‹‹ ይመለከተናል››

መካነ-ንባብ እንደመሆኑ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የማንበቢያ ከባቢ ከመፍጠር ተሻግሮ በኪነ ጥበብ ጎዳናም እንዲመላለሱ የበኩሉን አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጽሐፍት አገልግሎት። እኔም በቦታው ተገኝቼ አገልግሎት አሰጣጡ ምን እንደሚመስል በተቋሙ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ የአካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ሀገሬ መኮንን ጋር እየጎበኘሁ ነውና ውድ አንባቢያን ሆይ በምናብ ጉዘት አብራችሁኝ ዝለቁ። በቆይታዬ ኃላፊዋ የአካል ጉዳተኞችን የማንበቢያ ክፍል ለማደራጀት መነሻ ሃሳብ የሆናቸውን ትዝታቸውን እየጨለፉ አጫውተውኛል።

በደሴ ከተማ ‹‹ሆጤ›› አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመምህርነት ቆይታቸውን ሲያስቡት በዕንባ የተሞላ ትዝታቸው ቀድሞ ብቅ ይላል። አንድ ዓይነስውር ተማሪያቸው እየለመነ በሚያገኘው ምፅዋት ጓደኞቹን ሻይ ቡና እያለ መጽሐፍትን ያነባል። ይህን ልብ ያሉት መምህርቷም ዛሬ ላይ ላሉበት ተቋም እንዲህ አይነቱን የማንበቢያ ክፍል እንዲያደራጁ ጽናት ሆኗቸዋል።

ወይዘሮዋ በዚህ ብቻ አላበቁም። ተቋሙ 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር በመሥሪያ ቤቱ አስር ዓመታትን የደፈኑት ሀገሬ መኮንን ቆይታቸውን ሲበረብሩት መስማት የተሳናቸውን ያማከለ የአገልግሎት አሰጣጥ እንደሌላቸው ተገነዘቡ። ባቅራቢያቸው ወደሚገኘው ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት በማቅናት መስማት የተሳናቸውን ማነጋገር ያዙ። “በቋንቋችን ተግባብተን አገልግሎት ስለማናገኝ እንጂ እንደማንኛውም ሰው አገልግሎታችሁን መጠቀም እንችላለን” የሚል ተስፋ ሰጪ ምላሽ ያገኙት ሀገሬ አቻና ተዛማጅ ተቋማትን በማስተባበር በኢሲዲዲ ግብረ-ሠናይ ድርጅት አማካኝነት የምልክት ቋንቋ ሥልጠና ለሠራተኞቻቸው መስጠት ቻሉ።

ሀገሬ በዚህም ምክንያት ርቀውና ተገልለው የነበሩትን መስማት የተሳናቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ለማቅረብ በቅተዋል። ሥልጠናውን አስመልክቶ ሃሳባቸውን እንዲሰጡኝ የጠየኳቸው የድምፅና ምስል ዴስክ ኃላፊዋ ቅድስት ጌታቸውም በአስገራሚ አጋጣሚ የተዋዛ ሃሳባቸውን አካፍለውኛል።

“ሥልጠናው የአጭር ጊዜ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ተገልጋዮቹ ራሳቸው ዕለት በዕለት ስለማይመጡ የምልክት ቋንቋውን መርሳት ያጋጥመናል፤ ይሁን እንጂ በየደረስኩበት ሁሉ መስማት የተሳናቸውን ካገኘሁ ስለተቋማችን ገለጻ በማድረግ አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ ግንዛቤ እፈጥራለሁ። እዚህ ክፍል ሳለሁ የማልዘነጋው ገጠመኝ ቢኖር ማየትም መስማትም የተሳናት አንዲት ተገልጋይ ‹‹ስፒች›› ፈልጋ በመጣችበት ጊዜ የማደርገው ጠፍቶኝ ነበር። ብሬልም ንግግርም አትችልም፤ ምን ልሁን? እሷ ግን ልቦናዋ ብሩህ ነውና ጉዳቷ ከጊዜ በኋላ በመሆኑ ዓይናማ ሳለች የምታውቀውን የቀለም አጣጣል በማስታወስ በእስክሪብቶ ጽፋልኝ ለመግባባት ቻልን” ሲሉ በሥራው ሂደት ላይ የነበራቸውን ገጠመኝ አካፈሉኝ።

ሃሳብ መቀበሌን ቀጥያለሁ። ብርሃኑ ዓለም አንተነህ ይባላል። የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ሊረዱትና ሊገነዘቡት በሚችሉት ቋንቋቸው አገልግሎቱን ማግኘታቸው የተግባቦት አቅማቸውን ለማዳበር ከማገዙም በላይ ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀላቀል መልካም የሚባል መስተጋብር መፍጠር መቻላቸውን በእርካታ ተሞልቶ አጫውቶኛል። “እንዲህ አይነቱ በጎ ጅማሮም ይጠናከር ይስፋፋ” ሲል ምኞቱን ገለጸልኝ።

ሌላው ተማሪ መለሰ ፋጫም ዓይነስውር ሲሆን “የኛ የትምህርት ግብዓቶች ዋጋቸው የማይቀመስ ቢሆንም እነዚህንም ማግኘታችን የተቋሙን የአገልጋይነት ስሜት ያንፀባርቃልና ይበል የሚያሰኝ ነው” ሲል ሃሳቡን አከለ። በሪፈረንስ አብያተ መጽሐፍት አገልግሎት ክፍል የዴስክ ኃላፊ የሆኑት ዓለም ጌታቸውም ሃሳቡን ይጋራሉ። አገልግሎታቸውን ሽተው ለሚመጡት ዓይነስውራን ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ ከማድረግ ባለፈ “ይሄ ቢጨመር፣ እንዲህ ቢሆን” ብለው የሰጧቸውን አስተያየትና ጥያቄዎች ለሚመለከተው ዘርፍ በማድረስ አንባቢ ዜጎች እንዲሆኑ ብርቱ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የተቋሙ ሕዝብ ግንኙነት የኮሙዩኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ ሰብለወርቅ አበበም በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች መረጃ በመስጠት ለአካል ጉዳተኞች አገልግሎታቸውን ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ በገንዘብ ሲተመን አንድ መቶ ሰባ ሺህ ብር የሚደርስ ሦስት መቶ መጽሐፍትን ለአልፋ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት ድጋፍ ማድረጋቸውን አነሱልኝ። አያይዘውም በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ከሚሠሩ ባለድርሻ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትም እንደሚጥሩ በአፅንዖት ገለጹልኝ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የመሠረታዊ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚው ስመኝ ሺህመላሽ በግንባታው ዘርፍ የሄዱበትን ርቀት ይገልጻሉ። የሕንጻ አዋጁን ግምት ውስጥ ያስገባ ግንባታዎችን ከመሥራት ሌላ ለእንቅስቃሴ ድጋፍ ሳይሹ፣ ራሳቸውን ችለው በመቆማቸው በራስ መተማመናቸው ጎልብቶ በተፈጠረላቸው ምቹ የማንበቢያ ከባቢ እየተገለገሉ ስለመሆኑ አስገንዝበውኛል።

በመጨረሻም አካል ጉዳተኞች አንባቢ ዜጎች ሆነው ሀገር የሚያንጹ፣ ትውልድ የሚቀርጹ እንዲሆኑ ከማን ምን ይጠበቃል? ስል ላነሳሁላቸው ጥያቄ ሀገሬ መኮንን ተከታዩን መልስ ሰጥተውኛል። “አካል ጉዳተኞችን ያገለለ ዕድገትና ልማት ሙሉ ሆኖ ሀገርን አያሻግርም። ጉዳያቸውን ጉዳያችን በማድረግ የተሻለ የሥራና የሕይወት ከባቢ እንፈጥርላቸው ዘንድ ሁላችንም ይመለከተናልና ለእያንዳንዱ ሁነት ሰበብ ሳንደረድር ሕገመንግሥታዊ ብሎም ሰብዓዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ዕድሎችን ባለመንፈግ የቀና ጎዳና እንጠቁማቸው።” ብለዋል።

በሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You