ፌዴሬሽኑ ያሳለፈውን ውሳኔ እንደማይቀለብስ አስታወቀ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ባካሄደው ስብሰባ በተለያዩ አስር ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎች ማሳለፉ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ውዝግቦች የተነሱ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኑም ትናንት በጋዜጣዊ መግለጫ ምላሽ ሰጥቶባቸዋል።

የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች በዋናነት ሦስት ጉዳዮች ውዝግብ ፈጥረዋል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የፋይናንስ አስተዳደር መመሪያን በመተላለፍ መቻል ስፖርት ክለብ፣ ሃዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ እና ሲዳማ ቡና ስፖርት ክለቦች ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደርያ ደንብ ውጪ የተወሰነባቸውን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ፣ ክስ በመመሥረት እና ውሳኔውን በማሳገድ እግድ የተጣለባቸው ተጫዋቾች በሦስቱ ክለቦች ተሰልፈው እንዲጫወቱ መደረጉን ገምግሜያለሁ ብሏል። በመሆኑም ጉዳዩ ከይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔ በኋላ በዓለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት መታየት ሲገባው ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት መወሰዱ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንዳስከተለ ጠቁሟል። ይህም በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 14 ንዑስ አንቀፅ 1 እና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 17 ቁጥር 1/ረ የሚጥስ ነው ብሏል።

በዚህም መሠረት ሦስቱም ክለቦች የፍትህ አካላትን ውሳኔ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲያደርጉ እና መሰለፍ የሌለባቸውን የታገዱ ተጫዋቾች ተጠቅመው ያጫወቷቸው ጨዋታዎችን በሙሉ በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆኑ እና የተጣለባቸውን የገንዘብ ቅጣት በመክፈል ሪፖርት እንዲያደርጉ መወሰኑን ገልጿል። ሌሎቹ 14 ክለቦች የፋይናንስ መመሪያውን ተከትለው ስለመሥራታቸው ምርመራ እንዲደረግ እና ምርመራው እስከሚጠናቀቅ በፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መካከል የሚከናወን የተጫዋቾች የዝውውር እንቅስቃሴ ታግዶ እንዲቆይም ተወስኗል። የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበርም ፌዴሬሽኑ ይህን ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ እንደ አዲስ ሠርቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።

ከጥቂት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ስቴድየም በሲዳማ ቡናና በወላይታ ድቻ መካከል የተካሄደው የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ከተጫዋች ተገቢነት ጋር በተያያዘ ውዝግብ መፍጠሩ ይታወሳል። በዚህም የዋንጫው አሸናፊ የነበረው ሲዳማ ቡና በተጋጣሚው ወላይታ ድቻ ተገቢ ያልሆነ ተጫዋች አሰልፏል በሚል ክስ ቀርቦበት የነበረ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኑም በዚህ ጉዳይ ላይ የደረሰበትን ውሳኔ አሳውቋል። በዚህም “የሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ የታገዱ ተጫዋቾችን በማሰለፍ ያሸነፈው የኢትዮጵያ ዋንጫ በፎርፌ ተሸናፊ ሆኖ ዋንጫው ለወላይታ ድቻ ተመላሽ እንዲደረግ እና የወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የ2025/26 የውድድር ዘመን ተሳታፊ እንዲሆን” ሲል ፌዴሬሽኑ ውሳኔ አሳልፏል።

በ2018 የሊግ ውድድር በ2017 የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ የነበሩ 18 ክለቦች እና ከከፍተኛ ሊግ ያደጉ ሁለት ቡድኖችን በማካተት በ20 ክለቦች መካከል እንዲካሄድ እና በውድድር ዓመቱ ወራጅ የነበሩት አራት ክለቦች እንዳይወርዱ ተወስኗል። በዚህም መሠረት ወራጅ የነበሩት አዳማ ከተማ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ የሚቆዩ ይሆናል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ትናንት ውዝግብ በፈጠሩት ጉዳዮች ላይ በጋዜጣዊ መግለጫ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህም “ውሳኔዎቻችን እግርኳሳዊ ናቸው፣ የቢዝነስ ውሳኔ አልወሰንም” ብለዋል። እንደ ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ የታገዱት ክለቦች ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ይዘው መሄድ አልነበረባቸውም። ክለቦች ይግባኝ ካላቸው ወደ ፊፋ ነበር ማቅናት የነበረባቸው። ክለቦች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ሲወስዱ ግን ፌዴሬሽኑ ለፊፋ አቤቱታ አቅርቧል። ፊፋም የክለቦቹ አካሄድ ልክ ስላልሆነ እንዲመለሱ የሚያዝ ደብዳቤ ልኳል።

ሌላው ውዝግብ የፈጠረው ከፕሪሚየር ሊጉ ወራጅ ክለብ እንዳይኖር የተወሰነው ጉዳይ ሲሆን፣ ይህም የተደረገው ፍትህ እንዲሰፍን ነው ብለዋል። 14ቱ ክለቦች ሙሉ ምርመራ እስካልተደረገባቸው ድረስ ወራጅ እንዲኖር ማድረግ ተገቢ ነው ብለው እንደሚያስቡም አክለዋል። ፊፋ ለምን ሃያ ተሳታፊ ክለብ አደረጋችሁ አይልም ፣ በዚህ ጉዳይም መወሰን አይችልም። ምክረ ሃሳብ ከመስጠት ውጪ አስገዳጅ ሕግ የለውም ሲሉም አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል።

“ፌዴሬሽኑ የወሰነውን አልቀበልም ያለ ክለብ ሊጉን ለቆ መውጣት ይችላል” ያሉት አቶ ኢሳያስ የኮከብ ግብ አግቢ ደረጃ ሊጉ በሚያወጣው ሰንጠረዥ መሠረት እንደሚሆንና የተቀጣ ክለብ ተጫዋች ኮከብ ግብ አግቢ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

በቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You