መቋጫ ያላገኘው የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ በየጊዜው ያልተሰሙ አዳዲስ ክስተቶችን እያስተናገደ በአነጋጋሪነቱ መቀጠሉን አልጀዚራ ዘግቧል:: የሳውዲ ዓረቢያ መንግሥት ከግድያው ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት፤ ወንጀሉን ፈጽመዋል በሚል የጠረጠራቸውን 11 ኃላፊዎች ለፍርድ ማቅረቧ የሚታወስ ነው::
ይሁን እንጂ እነዚህን ሰዎች የሪያዱ መንግሥት ለፍርድ ማቅረቡ ከጀርባው የቋጠረው ሌላ ምስጢርና ሌላ ድራማ በውስጡ ይዟል የሚሉት አስተያየቶች አልጀዚራን ጨምሮ በበርካታ ሚዲያዎች የትርክት ያህል ከመነገራቸውም ባለፈ የብዙኃኑ የመስማሚያ ነጥብ የሆነ ይመስላል::
በቀላሉ እልባት አግኝቶ በዋዛ ሊደመደም ካለመቻሉም በላይ አሁን ላይ ሌላ ማዕቀብና ሌላ ጥያቄ ማስነሳቱ የማይቀረው የጀማል የካሾጊ ጉዳይ ወዴት እየሄደ ነው የሚያስብልና በርካቶችን የሚያነጋግር አዲስ አጀንዳ ይዞ መጥቷል::
አውሮፓዊቷ ሀገር ጀርመን፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ከሳውዲ መንግሥት ጋር ምንም የንግድ ልውውጥ እንዳያደርጉ ያሳሰበች ሲሆን፣ የአውሮፓ ሕብረት ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ተጠቅማ ለሌሎች የህብረቱ አባል አገራትም ተደራሽ ለማድረግ ያሰበች ይመስላል::
ከሰሞን አራት የጀማል ካሾጊ ልጆች ከሳውዲ መንግሥት የዘመነ የመኖሪያ ቤት ቪላ ተረክበዋል:: በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላርን ጨምሮ በየአምስት ወሩ የሚፈጸም ሌላ ተጨማሪ የክፍያ የውል ሥምምነት ተፈጽሞ በሪያዱ መንግሥት ቃል እንደተገባላቸው የአልጀዚራ ዘገባ በሰፊው አትቷል::
ይህ አፍ ማዘጊያ የሚመስለው ተግባር በግልጽ ምን አላማ እንዳለው ለመገመት ከማዳገቱም በላይ በዚህ ስምምነት የተነሳ ልጆቹ አፋቸው ተሸብቦ የአባታቸውን አማሟት ከማጣራት ያፈገፍጉ ይሆን? ወይስ ለጉዟቸው ስንቅ ሆኖ በሌላ አቅጣጫ የአባታቸውን ገዳይ ለማማተርና የበረታ ጥያቄ ለማንሳት ይጠቀሙበት ይሆን? ጊዜ ይፈታዋል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2011
ሙሐመድ ሁሴን