አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን የተወሰነ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ማቋረጧን አስታወቀች

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመው ጥቃት እየተባባሰ በመጣበት በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ለኪዬቭ የምትሰጠውን የተወሰነ የጦር መሣሪያ ማቆሟን ዋይት ሐውስ አስታወቀ። የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ አና ኬሊ ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቁት ውሳኔው ላይ የተደረሰው የመከላከያ ሚኒስቴር አሜሪካ “ለሌሎች ሀገራት የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ” መገምገሙን ተከትሎ“የአሜሪካን ጥቅም ለማስቀደም ነው” ብለዋል።

የሩሲያ ዩክሬን እአአ የካቲት 2022 ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሜሪካ በአስር ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመቱ ወታደራዊ ድጋፎችን ስትሰጥ የቆየች ሲሆን፣ የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ክምችት በጣም አነስተኛ ነው ሲል ቅሬታውን ማሰማት ጀምሮ ነበር። የዩክሬን መንግሥት በዚህ መግለጫ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም። የአሜሪካ ባለሥልጣናት የትኞቹ መሣሪያዎች ወደ ዩክሬን እንዳይጓጓዙ እንደተደረጉ ያሉት ነገር እንደሌለ ተገልጿል።

የሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የአየር መከላከያ ሚሳዔሎች እና አነጣጥረው ዒላማቸውን የሚመቱ ተተኳሾች ክምችታቸው ከቀነሱ መሣሪያዎች መካከል ይገኙበታል። የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ኤልብሪጅ ኮልቢ “የመከላከያ ሚኒስቴር ለዩክሬን የሚያደርገውን ወታደራዊ ዕርዳታ ለመቀጠል ለፕሬዚዳንቱ ጠንካራ አማራጮች መስጠቱን ቀጥሏል” ብለዋል።

ኮልቢ አክለውም፣ “ሚኒስቴሩ ይህንን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ አካሄዱን በጥብቅ እየፈተሸ እና እያስተካከለ ሲሆን፣ በተጨማሪም የአሜሪካ ኃይሎች ለሌሎች መከላከሎች ቅድሚያ ሰጥተው ዝግጁ የሚሆኑበትንም በማስጠበቅ ላይ ነው” ብለዋል። የአሜሪካ ባለሥልጣን ርምጃው የተወሰደው የአሜሪካ ወታደራዊ መሣሪያዎች ክምችት በጣም እየቀነሱ መምጣታቸውን ተከትሎ መሆኑን ተገልጿል።

ባለፈው ወር አሜሪካ በሦስት የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ላይ የፈፀመችውን ጥቃት በመጥቀስ “የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ጥንካሬ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ኢራንን ጠይቁ” ብለዋል። ይህ ውሳኔ የተላለፈው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬን አቻቸው ቭላድሚር ዘለንስኪ ጋር ባለፈው ሳምንት በኔዘርላንድስ በተካሄደው የኔቶ ጉባኤ ላይ ከተገናኙ በኋላ ነው።

በወቅቱ ትራምፕ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተጨማሪ ፀረ ሚሳዔሎችን ለዩክሬን ትሰጥ እንደሆን በቢቢሲ ለተጠየቁት ሲመልሱ “አንዳንዶቹን ማቅረብ እንችል እንደሆነ የምናየው ይሆናል” ብለው ነበር። ከዘለንስኪ ጋር ያደረጉትን ውይይቶች በመጥቀስ ትራምፕ “አንዳንድ ጊዜ ትንሽ አለመግባባቶች ነበረን፤ ግን ያ የበለጠ ጥሩ ሊሆን አይችልም” ብለዋል።

ትራምፕ እና ዘለንስኪ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር በትራምፕ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የተካረረ ውዝግብ ገጥመው ነበር። ከዚያ በኋላ ትራምፕ በባይደን አስተዳደር ለዩክሬን ወታደራዊ ርዳታ የተፈቀደውን ማስቆማቸውን ተናግረዋል። በማስከተልም ከዩክሬን ጋር የደኅንነት መረጃዎች መጋራታቸውንም አቁመዋል። ነገር ግን የሀገራቱ ግንኙነት መሻሻላቸውን ተከትሎ እገዳዎቹ ተነስተዋል።

በሚያዝያ ወር መገባደጃ ላይ አሜሪካ እና ዩክሬን በወታደራዊ ድጋፍ ምላሽ አሜሪካ የዩክሬን የማዕድን ክምችት አውጥታ መጠቀም የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራርመዋል። የአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ እገዳ የመጣው ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት ወቅት እንደሆነ ተመልክቷል።

በሳምንቱ መጨረሻ ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዩክሬን ላይ ካደረሰችው ትልቁ ነው የተባለ የአየር ላይ ጥቃት ፈጽማለች። በዚህ ጥቃት ከ500 በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ማለትም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ባሌስቲክ እና የክሩዝ ሚሳዔሎችን ተጠቅማለች ነው የተባለው።

ሞስኮ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓውያኑ 2014 በግዴታ የወሰደቻትን ክራይሚያን ጨምሮ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ትቆጣጠራለች። የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ያስከተለው ውድመትና የኢኮኖሚ ቀውስ በሁለቱ ሀገራት ብቻ ተወስኖ እንዳልቀረ የፖለቲካ ምሑራኑ ይናገራሉ። በተለይ በኢኮኖሚ ቀውሱ አውሮፓና አፍሪካ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደሆኑ ይገለጻል። ይህን አውዳሚ ጦርነት በአጭር ጊዜ አስቆመዋለሁ ያሉት ትራምፕም ማቆም ተስኗቸው ጦርነቱ እንደቀጠለ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You