
የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በየወቅቱ እያደገ ለመሆኑ በርካታ አመላካቾች አሉ። ሆኖም ግን ሀገሪቷ በዘርፉ ካላት እምቅ አቅም አኳያና ሊደረስበት ከሚገባው አንጻር ሲታይ ዛሬም በርካታ የቤት ስራዎች መኖራቸው ግልጽ ነው። በመንግሥት በኩል ለዘርፉ ትኩረት ሲሰጥ በቀዳሚነት ከተቀመጡት አላማዎች መካከል አንደኛው በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ከሌሎች ሀገራት የሚመጡ ምርቶችን መተካት ነው። ሁለተኛው ደግሞ የወጪ ምርቶች ላይ ትኩረት በመስጠት የውጪ ምንዛሪ ገቢን ማሳደግና የሥራ እድል ፈጠራ ናቸው። እነዚህ አላማዎች እንደ ሀገር የተቀመጡ ሲሆን በሁሉም ክልሎች ትኩረት ተሰጥቶባቸው እየተሠራባቸው ይገኛል።
በዛሬው የኢንቨስትመንት አምድ ዝግጅታችን አዲሱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንት ለመቃኘት መርጠናል። በክልሉ የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አባስ መሀመድ (ዶክተር) ጋር በበጀት ዓመቱ በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ የነበረንን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ዶክተር አባስ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ብዙ ምቹ ሁኔታዎች ያሉ ቢሆንም እንደየ አካባቢው የየራሳቸው የሆነ ልዩ ምቹ ሁኔታዎችንም የያዙ ናቸው። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ለኢንቨስትመንት ካሉት ምቹ ሁኔታዎች መካከል የሚከተሉትን በቀዳሚነት ማንሳት ይቻላል። በክልሉ ለሥራ ዝግጁ የሆነና በእውቀትም በጉልበትም ብቃት ያለው ከፍተኛ ወጣት ኃይል አለ። የአካባቢው ማህበረሰብ ከሚለይበት አንዱ ታታሪ ሥራ ወዳድና ፈጣሪ መሆኑ ነው። ይህም ለኢንቨስትመንት የሚወጣው ትልቁ ወጪ ለሰው ሀይል በመሆኑ ባለሀብቱ ይህንን አቅም በቅርበት በተመጣጣኝ ዋጋ መጠቀም የሚያስችለው ይሆናል። ሌላው ክልሉን ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምቹ የሚያደርገው 24 ሰዓት ለመሥራት፣ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ሰላም መኖሩና የጸጥታ ስጋት የሌለበት መሆኑ ነው።
ሌላው ኢንቨስትመንት ሲታሰብ ከግምት የሚገባው ከመንግሥት የሚገኝ አገልግሎትና የተቀናጀ የገበያ ትስስር ነው። በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የክልሉ መንግሥትም ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በዘርፉ የሚሳተፉትን ለመሳብም ሆነ ለመደገፍ ቁርጠኝነት ያለው መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ይህ ከክልሉ ፕሬዚዳንት ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ በተግባር እየተገለጸ ያለ እውነታ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ገበያንም በተመለከተ ቅርበትንም በተመለከተ ክልሉ የተለያዩ ምርቶችን ወደ አዲስ አበባ ሆነ ወደ ውጪ ለመላክና ከውጪ ለማስገባት በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው። በተጨማሪም በአንጻራዊነት ከመንገድ ከመሰረት ልማት አኳያና በመብራት በኤሌክትሪክ አቅርቦት ረገድ ሁሉም አካባቢዎች ሊባል በሚያስችል ደረጃ እየተሟሉ ይገኛል። እንደ ሀገርም እንደ ክልል ዋና ትኩረት የሚደረገው ተኪና ወጪ ምርት ላይ ትኩረት ማድረግ ነው። እንደ ሀገር ለእነዚህ አምራቾች ወጥ የሆነ ማበረታቻ ይደረጋል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በክልሉ በዚህ መስክ ለሚሰማሩ የመሬት ሊዝ ዋጋ ዝቅተኛ ነው። በዚህ ረገድ እስካሁንም በጨርቃ ጨርቅ፣ በአበባ ምርት፣ በቅባት እህልና ጥራጥሬ እንዲሁም ቡናን ወደ ውጪ የሚልኩ ኢንቨስትመንቶችን መፍጠር ተችሏል።
በበጀት ዓመቱ በዋናነት ለማከናወን በእቅድ ተይዞ ወደ ሥራ የተገባው አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብና ያሉትንም ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ በሚጠበቀው ደረጃ እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ እንደነበር ያመላክታሉ። አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ቀዳሚ ሥራ የተደረገው የፕሮሞሽን ሥራ መሥራት ነው። በዚህም በበጀት ዓመቱ ካለፈው ዓመት በተለየ በክልሉ ለኢንቨስትመንት ያለውን እምቅ አቅም የሚያሳይ የዶክመንተሪ ፊልም በማዘጋጀት በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲለቀቅ ተደርጓል ሲሉ ይገልጻሉ።
ኃላፊው እንዳብራሩት፤ በበጀት ዓመቱ 206 ኢንቨስተሮች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲያወጡ ታቅዶ፤ ባለፉት አስር ወራት ብቻ 187 ማድረስ ተችሏል። ከእነዚህ ፈቃድ ካወጡ ባለሀብቶች አስር ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ካፒታል ይመዘገባል ተብሎ የታቀደ ሲሆን ከእቅዱ በላይ 15 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ለማስመዝገብ ተችሏል። እነዚህ በዘርፍ ሲታዩም በግብርና በ33 ፕሮጀክቶች ከሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ፤ በኢንዱስትሪ በ41 ፕሮጀክቶች ስምንት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሁም፤ በአገልግሎት በ21 ፕሮጀክቶች አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ነው። የኢንዱስትሪ ዘርፍ ካፒታሉ ከፍ ያለበት ዋናው ምክንያት እንደ ክልል ብዙ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ስለሌሉ ትኩረት የተሰጠው በቀዳሚነት ኢንዱስትሪ ሲሆን ቀጥሎ ለአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን ያሳያል።
የሥራ እድል ፈጠራንም በተመለከተ እስካሁን ከ39 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚነትና በጊዜያዊ የሥራ እድል ለመፍጠር ተችሏል። በጊዜያዊ የሚባሉት በግብርና ወቅት ሰብል ሲደርስ የሚቀጠሩትን ሲሆን በእነዚህ ጊዜያት ከሌሎች ክልሎችም እስከማምጣት ይደረሳል።
በሌላ በኩል እንደ ክልል የኢንቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጡን ፈጣን፤ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበት ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። በክልሉ ሰባት ዞንና ሶስት ልዩ ወረዳዎች ያሉ ሲሆን አንድ ኢንቨስተር ምን ምን መስፈርቶችን ሲያሟላ መሬት ሊያገኝ እንደሚችል በግልጽ ተቀምጧል። ባለሀብቱ የት? ምን? ማልማት እንደሚፈልግ ከወሰነ በኋላ ፕሮጀክቱን የሚያቀርበው እዛው ዞኑ ወይንም ወረዳው ላይ ይሆናል። እዛ ያለው ባለሙያ የቀረበውን በመገምገምና መስፈርቶች መሟላታቸውን በማረጋገጥ በካቢኔ ወስኖ ወደ ክልል የሚልከው ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ኢንቨስተሮች ራሳቸው ማሟላት ያለባቸውን ነገሮች ሳያሟሉ ሲቀርቡ የመመላለስ ነገር መፈጠሩ አይቀርም። ይህም ሆኖ ቅሬታዎች ቢፈጥሩ ችግሩ ከእነሱ ነው ተብሎ ስለማይተው ቅሬታቸውን አቅርበው የገጠማቸው ችግር የሚፈታበት አሠራርም በየደረጃው ተዘርግቷል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአብዛኛው ባለሀብት ከውጣ ውረድ በላይ ጊዜ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው በመሆኑ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመሩትን እንደ መሶብ ያሉ አገልግሎት መስጫዎችን በክልሉ ለመጀመር በእንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን። እነዚህን መንገዶችና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አሠራሩን የበለጠ ቀልጣፋ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ ኃላፊው አባስ (ዶክተር) አስረድተዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከመልካም አስተዳደርና ሙስና ጋር በተያያዘም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ስለሚያስፈልግ ራሱን የቻለ እቅድ እንዲታቀድ የክልሉ መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጧል። በዚህ ረገድ እስካሁን የቀረበ ቅሬታና አቤቱታ ባይኖርም ሥራው ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል። በዘላቂነት ለመቆጣጠር ሥራውን በሙሉ በቴክኖሎጂ ለማድረግ በስፋት የተጀመሩ ሥራዎችም አሉ። ክልሉ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ በመሆኑ ሠራተኛው የተስተካከለ አመለካከት እንዲኖር በስፋት እየተሠራ ሲሆን የነበሩት አዋጆች፤ መመሪያና ደንቦች ላይ ማስተካከያም ተደርጓል። ይህም ሆኖ አላሠራ የሚሉ መሻሻል ያለባቸው ህጎችና ደንቦች ሲኖሩም ለማስተካከል ሁሉም ነገር ዝግጁና አዋጁም ለዚህ ክፍትም ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የክልሉ መንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራው የመሬት አስተዳደር ነው። በኢንቨስትመንት ረገድ ክልሉን የኢንዱስትሪ መናኸሪያና የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል። ይህ ማለት ደግሞ ለዚህም በቂ መሬት ማዘጋጀት ስለሚጠበቅ እያንዳንዱ አካባቢ ባለሀብት ከመምጣቱ በፊት ቀድሞ መሬት እንዲያዘጋጅ ተልእኮ ተሰጥቶታል። ይህም በመሆኑ ባለሀብቱ የሚጠበቅበትን መስፈርት አሟልቶ ሲመጣ ወዲያውኑ እንዲያገኝ የሚደረግ ይሆናል። በክልሉ የመሬት እጥረት መኖሩ ይታወቃል። በመሆኑም ያለውን በአግባቡ ማስተዳደርና ለሚያስፈልግ አገልግሎት ብቻ ማዋል በሌላ በኩል በአግባቡ የማይጠቀሙም ካሉ ተቀብሎ ለሚጠቀሙ ማስተላለፍ የግድ ይላል ሲሉ አብራርተዋል።
እንደ ክልል መሬት የሚተዳደረው የከተማና የገጠር ተብሎ ሲሆን የከተማውን የሚያስተዳድሩት ራሳቸው የየከተማው ከንቲባዎች ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ በመሆኑም ለኢንቨስትመንት፤ ለሆቴልና ለቱሪዝም አገልግሎት ሲፈለግ በእነሱ በኩል አቅርበው እንዲጸድቅ ወደ ክልል የሚመጣ ይሆናል። የገጠር የእርሻ መሬት በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ በየወረዳውና በየዞኑ ያሉ አመራሮች የሚወስኑ ይሆናል። የመሬት አቅርቦትን በተመለከተ የት አካባቢ ምን ቢሠራ ጥሩ ነው የሚለው ዝርዝር ጉዳይ በባለሀብቱ የሚወሰን ቢሆንም የተወሰነ መረጃ የሚሰጡ በጥናት የተደገፉ አመላካች ፕሮፖዛሎች በክልሉ የተዘጋጁ መኖራቸው ይገልጻሉ።
እነዚህ ፕሮፖዛሎች በየወቅቱ ማስተካከያ የሚፈልጉ ቢሆንም ለባለሀብቱ በከፍተኛ ሁኔታ በቂና ትክክለኛ መረጃ ለማቅረብ የሚያገለግሉ ናቸው። እንደ ምሳሌ አንድ ኢንቨስትመንት ጥያቄ ባቀረበ በሶስተኛው ቀን ፈቃድም መሬትም አግኝቶ በአራተኛው ቀን ወደ ግንባታ የገባ ባለሀብትም አለ።
ይህም ሆኖ መሬት ወስደው የማያለሙትን በተመለከተ ችግሩ በጣም የተለያየ ነው። በመሆኑም ክልሉ ከተቋቋመ ጀምሮ በእያንዳንዱ አካባቢ ምን ያህል መሬት ተላልፏል ማን እያለማ ነው፤ ማን ወደ ሥራ አልገባም የሚለውን የመለየት ሥራ ተከናውኗ። በዚህ መነሻነትም አምናም ዘንድሮም ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ ካልሆነ ቦታው ለሚሠራበት የሚተላለፍ መሆኑን ከባለሀብቶች ጋር በርካታ ውይይቶች በዞን ደረጃ ድረስ ተከናውኗል።
ይህንን ተከትሎ ወደ ሥራ የገቡ አሉ ባልገቡ 158 ፕሮጀክቶች ላይ ባለፉት አስር ወራት ብቻ ርምጃ ተወስዷል። ርምጃውም በውሉ መሰረት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ 44 ተቋማት ላይ ውል እንዲቋረጥ ተደርጎ መሬቱ ወደ መንግሥት እንዲገባ ተደርጓል። በቅርቡም እርሻ ላይ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ዝናብ ብቻ ጠብቀው ከማልማት በመላቀቅ ዓመቱን ሙሉ መሬቱን በመስኖና በሌሎች አማራጮች እንዲጠቀሙ ውይይት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ ሌላው ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ያለው ዳያስፖራውን ማህበረሰብ በኢንቨስትመንት እንዲሳተፍ የማድረግ ሥራ ነው። በርካታ የክልሉ ተወላጆች በተለያዩ አለማት እንደሚኖሩ ይታወቃል። በዚህም መነሻነት በኢንቨስትመንትን ዘርፍ የዳያስፖራውን ጉዳይ የሚከታተል የሥራ ክፍል ተቋቁሞ እየተከታተለ ይገኛል። በዚህ ረገድ ባሉበት ሀገር ሆነው በወኪላቸውን በመመደብም ሆነ ራሳቸው በማስጨረስ ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል። በዚህም በአስር ወራት ብቻ 187 ዳያስፖራዎች ወደ ክልሉ መጥተዋል። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑ ፈቃድ አውጥተው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን ቀሪዎቹ በሂደት ላይ ናቸው። የዳያስፖራ ኢንቨስተሮች ካፒታልን እውቀት አላቸው ተብሎ ስለሚገመት የቴክኖሎጂ ሽግግርም ስለሚኖር የተለየ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን እንገኛለን።
በሌላ በኩል የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የአንድ ወገን ሥራ ብቻ ባለመሆኑ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚኖር ቅንጅትና ተናቦ መሥራት ወሳኝ ነው።በመሆኑም በየወቅቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚደረጉ የውይይት መድረኮች አሉ። ከእነዚህም መካከል ከባንኮች፤ የመሰረተ ልማት ተቋማት፤ የንግድና ገበያ ቢሮ፤ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ይጠቀሳሉ። በተጨማሪ በክልሉ ካሉት ሶስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተለየ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስር በመፍጠር እየተሠራ ይገኛል።
በዚህም ዩኒቨርሲቲዎች አቅም በማጎልበት ረገድ በየአካባቢያቸው ያሉ ኢንቨስትመንቶችን እንዲደግፉ የደረጋል። ከባንኮች ጋር በተያያዘም የገንዘብ አቅርቦትን በተመለከተ ፈቃድ ወስደው መሬት ተረክበው ወደ ልማት ያልገቡትን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገናኝተው እንዲወያዩ ለማድረግም ተችሏል። በመብራት አቅርቦት ረገድ ብዙ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም አንዳንድ መቆራረጦች ያሉ በመሆኑ እነዚህን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሠራ ይገኛል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአንዳንድ አካባቢዎች በፍጥነት የኤሌክትሪክ አቅርቦት ማግኘት ካስፈለገ ከባለሀብቱ ጋር በመቀናጀት በመሥራት ላይ ነው ያሉት አባስ (ዶ/ር)፤ ሌላው እንደ ባለድርሻ አካል ተደርጎ በስፋት እየተሠራ ያለው ኢንቨስትመንት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ካሉ የማህበረሰብ አባላት ጋር ነው። ኢንቨስትመንቱን ከሚያካሂዱት አካላትም ማህበረሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸትና በዋናነትም የአካባቢ ጥበቃን መተገበር የግድ ነው። የአካባቢው ነዋሪ በአቅራቢያው የተካሄደውን ኢንቨስትመንት በእኔነነት መንፈስ እንዲደግፍ ማድረግ ይጠበቃል። ይህ በተሳካ መልኩ እንዲካሄድ ኢንቨስትመንት ከመጀመሩ በፊት በግንባ ሂደትና ወደማምረትና አገልግሎት ወደመስጠት ሲገባም በየደረጃው ማህበረሰቡ እንዲያውቅና ጥያቄ ካለውም እንዲያቀርብ እድሉ የሚመቻችለት ይሆናል ብለዋል።
በራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም