ኢትዮጵያ ወደ ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል መላክ ጀመረች

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በኬንያ በኩል ወደ ታንዛኒያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል በሙከራ ደረጃ መላክ መጀመሯን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለፁት፤ የሁለቱ ሀገራት የኤሌክትሪክ አቅርቦት ስምምነቱ ከተፈረመ የተወሰኑ ወራት ተቆጥረዋል። በዚህም መሠረት አሁን ላይ በኢትዮጵያ በኩል 200 ሺህ ሜጋ ዋት ድረስ የመሸከም አቅም ያለው የማስተላለፊያ መስመር ተሠርቷል ብለዋል።

አሁን በመስመሩ እየተላለፈ ያለው 200 ሜጋ ዋት መሆኑን በመጥቀስ፤ መስመሩ ተጨማሪ ግንባታ ሳይከናወን ተጨማሪ ኃይል ማስተላለፍ እንደሚችል ተናግረዋል።

ሙከራው በሂደት ላይ ያለ ነው ያሉት አቶ ሞገስ፤ በይፋ የኤሌክትሪክ ሽያጭ እንዳልተጀመረ ተናግረዋል።

የኃይል ልማት ትስስሩ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት ለሌሎች ሀገራት ጭምር ሞዴል የሚሆን ሥራ እየሠራች መሆኑን የሚያመለክት መሆኑን አንስተዋል።

ሀገሪቱ ያላትን ሀብት ለራሷ ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ከሚገኙ ጎረቤቶቿ ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን አረጋግጣ በጋራ የማልማት ፍላጎት ያላት ሀገር መሆኗን የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኬንያ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶክተር ኢንጂነር ጆን ማቲቮ ኤምቢኤስ በማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው እንዳስታወቁት፤ በሙከራው የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ በኬንያ በኩል ኤሌክትሪክ የማስተላለፊያ መስመር በተሳካ ሁኔታ ኤሌክትሪክ ማስተላለፍ መቻሉን ተናግረዋል።

በ2015 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገሮች ካቀረበችው የኤሌክትሪክ ሽያጭ ከ102 ሚሊዮን በላይ ዶላር ማግኘቷን ይታወቃል። ኢትዮጵያ ከጂቡቲ እና ሱዳን በተጨማሪ ከኅዳር 2015 ጀምሮ ለኬንያ የኤሌክትሪክ የኃይል መሸጥ መጀመሯ የሚታወስ ነው። የኤሌክትሪክ የኃይል ሽያጩ ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኢኮኖሚ የማስተሳሰር እቅድ አካል እንደሆነም ተገልጿል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You