው ነበር አመኔታን ያገኘው።

እንቁ ከበርካታ የውጪ አገር ዜጎች ጋር መስራት ጀመረ። ከካናዳ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከእንግሊዝ አገር የሚመጡ በርካታ ካምፓኒዎችም ጋር የመስራት ልምድ አዳበረ። በሶማሌ ጠረፍ ዶሎ መና (ቦረና አካባቢ) በሚደረግ የነዳጅ ፍለጋ ከተሰማሩ 67 የውጪ አገር ዜጎች ጋር የነበረው ቆይታ ይጠቀሳል። እርሱ የካምፓኒው ሰራተኞች የእለት ተእለት የሎጅስቲክ ፍላጎት ከማሟላት አንስቶ አስፈላጊ የሚባሉ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ ኃላፊነት ነበረበት።

‹‹በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ለውጥ ምክንያት አገሪቱ በሁሉም መስክ ክፈት የሆነችበት ነበር›› የሚለው እንግዳችን እንቁ ሙሉጌታ፤ በጊዜው ሁለት ሙያ ይዞ መገኘት ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝና የስራ እድል የሚከፍት እንደነበር ይናገራል። አጋጣሚው ከማዕድን ፍለጋና ስነ ምድር ጥናት ባሻገር ከውጪ አገር ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ቱሪስቶችን ወደ ልዩ ልዩ መዳረሻዎች (የመስህብ ቦታዎች) በመውሰድ የማስጎብኘት ልምድ በተደራቢነት እንዲሰራ አስችሎታል። የኢትዮጵያን ጓዳ ጎድጓዳ እንዲያውቅና ሀብቶቿን አብጠርጥሮ እንዲለይ ትልቅ እድል የፈጠረለትም ነበር። ከኢትዮጵያ ባሻገር የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የካምፓኒውን ኃላፊነት ተቀብሎም ሰርቷል።

የስነ ምድር ጥናት ድንበር የለውም የሚል እምነት አለው። የተማረው የስነ ምድር ጥናትም ይህንን ፍሬ ነገር ያስቀምጣል። በዚህ ምክንያት እንቁ በሙያው ለማገልገል በበርካታ የአገር ውስጥና የውጪ አገራት መልከዓ ምድሮችን አካልሏል። ከእነዚህ መካከል፣ አገረ ማሪያም በወለጋ ጊምቢ አካባቢ (በቱሉ ካፒና ቱሉ ዲምቱ በወርቅና በፕላቲኒየም ጥናት)፣ በኤርትራ ከረን፣ ጅቡቲ፣ ኬኒያ፣ ታንዛኒያና ሌሎች አገሮችን ይገኙበታል። ሙያው ፖለቲካዊ ከሆነ ፅንሰ ሀሳብ ውጪ ምድር ድንበር እንደሌላት እንዲረዳ ምክንያት ሆኖታል፤ ከማህበረሰብ እሴት ጋር ተዋድዶ፣ ከባህል ተስማምቶ፣ የሰው ልጆችን አብሮ የመኖር እሳቤ ተረድቶ መኖርን በጥልቅ የተማረበት አጋጣሚ ፈጥሮለታል።

በዚህም በካናዳ ኩባንያ (በጀማሪ የስነምድር ባለሙያ እና በመስክ ካምፕ አስተዳዳሪነት)፣ በወለጋና ጉጂ ዞኖች የወርቅ እና ፕላቲኒየም ምርመራ ስራዎች ላይ፣ ሻኪሶ በሚድሮክ የማዕድን ኩባንያ ውስጥ ለገደንቢ

የወርቅ ስራ ቡድን መሪ፣ በቡሌ ሆራ የኢትዮ ዱባይ የወርቅ ፍለጋ ድርጅት ውስጥ የፕሮጀክት ኃላፊ በመሆን እስከ ቁፋሮ የሚደርስ የማዕድን ስራ አብቅቷል።

የእንቁ መንገድ በስነ ምድር ጥናት ላይ ብቻ የተገደበ አልነበረም። ሙያው የፈጠረለት አጋጣሚ ከኢትዮጵያ የመስህብ ሀብቶች፣ የተፈጥሮ ፀጋዎች፣ ባሕልና ታሪክ ጋር ሳያስበው አቆራኝቶታል። በተማሪ ቤት ቆይታው ቱሪዝምን እንደ አንድ ሙያ መማሩ ደግሞ ልምዱን ከእውቀት ጋር አስተሳስሮለታል። በዚህ ምክንያት ከተለያዩ አስጎብኚ ድርጅት ካላቸው (ጓደኞቹ) ጋር ይሰራ ጀመር። ከስነ ምድር ጥናት መስክ ስራ በሚመለስባቸው ማንኛውም አጋጣሚዎች የውጪ አገር ቱሪስቶችን ወደ መዳረሻዎች በመውሰድ ያስጎበኛል።

ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርትነት ወዲህ የማዕድን ኩባንያዎች ስራቸውን አቋርጠው ነበር። በዚህ ምክንያት ለሁለት ዓመት አካባቢም እንቁ አስቸጋሪ ጊዜያትን አሳልፏል። በ1994 ግን ሚድሮክ ኢትዮጵያ ሲቋቋም ‹‹ማይን ጂኦሎጂስት›› ሆኖ ለሶስት ዓመት በሻኪሶ፣ ክብረ መንግስት እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ በመዘዋወር አገልግሏል። ከዚህ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ወደ ቱሪዝሙ በመግባት አዲስ አቅጣጫን አበጀ።

ይህ አጋጣሚ የኢትዮጵያን ሀብቶች (በቱሪዝም ዘርፍ) አብጠርጥሮ እንዲያውቅና ሌላ የሕይወት ልምድ እንዲያዳብር አገዘው። በግዜው አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ባሕርዳር፣ የቀድሞው ደቡብ ክልል የሚገኙ መስህቦች፣ የኦሮሚያ፣ ሐረሪና ሌሎችም አካባቢዎች የሚገኙ የተፈጥሮ፣ የባሕል እንዲሁም የታሪክ ስፍራዎች ላይ የውጪ ዜጎችን ይወስድ ነበር።

ጂኦ-ቱሪዝም

ግዜው በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2005 አካባቢ ነው። እንቁ የጂኦ-ቱሪዝም ፅንሰ ሀሳብን ለማስተዋወቅ ጥረት ያደርግበት የነበረበት ወቅት፤ የስነ ምድር ጥናት የመስክ ስራውንና አስጎበኚነቱን አጠንክሮ የያዘበት አጋጣሚ። በግዜው ሀሳብ በውስጡ በተደጋጋሚ ይመላለስ ነበር። ይህንን ጉዳይ ከውጪ ከሚመጡ በርካታ ቱሪስቶች ጋርም በጨዋታ መልክ አውግቶት ያውቃል። ጉዳዩ በአገራችን ቱሪዝም ውስጥ ያልተለመደም ነበር። የኢትዮጵያን መልከዓ ምድር የሚጎበኙ ቱሪስቶች ከእንቁ ጋር ሲገናኙ የመሬቱን አቀማመጥ፣ የመልከዓ ምድሩን ሁናቴና ሌሎች የጂኦሎጂ ባለሙያ የሚመልሳቸው ጥያቄዎችን ያነሱ ነበር። ይህን ጊዜ ነበር ከትምህርት፣ ንባብ እና የረጅም ዓመት የስራ ልምድ ያዳበረውን ሙያ ለማጣመር የወደደው።

የጂኦ-ቱሪዝም ፅንሰ ሀሳብ በዓለማችን (እንደ ኢንዶኔዢያ፣ ሜክሲኮ፣ጣሊያን፣ አይስላንድ ያሉ አገራት) ላይ የቆየ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን አልተለመደም ነበር። ይህንን እሳቤ ነበር እንቁ በኢትዮጵያ ለማስረፅ የፈለገው። የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆዎች፣ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆችን (ዝዋይ፣ ላጋኖ፣ አብያታና ሻላ፣ ጫሞ አባያ) አስደናቂ መልክዓ ምድሮች ለሀሳቡ እጅግ ምቹ ነበሩ።

‹‹ኢትዮጵያ ለጂኦ-ቱሪዝም የተመቸች አገር ነች›› ይላል እንቁ ስለ ሁኔታው ሲያስረዳ። አፋርን እንደ ምሳሌ ያነሳል። ለዓመታት በአፋር ኤርታሌ፣ ዳሎል፣ ሀዳር (የሉሲ መገኛ) እና ሌሎች አካባቢዎች ቱሪስቶችን በመውሰድ የዓለማችንን ተወዳጅ ስፍራ ሲያስጎበኝ ቆይቷል። በኢትዮጵያ አስደናቂ ውበትና የተፈጥሮ ስጦታዎች የሚደነቁ ጎብኚዎችን ፈጥሯል። አገሪቱ አላት ብለን ከምናስበው በላይ በስነ ምድር ቅርስ፤ የጂኦ- ቱሪዝም የታደለች እንደሆነች ያውቃል። ይህንን እምቅ ሀብት ለዓለም ሕዝብ ገልጦ በማሳየት እንደ አይስላንድና ሜክሲኮ ታዋቂ አገር እንድትሆን ይመኛል። ለዚህም ይመስላል ረጅም ዓመታት ልምዱን አቀናጅቶ በዘርፉ ላይ በስፋት ለመስራት የወደደው።

ጂኦ-ቱሪዝም እንደ መዳረሻ

እንቁ የአፋር ክልል ለስነ ምድር ቅርስ የተመቸች እንደሆነ ያምናል። እያንዳንዱ የአፋር ቀበሌ በዚህ ሀብት የተጥለቀለቀ መሆኑን ተረድቷል። ይህንን ሀብት ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ማስተዋወቅ ድርሻው እንደሆነ ይገለፃል። የአፋር ሕዝብ እና አገር ከዚህ ፀጋ ተጠቃሚ መሆን አለበት ይላል። ፀጋውን ወደሚጨበጥ ጥቅም ቀይሮ በጂኦ-ቱሪዝም ኢትዮጵያ የታወቀች እንድትሆን እየሰራ ይገኛል።

የእንቁን ሀሳብ የሚጋሩ ባልንጀሮችም በዚህ እሳቤ ውስጥ አብረውት እየሰሩ ነው። የኢትዮጵያን ስነ ምድር እና የመስህብ ሀብቶች በማስጎብኘት ስራ ላይ ተሰማርተዋል። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታወቀው የጉብኝት እሳቤ በተጨማሪ ጂኦ-ቱሪዝምን እያስተዋወቁም ነው። በዚህ ምክንያት በአፋር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት እየተገኘ ነው። ለዚህ የእንቁና ጓደኞቹ ድርሻ ላቅ ያለ ነው።

ኢትዮጵያ በስነ ምድር ቱሪዝም ሀብትነት ያላት አቅም በአፋርና ስምጥ ሸለቆ አካባቢን ብቻ እንደማይወሰን እንግዳችን ይናገራል። ለዚህ የሰሜን ተራሮች፣ የባሌ ተራሮች (ወደ 37 የሚጠጉ የመቻራ የዋሻ ስሪቶች) እና ሌሎች ሀብቶችም የዚሁ አካል እንደሆኑ ይገልፃል። ሀብቶቹ በድርብ የዓለም ቅርስነት ከአንድ ግዜ በላይ እውቅና እንዲሰጣቸው እየሰሩ መሆኑንም ያስረዳል። አትዮጵያ እነዚህን ሀብቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲቸራቸው መስራቷ ለቱሪስት ፍሰትና ለኢኮኖሚ እድገት በር ከፋች መሆኑን ነው እንቁ የሚያምነው።

የእንቁ ስኬቶች

እንቁ የጂኦ-ቱሪዝም እሳቤንና የኢትዮጵያን ሀብቶች ለማስተዋወቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፔን ላንዛሮቲ ግዛት በተካሄደ ኮንግረንስ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርቧል። በዚህም ኢትዮጵያ ካሏት እምቅ የጂኦ-ቱሪዝም ሀብቶች መካከልም ስምጥ ሸለቆ እና አካባቢው፣ በስምጥ ሸለቆ ጠርዝ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ መልከዓ ምድራዊ ገፅታዎች እና የአፋር ንቁ የእሳተ ገሞራ ውጤቶችን ጨምሮ የኢትዮጵያን የስነ ምድር ሀብቶች በጥናታዊ ፅሁፉ ላይ በማካተት አስተዋውቋል።

በተጨማሪ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ድርጅት ግሎባል የጂኦ-ፓርክስ የሚባለው ክፍል ውስጥ የኢትዮጵያን የስነ ምድር ሀብቶች ለማስመዝገብ ከጓደኞቹ ጋር ቅድመ ሁኔታዎችን እና ዶክመንት ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።

እንቁና ጓደኞቹ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ውስጥ ጂኦ-ቱሪዝም በፖሊሲ ደረጃ እንዲካተት ሰፊ ጥረት አድርገው በመጨረሻም ተሳክቶላቸዋል። በቅርቡ የቱሪዝም ፖሊሲ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሲፀድቅ ሙሉ ለሙሉ ዘርፉ በፖሊሲው እንደሚደገፍ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ በጂኦ-ቱሪዝም ሀብትና እና የተፈጥሮ ቅርስ የታደለች ሀገር ብትሆንም የሀብቷ ተጠቃሚ ሳትሆን ቀርታለች። ፖሊሲው ይህንን ታሪክ እንደሚቀይር ይጠበቃል።

የዛሬው የሕይወት ገጽታ እንግዳችን እንቁ ጂኦ-ቱሪዝም በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ እየተጋ ይገኛል። ይህንን ከግብ ለማድረስ የተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ በመግባት እየሰራ ነው። ስልጠናዎችንም ይሰጣል። አብሮ ከሚሰራባቸው ድርጅቶች ውስጥ ቮልካኖ ዲስከቨሪ የስነ-ምድርና ንቁ ምድሮችን የሚመረምር ኩባንያ በኢትዮጵያ አስተባባሪ እና ቡድን መሪ፣ የአፍሪካ ቮልካኖሎጂስቶች ማሕበር ፀሀፊ፣ የሕንድ የስነ ምድር ተመራማሪዎች ቡድን በኢትዮጵያ አስተባባሪ፣ የታላቅ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማሕበር ምክትል ሊቀመንበር እና በዓለም ትታይ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት መስራችና ሥራ አስኪያጅ ነው።

በቱሪዝም ዘርፉ ላለፉት 30 ዓመታት በተለይ የአፋር ኤርታሌና ዳሎል የጂኢ-ቱሪዝም ሀብትን እንዲተዋወቅ ላበረከተው አስተዋፆ መቀመጫውን በአሜሪካ ዳላስ ቴክሳስ ያደረገው ‹‹አርአያ ሰው ሽልማት›› አሸናፊ ሆኗል።

እንቁ ዛሬም ለቆመለት ሙያ እስከመጨረሻው ፀንቶ ለመስራት ለራሱ ቃል ገብቷል። በኢትዮጵያ የሚገኙ ማራኪ የስነ ምድር ሀብቶች ወደ ጂኦ-ፓርክነት እንዲቀየሩ፤ ዓለም እንዲጎበኛቸው ለማድረግ የስራ ዘመን ልምዱን ተጠቅሞ ውጤት ለማምጣት እየተጋ ነው። ሀብቱ እያለ እንደ አገር ተጠቃሚ አለመሆናችን ያስቆጨዋል። ይህ እርሱ ሊያመጣ ላሰበው መነቃቃት ገፊ ምክንያት ነው። ከተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጋር አብሮ በመስራት የኢትዮጵያ ጂኦ-ቱሪዝም ፀጋ ቦታ እንዲኖረውና እንዲታወቅ፤ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ሀገራችን እና ሕዝቦቿ ተቋዳሽ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል። በኢትዮጵያ የስነ ምድር ታሪክና አወቃቀር፤ እንዲሁም የስነ ምድር ቅርስና የሚገኙበትንም ዝርዝር መረጃ የያዘ መፅሀፍ በአማርኛ ቋንቋ እንዲሁም በሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚተረጎም እያዘጋጀ ይገኛል።

ትውልዱ እንዲነቃ

‹‹ትውልዱ አቋራጭ መንገድ አይውደድ›› ይላል እንቁ፤ በዚህ መንገድ የሚገኝ አንዳችም ስኬት እንደሌለ በእርገጠኝነት እየተናገረ። ንባብን ባሕል ማድረግ እንዲሁ ከሕልማቸው ዳርቻ እንደሚያደርሳቸው ይገልፃል። እርሱ ላለፉት 30 ዓመታት ንባብን ባሕል ማድረጉና አዲስ ነገር ለማወቅ ጉጉት በራሱ ላይ ማሳደሩ ለሙያው ወዳድነት መሰረት እንደሆነው ይገልፃል። ዛሬም ድረስ ይህንን ልምዱን በመቀጠሉ ብዙ እውቀቶች እየገበየ ለመሆኑ በማስረጃነት ይጠቅሳል። ከማንበብም ባሻገር ኢትዮጵያ አስደናቂ የስነ ምድር ባለቤት እንደሆነች በመግለፅ ትውልዱ የአገሪቱን የተፈጥሮ ስጦታዎች ቦታው ድረስ በመሄድና በመጎብኘት እንዲያውቅ ይመክራል።

ትውልዱ ለመረጠው ሙያ ፍቅር ሊኖረው እንደሚገባም ይናገራል። ሰው መክሊቱን ሲከተል በሙያው፣ ስነ ምግባርና ውጤትን አጣምሮ ሁለንተናዊ ስኬት ላይ እንደሚደርስ ያስረዳል። ፖለቲከኛው ፖለቲካውን፣ የስነ ምድር ተመራማሪው እንዲሁ በሙያው ላይ ብቻ ማተኮር እንደሚገባ ይመክራል። ‹‹እድሜ ልክ አንኖረም›› የሚለው እንቁ የተሰጠንን እድሜ በአግባቡ ተጠቅመን ለተፈጠርንበት ሙያና ዓላማ አውለን ለኢትዮጵያ ቁምነገር ልንሰራ እንደሚገባ ይገልፃል።

እንግዳችን እንቁ ሙሉጌታ ቤተሰብ መስርቶ የሶስት ልጆች አባት ሆኗል። ሴት ልጁ ሜራ እንቁ የአባቷን ፈለግ ተከትላ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ እየሰራች ነው። ወደ ማራኪ ስፍራዎች የእግር ጉዞ (ሀይኪንክ) በማዘጋጀትና የማሕበሩ ፀሀፊ በመሆን ትሰራለች። ሁለት ወንድ ልጆቹም እንዲሁ አርዓያውን ተከትለው በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ላይ እየተጉ ነው። መኖሪያ ቤቱን በኢትዮጵያ ባሕል፣ እሴትና ኢትዮጵያዊነት በሚገልፁ ጌጣ ጌጦች ያስውባል። ይህ ልምዱ ለልጆቹ የእርሱን ፈለግ መከተል፤ ሀገርን ለመውደድ ምክንያት ከመሆን ባሻገር ለበርካታ ዓመታት ለኖረበት ሙያ መታመኑን የሚያንፀባርቅ ምስክር ነው። ለዚህ ነው ወላጆች ልጆቻቸው ኢትዮጵያዊነትን፣ የማሕበረሰብ ባህልን፣ እሴቶችና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በማስተዋወቅ ትውልዱ እንዲነቃ የድርሻቸውን ይወጡ የሚል ምክር በንግግሩ መቋጫ ላይ ያነሳው።

ዳግም ከበደ

 አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You