
ጋምቤላ፡- ጋምቤላ ከተማ ሰላምና ፀጥታዋን አስከብራ ልማቷን እያስቀጠለች ነው ሲሉ የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ ሳይመን ሙን (ዶ/ር) አስታወቁ።
ሳይመን ሙን (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በተለይም ከ2014 እስከ 2016 ዓ.ም በጋምቤላ ከተማ ውስጥ ግጭቶችና የተለያዩ ዘረፋዎች ነበሩ፤ በየቦታው የሰው ሕይወት ያልፍ ነበር። ከነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልልና በተለያዩ እርከኖች አዳዲስ አመራሮች መቀየራቸውን ተከትሎ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጠናከር የከተማዋን ሰላም ማስፈን ተችሏል።
ሰላም ለልማትና እድገት ወሳኝ ሚና እንዳለው የተናገሩት ከንቲባው፤ አመራሩ የተገኘውን ሰላም በልማት ለመደገፍና ለማስቀጠል ጠንክሮ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። በርካታ የልማት ሥራዎች በከተማዋ እየተከናወኑ መሆኑን ከንቲባው አስረድተዋል።
አመራሩ ኅብረተሰቡ ወደሚኖርበት ሰፈር ድረስ በእግሩ እየሄደ በማነጋገርና ከሕዝቡ ጋር ተቀራርቦ በመሥራት እንዲሁም ተራርቀው የነበሩ ማኅበረሰቦችን በቅርበት እንዲገናኙ በማድረግ እና የሕዝብ ቅሬታ ቢሮዎችን በማቋቋም የከተማውን ሰላምና ፀጥታ የማስፈን ሥራ እየሠራ መምጣቱን ከንቲባው ተናግረዋል።
በዚሁ መሠረት በከተማዋ የጥይት ድምፅ ሳይሰማ ሕዝቦች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ሲሠራ እንደቆየ አስረድተዋል። በአሁኑ ጊዜ የከተማው ማኅበረሰብ በሰላሙ ጉዳይ ተግቶ የሚሠራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ጊዜ የከተማዋን ሰላም ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የመንገድ፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን የማስፋፋት እና የከተማዋን ስፋት እና የሕዝቡን ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገቡ የልማት ሥራዎችን ከፌደራል መንግሥት ተቋማት እና ከሕዝቡ ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑን ከንቲባው አመልክተዋል።
የባሮ አኮቦ ወንዝ እስከ አሁን ድረስ በሚፈለገው ልክ ጥቅም እየሰጠ አለመሆኑን ተናግረው፤ በቱሪዝም፣ በዓሣ ርባታ፣ በመስኖ ልማት እና በሌሎችም የሥራ ዘርፎች ወንዙ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል አቅም እንዳለው አስረድተዋል።
አሁን ላይ ምንም አይነት የሞተር ጀልባ ወንዙ ላይ እየታየ አለመሆኑን አንስተው፤ የሞተር ጀልባዎችን በማሰማራትና፤ ለወጣቱ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ የቱሪስት መስኅቦችና መዝናኛዎችን መሥራት በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንደሆኑ አመልክተዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም