ኢትዮጵያዊነት በጀግኖች ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረ የህብረ ብሔራዊነት መገለጫ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በጥብቅ ያቆራኙት የጋራ እሴቶቹ የሚደምቁት በኢትዮጵያዊ አንድነቱ ነው፡፡ የጋራ እሴቶቹ በኢትዮጵያዊ አንድነት ጠንካራ ገመድ የተያያዙ በመሆናቸው፣ ሕዝቡ በተለያዩ መልክዓ ምድሮች ውስጥ ቢኖርም ሥነ ልቦናው ግን በጣም ተቀራራቢ ነው፡፡ የቋንቋ፣ የባህል፣ የእምነትና የመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገድቡት ተጋብቶና ተዋልዶ አንድ ላይ መኖር የቻለውም፣ የጋራ እሴቶቹ ቁርኝት ጠንካራ ስለሆኑ ነው፡፡ በዚህም ቁርኝቱ ለዘመናት የዘለቀውን አንድነቱን እያስከበረ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በተፈጥሮ የታደለው አስተዋይነትና አመዛዛኝነት የአገር ፍቅር ስሜትን ጥልቅ በማድረግ፣ ኢትዮጵያውያን እጅግ በጣም የሚኮሩበትን በቅኝ ያለመገዛት አንፀባራቂ ታሪክ አጎናፅፏል፡፡ ይህ ድልም የአንድነቱ ድምር ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ከዚህም አልፎ ተርፎ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች መመኪያ የሆነውን ታላቁን የዓድዋ ጦርነት ድል አስገኝቷል፡፡ በዚህ ድል ምክንያትም ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ጋሻ በመሆን፣ የጋራ መሰባሰቢያ ቤታቸው እንድትሆን አስችሏል፡፡ የአንድነታችንም ፍሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ተችሮት ከፍ ብሎ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በይበልጥ በማፋጠን የኢትዮጵያን አንድነት እና ሰላም ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይ ደግሞ በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እናገኘዋለን፡፡ ብዝሃነታችንን ለመቻቻልና ብሎም ለአገራዊ አንድነት ግንባታ ማዋል የወቅቱ አጀንዳ ሊሆን ግድ ብሏል፡፡ ምክንያቱም ብዝሀነታችን የአንድነታችን ዋና መሰረት ነውና፡፡
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የሚታየውን ብዝሀነትን እንደ እርግማን እና ችግር በማስመሰል አግባብ ያልሆነ ልዩነት በመፍጠር በህዝቦች መካከል የቆውን ኢትዮጵያዊ አንድነት ክፉኛ እየጎዳው እንደሆነ ገሀድ የወጣ ገመናችን ነው፡፡ ለዚህም ነው አገራዊ አንድነትና ሰላም ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትኩረት መስጠት ይገባዋል የሚባለው፡፡ ምክንያቱም የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥና ለማጠናከር የአገር ሰላምንና አንድነትን መጠበቅ አስፈላጊ ነው የሚባለው፡፡ ይህ ጉዳይ ለአንድ ወገን በተለይ ደግሞ ለመንግሥት ብቻ መተው የማይገባው ሥራ መሆኑ በተግባር ጭምር ያየነው ጉዳይ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ህዝቡን የማይወክሉ መጥፎ ተግባራት ጭምር እየተከሰቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች ቀድሞ የነበረውን የኢትዮጵያውያንን አንድነት፣ የአብሮነት ባህልና እሴት የሚሸረሽር ነው፡፡ ለዚህም አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳመለከቱት በአንዳንድ የውይይት መድረኮች የሚቀርቡ ጥናታዊ ፅሁፎች ጭምር በአገሪቱ የቆየውን ጠንካራ አገራዊ አንድነት ከእነ ስረ መሰረቱ የረሱ ናቸው፤ ስለሆነም ሊፈተሽ ይገባል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
እነዚህን እና ሌሎች አገራዊ አንድነትን የሚጎዱ ተግባራትን የማስወገድ ጉዳይ ሁሉንም የሚመለከት ስለሆነ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሊሰሩበት ይገባል፡፡ ይህ ሲሰራበት ለምንፈልገው የሰላምና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
በአጠቃላይ በአገራችን ከቤተሰብ ጀምሮ ያለው የኢትዮጵያዊ አንድነት ጠንካራ መሰረት ያለው ነው፡፡ በመሆኑም ስለ አንድነት ሲነሳ ኢትዮጵያውያን ያደግንበት ሁኔታ በግልፅ የሚያስረዳን መሰረቱ ቤተሰባዊ ፍቅርና ሰላም መሆኑ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም ማህበረሰቡ በእያንዳንዳችን እድገት ላይ እያበረከተ ያለው የሰላም እና የአንድነት እሴቶች ዛሬ ማናችንም በተዛባ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ልንሸረሽረው አይገባም፡፡ በመሆኑም የትኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ ሆነ የመብት ተሟጋች ነኝ የሚል ሁሉ ይህን መሰረት ማጠናከር እንጂ መሸርሸር አይገባውም፡፡ ይልቁኑ በጎደለው ላይ እየሞላን መጓዙ ለሁለንተናዊ አገራዊ ብልፅግና የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡ስለዚህ ለአገራዊ አንድነታችን መጎልበት ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ፡፡ሰላም፣ይቅር ባይነትና መተሳሰብ እናጎልብት፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2011