የጨው አልጫ

የቀዬው ገበሬ ማሳውን እየሸጠ “አልማዝ አለ” ሲባል ወደሰማበት ሀገር ነጎደ፤ በመንደሩ የቀረው ብቸኛ ገበሬም አንድያ መሬቱን ይሸጥና ሚስቱን ይዞ እሱም በተራው ከተባለው ስፍራ አልማዝ ለማውጣት አቀና፤ ይሁን እንጂ በጉዟቸው ደህና ነገር አልገጠማቸውም።

ያልቅ ያልመሰላቸው ገንዘብ ረብ ሳይኖረው አለቀና ለጸጸት ዳረጋቸው፤ በተለይ ከነሚስቱ የተሰደደው ገበሬ ርሃብና ጥሙ ሲጠብሰው ባይኑ ያላረጋገጠው ነገር ግን በስማ በለው ጆሮው እስኪግል ድረስ በወሬ ተሞልቶ የጎመጀለት አልማዝ እንደ አድማስ ሲቀርቡት እየራቀ ሃብታም የመሆን ሕልሙን አሟሸሸውና “በቀረብኝ ኖሮ” አስባለው።

መሬቱን የገዛው ገበሬም ቢሆን እንደሌሎቹ አይሰደድ እንጂ በጁ ያለውን ጸጋ ልብ ማለት አልቻለም። አልማዝ ፍለጋ የሚሄዱ ሰዎች ይመሽባቸውና በእግዜር እንግድነት ከቤቱ ያድራሉ። ቤት ያፈራውን አሰናድተው አፋቸውን ይሽሩ ዘንድ ሞሰብ ሲሰይሙ እንግዶቹ ከምድጃው በላይ የሚያብረቀርቁ ጌጠኛ ድንጋዮችን ሲመለከቱ መገረምም መደነቅም እየቃጣቸው “እነዚህን ድንጋዮች ከየት አገኘሃቸው?” በማለት አባወራውን ቢጠይቁት ጊዜ “ይህማ ከጓሮዬ ሞልቶ አይደል? ብልጭልጭ ሆኖ ሳየው ደስ አለኝና ለልጆቼ መጫወቻ እንዲሆን አመጣሁት፤ እኔ እንዳውም ትልልቁን ብቻ ነው ያመጣሁት” ብሎ ሲመልስላቸው “ለካስ ጸጋን ማስተዋል የሚችለው ራእይ ያለው ብቻ ነው?” አሉ። ገበሬዎቹ ከደጃፋቸው ያለውን ሃብት ካለመገንዘባቸው የተነሳ ስደታቸው የመጣ እንደሆነ እጅጉን አሳዝኗቸው።

እንግዶቹ ጥሩ ታዝበዋል። ገበሬዎቹ መሬትን አረንጓዴ ወርቅ አልብሶ በማዝመር ፍጡርን መመገብ እንጂ መቅድም ራእያቸው አልማዝ ባለመሆኑ ከጓሯቸው የተነጠፈውን ጸጋ ማየት አልቻሉም፤ ይህን የገበሬዎቹን ሁናቴ ራሱን በማጣት አዙሪት ለሚዳክረው ለኔ ትውልድ ምሳሌነቱን እንጋተውና ቀልብ ገዝቶ ጆሮውን ቢቸረን “ልጅህን ቢያንስ በቀን አንዴ ግረፈው” እንዲል መጽሃፉ በቁጭት በትር ሕሊናውን ሸንትረን ልቦናውን ሞርደን ከተኛበት የዘመን እንቅልፍ እንቀስቅሰው።

መልካም መንገድ ውጥኑ አህዱ የሚባለው ልብን ከማንበብ ነው፤ ልባችንን ማንበብ ያቃተን እንደሆነ ወደተፈጥሮ እንሻገር፤ ተፈጥሮንም እንኳን ማንበብ ቢሳነን መገለጥን ልብ እንበል፤ መገለጥም ባይገለጥልን የመጨረሻው ንባቤ ብልሃታችንና የውቀት ምንጭ እንዲሁም ራሳችንን ማግኛ መንገዳችን ማንበብ ነው፤ ልብና ተፈጥሮን አዋህደው የያዙት መጽሃፍት ናቸውና።

እንደ ሊቃውንት አስተምሮ መጽሃፍት የሚጻፉት አንብበናቸው እንድንቀር ብቻ ሳይሆን እኛ ራሳችንም ብንሆን መጽሃፍ እንድንሆን ነው። በዚህ እሳቤ መሰረት ስንቶቻችን ካለማንበብ ወደማንበብ፣ ከማንበብ ወደመነበብ ብሎም ከጸሃፊነት ወደመጽሃፍነት ተሸጋግረን ይሆን? “ያነበበ ሰው አንድ ሺህ ጊዜ እንደኖረ ይቆጠራል፤ ያላነበበ ሰው ግን አንድ ጊዜ ብቻ እንደኖረ ይቆጠራል” የሚለውን ምሁራዊ ብይንስ ከልቦናችን ጽላት ከትበን ጠንካራ ሃሳብ፣ የሰላ ምናብ በመታጠቅ ምን ያህሎቻችን የሕይወት ዘይቢያችንን አስውበነው ይሆን?

“ስሜትና ስሌትን የቀላቀለ፣ ምክንያታዊነትን ያገለለ ትውልድ የመፍራቱ መንስዔ ከንባብ መራቁ ነው” ይላሉ በዘርፉ አያሌ ጥናቶችን ያካሄዱ ምሁራን። እንደ ሃምሌ ቆፈን ካጥንታችን ዘልቆ የሚያንዘፈዝፈን ያለማንበብ ሰንኮፍ ሃሳብንና ሰብዕናን ደባልቆ መከባበርን፣ መደማመጥን፣ በወግና ባሕል ማደርን ነስቶናል፤ ከዚህም ሌላ በብዙሃኑ መሃል እየኖረ ባይተዋርነት የሚሰማው፣ እልፍ መልካም እሴቶች ያሉት ሆኖ ሳለ መንፈሱ የተራቆተ፣ ሞራሉ የደቀቀና ስነልቦናው የላሸቀ ትውልድ እንዲበቅል ምድሪቱን እንክርዳድ ዘርቷታል፤ እናም ጎበዝዬ ከንባብ የተጣላ ትውልድ ይዘን ለውጥ፣ እድገት፣ ብልጽግና ስንል የሰሙቱ እማማ ሽጉልቴ የማያነብ ትውልድ ይዘን እንዴት ሀገራችንን ማሳደግ እንችላለን የሚለው ስጋት ሽው ብሎባቸዋል። እኔም ለምን በርዕሰ/ጉዳዩ ዙሪያ አላወራቸውም? በዚያውም የናፈቀኝን ቡናቸውንና ጨዋታቸውን እልፋለሁ ብዩ ወደ እማማ ቤት ለመሄድ ተነሳሁ ።

ወደ ዕማማ ሽጉልቴ ቤት ሳዘግም የዩኒቨርሲቲ ጓደኛዬ የቤቲ ቁጥር ከስልኬ ደረት ሰፍሮ አንቃጨለና ከማንቀራጨው ሃሳብ አናጠበኝ። በመጀመሪያ ቀን ትውውቃችን “ገደል ግቡ” ሆቴል ገብተን ያዘዝነው ምግብ እስኪመጣ ድረስ አብዝቼ የምወደውን መጽሃፍ እየገለጥኩ “ኦሮማይን” ታውቂዋለሽ? ብዬ ብጠይቃት “የጾም ነው የፍስክ?” አለችኝና በሳቅ ወደኩ፤ እውነቴን ነው የምላችሁ እንደዚህ ስቄ የማውቀው ሱባዔ በገባሁበት አጋጣሚ አይጥ ጋን ተሸክማ ስትንጎማለል ያየሁ እለት ነው።

ይግረማችሁና ንባብን በተመለከተ በርካታ የማይረሱ ገጠመኞች አሉኝ። አንድ ጊዜ ደግሞ ማረሚያ ቤት የገባ አንድ ወዳጄ መጽሃፍ እንድወስድለት ይጠይቀኝና የአዳም ረታን ድንቅ ሥራ ይዤለት ሄድኩ። እንደጠፍር የደረቀ አንድ ፈታሽ ፖሊስ “ምንድነው?” አለኝ ከያዝኩት የምግብ ሳህን ጋር የደበልኩትን መጽሃፍ እየመነቀረ። መጽሃፍ መሆኑን ገልጬ ልገባ ስል “ለመሆኑ ርዕሱ ምንድነው?” አለኝ በድጋሚ እንደ መርፌ በሚወጋ አስተያየቱ ሰቅዞ ይዞኝ። “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር” ነው የሚለው ብዬ ልገላገለው ስሻ እሱ ግን ከበፊቱ አስተያየት በባሰ ሁኔታ እየተመለከተኝ “ቅመሰው” አለኝ። ምን? አልኩት ያላዋቂነቱ ጥግ አግራሞቴን እያበዛው።

“ምን ወሬ ታዳንቃለህ? ቅመሰው አልኩህ ቅመሰው፤ እዚህ ቤት ምንም ነገር ሳይቀመስ አያልፍም፤ ደግሞምኮ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር ነው የሚለው ብልህም የለ! አትርሳ እንጂ ጃል? እኮ በል ቅመሰው?” አለኝ አሙካ እንዳቆረፈደው የሸሚዝ ኮሌታ ግብዝነቱን እየለደፈብኝ።

ለነገሩ አንተ ምን ታደርግ? ሆዱን ብቻ “እሽሩሩ” በሚል ማኅበረሰብ መሃል በቅለህ እንዴት የመንፈስን ርሃብ ልታውቅ ትችላለህ? አልኩ በለሆሳስ ባልወለድ አንጀቱ እንዳይረግጠኝ ፈርቼ። መቼም ያገር ሰው! “ወይ ድንግርግር ተጓዝ ያለው እግር” ነውና የማረሚያ ቤቱ ግርምቴ ሳያበቃ ምሽት ላይ ከአንድ ግሮሰሪ ቤት ስዘልቅ ያየሁት ነገር ይበልጡን ልቤን ነካኝና የሞራል ዝቅጠታችን የመንፈስ እርቃናችን ግሃድ መውጣቱ አንጀቴን በላውና ብደብንም እንዳላየ ሆኜ ለማለፍ ብታገልም የሀገር ነፍሰ/ስጋ ክፋይ የትውልድ ገጸ/ግንጣይ አይደለሁ? ድርጊቱ ከንክኖ ቆሽቴን አሳረረው።

የመጠጥ ቤቱ ቀጭን ጌታ የጠርሙሱን አንገት አንቀው ቆርኪውን እየፈነቀሉ “በሉ እንጂ” ይላሉ ደንበኞቻቸውን። ታዲያ አንድ መጽሃፍ አዟሪ የቤቱን መድመቅ አይቶ ወደ ውስጥ ዘለቀና ጭነቱ እንደበዛበት ጋማ እያቃሰተ የደራሲዎችንና የመጽሃፍቱን አርዕስት ሲያነብልን የበአሉ ግርማን “ኦሮማይ” መጽሃፍ በመግዛት እጁን ፈታሁለት፤ ይህን የተመለከቱት ሴትዮዋ ግን አራስ ነብር መስለው ታዩኝ። አይነ/ውሃቸው ስላላማረኝ ልጅ እግር መሳዩን መጽሃፍ አዟሪ ጠቀስኩትና ፈጥኖ እንዲወጣ ነገርኩት፤ ወይዘሮዋ ግን የዋዛ አይደሉም። ተከትለውት ወጡና “ቤቱን ስታየው ምኑ የሕዝብ ቤተ/መጽሃፍት መሰለህ እባክህ? ያንተን አንድ መጽሃፍ በገዙ ቁጥር የሚጠጡትን መጠን እንደሚቀንሱና የኔም ገቢ እንደሚቀጭጭ አጥተኸው ነው እዚህ ጥንብ እንዳየ ጆቢራ የምታንዣብበው? እንኳንስ እዚህ ቤት ይቅርና በዚህ አካባቢም ዳግመኛ ድርሽ እላለሁ ብትል ውርድ ከራሴ” ሲሉ በቁጣ አባረሩት።

የድንፋታቸው ሾርኒ ከወጣቱ አልፎ ለእኔም ተረፈ። “ለቅልውጥና አሊያም ወንበር ለማሞቅ የመጣ ካለ ቀስ ብሎ ውልቅ ይበል፤ አለበለዚያ ግን የመጣበትንና የማይናገረውን ይጠጣ” አሉ ማንቆርቆሪያቸውን ይዘው በወለሉ መሃል ወገብ ቆመው ወዲያ ወዲህ እያማተሩ።

ይናገራል እንጂ እመይቴ፤ እንዴት አይናገር? ከጠጣነው ከእኛ አልፎ ይኸው እርስዎንስ በሽታ ብቻ አናገረዎት አይደል? አልኳቸው “ለቅልውጥና” ያሉት ነገር እንደቂጥ ቡግንጅ መቀመጫ ነስቶ አሁንም አሁንም እየነዘገኝ። “ድከም ቢለው ነው እባክህ፤ ንባብና ፍቅር ከደብዳቤው ጋር አብሮ ተዘንግቷል” አሉኝ በመታከት እየተንቆራጠጡ።

እኔኮ አንዳንዴ የሚገርመኝ ደርሼ ጋሼ ስብሃትን ካልሆንኩ የምለው ጉድ አለ! ክንዳቸውን ይዤ ሳብ አደረኳቸውና ከጎኔ ካስቀመጥኳቸው በኋላ መለኪያ አስጨብጬ የፍቅር ደብዳቤ ትዝታቸውን አስለፈልፋቸው ገባሁ። “የሚያፈቅሩትን ሰው ልብ ለማግኘት ሲባል እንዲሁም ኮርኳሪ ጥቅሶችን ለመውሰድ መጽሃፍትን ማገላበጡ ለንባብ ልምዳችን አቅም ሆኖን ነበር፤ ዳሩ ምን ይሆናል እሱ ሲቀር የንባብ ባሕላችንም አብሮ ተቀበረ እንጂ” ብለው ፉት አሉና እንደገና “እድሜ ለቴክኖሎጂ” ሲሉ ሃሳባቸውን ለመቀጠል ውሃ የሚቋጥር ሰበብ ሲሸምኑ የውቤ በረሃ ውቃቢ ይይለትና ሙዚቃው አልቆ በጀመረ ቁጥር እየተነሳ የሚወላከስ አንድ ሰኬ ጠረጴዛውን ሙጀሌ በጨረሰው እግሩ ሚዛን ሲያስተው ከላዩ ላይ የተከመረው ጠርሙስ መሬት ሲረግፍ እንደሲኦል ጥርስ አፏጨና ከወጋችን አናጠበን።

እኔም ሂሳቤን ዘግቼ ወጣሁና የማምሻ ወግ ፍለጋ ከዕማማ ሽጉልቴ ቤት ተከተትኩ። እግሬን እንዳጠፍኩ “አንተ ዞረቲ ጀበና ወርዶ ታስጠብቀኛለህ? ኋላ ከራማው ቢቆጣ እኔ የለሁበትም” አሉና በማስከተል “የምቀኞችህን የረዘመ ጥፍር አዋምሳግ ትመልስልህ፤ የፈሪ አርበኛ ለደሞዝ የሚሰራ ጋዜጠኛ ከመሆን ይጠብቅህ፤ ብዕርህንና አንደበትህን እንደውሽማ ወጥ ያጣፍጥልህ፤ ከጭቃው ውልቅ ከፎቁ ጥልቅ ያድርግህ” ሲሉ በምርቃት አለመለሙኝ።

ቀጠሉና እጄ ላይ ያለውን መጽሃፍ ሲያስተውሉ ቆይተው “የዘመድና የንባብ ክብር ድሮ ቀረ ልጄ” አሉ በቁጭት ከንፈራቸውን ነክሰው። ዛሬን ተንከባሎ ነገን ተቀብሎ ለመሻገር ምን አገደው እማማ? አልኳቸው እንደጣዝማ ማር የሚጣፍጥ ወጋቸውን ለመቅለብ ብዕሬን እያሰላሁ።

“የድስት ጌጡ ያው ወጡ ነው ልጄ” አሉና ሃሳባቸውን ያብራሩልኝ ገቡ። “አንድ ሀገር የቱንም ያህል በድንጋይ ቁልል ቢያሸበርቅ ጌጡ ያው ሰው ነው፤ ስለሆነም የተገነባን ሀገር ያልተገነባ አምሮ እንዳያፈርሰው የዜጎቹ ንቃተ ህሊና በንባብ መጎልበት ይኖርበታል” ሲሉ ከብረት የጠነከረ ከድንጋይ የጠጠረ ፍሬ ነገር ጣል አደረጉልኝ። ይህ አባባላቸው የደራሲያን ማሕበር ፕሬዚዳንቱ አበረ አዳሙ ክረምትንና ንባብን በማስተሳሰር የንባብ ባሕላችንን ለማሻሻል ይመክር ዘንድ ታስቦ በተዘጋጀ መድረክ ላይ “ጨው አልጫ ቢሆን በምን ይጣፍጣል? በንባብ ያልተቃኘ ዜጋ የሞላባት ሀገር አኳኋኗ ተመጥጦ እንደተጣለ ሸንኮራ ነው” በማለት የተናገሩትን አስታወሰኝ።

በደራሲያን ማሕበር አስተባባሪነት ሰኔ ሰላሳ የንባብ ቀን ተደርጎ ይከበራልና ለመሆኑ ክረምትን አስታካችሁ የጀመራችሁት የንባብ ቀን መነሻው ምንድነው? ያገኛችሁት ውጤትስ? ስል አቶ አበረን ለሰጡኝ ፈቃደኝነት በማመስገን ጥያቄ ዘረጋሁላቸው። ሰኔ ግም ሲል ፓርላማ፣ ፍርድ ቤቶችና ትምህርት ቤቶች ስለሚዘጉ ሰኔ ሰላሳ የንባብ ቀን ተብሎ እንዲሰየም ማሕበሩ ለፓርላማ ጥያቄ ቢያቀርብም ፓርላማው ግን “ራሳቸው መወሰን ይችላሉ” የሚል መልስ ሰጣቸው፤ ደራሲያኑ የተሰጣቸው መልስ ባያጠግባቸውም በጠቅላላ ጉባያቸው አስወስነው ሰኔ ሰላሳን የንባብ ቀን በማድረግ የወደቀውን የንባብ ባሕላችንን ለማንሳት ጥረት ጀመሩ፤ ይሁን እንጂ እንደትምህርት ሚኒስቴር፣ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ያሉ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይቅርና “አይዟችሁ” አለማለታቸው “እንኳን ተልባ ሸቶሽ እንዲያውም ዘጠኝ ቂጣ ትፈጃለሽን” አስተርቶባቸዋል። በዚህም የተነሳ የታሰበውን ዓላማ ማሳካት እንዳልቻሉ ፕሬዚዳንቱ አጫወቱኝ።

እኔም በንባብ የዳበረ ያኗኗር ዘይቤ እንዲኖረን እሻለሁና የፕሬዚዳንቱን የማብቂያ መልዕክት በማስፈር ጽሁፌን ቋጨሁ። “ከፍተኛውን ድርሻ መንግሥት ቢወስድም በሀገር ጉዳይ ሁላችንም ያገባናልና የዛለውን የንባብ ባሕላችንን በማበርታት ትውልድን ከጥፋት እንታደግ።”

በሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You